EPRDF is a ruling party committed to realize Ethiopia's Renaissance.

Monday 15 December 2014

የንስር ህዳሴና አሮጌ አስተሳሰቦች

በአዲሱ አረጋ ቂጤሳ (ሚኒስትር ዲኤታ)
ከበራሪ አዕዋፋት እንደ ንስር ፈጣን የመብረር ችሎታና ጥሩ የእይታ ብቃት ያለዉ የለም፡፡ ንስር ከሌሎች አዕዋፋት ረጅም ዕድሜም እንደሚኖር ይታወቃል፡፡ ቢያንስ እስከ ሰባ አመታት በህይወት መቆየት ይችላል፡፡ ይህን ሁሉ ዘመን በህይወት ሲኖር ግን ነገሮች አልጋ በአልጋ ሆነዉለት አይደለም፡፡ በህይወት ዘመኑ እጅግ የሚያሳምም የመታደስ ዉሳኔመወሰን፣ የወሰነዉን ዉሳኔ ደግሞ በጥብቅ ንስራዊ ዲሲፕሊን ለመፈጸም ይገደዳል፡፡ ይህን ዉሳኔ ወስኖ ህመሙን ችሎ ካልፈጸመው ያለዉ አማራጭ መሞት ብቻ ይሆናል፡፡
ንስር እድሜዉ አርባ አመት ሲሞላዉ አካሉ ያረጃል፡፡ ሹል፣ ረዣዥም እና ጠንካራ ጥፍሮቹ ይዶለዱሙና ይደክማሉ፡፡ ለንስሩ የዕለት ምግቡን መንጭቀዉ ማንሳት ያቅታቸዋል፡፡ ንስሩ የሚታወቅበት የሾለ ምንቃሩ ወይም አፉ ከዕድሜ ብዛት ወደ ደጋንነት ይቀየራል፡፡ ክንፎቹም ይዝላሉ፡፡ ላባዎቹ ይነትቡና በበረራ ፍጥነቱ ይታወቅ የነበረዉ ፍጡር እንደዶሮ ጫጩት መብረር ያቅተዋል፡፡
በዚህን ጊዜ ንስሩ ሁለት አማራጮች ብቻ ይኖሩታል፡፡ ወይ አምስት ወራት የሚፈጅ እጅግ የሚያሳምም የመታደስ ዉሳኔ መወሰን አሊያም መሞት፡፡ ደግነቱ ንስር በደመነፍሱ አሮጌ አስተሳሰብ ሞትን እንደሚያስከትልበት ስለሚረዳ ሁሌም አንደኛዉን አማራጭ ብቻ በመዉሰድ በአዲስ አስተሳሰብ ይወስናል፡፡ ለዚህም ነዉ ንስሩ በአዲስ አስተሳሰብ ከሚያደርገዉ የመታደስ ጉዞ አንድንማር ይችን አጭር ጽሁፍ የጫርኩት፡፡
ንስሩ የመታደስ ዉሳኔዉን ተግባራዊ ማድረግ የሚጀምረዉ ለመታደስ በሚፈጽማቸዉ ተግባራት የሚያጋጥሙትን ህመሞች አስቀድሞ በመረዳትና ህመሙን የመታገስ አዲስ ንስራዊ አስተሳሰብ በመያዝ ነዉ፡፡ ያረጀ ምንቃሩን ለማስወገድ በተደጋጋሚ ከአለት ጋር መጋጨት ግድ ይለዋል፡፡ በዚህ በሚያሳምም ሂደት አሮጌዉ ምንቃር ተነቅሎ ይወገዳል፡፡ በአሮጌዉ ፈንታም አዲስ፣ ጠንካራና የሾለ አዲስ ምንቃር ይተካል፡፡ በዚህ አዲስና ጠንካራ ምንቃርም እነዚያ ያረጁና እንደወትሮ በቅልጥፍና በጥንካሬ ምግብ መንጭቀዉ ማንሳት የተሳናቸዉን ጥፍሮቹን ህመሙን ቻል አድርጎ ይነቃቅላቸዉና ያስወግዳቸዋል፡፡ በተወገዱት ጥፍሮች ምትክም አዲስ፣ የሾሉ ጠንካራ ጥፍሮችን ያበቅላል፡፡ በአዲስ ምንቃር እና ጥፍሮቹ በመጠቀምም የወየቡና የነተቡ ላባዎቹን በማስወገድ ክንፉን ያድሳል፡፡
