EPRDF is a ruling party committed to realize Ethiopia's Renaissance.

Saturday, 13 December 2014

መተላለቅ ድሮ ቀርቶ በመቻቻል ተተክቶ



በእውነቱ ብላታ (ሚኒስትር ዲኤታ)
የኢፌዴሪ ህገ መንግስት በኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች የነቃ ተሳትፎ ከፀደቀ እነሆ ድፍን ሃያ አመት ሞላው፡፡ እንደ ሀገር ከየት ተነስተን እዚህ ደረስን ብለን ትላንትን በዓይነ ህሊና መለስ ብለን ማስታወስ ዛሬ ለደረስንበት ስኬትና ለነገው ቀሪ ጉዞ ትልቅ አቅም ይሆናል፡፡ ባለፉት ሃያ አመታት ውስጥ የተመዘገቡ ድሎች፣ የተከፈሉ አኩሪ መስዋዕትነቶች፣ የታለፉት ፈታኝ ተግዳሮቶች እና የተቀመሩ ልምዶች በሙሉ እየገነባን ላለነው ህብረ ብሔራዊ ዴሞክራሲያዊ ስርዓትና ብዝሃነት መጐልበት ጉልህ ማሳያዎች ናቸው፡፡
ሀገራችን ኢትዮጵያ ለዘመናት በውስጧ የያዘቻቸውን እጅግ ብዙ ማንነቶች ማስተናገድ አቅቷት በእርስ በእርስ ጦርነት ስትናጥ ቆይታ ልትፈርስ ጥቂት እርምጃዎች ሲቀራት የቁርጥ ቀን ልጆቿ በከፈሉት አኩሪ መስዋዕትነት ከዘግናኝ እልቂትና ብተና ለጥቂት ማምለጧ የቅር ጊዜ ታሪካችን ነው፡፡
በእርግጥ በውስጧ አቅፋ የያዘቻቸውን ቱባ ማንነቶች ማስተናገድ ያቃታት ሀገሪቷ ሳትሆን የሰላሟና የእድገቷ ፀር የነበሩ ፊውዳልና አምባገነን መሪዎቿ ስለነበሩ እነርሱ በተገረሰሱ ማግስት የእልቂትና የብተና ምዕራፍ ተዘግቶ የሰላምና የዴሞክራሲ ጮራ ከዳር እስከ ዳር መፈንጠቅ ችሏል፡፡ የምን እልቂትና ብተና? የሚል ሰው አይጠፋምና ይህን በአግባቡ መግለጽ አስፈላጊ ይሆናል፡፡
1991 ... የቀዝቃዛው የአለም ጦርነት አብቅቶ የሶሻሊስቱ ጐራ እንደ እንቧይ ካብ ሲናድ በካምፑ የነበሩ አብዛኛዎቹ ሀገሮች ከፍተኛ ችግር ውስጥ ገብተው እንደነበር ይታወቃል፡፡ በስልጣኔና በኢኮኖሚ እድገታቸው ከእኛ ሀገር የተሻሉ የነበሩት የምስራቅ አውሮፓ የሶሻሊስት ሀገሮች ወደ መተላለቅና መፈረካከስ ያመሩበት፤ በጣም በቅርባችን የአንድ ብሔር እና የአንድ ሃይማኖት ሀገር የሆነችው ጐረቤታችን ሶማሊያ ወደ መፈረካከስና የእልቂት አዙሪት የገባችበት ወቅት ነበር፡፡ በዓይነ ህሊና መነጽር መለስ ብሎ የወቅቱን አለማዊ፣ ከባቢያዊና ሀገራዊ ሁኔታ ላገናዘበ ሰው የቁርጥ ቀን ልጆቿ ባይታደጓት ኖሮ የእርስ በእርስ እልቂትና ብተና በኢትዮጵያችንም ላይ የተደቀነ ግልጽ አደጋ ነበረ፡፡ ብዙዎችም የወቅቱን አደጋ ከሩቅ አይተው ይች ሀገር ልትፈራርስ ትችላለች ብለው ተንብየው እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው፡፡ 
ሀገራችን ከዚህ የእልቂት አደጋ የዳነችበት ሂደት እጅግ ድንቅ ነው፡፡ 17 በላይ የፖለቲካ ድርጅቶች በትጥቅ ትግል ጭምር የሚፋለሙባት፤ የብሔር ቅራኔ ጣሪያ የነካባት፤ የዴሞክራሲ ጭላንጭል የማይታወቅባት፤ ድህነትና ኋላቀርነት የነገሰባት ሀገር ያለማንም የውጭ ኃይል ድጋፍና ጣልቃ ገብነት በራሷ በውድ ልጆቿ አኩሪ ተጋድሎና በሳል አመራር ሰላማዊ የሽግግር መድረክን ማጠናቀቋን መለስ ብሎ ላገናዘበው እጅግ የሚያኮራ ድል ነው፡፡
