EPRDF is a ruling party committed to realize Ethiopia's Renaissance.

Monday, 6 October 2014

የኢፌዴሪ ፕሬዚዳት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ ሙሉ ንግግር

የኢፌዴሪ ፕሬዚዳት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ በአራተኛው የህዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች አምስተኛ የሥራ ዘመን የመጀመርያ የጋራ ስብሰባ ላይ ያደረጉት የመክፈቻ ንግግር

የተከበራችሁ የህዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባላት፣
ጥሪ የተደረገላችሁ እንግዶችና
መላው የአገራችን ህዝቦች

ከሁሉ አስቀድሜ የሁለቱን ምክር ቤቶች 4 ዙር አምስተኛ ዓመት የስራ ዘመን የጋራ ስብሰባ በማካሄድ የአዲሱን ዓመት ሥራ በይፋ በመጀመራችን የተሰማኝን ደስታ በኢፌዴሪ መንግስትና በራሴ ስም ለመግለጽ እወዳለሁ፡፡ እንኳን አደረሰን፡፡

2007 በጀት ዓመት መንግስትና መላው የአገራችን ህዝቦች ዕድገት እና ትራንስፎርሜሽን ለማምጣት የያዙት የአምስት ዓመት የዕቅድ ዘመን የመገባደጃ ዓመት ነው፡፡ በመሆኑም የዓመቱን የዕቅድ አቅጣጫዎች በውል ለመገንዘብ እንዲያስችለን ያለፉትን አራት የመርሃ ግብር ዓመታት ዋና ዋና ጉዳዮች በመዳሰስ የ2006 አፈጻጸም መመልከት ተገቢ በመሆኑ እንደሚተለው አቀርባለሁ፡፡
የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዳችን መተግበር ከጀመርንበት 2003 ወዲህ ባሉት ተከታታይ አራት የትግበራ ዓመታት ኢኮኖሚያችን በአማካይ በ10ነጥብ1 በመቶ ዕድገት አስመዝግቧል፡፡ በኢኮኖሚያችን ፈጣን መዋቅራዊ ለውጥ ለማምጣት የሚቻለው የማኑፋክቸሪንግ ንዑስ ዘርፍ በኢኮኖሚው ውስጥ ያለው ድርሻና የሚፈጥረው የስራ ስምሪት መጠን በፍጥነት እያደገ ሲሄድ ነው፡፡ በኢኮኖሚው አወቃቀር የታቀደውን ትራንስፎርሜሽን ለማምጣት፤ ማኑፋክቸሪንግ በኢኮኖሚው ውስጥ የላቀ አስተዋጽኦ እንዲጫወት ለማድረግና ኢንዱስትሪላይዜሽን ለማረጋገጥ በማኑፋክቸሪንግ ንዑስ ዘርፍ አሁን እየታየ ካለው ዕድገት በላይ የፈጠነ የዕድገት ምጣኔ ማረጋገጥ ያስፈልጋል፡፡ በዚህ ረገድ ባለፉት አራት ዓመታት የነበረውን ልምድ መነሻ በማድረግ 2007ዓም ለዘርፉ ፈጣን ዕድገት አበክረን መስራት ይገባናል፡፡
2006 አፈጻጸም ዓመታዊ እድገት 10.3 በመቶ መሆኑ ተረጋግጧል፡፡ ይኸው እድገት ባለ ሁለት አሃዝ በመሆኑ የኢኮኖሚያችንን የእድገት ፍጥነት ቀጣይነት የሚያረጋግጥ ነው፡፡ ከዚህ ውስጥም የኢንዱስትሪው የዕድገት በላቀ ፍጥነት እየተጓዘ መሆኑ ታይቷል፡፡ በያዝነው ዓመትም ባለ ሁለት አሃዙን ዕድገት በማስቀጠል 11.4በመቶ የጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት ዕድገት ለማምጣት ርብርብ ይደረጋል፡፡ ከእድገት ፍጥነቱ ባሻገር በጤናማ ሁኔታ የተረጋጋ ማክሮ ኢኮኖሚ ውስጥ እየተመራ የመጣ መሆኑ ሊሰመርበት የሚገባ ነው፡፡ የዋጋ ግሽበትን መቆጣጠር አንዱ መሰረታዊ ጉዳይ ሲሆን በዚህ ረገድ መንግስት አስፈላጊ ናቸው ብሎ ያመነባቸውን የሞኒተሪና ፊስካል ፖሊሲዎችን ተግባራዊ በማድረግ የዋጋ ንረቱ በአንድ አሃዝ ተወስኖ እንዲቆይ ለማድረግ ተችሏል፡፡ 2007. ይኸው የመንግስት ፖሊሲ ተጠናክሮ ይቀጥላል፡፡ የዋጋ ንረቱ በአንድ አሃዝ ደረጃ ተወስኖ እንዲቆይ ለማድረግ የመሰረታዊ ምግብ ፍጆታ ዕቃዎችን አቅርቦት ቀጣይነት በማረጋገጥ እንዲሁም የንግድ ርዓቱን ዘመናዊና ቀልጣፋ ለማድረግ የተጀመረው አቅጣጫ ተጠናክሮ ይቀጥላል፡፡