ይህ የንስር የህዳሴ ጉዞ ቢያንስ አምስት ወራትን ይወስዳል፡፡ በህመም የተሞላ ከሞት በስተቀር ሌላ አማራጭ የሌለዉ የዉሳኔና የተግባር ምዕራፍ የህዳሴ ጊዜ ነዉ፡፡ ንስሩ ይህን የህዳሴ ጊዜ እንደፈጸመም ወደ ከፍታዉ ይመለሳል፡፡ ሰማይ ላይ ከአዕዋፋት በላይ በተለመደዉ ፍጥነቱ ከነሙሉ ንስራዊ የእይታ ችሎታዉ ከፍ ብሎ መብረር ይጀምራል፡፡ እንደዶሮ ጫጩት ቆሻሻ መጫር አቁሞ ወደ ንስርነቱ ይመለሳል፡፡ ይታደሳል፡፡
የሀገራችን አጠቃላይ የህዳሴ ጉዞም ከንስሩ የህዳሴ ጉዞ ጋር ተመሳሳይ ነዉ፡፡ ንስሩ እርጅና ሳይጫጫነዉ በፊት እንደነበረዉ ገናናትና ከፍታ እኛም እንደሃገር በአለም ሥልጣኔ ገናና ታሪክና ከፍታ ላይ ነበርን፡፡ በኪነ ሕንጻ፣ በፖለቲካ፣ በስነ ጽሁፍ፣ በጦርነት ጥበብና ጀግንነት ሀገራችን በጥንቱ ዘመን የነበረችበትን ከፍታ ለመገንዘብ ሌላ ምስክር አያሻንም፡፡ ታሪካዊ ቅርሶቻችን ብቻ በቂ ምስክሮች ናቸዉ፡፡
በሂደት በተለያዩ ዉጭያዊና ባብዛኛዉ ግን ዉስጣዊ በሆኑ ችግሮች ከስልጣኔ ከፍታችን አቆለቆልን፡፡ እርሻንና የተለያዩ የእህል ዝርያዎችን ያስተዋወቅን የዳቦ ቅርጫት የነበርን ህዝቦች፤ የእርሻ ስልጣኔያችን ከስሞ ራሳችንን መመገብ ያቃተን ረሃብተኛ ሕዝብ ሆንን፡፡ ድንቅ የኪነ ሕንጻ ጥበብ ላይ ደርሰን የነበርን ህዝቦች ከከፍታችን ለቀን የረባ ጎጆ ሰርተን መኖር አቃተን፡፡ በአለም ሕዝቦች ዘንድ መታወቂያችን ገናናነታችንና ስልጣኔያችን መሆኑ ቀርቶ ረሃብ፣ ችግር፣ ኋላ ቀርነትና ድንቁርና ሆነ፡፡
ይሄኔ አርባ እድሜ እንደሞላዉ ንስር ሁለት አማራጮች ብቻ ከፈታችን ተደቀኑ፡፡ ጊዜ የሚወስድ እጅግ የሚያሳምም የመታደስ ዉሳኔ መወሰን አሊያም እንደሀገር መሞት፡፡ በርግጥም በህዳሴዉ ጀግና ትዉልድ በአዲስ አስተሳሰብ አንደኛዉን ዉሳኔ ወስኖ በሀገር ፍቅር ስሜት የህዳሴ ጉዞ ጀምረናል፡፡ የህዳሴ ጉዞአችንን የተጋረጡ አሮጌ አስተሳሰቦች ቢኖሩም ጉዞአችንን ወደፊት ቀጥለናል፡፡
