በከበደ ካሳ
የኢፌዴሪ ህገ መንግስት ለዘመናት የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ጥያቄ ለሆኑት ለዴሞክራሲያዊ መብቶች በተለይም
ለእኩልነት መብት ጥያቄዎች መልስ የሰጠ የቃል ኪዳናቸው ሰነድ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝቦች በህግ የበላይነት ላይ የተመሰረተ ብዙህነታቸውን
ማስተናገድ የሚችል ዴሞክራሲያዊ ስርዓት መሰረት የጣሉትም በዚህ ህገ መንግስት ላይ ነው፡፡ ህገ መንግስቱ ለብሔሮች፤ ብሔረሰቦችና
ሕዝቦች የእኩልነት መብቶች ያረጋገጠው መብት ምን ያህል ስፋትና ጥልቀት ያለው እንደሆነ በአንቀፅ 39/4 የሰፈረውን የራስን እድል
በራስ የመወሰን እስከ መገንጠል መብትን በማየት መገንዘብ ይቻላል፡፡ ስለ ህገ መንግስቱ ማብራሪያ ከሚሰጠው የሰነዱ መግቢያ ጀምሮ
ስለ ሕዝቦች የስልጣን ባለቤትነት፤ ስለመንግስት አሰራር፤ ስለ ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል፤ ወዘተ… የተቀመጡትን ድንጋጌዎች በማየት
ደግሞ ህገ መንግስቱ ለዴሞክራሲያዊ አንድነታችን ምን ያህል ቦታ የሰጠ የዘመነ ዴሞክራሲያዊ ህገ መንግስት እንደሆነ መረዳት ይቻላል፡፡
የኢፌዴሪ ህገ መንግስት ግን ከዘመኑ ጋር የሚሄድ ብቻ ሳይሆን የሩቁን አቅርቦ ያስቀመጠም
ጭምር ነው፡፡ መግቢያው ላይ ከተጠቀሱት አንቀፆች መካከል አንዱ “ጥቅማችንን፤ መብታችንንና ነፃነታችንን በጋራ እና በተደጋጋፊነት ለማሳደግ
አንድ የኢኮኖሚ ማህበረሰብ የመገንባቱን አስፈላጊነት በማመን…” በማለት ሊያሳካ የሚፈልገውን አላማ በማያሻማ አኳኋን
ገልፆታል፡፡ ህገ መንግስቱ ሁሉን አቀፍ የዴሞክራሲ እሴቶችን በመያዝ አንድ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማህበረሰብ በመፍጠር ዘላቂ ሰላምና
ዋስትና ያለው ዴሞክራሲያዊ አንድነት የሰፈነበት ማህበረሰብ የመገንባት የማይናወጥ ራዕይ፤ አላማና ግብ ያለው ነው፡፡ ህገ መንግስታችን ካሉት አንቀፆች ውስጥ ከሁለት ሶስተኛ የማያንሱት
ስለ ሰው ልጅ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች የሚደነግጉ ሲሆኑ በአለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ያላቸውን ሰነዶችም እንደ እራሱ አካል
የተቀበለ ነው፡፡
በውጤት ደረጃም የኢፌዴሪ ህገ መንግስት እጅግ ስኬታማ በሆነ መንገድ ኢትዮጵያን
ከመበታተን ቋፍ መልሶ እንደ አገር ከማስቀጠሉም ባለፈ አንድነቷ በፅኑ መሰረት ላይ እንዲቆም በማድረግ በአገራችን ዘመናዊ ታሪክ
ረጅሙን የሰላም ጊዜ እንድናሳልፍ ያስቻለን ነው፡፡ ህገ መንግስቱን መሰረት በማድረግ የቀረፅንው የኢኮኖሚ ፖሊሲና የምንከተለው ልማታዊና
ዴሞክራሲያዊ መስመር ለ12 አመታት በፈጣን የኢኮኖሚ እድገት ውስጥ እንድናልፍ አስችሎናል፡፡
በሀገራችን የሚካሄደው ልማት ዋና አላማ የዜጎችን የኑሮ ደረጃ
ማሻሻል መሆኑ በህገ መንግስቱ አንቀፅ 43/4 ላይ ተደንግጓል፡፡ ከህገ መንግስቱ የተቀዱት ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎችም ፈጣን እድገት
ብቻ ሳይሆን ህዝቡን በየደረጃው በልማቱ ተሳታፊና ተጠቃሚ የማድረግ ተልዕኮን ያነገቡ ናቸው፡፡ በዚህም መሰረት በገጠር አርሶ አደሩ
መሬቱን፤ ጉልበቱንና የእንስሳት ሃብቱን አቀናጅቶ ምርትና ምርታማነቱን እንዲያሳድግ፤ መሬት የሌላቸው ወጣቶች ደግሞ ከግብርና በተሳሰሩና
ከግብርና ውጭ ባሉ የገቢ ማስገኛ ዘርፎች ተሰማርተው ገቢያቸውን እንዲያሳድጉ ማድረግ ተችሏል፡፡ በከተማም በዋናነት አነስተኛና ጥቃቅን
ተቋማትን ማዕከል ያደረገ የስራ እድል ፈጠራ በማካሄድ የዜጎችን የኑሮ ደረጃ ማሻሻል ተችሏል፡፡ በዚህም በ1988ዓ.ም 45.5በመቶ
የነበረውን በድህነት ውስጥ የሚኖሩ ዜጎች ብዛት በ2005 ወደ 26በመቶ ማውረድ ተችሏል፡፡ የዜጎች የነፍስ ወከፍ ገቢም በቀጣይነት
እያደገ መጥቶ በ1983 ከነበረበት 70ዶላር በ2006 ዓ.ም 630ዶላር ደርሷል፡፡
የህገ መንግስታችን ትሩፋቶች በሀገር
ውስጥ ብቻ ሳይወሰኑ በአለም አቀፍ መድረኮች ሰንደቅ አላማችን ከፍ ብሎ እንዲውለበለብና ስማችንም በመልካም እንዲነሳ አድርገውናል፡፡
ዛሬ ኢትዮጵያ በጦርነትና እርስበርስ ጦርነት ሳይሆን በአለም አቀፍ ሰላም ማስከበርና በፀረ ሽብር ዘመቻ አጋርነት ስሟ ቀድሞ የሚነሳ
ሆናለች፡፡ በረሃብና ድርቅ ሳይሆን በምግብ እህል ምርት ራሷን በመቻል ስኬቷ ተጠቃሽ ሆናለች፡፡ በፈጣንና ተከታታይ የኢኮኖሚ እድገት
እንዲሁም የውጪ ኢንቨስትመንትን በመሳብ ግንባር ቀደም ከሆኑት ሀገራት ተርታ የተሰለፈች ነች፡፡
በድምሩ ህገ መንግስታዊ ስርዓት መከተላችንና
ባለፉት 20 አመታት ስኬታማ አተገባበር መኖሩ አገራችን ከመበታተን አደጋ ወጥታ በፅኑ መሰረት ላይ ያረፈ ዴሞክራሲያዊ አንድነትና
ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት በዚሁ መነሻነት በጎ አለም አቀፍ ገፅታና ተሰሚነት እንዲኖረን አስችሏል፡፡ እነሆ የኢፌዴሪ ህገ መንግስት
የፀደቀበትን 20ኛ አመት ስናከብር ታዲያ እነዚህን ሁሉ ትሩፋቶች
ያስገኘልንን ህገ መንግስት ለዜጎቻችን በተለይም ለወጣቱ ትውልድ በማስረፅ ረገድ የደረስንበትን ደረጃ ማየት ተገቢ ይሆናል፡፡