የገቢና ወጪ ንግድ አፈጻጸም ጤናማ መሆን ለኢኮኖሚ ዕድገቱ ዘላቂነት ወሳኝ ነው፡፡ ከዚህ አኳያ ባሳለፍነው አመት ከሸቀጦች ኤክስፖርት ንግዳችን የተገኘው ገቢ ከእርሱ ቀደም ባለው ዓመት ከተገኘው ገቢ ጋር ሲነጻጸር 4 ነጥብ በመቶ ዕድገት ያስመዘገበ ሲሆን በዓመቱ ይመዘገባል ተብሎ ከተያዘው ግብ አንጻር ግን ከፍተኛ ጉድለት የታየበት ነው፡፡ የጉድለቱ ዋነኛ መንስኤም በዓለም ገበያ ዋጋቸው የወረደው ወርቅና ቡና ለማካካስ ባሰብነው ልክ በመጠን ከፍ በማድረግ ለዓለም ገበያ ማቅረብ አለመቻላችን ነው፡፡ የኢንዱስትሪ ምርቶችን በመጠንና በጥራት ለዓለም ገበያ ማቅረብ አለመቻላችን ሌላው ችግር ነበር፡፡ በአንጻሩ ደግሞ የገቢ ንግድ አፈጻጸማችን በከፍተኛ መጠን ያደገ በመሆኑ የንግድ ሚዛኑ ከፍተኛ ጉድለት የታየበት ዓመት ነበር፡፡ ባሳለፍነው ዓመት የነበረውን ይኸን ጉድለት ለማማካካስ የተቻለው ከቱሪዝም ዘርፉና ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ከመቼውም ጊዜ የተሻለ አግልግሎት ኤክስፖርት በመደረጉ እንዲሁም ከሬሚታንስ ነው፡፡ ከዚህ አኳያ የውጭ ንግዱን ምጣኔ ለማሻሻል የፌደራልና የክልል መንግስታት በክፍተኛ ቅንጅት የሚሰሩበት ዓመት ይሆናል፡፡ በዚህ መሰረት የበጀት አመቱን የኤክስፖርት ገቢ ወደ አምስት ቢሊዮን ለማድረስ ርብርብ ይደረጋል፡፡
የፌደራል መንግስት ያለፈው ዓመት ፋይናንስ አፈጻጸም ከታክስ፣ ታክስ ካልሆኑ ገቢዎች፣ የቀጥታ በጀት ድጋፍና ዕዳ ቅነሳን ጨምሮ 122ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ ተችሏል፡፡ ከዕቅዱ ጋር ሲነጻጻር 106 በመቶ አፈጻጸም ያለው ሲሆን ካለፈው በጀት ዓመት ጋር ሲነጻጸር 17 ነጥብ 6 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል፡፡ የተመዘገበው የገቢ አሰባሰብ ውጤት በሚታይበት ጊዜ የገቢ አቅማችንን በየወቅቱ ይበልጥ በማስፋት የልማት ፍላጎታችንን በራሳችን ገቢ ለመሸፈን ያለን አቅም ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን ያሳያል፡፡ ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ አሁንም ከሰሃራ በታች ከሚገኙት የአፍሪካ ሀገራት አንጻር የታክስ ገቢው ከአጠቃላይ ሀገር ምርት ጋር ያለው ንጽጽር ሲታይ የእኛው በእጅጉ አንሶ ይገኛል፡፡ ስለሆነም አሁንም ተሟጦ ያላለቀ አቅም ያለን በመሆኑ ይበልጥ ጠንክሮ መስራት ያስፈልጋል፡፡ በመሆኑም የተገኘውን ልምድ በማጠናከር በያዝነው ዓመትም ገቢያችንን ለማሳደግ ከፍተኛ ርብርብ ይደረጋል፡፡
የባለፈው ዓመት የመንግስት የወጪ አሸፋፈን በሚታይበት ጊዜ ለፌደራል መንግስት መደበኛ፣ ካፒታልና ለክልሎች ጠቅላላ የበጀት ድጋፍ አፈጻጸም ከዓመቱ ዕቅድ አንጻር 96 በመቶ ክንውን ነበረው፡፡ በ2005ዓም ከነበረው አፈጻጸም 15 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል፡፡ በተከታታይ የተመዘገበው የክዋኔ መሻሻል የመንግስት የወጪ አስተዳደርን በዕቅድ ለመምራት የተደረገው ጥረት ውጤታማ መሆኑን ያሳያል፡፡ ይኸው የበጀት ዲሲፕሊን በያዝነው ዓመትም ተጠናክሮ ይቀጥላል፡፡

የተከበራችሁ የህዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባላት፣
ጥሪ የተደረገላችሁ እንግዶችና
መላው የአገራችን ህዝቦች
የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዳችንን ተግባራዊ ለማድረግ የሚጠይቀው የኢንቨስትመንት መጠን ከፍተኛ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ከዚህ አኳያ ኢንቨስትመንታችንን በአገር ውስጥ የፋይናንስ አቅርቦት ለመሸፈን እንዲቻል በዝቅተኛ ደረጃ የሚገኘውን የሀገሪቱን የቁጠባ መጠን ማሳደግ ይጠይቃል፡፡ ይህንን የአገር ውስጥ ቁጠባ ምጣኔ ለማሳደግ የተጀመሩትን የሪፎርም ስራዎች ትግበራና ህብረተሰቡን የማስተማርና የማነሳሳት ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ፡፡ የፋይናንስ አገልግሎቶች የሚሰጡባቸውን ተቋማት በማስፋፋት፣የወለድ ምጣኔ በማሻሻል፣ የግል ማህበራዊ ዋስትና አገልግሎት በመዘርጋት እንዲሁም የመንግስት የማህበራዊ ዋስትና ሽፋንን ይበልጥ ለማጠናከር በተጀመሩት  እንቅስቃሴዎች ባለፉት ዓመታት አበረታች ውጤት ተመዝግቧል፡፡ አገራዊ ቁጠባ በዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዳችን ስንጀምር ከነበረበት 5 ነጥብ 2 በመቶ ባሳለፍነው ዓመት 22 በመቶ ደርሷል፡፡ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ቁጠባ ቦንድን ጨምሮ ሌሎች በጅምር ላይ ያሉ የቁጠባ መንገዶች ለቁጠባ ባህል መዳበር አስተዋጽኦ በማድረግ ላይ ይገኛሉ፡፡ በመሆኑም በዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዳችን መጨረሻ ይደረስበታል ብለን ያስቀመጥነውን 15 በመቶ ግብ አስቀድመን ያሳካን ስለሆነ የተጀመረውን ግለት ጠብቆ እንዲሄድ በያዝነው ዓመት በከተማም በገጠርም ተጠናክሮ ይቀጥላል፡፡
በተያያዘም ከአራት ዓመት በፊት ዕቅዳችንን ስንጀምር በኢኮኖሚው ውስጥ የተደረገው የኢንቨስትመንት መጠን ከአጠቃላይ የሀገር ውስጥ ምርት የነበረው ድርሻ 28 በመቶ ብቻ ሲሆን ባሳለፍነው ዓመት መጨረሻ 40 በመቶ ደርሷል፡፡ አፈጻጸሙ እጅግ መልካም የሚባል ሲሆን በያዝነው ዓመትም ተጠናክሮ ይቀጥላል፡፡ በዚህ ረገድ ትኩረት የሚሻው ጉዳይ አሁንም መጠኑ የማይናቅ የኢንቨስትመንት ክፋይ በሀገር ውስጥ ቁጠባ ሳይሆን በውጭ ሀገር ቁጠባ ገንዘብ የሚሸፈን መሆኑ ነው፡፡ የዜጎችን የቁጠባ ባህል ከፍ ማድረግ የኢንቨስትመንት አቅማችን በቀጣይነት ከማሳደግ አንፃርም ወሳኝ ነው፡፡
ሀገራችን ምንም እንኳን በመንግስት ዋስትናም ሆነ ከዚያ ውጭ የምትወስደው የብድር መጠን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣ ቢሆንም በተለያዩ የዕዳ መለኪያዎች መሰረት ዝቅተኛ የዕዳ ጫና ካላቸው አገሮች ተርታ ትገኛለች፡፡ የያዝነውን በጀት ዓመት ጨምሮ በሚቀጥሉት ዓመታትም ይኸው ደረጃ ተጠብቆ ይቀጥላል፡፡
የተከበራችሁ የህዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባላት፣
ጥሪ የተደረገላችሁ እንግዶችና
መላው የአገራችን ህዝቦች
ከፍ ሲል የተገለጸውን የማክሮ ኢኮኖሚ አፈጻጸም መሰረት በማድረግ በኢኮኖሚና በማህበራዊ ልማት ዘርፎች ልማት የነበረው አፈጻጸም ሲታይ ግብርና አሁንም የኢኮኖሚያችን የጀርባ አጥንት ሆኖ ቀጥሏል፡፡ ከግብርና መስክም በአነስተኛ ማሳ የሚካሄደው የአርሶ አደርና ከፊል አርሶ አደር ግብርናና የአርብቶ አደር የእንስሳት እርባታ ስራ ከፍተኛውን ድርሻ ይዟል፡፡ የግብርና ምርታማነት ደረጃ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዳችንን ስንጀምር ከነበረበት በከፍተኛ መጠን አድጎ ባሳለፍነው ዓመት በሄክታር ወደ 20 ነጥብ 27 ኩንታል ማድረስ ተችሏል፡፡ ይህ ዕድገት 2005. ከነበረውም 7ነጥብ 6 በመቶ ብልጫ ያለው ነው፡፡ ይኸውም የግብርና ዕድገታችን መሬታችን በማስፋት ሳይሆን ምርታማነትን ማሳደግ ላይ የተመሰረተ መሆኑን ያሳያል፡፡
የምርታማነት እድገቱ ምንጭ ከዋና ዋና የምግብ ሰብሎች በተጨማሪ የኢንዱስትሪ ግብዓቶች የሆኑግብርና ምርቶች እና የኤክስፖርት ምርቶች የሆኑ እንደ ሰሊጥ እና ጥራጥሬዎች የመሳሰሉት ዝርዝር የልማት ዕቅድ ላይ ተመስርቶ በትጋት በመትግበር በመተግበሩ ነው፡፡ እንዲሁም ከምርት ዝግጅትና የተመረጡ ግብዓቶች ከመጠቀም ጋር የተያያዙትን ጨምሮ እስከ ድህረ ምርት ዝግጅትና የተመረጡ ግብዓቶችን ከመጠቀም ጋር የተያያዙትን ጨምሮ እስከ ድህረ ምርት ድረስ የተሟላ ፓኬጅ ተዘጋጅቶ ለመተግበር ጥረት በመደረጉ ነው፡፡ በተጨማሪም የተፈጥሮ ሚዛንን ለመጠበቅና የማሳና ከማሳ ውጭ ግብርናን በማስፋፋት የዜጎችን ተጠቃሚነት ለማሳደግ መንግስትና ህዝቡ ተቀናጅተው በማህበረሰብ ተፋሰስ ልማት ያደረጉት ጥረት ውጤት ነው፡፡