ይህ ወቅት የምዕራቡ አለም ርዕዮት በአሸናፊነት የወጣበትና ሁሉንም ነገር ለማስተዳደር የሚዳዳበት ወቅት ስለነበረ በስመ ማረጋጋት ወደ ሀገራችን ገብቶ ቢሆን ምን ሊሆን እንደሚችል ማሰብ ይቻላል፡፡ የገልፍ ጦርነትን ያጠናቀቀው የምዕራቡ ጦር እዚሁ ጅቡቲ አፍንጫችን ስር ሰፍሮ ስለነበር በስመ ሰላምና ማረጋጋት ወደ ሀገራችን ጐራ ብሎ ሊከርም የሚችልበት አደጋም ያንዣበበት ወቅት ነበረ፡፡ ከዚህ ሁሉ አስፈሪ ክስተት ሀገራችንን የታደጓት ለሰላም፣ ለእኩልነትና ለዴሞክራሲ የታገሉና አኩሪ መስዋዕትነት የከፈሉ የቁርጥ ቀን ልጆቿ ናቸው፡፡ 
በኢትዮጵያ ሀገራችን ላይ አንዣቦ የነበረውን የእልቂትና የብተና አደጋ በመቀልበስ እና የጦርነትና የረሀብ ተምሳሌነቷን ምዕራፍ በመዝጋት ለሁሉም ብሔሮች፤ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች የምትመች ሀገር መገንባት የተቻለው በዚህ ሁሉ ከባድና አስቸጋሪ ምዕራፍ ውስጥ በድል ማለፍ ስለተቻለ ነው፡፡ ይህን አስቸጋሪ ወቅት ማለፍ ከተቻለባቸው መሠረታዊ ጉዳዮች አንዱና ዋነኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች፤ ብሔረሰቦችና ህዝቦች መብቶችና ነፃነቶች በሀገሪቱ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ መከበራቸውና ዋስትና ማግኘታቸው ነው፡፡
በዚያን አስቸጋሪና ፈታኝ ወቅት መብትና እኩልነት ማረጋገጥ መቻል ስር ነቀል የሆነ አዲስ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ የግንኙነት ስርዓትን ከመዘርጋቱም በተጨማሪ ለዘላቂ ሰላምና ዋስትና ላለው የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ የማይናወጥ መሠረት ሆኗል፡፡ ለዘመናት የፖለቲካ አዙሪት ሆኖ ሀገሪቱን ሲያምሳት የኖረው የማንነትና የመሬት ጥያቄ ዋስትና ያለው መልስ ስላገኘ ሀገራችን ከወደቀችበት አዘቅት ወጥታ ቀና ማለት የቻለችው ባለፉት ሁለት አስርተ የህገ መንግስቱ አመታት ነው፡፡  
ይህ የኢፌዴሪ ህገ መንግስት በአፄዎቹ ተጀምሮ በደርግ ቀጥሎ የነበረውን የተሳሳተ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የማህበራዊ ግንኙነትን ስር ነቀል በሆነ መንገድ ያረመና ለአዲሲቱ ኢትዮጵያ ግንባታ ምቹ ሁኔታ የፈጠረ እጅግ ዘመናዊና ዲሞክራሲያዊ ህገ መንግስት ነው፡፡ ለህብረ ብሔራዊነትና ለብዝሃነት እውቅና የሰጠ፣ የብሔሮች፤ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ሉአላዊ የስልጣን ባለቤትነት ያረጋገጠ ህገ መንግስት ነው፡፡ 