እነሆ በአዲስና ተራማጅ አስተሳሰብ አሮጌ ማንነታችን አፈራርሰን በአዲስ ወደ መተካት ገባን፡፡ አሮጌ መንገዶቻችንን ማፈራረስ ተያያዝነዉ፡፡ አሮጌ መንገድ ሲፈርስ አሮጌ መንደርም አብሮት መፍረሱ አይቀሬ ሆነ፡፡ አሮጌ መንገዶች ሲፈርሱ በአዲስ እስኪተኩ መንገድ ተዘጋግቶ ሊያበሳጨን ሊያሳምመን ይችል ይሆናል፡፡ አሮጌ ሰፈር ፈርሶ በአዲስ እና ዘመናዊ የመኖሪያ መንደር ዉስጥ እስከምንደላደል ድረስ የአሮጌዉ ሰፈር ትዝታና አሮጌዉ አስተሳሰባችን ሊያሳምመን ይችላል፡፡ ነገር ግን ከንስሩ ተምረን ቻል ማድረግ ነዉ፡፡ ንስሩ ምንቃሩን ሲያድስ እንዳመመዉ አይነት አይቀሬና ልንታገሰዉ የሚገባን የለዉጥ ህመም፡፡ ያለን ብቸኛዉ አማራጭ ህመሙን ዋጥ አድርጎ እንደሃገር ወደ ከፍታችን መመለስ ነዉ፡፡
ይህ መፍረስ እንደ ሞቃዲሾ በእርስ በርስ ጦርነት በላዉንቸርና በመድፍ ጥይት የተሰከተ መፍረስ አይደለም፡፡ ይህ የህዳሴ ሂደት ያመጣዉ መፍረስ ነዉ፡፡ ባጭር ጊዜ በርካታ አዳዲስ ዘመናዊ መንገዶችንና የባቡር ኔትዎርኮችን ገንብተን ወደ ከፍታችን የምንንደረደርበት የህዳሴ ጉዞ ነዉ፡፡  
አፍርሶ የመገንባቱ ሂደት ከሚያደርስብን ጊዜያዊ ህመም ይልቅ ለመንገድ ልማት የሚያስፈልገንን ገንዘብ በብድር እንዳናገኝና ህዳሴያችንን እንዳናረጋግጥ ሌት ተቀን የሚሰሩ ባለ አሮጌ አስተሳሰብ ሃይሎች ሃገርን ስለሚጎዱ አሮጌ አስተሳሰባቸዉ ይታደስ እንላለን፡፡ ለመንገድና ለባቡር መስመር ዝርጋታ ወሳኝ የሆነዉን የዜግነት ድርሻቸዉን ግብር እና ታክስ በመክፈል መወጣት ሲገባቸዉ ግብር እና ታክስ በመሰወር አፍርሶ የመገንባቱ ሂደት ከሚያደርስብን ጊዜያዊ ጉዳት በባሰ ሀገራዊ ሞትን ሊያስከትሉብን የሚችሉ አሮጌ አስተሳሰቦች ስላሉ መወገድ አለባቸዉ፡፡ አሮጌ መንገዶችና አሮጌ መንደሮችን አፍርሰን በአዲስ ለመተካት በምናደርገዉ ጥረት ከሚደርስብን ጊዜያዊ የስሜት መጎዳት ይልቅ የመንገድ ፕሮጀክቶች በሚፈለጉ የጥራት ደረጃ እንዳይፈጸሙ የሚያደርጉ የሙስና አሮጌ አስተሳሰቦች ሀገራዊ ሞት ስለሚያስከትሉ በአዲስ ህዝባዊ አስተሳብ ይቀየሩ፡፡