በተያያዘም የተፋሰስ ስራው ከዕቅድ በላይ የተፈጸመ ከመሆኑም በላይ ከገጠሩ ህዝባችን በቁጥር እስከ 26 ሚሊዮን ህዝብ የተሳተፈበትና በሰፊ ህዝባዊ ንቅናቄ የተፈጸመ ሥራ ነው፡፡ የተፈጥሮ ሃብትና የተፋሰስ ልማትን ተንተርሶ የተሰራው አነስተኛ የመስኖ ልማት ስራ ባሳለፍነው ዓመት በአንደኛና ሁለተኛ ዙር በሀገር አቀፍ ደረጃ እስከ 220 አዳዲስ መስኖ አውታሮችን በመጠቀም ማምረት ተችሏል፡፡ በአጠቃላይ የመስኖ እርሻ ሽፋን 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሄክታር ደርሷል፡፡ የአርሶ አደሮችና ከፊል አርብቶ አደሮች የተደራጀ እንቅስቃሴ ለተገኘው ውጤት መሰረት ነው፡፡ ይኸው እንቅስቃሴ በያዝነው ዓመትም ተጠናክሮ ይቀጥላል፡፡ በዚህ ሂደት የሀገር ውስጥ የምግብ ፍላጎት ለማርካት፣ ለኢንዱስትሪ ግብዓት የሚሆን በቂ ምርት ለማምረት፣ እንዲሁም የኤክስፖርት ምርቶችን ለማሳደግ እንዲቻል የግብዓት አቅርቦትና የኤክስቴንሽን ድጋፍ አሰጣጡ የተሟላ እንዲሆን ጥረት ይደረጋል፡፡
ከእንስሳት ሀብታችን በተገቢው ደረጃ ተጠቃሚ እንሆን ዘንድ ዝርያ የማሻሻልና የእንስሳት ጤና አገልግሎት የማደረስ ስራ በተቀመጠው አቅጣጫ መሰረት ለመፈጸም ጥረት ተደርጓል፡፡ ይህንኑ ትክክለኛ አቅጣጫ በማጠናከር ሀገራችን ያላትን ሰፊ የእንስሳት ዘርፍ ዕምቅ አቅም ታሳቢ ያደረገ ሰፊ የኤክስቴንሽን ሥራ በአርሶ አደሩ፣ ከፊል አርሶ አደሩ እና አርብቶ አደሩ አካባቢ ይሰራል፡፡
የተከበራችሁ የህዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባላት፣
ጥሪ የተደረገላችሁ እንግዶችና
መላው የአገራችን ህዝቦች
በሃገራችን እየተመዘገበ ያለውን የኢኮኖሚ እድገት ቀጣይነት ለማረጋገጥ የኢንዱስትሪውን ዘርፍ ማጠናከር ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ይገኛል፡፡ በተለይም የማኑፋክቸሪንግ ንዑስ ዘርፍ ገና በጣም ጠባብ ከሆነ መሰረት እየተነሳ ያለና በሀገራችንም የረባ ልምድ ያልዳበረበት ነው፡፡ በርካታ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት እየገባበት በመሆኑ የሚያበረታታ ሁኔታ የተፈጠረ ቢሆንም ሀገራዊ ባለሃብቱ አሁንም በዚህ መስክ እያደረገ ያለው ተሳትፎ አነስተኛ ነው፡፡ ከዚህ ባሻገር አነስተኛና ጥቃቅን አንቀሳቃሾችን ከወዲሁ በመኮትኮት ውጤታማ እንዲሆኑ ያልተቆጠበ ጥረት ያደርጋል፡፡
ባለፈው ዓመት ከዘርፉ የተገኘው ገቢ ይገኛል ተብሎ ከተጠበቀው በታች ነው፡፡ በማምረት ሂደት ላይ ያሉ ነባር ፋብሪካዎች ቢያንስ 80 በመቶ የማምረት አቅማቸውን እንዲያመርቱ፣ በግንባታ ሂደት ያሉ ፕሮጀክቶች ደግሞ በተያዘላቸው መርሃ ግብር መሰረት ወደ ስራ እንዲገቡና የተመረተው ምርት ለውጭ ገበያ እንዲቀርብ በመንግስት በኩል ድጋፍ ለመስጠት ጥረት እየተደረገ ቢሆንም የተሰጠው ድጋፍ ሙሉ እና በቂ አልነበረም፡፡ በተጨማሪም በዓመቱ ለነበረው የአፈጻጸም ጉድለት መንስኤ ከሆኑት መካከል የግብዓት አቅርቦት ማነስ፤ የምርት ጥራት ጉድለት፤ የኩባንያዎች የማኔጅመንትና የሰራተኞች ምርታማነት አናሳነት፤ የኩባንያዎች የቴክኖሎጂ አቅምና ትስስር ውስንነት፤ የመሰረተ ልማት አቅርቦት (በተለይም የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ማነስ፤ መቋረጥና የኃይል መዋዠቅ) ዋና ዋናዎቹ ችግሮች ነበሩ፡፡
በያዝነው በጀት ዓመት የተጠቀሱተን ችግሮች ለመፍታት ጥረት ይደረጋል፡፡ የማኑፋክቸሪንግ ኢንዳስትሪውን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ ጠንካራ፤ የተደራጀና የተቀናጀ ድጋፍና ክትትል በማድረግ፤ በፋብሪካዎች ላይ ያሉ ማነቆዎች እንዲፈቱ በኤክስፖርት ላይ ከፍተኛ አስተዋጾ ያላቸውን አዳዲስና የማስፋፊያ ፕሮጀክቶች ወደ ምርት እንዲሸጋገሩ ጠንካራ ክትትልና ድጋፍ በማድረግ፤ የአቅም ግንባታ ስራዎች ይሰራሉ፡፡ በአጠቃላይ የኢንዱስትሪ ልማታችንን ለማፋጠን በያዝነው በጀት ዓመትም የኢንዱስትሪ ግብዓት አቅርቦት እንዲሟላ፤ የሎጂስቲክሰና የተፋጠነ የጉምሩክ ስርዓት እንዲሰፍን፤ ቀጣይነት ያለውና እየሰፋ የሚሄድ የገበያና ምርት ትስስርን የሚያጠናክር የተቀናጀ መንግስታዊ ድጋፍ ለባለሀብቱ ለመስጠት ጥረት ይደረጋል፡፡
የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪዎችን ለማጠናከር የኢንቨስትመንትና የስራ ማስኬጃ ፋይናንስ አቅርቦት በወቅቱና በሚፈለገው መጠን መቅረቡን እና ፋብሪካዎች ያልተቆራረጠ፤ የማይዋዥቅ፤ የተረጋጋና አስተማማኝ የኤሌክትሪክ ሃይል ማግኘታቸውን ለማረጋገጥ ቀጣይነት ያለው ክትትል ይደረጋል፡፡ አምራች ኢንዱስትሪዎችን በጥራትና ምርታማነት ተወዳዳሪ ለማድረግ የአለም አቀፍ ምርጥ ተሞከር በመተግበር ኤክስፖርት ላይ ለተሰማሩ ፋብካዎች ምርታማነትን የሚያሳድገውን የካይዘን ፅንሰ ሃሳብ  አጠናክሮ በመተግበርና የሰራተኛው የስራ ባህልና ዲሲፒሊን እንዲዳብር አመላከከቱን የመቀየር ስራዎች ይሰራሉ፡፡
የጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማት ልማት የዜጎችን ተጠቃሚነት የሚያሳድግ ከመሆኑም በላይ የኢንዱስትሪ መሰረት እንደሆነ ከጅምሩ በማመን መንግስት ስትራቴጂ ቀርጾ ሲረባረብ ቆይቷል፡፡ በዚህ መሰረት የመስሪያና የመሸጫ ቦታ አቅርቦት፣ የስልጠና፣ የገበያ ትስስር፣ የብድር አቅርቦትና የምክር አገልግሎት ለማቅረብ ጥረት ይደረጋል፡፡ በመሆኑም የጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማትን በማስፋፋት ረገድም በተለይ በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ላይ ትኩረት ይሰጠዋል፡፡ ከዚህም ጋር በተያያዘ በፍጥነትና በአቋራጭ ለመክበር ያለውን የተሣሣተ አመለካት መታገል የስራ ፈጠራና በልማታዊ መንገድ የማደግ እድልን ማጠናከር ያስፈልጋል፡፡

የተከበራችሁ የህዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባላት፣
ጥሪ የተደረገላችሁ እንግዶችና
መላው የአገራችን ህዝቦች
የህዝቡን ተጠቃሚነት ማዕከል በማድረግ ልማታዊ መንግስታችን በትጋት እየተገበራቸው ከሚገኙት ፕሮግራሞች አንዱ የቤቶች ልማት ነው፡፡ በዚህ ፕሮግራም በተለይም በአዲስ አበባ ቁጠባን መሰረት በማድረግ ቀደም ሲል ለሴቶች ተጠቃሚነት ከተሰጠው ትኩረት ባሻገር የመንግስት ሰራተኛውን አካቶ ይቀጥላል፡፡ በማህበር ተደራጅተው የሚሰሩ ዜጎች በተያዘው አቅጣጫ መሰረት የሚስተናገዱ ይሆናል፡፡ ባለፈው ዓመት 22 ቤቶች ለተጠቃሚዎች የተላለፉ ሲሆን በያዝነው ዓመትም 73 ቤቶች ይተላለፋሉ፡፡ ባለፈው የበጀት ዓመት 65 ቤቶች ግንባታ የተጀመረ ሲሆን በያዝነው ዓመትም 65 ቤቶች ይጀመራሉ፡፡ በቤቶች ግንባታ ዙርያ የሚታየውን የፕሮጀክት ማኔጅመንት፤ የኮንትራክተሮችና አማካሪዎች የአቅም ውስንነት ችግሮች ለመቅረፍ ጥረት ይደረጋል፡፡ የዜጎችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በልማታዊ መንግስታችን ርብርብ ከሚደረግባቸው ጉዳዮች አንዱ ዜጎች የራሳቸውን ስራ እንዲፈጥሩ ከሚደረገው ድጋፍ ባሻገር በርካታ የስራ እድሎችን መፍጠር ነው፡፡ በዚህ መሰረት በሜጋ ፕሮጀክቶቻችንና በመደበኛ የስራ መስኮች ባሳለፍነው ዓመት 2.7 ሚሊየን ዜጎች ቋሚና ጊዜያዊ የስራ እድል መፍጠር ችለናል፡፡ ከዚህ ውስጥም 75 በመቶ በቋሚነት የተፈጠረ ነው፡፡
የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅዳችን መለያ ባህሪያት ተደርገው ከሚወሰዱት አንዱ የበርካታ ግዙፍ ሜጋ ፕሮጀክቶች ግንባታዎች ተጀምረው በእንቅስቃሴ ላይ መሆናቸው ነው፡፡ ከነዚህ ውስጥም ሀገር አቀፍ የገጠር መንገዶች ተደራሽነት ፕሮጀክቶች 11500. ባለፈው በጀት ዓመት በመገንት የእቅዱ 45 በመቶ ተፈጽሟል፡፡ የኮንትራክተሮች አቅም ማነስ፤ የፕሮጀክት ማኔጅመንት ልምድ ማነስ እንዲሁም በአመለካከት ችግሮች ምክንያት አፈጻጸሙ ዝቅተኛ ሆኗል፡፡ በያዝነው ዓመት ችግሮቹን በመቅረፍ አፈጻጸሙን ለማሻሻል ጥረት ይደረጋል፡፡