መፍረስ እና መተላለቅ ቀርቶ በመቻቻልና በመከባበር ላይ የተመሰረተ አዲስ ግንኙነት በመረጋገጡ ምክንያት ሀገራችን በሰላም፣ በልማትና በዴሞክራሲ ጐዳና መራመድ ችላለች፡፡ ላለፉት አሥራ ሁለት አመታት በተከታታይ ፈጣን እድገት ማስመዝገብ የተቻለው ህገመንግስቱና ህገመንግስታዊ ስርዓቱ በፈጠረው ምቹ ሁኔታ ነው፡፡
ዛሬ የኢትዮጵያ // ዴሞክራሲያዊና ህብረ ብሔራዊ አንድነት በማይናወጥ አለት ላይ እየተገነባ ይገኛል፡፡ አልፎ አልፎ በአፍራሽ ሃይሎች በሚነሱ አቧራዎችና የሲኒ ውስጥ ማዕበሎች የማይናወጥ በመፈቃቀድ ላይ የተመሰረተ የአንድ ፖለቲካና ኢኮኖሚ ማህበረሰብ ግንባታን ማዕከል ያደረገ አንድነት እየተገነባ ይገኛል፡፡ 
ባለፉት ስርዓቶች ተገልለውና ተገፍተው የነበሩ // ህገ መንግስቱ ባረጋገጠላቸው መብት ተጠቅመው ለአዲሲቱ ኢትዮጵያ ግንባታ የበኩላቸውን ሚና በመወጣት ላይ ይገኛሉ፡፡ ራሳቸውን በራሳቸው በማስተዳደር የዴሞክራሲና የኢኮኖሚ ተጠቃሚነታቸውን በማረጋገጥ ላይ ይገኛሉ፡፡ ይህ ሁሉ ድል የተገኘው ህብረ ብሔራዊነትንና ብዝሃነትን የሚያስተናግድ ስርዓት መገንባት ስለተቻለ ብቻ ነው፡፡
ስለሆነም እስከአሁን የተገኙትን ውጤቶች ጠብቆ ለቀጣይ ድሎች መዘጋጀት ወሳኝ መሆኑ መዘንጋት የለበትም፡፡ በርግጥ ለዘመናት የተከማቹትን የሀገራችንን ዘርፈ ብዙ ችግሮች በሃያ አመት ጊዜ ውስጥ መፍታት አይቻልም፡፡ እጅግ ጥልቅ ከሆነ ድህነትና ፀረ ዴሞክራሲ ስርዓት ወጥቶ እንደ ሀገር መቀጠላችን በራሱ ትልቅ ስኬት ቢሆንም አሁንም ከፊታችን የተደቀኑት ፈታኝ ሁኔታዎች ብዙ ናቸው፡፡
ኪራይ ሰብሳቢነት፣ የመልካም አስተዳደር ጉድለቶች እና የሀይማኖት አክራሪነት በስርዓቱ ላይ የተጋረጡ አደጋዎች ናቸው፡፡ በተለይም የጠባብነትና የትምክህት መሸሸጊያ ዋሻ የሆነው ኪራይ ሰብሳቢነት ከሀይማኖት አክራሪነት ጋር ያልተቀደሰ ጋብቻ በመፍጠር ሰላማችንን በመፈታተን ላይ ይገኛል፡፡ የመልካም አስተዳደር ጉድለቶች በአብዛኛው የሚከሰቱት አለአግባብ ለመጠቀም ከሚፈልግ የኪራይ ሰብሳቢ ሀይል ስለሆነ የፀረ ኪራይ ሰብሳቢነት ትግሉ እዛው ካለ የመልካም አስተዳደር ትግል አካል ይሆናል፡፡ 
እነዚህን አደጋዎች በብቃት መመከት የህዳሴውን ጉዞ በብቃት ማረጋገጥ የመቻላችን ዋነኛው ምዕራፍ ስለሆነ በዚህ እልህ አስጨራሽ ትግል መውደቅ እንደ ሀገር ያፈርሰናል፡፡ ታጋዮች ደርግን ሲታገሉ እንደተቀኙት ዛሬም ትግሉ መራራ ቢሆንም ድል ማድረጋችን የማይቀር ነው ብሎ በራስ ላይ ጭምር ክተት ማወጅን ይጠይቃል፤ ከመድረክ ባሻገር ወደ ተጨባጭ ትግል መግባት የግድ ይላል፡፡ ይህ ሲሆን ህብረብሔራዊነት ይደምቃል፤ ብዝሃነት ያብባል፤ ዴሞክራሲያዊነት ይጎመራል፡፡ መፍረስ እና መተላለቅ ድሮ ቀርቶ በመቻቻልና በመከባበር ተተክቶ የበለጸገች አዲሲቷን ኢትዮጵያ መገንባት ተችሏል እያልን ለቀሪዎቹ ድሎች በአንድነት በህብረት እጅ ለእጅ ተያይዘን ህዳሴያችንን እናበስራለን፡፡

No comments:

Post a Comment