በየከተማዉ ጎዳናዎች ዳር፣ በየአዉራ ጎዳናዉ የተቆፈሩት ጉድጓዶች የተሌኮም መሰረተ ልማታችንን ማዘመኛ የፋይበር ኦፕቲክ መቅበሪያ እንጂ ባለአሮጌ አስተሳሰቦች እንደሚያሽሟጥጡት ‹‹ምሽጎች›› አይደሉም፡፡ በከተማ አዉራ ጎዳናዎች ምሽግ ያማረዉ ባለአሮጌ አስተሳሰብ በካይሮ ከተማ ጎዳናዎች በሚደረገዉ የርስበርስ ጦርነት ራስን ከጥይት ለመከላከል የተቆፈሩ ምሽጎችን መጎብኘት ከፈለገም መመሸግ ይችላል፡፡ በርግጥ አሮጌ ኬብሎች በአዲስ በመተካት ሂደት የቴሌፎንና የኢንተርኔት ኔትዎርክ መቋረጥ ያጋጥማል፡፡ ሳያሰተዉል ጊዜያዊ የኬብል መቅበሪያ ጉድጓዱ ዉስጥ ገብቶ ለመጠነኛ ጉዳት የተዳረገ ሰዉም ሆነ እንስሳ ሊኖር ይችላል፡፡ ይህ ጊዜያዊ ህመም ነዉ፡፡
ስለሆነም ባለ አሮጌ አስተሳሰቦች ሆይ! ኢትዮ ቴሌኮም ባቀረበላችሁ ኔትዎርክ እየተጠቀማችሁ፣ በየማህበራዊ ድረ ገጾቻችሁ በርግማን ዉርጅብኝና በነቆራ አሮጌ አስተሳሰባችሁ በዘመቻ አታንቋሹት፡፡ የአራተኛዉ ትዉልድ ኔትዎርክ በመዘርጋት እንደሀገር ወደ ከፍታችን እንድንመለስ በከፍተኛ ሕዝባዊ ዲሲፕሊን ተልዕኮዉን በመወጣት ላይ ያለ ልንኮራበት የሚገባን ሀገራዊ ተቋም ነዉ፡፡
ባለ አሮጌ አስተሳሰብ አሽሟጣጮች ሆይ! ከቻላችሁ አስተሳሰባችሁን በማደስ ተቋሙን በዕዉቀትና በጉልበት በመደገፍ የዘርፉ የልማት ተልዕኮ እንዲሳካ የበኩላችሁን አስተዋጽኦ አድርጉ፡፡ ካልቻላችሁ ግን ጊዜያዊ የለዉጥ ጉዞአችን ያስከተለዉን ሕመም ቻል አድርጉት፡፡ እኛ አሮጌ አስተሳሰቦችን በመፍራት ሀገራዊ ሞት መሞት አንፈልግም፡፡ ከቴሌ አሮጌ ኔትዎርክ በባሰ ሁኔታ እኩይ ድርጊቶችን የሚወልዱ፣ ሀገርንና ህዝብን የሚጎዱ ሀገራዊ ሞትን ሊያስከትሉ የሚችሉ በሀገር በቀል ታላላቅ ተቋማት ላይ ያነጣጠሩ የገነገኑ አሮጌ አስተሳሰቦች ስላሉ ይታደሱ እንላለን፡፡
ያለንን የተፈጥሮ እምቅ ሀብቶች በመጠቀም በቂ የኤሌክትሪከ ሃይል በማመንጨት የሃይል ፍላጎታችንን በማሟላት፣ የሚተርፈንን ደግሞ ለጎሮቤት ሀገራት በመሸጥ የዉጪ ምንዛሪ ለማገኘት፤ ከምንም በላይ ደግሞ መልካም ጉርብትናና ኢኮኖሚያዊ ትስስርን ለማጠናከር በአዲስ አስተሳሰብ ወስነን በመስራት ላይ እንገኛለን፡፡ የኤሌክትሪክ ሃይል አቅርቦታችንን ለማሳደግ ታላቁ የሕዳሴ ግድብ፣ የግልገል ጊቤ 3 ፕሮጀክቶችን ጨምሮ በርካታ ፕሮጀክቶች እየተሰሩ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ የሀይል ማሰራጫ ኔትዎርካችንም የምናመነጨዉን ሃይል መሸከም የሚችልና የሃይል ብክነትን እንዲቀንስ ለማድረግ አሮጌዉን የኤሌክትሪክ ማሰራጫ መሰረተ ልማት በአዲስ የመተካት ስራ በመሰራት ላይ ይገኛል፡፡