በፌዴራል መንግስት በሚሰራው የመንገድ ዘርፍ ልማት ፕሮግራም በመንገድ ማጠናከር፤ ማሻሻልና ግንባታ ከጊዜ ወደ ጊዜ መሻሻል እየመጣ ይገኛል፡፡ ባሳለፍነው ዓመትም በግንባታ መስክ 90 በመቶ በላይ አፈጻጸም የተመዘገበ ሲሆን በጥገና መስክም ተመሳሳይ ነበር፡፡ ይህም በአንዳንድ ኮንትራክተሮች ዘንድ ከታየው መስተጓጎል በስተቀር በዘርፉ እየጎለበተ የመጣ አቅም መፈጠሩን ያሣያል፡፡ በመሆኑም የተገኘውን ልምድ በማዳበር የሚታዩትን ችግሮች ለመቅረፍ ጥረት ይደረጋል፡፡
የዘመናዊ የባቡር ግንባታ ለሀገራችን አዲስ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ በእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅዳችን የተጀመሩት የአዲስ አበባ/ሰበታ -ሚኤሶ-ጅቡቲ ፕሮጀክት በሁለት ኮንትራክተሮች ተይዞ እየተፋጠነ ይገኛል፡፡ እንዲሁም የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ፕሮጀክትን በተያዘለት መርሃ ግብር መሰረት በመከናወን ላይ ነው፡፡ በያዝነው ዓመትም አገልግሎት መስጠት ይጀምራል፡፡
በአገር አቀፍ ኤሌክትሪክ ማዳረስ ፕሮግራም ባለፈው በጀት ዓመት 3000 ታቅዶ 643 መንደሮችና ከተሞች ተጠናቀው ኤሌክትሪክ እንዲያገኙ ተደርጓል፡፡ በአስፈጻሚ የሰው ሀይል እጥረትና በቁሳቁስ አቅርቦት ረገድ ያጋጠመ ችግር ተገምግሞ ለማስተካከል ጥረት በመደረጉ መሻሻል የታየበት ቢሆንም አፈጻጸሙ ዝቅተኛ ነው፡፡ በመሆኑም በያዝነው ዓመትም ጉድለቶቹ ታርመው የተጀመረው ጥረት ተጠናክሮ ይቀጥላል፡፡
ከሀይል አቅርቦት አንጻር ግዙፉና ከኤሌክትሪክ ኃይል በላይም ፋይዳ ያለውና መንግስትና መላው የሀገራችን ህዝቦች እየተረባረቡበት ያለው የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድብ ፕሮጀክት ሲሆን በተያዘለት መርሃ ግብር መሰረት በመከናወን ላይ ይገኛል፡፡ በአሁኑ ወቅት ግንባታው 40 በመቶ ገዳማ ደርሷል፡፡ በዚሁ አጋጣሚ መላውን የሀገራችንን ህዝቦች ለማመስገን እወዳለሁ፡፡
የግልገል ጊቤ3 የገናሌ ዳዋና ሌሎችም የንፋስና የጂኦተርማል እንዲሁም የውሃ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው መርሃ ግብር መሰረት በመከናወን ላይ ናቸው፡፡
ቀደም ሲል የተጠናቀቁትና ማመንጨት የጀመሩትን ይዘን 2300 ገዳማ ሜጋ ዋት ያለን ቢሆንም ከፈጣኑ ልማታችን እንዲሁም በትላልቅ ከተሞች አካባቢ ከተፈጠረው ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ኃይል ፍላጎት አንጻር ካለው የማስተላለፊያና ማሰራጫ መስመሮች እንዲሁም በተቋሙ ከቆየው የመልካም አስተዳደር ችግር ጋር ተደማምሮ ህዝባችንና ልማታዊ ባለሃብቱ በቂና የማያቆራረጥ ኃይል እያገኙ እንዳልሆነ መንግስት ይገነዘባል፡፡ በዚሁ አጋጣሚ ለተፈጠረው መስተጓጎል በታላቅ አክብሮት ይቅርታ እንጠይቃለን፡፡
የመገናኛና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ዘርፍ ከእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ አኳያ አንዱ እድገት የታየበት ዘርፍ ነው፡፡ የአገሪቱን የገጠር ቀበሌዎች የስልክ አገልግሎት ተጠቃሚ ለማድረግ በተያዘው እቅድ መሰረት በአጠቃላይ የቴሌኮም አገልግሎት ተጠቃሚ የገጠር ቀበሌዎች ቁጥር 15875 ደርሷል፡፡ ይህ አፈጻጸም GTP እቅዳችን ጋር ሲነጻጸር 96 በመቶ ደርሷል፡፡ በዚህ መሰረት የሞባይል ተጠቃሚዎች ቁጥር 28.5 ሚሊየን፤ የኢንተርኔት 6.7 ሚሊየን የደረሰ ሲሆን የገመድ አልባ አገለግሎት አገራዊ የቆዳ ሽፋን 73በመቶ ደርሷል፡፡ ይሁን እንጂ በአገልግሎት አሰጣጡ የሚታዩትን መቆራረጥና ሌሎች የጥራት ችግሮች ለመፍታት ብዙ ስራ መስራት ይጠበቃል፡፡ በአዲስ አበባ የነበረውን የአገልግሎት ጥራትና ተደራሽነት ችግር 2006 መጨረሻ መቅረፍ ተችሏል፡፡