ህገ መንግስት በባህሪው ቋሚ ሰነድ ሲሆን በአንጻራዊነት
ለረጅም
ጊዜ እንዲያገለግል ሆኖ የሚቀረጽ ነው፡፡ በአለማችን ረጅም እድሜ በመያዝ
ተጠቃሹ ህገ መንግስት 226 አመት እድሜ
ያለው የአሜሪካ ህገ መንግስት ነው፡፡ በሕብረተሰብ እድገት ውስጥ ሁልጊዜም ለውጥ ስለሚኖር በዚህ ማዕቀፍ ውስጥ የሚታዩ መጠነኛ ለውጦች ከመኖራቸው በስተቀር የስርዓትም ሆነ የፖለቲካ
ፍልስፍና ለውጥ በመጣ ቁጥር እንደገና የማይፃፍ ወይም የማይለወጥ ለብዙ ጊዜ የሚያገለግል ሰነድ ነው፤
ህገ መንግስት፡፡ በመሆኑም ህገ መንግስትን ለዜጎች
ማስረፅ ወይም የህገ መንግስት አስተምህሮ ሲባል ይህን ዘመን ተሻጋሪ ሰነድ የየዘመኑ ትውልዶች በእውቀት ላይ ተመስርተው በቅብብሎሽ
ይዘውት እንዲዘልቁ የማድረግ ጉዳይ ነው፡፡
ኢትዮጵያ በ3ሺ አመት ታሪኳ ቀድሞ
ከነበረችበት የስልጣኔ ማማ በየጊዜው ቁልቁል ስትንሸራተት ቆይታ በ21ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ አካባቢ በአለም ኋላ የቀሩ ከሚባሉ
ድሃ ሀገራት ተርታ ለመሰለፍ በቅታለች፡፡ የጥቁር ሕዝቦች ስልጣኔና የነፃነት ቀንዲል የመሆን ታሪኳ በእርስ በርስ ጦርነትና የረሃብ
ክስተቶች ተሸፍኖ አንገት በሚያስደፋ አዋራጅ ምዕራፍ ውስጥ አልፋለች፡፡ ከ21ኛው ክፍለ ዘመን ማገባደጃ ጀምሮ ደግሞ ይህን አንገት
የሚያስደፋ ታሪኳን በሚቀለብስ አዲስ የታሪክ ምዕራፍ ጉዞ ውስጥ ትገኛለች፡፡ የዚህች አዲሲቷ ኢትዮጵያ አስተማማኝ መሰረት የተጣለበት
ህገ መንግስትም ከፀደቀም እነሆ ሁለት አስርት አመታትን አስቆጥሯል፡፡
አዲሱ ትውልድ የጀመርንው የሕዳሴ ጉዞ ተሳታፊና ባለቤት ቢሆንም
ቅሉ ሀገሪቱ ባለፈችበት አባጣ ጎርባጣ የታሪክ ምዕራፍ ውስጥ ያለፈ አይደለም፡፡ ያለፉትን ስርዓቶችም አያውቃቸውም፡፡ ታሪካችን ሲፃፍም የመላ የኢትዮጵያ
ብሔሮች፤ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ታሪክ ከመሆን ይልቅ በነገስታትና በገዢዎች ገድል ላይ የሚያጠነጥን ከዛም አለፍ ሲል ውስን አካባቢዎችና
ሕዝቦች ላይ የሚያነጣጥር ተደርጎ ነው፡፡ ስለሆነም በዘመናት የኢትዮጵያ ህዝቦች የዴሞክራሲና የኢኮኖሚ ጥያቄዎች፤ ኢትዮጵያውያን
ለእኩልነት በከፈሉት መስዋዕትነት እንዲሁም በፌዴራል ስርዓቱ ምንነትና ፋይዳ ላይ የተሟላ ግንዛቤ አለው ለማለት አይቻልም፡፡ የኢፌዴሪ
ህገ መንግስት ምንነትና ፋይዳ በግልፅ የሚታየው ደግሞ ከዚህ የታሪካችን ዳራ ተነስቶ ሲመዘን ነው፡፡ ለዚህም ነው በህገ መንግስቱ መግቢያ ላይ “መጪው የጋራ
እድላችን መመስረት ያለበት ከታሪካችን የወረስነውን የተዛባ ግንኙነት በማረምና የጋራ ጥቅማችንን በማሳደግ ላይ መሆኑን በመቀበል...