አሮጌዉን ኔትዎርክ በአዲስ ለመተካት በሚደረገዉ ጥረት መብራት ተቋርጦብን ጨለማ ዉስጥ አድረን ተበሳጭተን ይሆናል፡፡ በሃይል መቋረጥ ዕለታዊ ስራችን ተስተጓጉሎብን ይሆናል፣ በሃይል መዋዠቅ ዕቃዎች ተቃጥለዉብንም ይሆናል፡፡ ከዚህም የከፋ ችግር ደርሶብን ሊሆን ይችላል፡፡ ይህ ሁሉ እንደሚያሳምም ጥርጥር የለዉም፡፡ ነገር ግን ይህ ህመም ንስሩ ያረጁ ጥፍሮቹን ነቃቅሎ ሲያስወግድ እንደተሰማዉ አይነት የመታደስ የለዉጥ ሂደት የሚያስከትለዉ ህመም እንደሆነ መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡
ችግሮቹ የተከሰቱት አሮጌ የሃይል መሰረተ ልማት አዉታሮቻችንን በአዲስ ለመተካት በምናደረገዉ ሂደት እንጂ እንደ ሶሪያ በርስ በርስ ጦርነት የሃይል መሰረተ ልማት ስለወደመብን አይደለም፡፡ የሀይል መሰረተ ልማት እንዳይስፋፋ በመንግስት በኩል ዳተኝነት ስላለም አይደለም፡፡ ከአሮጌዉ የኤሌክትሪክ ማሰራጫ መሰረተ ልማታችን እደረሰብን ካለዉ ጉዳት የበለጠ ሃገራችንን ለአደጋ የሚያጋልጠዉ ግን አሮጌ አስተሳሰብ ነዉ፡፡ ‹‹የህዳሴዉ ግድብ ለወያኔ የፕሮፖጋንዳ ፍጆታ ባለፈ ሊሳካ የሚችል አይደለም›› … ወዘተ የሚሉት አሮጌ አስተሳሰቦች አሮጌዉ የኤሌክትሪክ ማሰራጫ መሰረተ ልማታችን ካስከተለዉ ጉዳት በበለጠ ሃገራችንን የሚጎዳ አስተሳሰብ ስለሆነ ይታደስ እንላለን፡፡
ዲያስፖራዉ አካባቢ የህዳሴዉ ግድብ ግንባታን ለማሳካት የሚደረገን እንቅስቃሴ ለማስተጓጎል፤ ይህን ታላቅ ሀገራዊ ፕሮጀክት የኢህአዴግ ብቻ ፕሮጀክት አስመስሎ በማቅረብ የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራሞችን ለማደናቀፍ የሚደረጉ ካሮጌ አስተሳሰብ የመነጩ እንደሀገር የሚገድሉን አደገኛ አሮጌ ድርጊቶች ስላሉ በአዲስ አስተሳሰብ ይቀየሩ እንላለን፡፡
የህዳሴዉ ግድብ እንዳይሳካ ከግብጽ እና ከኤርትራ እርዳታ በመቀበል መሰረተ ልማቶቻችንን በፈንጂ ለማጋየት የተነሱ ባለአሮጌ አስተሳሰብ የሃገር ጡት ነካሽ ጠላቶች ስላሉ ይታደሱ እንላለን፡፡ ከአሮጌዉ የኤሌክትሪክ ማሰራጫ መሰረተ ልማታችን በከፋ ሁኔታ ሕዝባችንን ለአደጋ የሚጋልጠዉና ሀገራዊ ሞትን የሚያስከትለዉ ከአሮጌ መሰረተ ልማት ይልቅ አሮጌ አስተሳሰብ ነዉና!

No comments:

Post a Comment