የትራንስፎርሜሽን እቅዱን ለማሳካት ቁልፍ ሚና የሚኖራቸውን የመንገድ፤ የአየርና የማሪታይም ትራንስፖርት ግንባታዎች ጥራታቸውን ጠብቀው በተመጣጣኝ ወጪ ሀገራዊ አቅምን በሚገነባ መልኩ ለማከናወን ጥረት ይደረጋል፡፡ በተያያዘምተለያዩ የሀገሪቱን የልማት ማዕከላት እንዲሁም ከጎረቤት ሀገሮችና ከተለያዩ ወደቦች ጋር የሚያስተሳስር ሀገራዊ የባቡር ኔትወርክ ግንባታ ተጠናክሮ ይቀጥላል፡፡ የአዲስ አበባን የቀላል ባቡር ፕሮጀክት የግንባታ ስራ በማፋጠን በተባለው ጊዜ እንዲጠናቀቅ ይደረጋል፡፡
በሌላ መልኩም የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብና የግልገል ጊቤ3 እንዲሁም ሌሎች የሃይል ማመንጫ ፕሮጀከቶቻችን የስራ አፈጻጸም በማሻሻል የኢነርጂ ግቦቻችንን ለማሳካት ከፍተኛ ጥረት ማድረግ ይጠበቅብናል፡፡ ከተለያዩ የታዳሽ ምንጮች በተጨማሪ የኃይል ምንጭ ማልማቱም ተጠናክሮ ይቀጥላል፡፡ ተፈላጊ የሆኑ የኃይል ማስተላለፊያና ማከፋፈያ መስመሮች ዝርጋታና ነባሮቹንማሻሻል ስራም እንዲሁ በተደራጀ መልኩ በማከናወን የአገልግሎት አቅርቦት ጥራቱን የተሻለ ለማድረግ ጥረት ይደረጋል፡፡ ለዚህም ይረዳ ዘንድ የተጀመረውን የተቋማት የለውጥ ስራ እንቅስቃሴ በጥራት የማከናወን ጉዳይ ትኩረት ተሰጥቶት ይከናወናል፡፡
በተመሣሣይም የቴሌኮም መሰረታዊ ልማቱን በማስፋፋት የአገልግሎቱን ተደራሽነት ማሳደግና የአገልግሎቱን ጥራት የማሻሻል ስራ በበጀት ዓመቱ ይከናወናል፡፡  በእድገትና ትራንስፎርሜሽኑ እቅዱ ተግባራዊ መደረግ ያለባቸውን ሌሎች ሜጋ ፕሮጀክቶችን ማለትም የስኳር ልማት እና የማዳበሪያ ፋብሪካ ግንባታዎች በከፍተኛ ትኩረት እና ክትትል በተያዘላቸው ጊዜ እንዲጠናቀቁ ርብርብ ይደረጋል፡፡
የመጠጥ ውሃ አቅርቦትን በተመለከተ የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅዱ መጀመሪያ ሲዘጋጅ በዓመት በአማካይ 6.5 ሚሊየን ህዝብ የንጹህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚ በማድረግ አገራዊ ሽፋናችንን 98.5 በመቶ ለማድረስ ታሳቢ ያደረገ ነበር፡፡ የመጀመሪያ ሶስት ዓመት አፈጻጸም መልካም የነበረ ቢሆንም 6.5 ሚሊየን ህዝብ በዓመት የንጹህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚ ለማድረግ የተያዘው 98.5 በመቶ ግብ ጋር መድረስ እንደማያስችል ታውቋል፡፡ በመሆኑም በያዝነው ዓመት አፈጻጸሙን ለማሻሻል ጥረት ይደረጋል፡፡
ከተሞቻችን በፈጣን እድገት ውስጥ ቢሆኑም ከመጠጥ ውሃ አቅርቦት በቀር የከተማ ሳኒቴሽን አገልግሎት አልነበራቸውም፡፡ ይህም ከተሞቻችን ለኑሮ የተመቹና የቱሪስት መዳረሻ ከማድረግ አንጻር አሉታዊ ሚና አለው፡፡ በሚቀጥለው የዋሽ ፕሮግራም የከተማ ሳኒቴሽን ስራ አንድ የትኩረት አቅጣጫ የተያዘ ሲሆን ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል፡፡

የተከበራችሁ የህዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባላት፣
ጥሪ የተደረገላችሁ እንግዶችና
መላው የአገራችን ህዝቦች
ማህበራዊ ልማትን በተመለከተ በተለይም የትምህርት ጥራትን ለማሳደግ ትኩረት በማድረግ በተቀረጹት ፓኬጆች ትግበራ በትምህርት ጥራት ላይ አወንታዊ መሻሻል ተመዝግቧል፡፡ የትምህርት ጥራት ማሻሻያው ማዕከል አቅም ግንባታ በመሆኑ የመጀመሪያ ደረጃና ሁለተኛ ደረጃ /ቤቶችን ርዕሳነ መምህራንና ሱፐርቫይዘሮችን አቅም ከማሳደግ አንጻር ከፍተኛ ስራ የተሰራ ሲሆን ዲፕሎማ የነበራቸውን ወደ መጀመሪያ ዲግሪ፤ የመጀመሪያ ዲግሪ ያላቸውን እንዲሁ ወደ ሁለተኛ ዲግሪ የማሸጋገር ስራ ተሰርቷል፡፡ በስራ ላይ ያሉ የዲፕሎማ መምህራንን ዲግሪ፤ 2 ደረጃ ባለዲግሪ መምህራንን የሁለተኛ ድግሪ ትምህርት እንዲጀምሩ ተደርጓል፡፡ በዚሁ ሂደት በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት በእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ዘመን መጨረሻ ሁሉም መምህራን ስታንዳርዱን እንደሚያሟሉ የተቀመጠውን ግብ ለማሳካት የሚያስችል ውጤት በመመዝገቡ የተሳካ አፈጻጸም ተመዝግቦበታል፡፡