ይህን ህገ መንግስት… ህዳር 29/1987 አፅድቀነዋል” የሚለው መልዕክት የተካተተው፡፡
በመሆኑም በህገ መንግስታችን ትሩፋቶች
ላይ ተመስርቶ በህገ መንግስቱ መሰረታዊ መርሆዎች፤ በፌዴራል ስርዓቱ መሰረታዊ አስተሳሰቦች፤ መርሆዎችና ባህርያት ላይ የዜጎችን
ግንዛቤ ማስፋት ያስፈልጋል፡፡ ያለፈ ታሪካችን መልካም ጎኖች እንደነበሩት ሁሉ የተዛቡ ግንኙነቶችን ፈጥሮ ያለፈ መሆኑንና ይህንን
ማረም ብቻ ሳይሆን ዳግም እንዳይፈፀም መከላከል እንደሚገባን፤ ተስፋችንም በልዩነት ውስጥ የፈጠርነው ዴሞክራሲያዊ አንድነት ብቻ
እንደሆነ ዜጎችን ማስተማር ይጠበቃል፡፡ ይህ ተግባር ደግሞ በትምህርት ተቋማት፤ በመገናኛ ብዙሃን፤ በሲቪክ ማህበራትና መሰል አደረጃጀቶች
ሁሉ ሊፈፀም የሚገባው ነው፡፡
እስካሁንም ይህን የሰላማችን፤ የልማታችንና የዴሞክራሲያችን ዋስትና የሆነውን ህገ መንግስት ለማስረፅ እየተፈፀሙ ያሉ
ተግባራት አሉ፡፡ ከዚህ አንፃር ቀድሞ የሚታየው ተግባር በትምህርት ተቋማት በስነ ምግባርና ስነ ዜጋ ትምህርቶች አማካኝነት የሚሰጠው
አስተምህሮ ነው፡፡ መንግስት ለትምህርት መስፋፋትና ተደራሽነት በሰጠው ከፍተኛ ትኩረት የተነሳ በአሁኑ ወቅት ከ20 ሚሊዮን የማያንሱ
ዜጎች በትምህርት ገበታ ላይ ናቸው፡፡ እነዚህን ዜጎች በትምህርት ቤቶች በኩል መድረስ ማለት በቁጥር የላቀውን ዜጋ በመደበኛነት
ከመድረስ ባሻገር ዘለቄታዊ ፋይዳም ያለው ነው፡፡ ምክንያቱም የአሁን ተማሪዎች የነገ መምህራንና አገር ተረካቢዎች በመሆናቸው አስተምህሮው
ለቀጣይ መልካም መሰረት የመገንባት ያህል ነው፡፡ ሀገሩን የሚወድ የሰለጠነና ዲሞክራሲያዊ ባህል ያለው ትውልድ የመፍጠር ሚናውም የማይተካ ነው፡፡
አሜሪካ ከ10 አመት በፊት ባፀደቀችው
H.R.4818 ህግ ከፌዴራል መንግስት የበጀት ድጎማ የሚደረግላቸው በሁሉም ደረጃ ያሉ ትምህርት ቤቶች ለተማሪዎቻቸው የህገ መንግስት
ኮርሶችን እንዲሰጡ ታስገድዳለች፡፡ በት/ቤቶች ያለው የህገ መንግስት አስተምህሮ በየእለቱም የሚፈፀም ነው፡፡ በየእለቱ ተማሪዎች
በህገ መንግስቱ ድንጋጌዎች ላይ እንዲመራመሩ፤ ክርክሮቻቸውን ከህገ መንግስቱ በሚጠቀሱ አንቀፆች እንዲያስደግፉ፤ ህገ መንግስቱ ያረጋገጠላቸውን
መብት ተጠቅመው አመለካከታቸውን እንዲገልፁ በማድረግ ተማሪዎች ሀግ መንግስቱን በተግባር እንዲማሩት ይደረጋሉ፡፡ ተማሪዎች ወቅታዊ
ሀገራዊና አለም አቀፋዊ ክስተቶች መነሻ በማድረግ እንዲከራከሩ፤ ሲከራከሩም የህገ መንግስቱን ድንጋጌዎች እየጠቀሱ እንዲሆን ያደርጓቸዋል፡፡
ሌላው የህገ መንግስት
አስተምህሮ የሚፈፀምበት አግባብ ህገ መንግስቱ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ታሳቢ ሆኖ በሚውልባቸው በዓሎች ናቸው፡፡ በእኛ ሀገር ሁኔታ
በየአመቱ ህዳር 29 የሚከበረው የኢፌዴሪ ህገ መንግስት የፀደቀበት የኢትዮጵያ ብሔሮች፤ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን ከዚህ አንፃር
ቀዳሚው ነው፡፡ የጥቅምት ወር በገባ የመጀመሪያው ሰኞ የሚከበረው የሰንደቅ አላማ ቀን፤ መስከረም 5 ቀን የሚከበረው አለም አቀፉ
የዴሞክራሲ ቀንና ሌሎች አለም አቀፍ የበዓል ቀናትም በዚሁ ማዕቀፍ የሚታዩ ናቸው፡፡ በእነዚህ ቀናት ዜጎች በየስራና የኑሮ አካባቢያቸው
ተሰባስበው በህገ መንግስቱ ትሩፋቶች ላይ እንዲመክሩ ይደረጋል፡፡ በህገ መንግስቱ ድንጋጌዎች ላይ ያተኮሩ መልዕክቶችም ይተላለፋሉ፡፡
በዓሎችን በማስመልከት መፅሄቶች፤ የመወያያ ፅሁፍ ቅጅዎች፤ የዘጋቢ ፊልም ሲዲዎች፤ በተለያዩ ቋንቋዎች የተዘጋጁ ፖስተሮቸና በራሪ
ፅሁፎች በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች ይሰራጫሉ፡፡
አሜሪካውያን
በየአመቱ ሴፕቴምበር 17ን የህገ መንግስት
ቀን /Constitution Day/ Citizenship Day/ በሚል ያከብሩታል፡፡ ኢኳቶሪያል ጊኒ፤ ጋና፤ ሜክሲኮ፤ ጃፓን፤ ፖላንድ፤
ኡራጓይና ዴንማርክም የህገ መንግስት ቀንን ከሚያከብሩ ሀገራት መካከል ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ በስፔን እለቱ የሚከበረው የታሪክና የፖለቲካና የህግ ትምህርቶችን በመስጠት ነው፡፡ የተመረጡ ተማሪዎች በታችኛው ም/ቤት ተገኝተው የህገ መንግስቱን አንቀፆች እንዲያነቡ ይጋበዛሉ፡፡ የፓርላማው ግቢም ለህዝብ ጉብኝት ክፍት ይሆናል፡፡ ጃፓናውያን የህገ መንግስቱን ትሩፋቶች የሚያስረዱ ገለፃዎችን በማዳመጥ ያከብሩታል፡፡ ፖላንዶች ደግሞ ወታደራዊ ሰልፎችን በማየትና ለሀገራቸው መስዋዕት የሆኑ ጀግኖቻቸውን በመዘከር ያሳልፉታል፡፡ በጋና ብሔራዊ መዝሙር በመዘመር፤ ሰንደቅ አላማ በመስቀልና የሰልፍ ትርዒት በማሳየት ይከበራል፡፡ በኡራጓይ የመገናኛ ብዙሃን በዓሉን አስመልክቶ ሰፊ ዘገባዎችን የመስጠት ባህልን አዳብረዋል፡፡ በሜክሲኮ ከበዓሉ ቀን በፊት ባሉት ሶስት ቀናት የአልኮል መጠጦች ሽያጭ የተከለከለ ሲሆን የበዓሉ እለት ግን ዜጎች ስጦታ በመለዋወጥና በመላ ሀገሪቱ የሰልፍ ትርኢቶችን በማሳየት በድምቀት ያከብሩታል፡፡ ብዙዎቹን ሀገራት የሚያመሳስላቸው ስነ ስርዓት ግን በብዙዎቹ ሀገራት ህዝባዊ በዓል ሆኖ ስለሚከበር መስሪያ ቤቶች መዘጋታቸውና የበዓሉ ቀዳሚ ታዳሚዎች ህፃናትና ወጣቶች መሆናቸው ነው፡፡ በሁሉም በዓሎች ላይ ከፍተኛ የሀገራቱ መሪዎች እየተገኙም መልዕክት ያስተላልፋሉ፡፡
በአሜሪካ
በዚህ
እለት የሚደረጉ አስተምህሮዎች ከእለት ተዕለት የትምህርት ቤቶች፤ የዴሞክራሲ ተቋሞችና የፊልም ኢንዱስትሪውን ጨምሮ የሌሎች ተቋማት
ቅንጅታዊ እንቅስቃሴ ጋር ተዳምሮ ዜጎች ህገ መንግስቱ በሂዎታቸው ቁልፍ የሆነው የህግ ሰነድ እንደሆነና በየእለቱ በሚያደርጉት እንቅስቃሴያቸው
ውስጥ ተፅዕኖ የሚያሳርፍ እንደሆነ አምነው
እንዲቀበሉ አድርጓቸዋል፡፡ አሜሪካኖች በአለም የሚታወቁበት መብትን አሟጦ የመጠቀም ልምድም ከዚሁ ከህገ መንግስታቸው ጥልቅ አስተምህሮ
የመነጨ እንደሆነ ብዙዎች ይስማማሉ፡፡
በመገናኛ ብዙሃን
አማካኝነት የሚካሄደው የህገ መንግስት አስተምህሮም ሌላው ስልት ነው፡፡ በአገራችን ያሉ አንዳንድ የብሮድካስትና የህትመት መገናኛ
ብዙሃን መደበኛ የአየር ጊዜና አምድ በመስጠት የህገ መንግስት ማስረፅ የሚተገብሩ ሲሆኑ አንዳንዶቹም ወቅታዊ ክስተቶችን መሰረት
አድርገው የአስተምህሮ ተግባሮችን ይፈፅማሉ፡፡ የፌዴሬሽን ምክር ቤትም በቋሚነት መልዕክት ቀርፆ የሚያስተላልፍባቸው የመገናኛ ብዙሃን
ፕሮግራሞች አሉ፡፡ በተለያዩ ቋንቋዎች ተዘጋጅተው በሬዲዮና ቴሌቪዥን የሚተላለፉት የፌዴራሊዝምና የህገ መንግስት ጥያቄና መልስ ውድድሮች፤
የህፃናትን ንቃተ ህግ የሚያጎለብት “አበባ እና አበበ” የካርቱን
ፊልም ተጠቃሽ ናቸው፡፡ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን ማዕከል አድርገው የሚቀረፁት እነዚህ ፕሮግራሞች አገር አቀፍ ተደራሽነት
ያላቸው ሲሆኑ የዜጎችን የህገ መንግስት እውቀት በማሳደግ ረገድ ጉልህ ሚና አላቸው፡፡
ጥረቶቹ እንዳሉ ሆነው
ላለፉት አመታት ስኬታማ ጉዟችን መነሻ የሆነውን ህገ መንግስት በዜጎች
ዘንድ በሚገባው ደረጃ ማስረጽ ላይ አሁንም ክፍተቶች አሉ፡፡ በመሆኑም ህገ መንግስቱ ሊያገኝ የሚገባውን እውቅናና ክብር እየተቸረው
አይደለም ማለት ይቻላል፡፡ ለዚህ አንዱ መገለጫ በየወቅቱ ከህገ መንግስቱ ድንጋጌዎች ጋር የሚላተሙ አመለካከቶችና ተግባሮች መኖራቸው
ነው፡፡ በህገ መንግስቱ የሰፈሩ (ለምሳሌ “መሬትና የተፈጥሮ ሃብት የመንግስትና የህዝብ ነው” /40፡3/፤
“በህገ
መንግስቱ ከተደነገገው ውጭ በማንኛውም አኳኃን ስልጣን መያዝ የተከለከለ ነው”/9፡3/፤ “መንግስታዊ
ሃይማኖት አይኖርም”/11፡2/) አቢይ ድንጋጌዎችን በአመላከትና በተግባር ለመጣስ የሚደረጉ ጥረቶችን መጥቀስ ይቻላል፡፡
በአንዳንድ ወገኖች ዘንድ የህገ መንግስቱን መነሻና ፋይዳ አሳንሶ የማየት ዝንባሌ መኖሩም ሌላው በቂ ግንዛቤና መግባባት ያለመፈጠሩ
መገለጫ ነው፡፡
በርግጥ የህገ መንግስት
አስተምህሮ በአንድ ወቅት ተጀምሮ ሌላ ጊዜ የሚጠናቀቅ አይደለም፡፡ እንደውም ከየጊዜው ጋር እየተጣጣመ መቀጠል ያለበት የእለት ተዕለት
ስራ ነው፡፡ የህገ መንግስት እውቀት በተለይም እንደኛ ህገ መንግስት ያለውን መሰረታዊ የሆኑ የአስተሳሰብ ለውጦችን ያቀፈ ህገ መንግስት
በአንድ ጊዜ የሚጨበጥ አይደለም፤ በየጊዜው እየበለፀገ የሚሄድ እንጂ፡፡ ስለሆነም ይህን ታሳቢ ያደረገ ቀጣይነት ያለው ስራን ግድ
ይላል፡፡
የህገ መንግስት አስተምህሮ
የዜጎችን ንቃተ ህግ በማሳደግ በምክንያታዊነት የሚያምን፤ ልዩነትን የሚቀበልና ልዩነቶችን በዴሞክራሲያዊ መንገድ በውይይትና በድርድር
የሚፈታ፤ መልካም እሴቱ የተገነባ ዜጋን ለማፍራት ያስችላል፡፡ ዘላቂ ውጤቱም በማንኛውም ጊዜና ምክንያት የማይናወጥ የፖለቲካ ስርዓት
የሚፈጥር ነው፡፡ ስለሆነም ጅምር የአስተምህሮ ስራዎቹን አጠናክሮ ማስቀጠል እንደተጠበቀ ሆኖ አዳዲስ አሰራሮችን መቀየስና መተግበርን
ይጠይቃል፡፡
አሜሪካኖች የህገ መንግስት አስተምህሮ
ለመፈፀም የሚያግዛቸው /Resoruces for Teaching the Constitiution/ የሚባል ግዙፍ የመረጃና የእውቀት ማከማቻ
ድረ ገፅ አላቸው፡፡ ይህ ገፅ በየጊዜው
እየዳበረ የሚሄድ ሲሆን ማንኛውም ዜጋ እንደፍላጎቱና አቅም ደረጃው ለማስተማርም ሆነ ለመማር የሚያስችለውን እውቀት የሚሸምትበት
የተደራጀ ድረ ገፅ ነው፡፡ ተማሪዎች በየጊዜው የሚያነሷቸውን የህገ መንግስት ጥያቄዎች፤ በህገ መንግሰቱ ድንጋጌዎች ላይ የተደረጉ
ክርክሮችና የተደረሱባቸው ማደማደሚያዎች፤ ህገ መንግስቱን አስመልክቶ በመገናኛ ብዙሃን የወጡ ትንታኔዎች ሁሉ ተደራጅተው ይገኙበታል፡፡
ይህን አይነት የተደራጀ የእውቀት ማዕከል ለእኛም ያስፈልገናል፡፡ እዚህም እዚያም ተበታትነው ያሉ መፃህፍት፤ ጥናታዊና የትንታኔ
ፅሁፎች፤ የመገናኛ ብዙሃን ዘገባዎች፤ የውይይቶችና ኮንፈረንሶች ማጠቃለያዎች /proceedings/፤ ወዘተ… ተደራጅተው የሚቀመጡበትና
የፊዚካልና የኦንላይን ላይብረሪ ያስፈልጋል፡፡
የህገ መንግስት አስተምህሮ
ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ወይም ለሌሎች ጥቂት ተቋማት የሚተው ተልዕኮ አይደለም፡፡ በርካታ ባለድርሻና አጋር አካላት ተቀናጅተው ሊፈፅሙት
የሚገባ ሀገራዊ ስራ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ደግሞ በተለይ በሀገሪቱ ያሉ የዴሞክራሲ ተቋማት ከፍተኛ ሃላፊነት አለባቸው፡፡ የሕዝብ
ተወካዮችና የፌዴሬሽን ም/ቤቶች፤ የሕዝብ እምባ ጠባቂና የሰብዓዊ መብት ኮሚሽኖች፤ ምርጫ ቦርድና መገናኛ ብዙሃን ከትምህርት ተቋማትና
ከሲቪክ ማህበራት ጋር በመሆን በፊተኛው ረድፍ ላይ መሰለፍ ይጠበቅባቸዋል፡፡ እነዚህ ተቋማትና ሌሎች አጋሮች ተቀናጅተው የሚሰሩበት
የጋራ አደረጃጀት፤ አሰራርና እቅድ ሊኖርም ይገባል እላለሁ፡፡
No comments:
Post a Comment