በአንደኛ ደረጃ በተለያዩ መርሃ ግብሮች የሚሰጡ ስልጠናዎች አበረታች ቢሆኑም አሁን ካለን አፈጻጸም አንጻር ክፍተቱ ያለባቸውን ክልሎችን በመለየት በትኩረት መስራትን የሚጠይቅ ተግባር ነው፡፡ ከፍተኛ ትምህርትን በተመለከተም የጥራት ማሻሻያ ፕሮግራሙ ይበልጥ ግንዛቤና ይሁንታ እያገኘ በመተግበር ላይ በመሆኑ ይህንኑ አቅጣጫ አጠናክሮ በመቀጠል የትምህርት ጥራትና አግባብነትን ከማረጋገጥና የምዕተ ዓመቱን ግብ ከማሳካት አኳያ ተቃኝቶ ይተገበራል፡፡ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት አሁን ያለበት ደረ ጃ ዝቅተኛበመሆኑ ለየት ያለ ዘመቻ በማድረግ ሽፋንን በጥራት በማሳደግና በስታንዳርዱ መሰረት በማስፋፋት ደረጃቸውን የማሻሻል ሥራ ይሰራል፡፡ የተቀናጀ ተግባር ተኮር የጎልማሶች ትምህርትን እንደዚሁ የህዝብ ንቅናቄ በመፍጠር መሰረታዊ ለውጥ ለማምጣት ሰፊ ርብርብ ያስፈልጋል፡፡
የጤና ልማትን በተመለከተ የቤተሰብ ዕቅድ ተጠቃሚዎችን ማሳደግ የተመጣጠነ ጤናና እንዲሁም አምራች ህብረተሰቡ ለመገንባት ጠቃሚ መሆኑን ታሳቢ ያደረገው እንቅስቃሴ መሻሻል የሚገባው አበረታች ውጤት ታይቶበታል፡፡ ወደ ጤና ተቋማት መሄድና በዚያው አገልግሎት ለማግኘት ማነቆ የሆኑ ከአመለካከት፤ ከትራንስፖርትና ከአግልግሎት ተደራሽነትና ጥራት ጋር የተያያዙ ችግሮች በተደራጀ አኳኃን ለመፍታት የተደረገው ጥረትም አበረታች ነው፡፡ በዚህም መሰረት የአመቱ የአፈጻጸም የበጀት አመቱ ሲጀመር ከነበረበት 23 በመቶ ወደ 44ነጥብ9 በመቶ ከፍ እንዳለ ለማየት ተችሏል፡፡ በተመሳሳይም የሙያ እርዳታ እየተደረገላቸው የተገላገሉ እናቶች ሽፋን ወደ 56 በመቶ አድጓል፡፡ ኤች አይ ኤድስን የመከላከልና የመቆጣጠሩን ሥራ በአጥጋቢ ደረጃ ለማከናወን ከጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም ጋር በቅንጅት እየተሰራ ይገኛል፡፡
የመንስትና የግል ጤና ተቋማት አገልግሎቱን መስጠጥ ጀምረዋል፡፡ የህጻናት ጤናን ለማሻሻል ከሚተገበሩ ቁልፍ ስራዎች ውስጥ አንዱ የሆነው ክትባት መርሃ ግብር አመርቂ አፈጻጸም የታየበት ነበር፡፡ በመሆኑም በያዝነው በጀት ዓመት ከጤና ልማት ዘርፍ አኳያ ቁልፍ ስራ የሆነውን የጤና ልማት ሰራዊት ግንባታ በማጠናከር የጤና ኤክስቴንሽን ፓኬጆችን በተሟላ መልኩ እንዲተገበር፣ በተለይ የእናቶችን ሞት ለመቀነስ በሚያስችሉ ተግባራት ላይ ግልጽ ተልእኮ በመስጠት አቅሙን መገንባት የተለየ ትኩረት ይሰጠዋል፡፡ የጤና ጣቢያዎችን ጤና ኬላዎች ተቀናጅተው እንዲሰሩ የተዘጋጀው የአሰራር ስርአት በሁሉም ተቋማት ተግባራዊ በማድረግ፣ የጤና ተቋማት የጤና ልማት ሰራዊት ግንባታን በማጠናከር የሆስፒታልና የጤና ጣቢያ ሪፎርም በሁሉም ክልሎች እንዲስፋፉ ይደረጋል፡፡ በሌላ በኩልም አርብቶ አደርና በከፊል አርሶ አደር አከባቢዎች በሴክተሩ ትኩረት የተሰጣቸው ፕሮግራሞች አፈጻጸም በሚፈለገው ደረጃ ያልደረሰ በመሆኑ የማስፈጸም አቅም ግንባታና ሌሎች የልዩ ድጋፍ ስራዎች ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቷቸው ይተገበራሉ፡፡
የጤና አገልግሎት ተደራሽነትን ለማሻሻል የቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎት ሽፋንን እና በጤና ተቋም የሚሰጥ የወሊድ አገልግሎትን በማዳረስ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ግቡን ማሳካት ያስፈልጋል፡፡ እንደዚሁም የኤች አይ /ኤድስ ቲቢና ወባ በሽታዎችን መከላከልና መቆጣጠርን በተመለከተ የበለጠ ተጋላጭ በሆነው የወጣቱ ክፍል ዘንድ መዘናጋቱ አሳሳቢ እየሆነ ስለመጣ ከጸረ ኤች አይቪ (ART) ሽፋን መጨመር በተጓዳኝ የመከላከል ስራው የበለጠ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት፡፡ በመጨረሻም በጤና ዘርፍ የህክምና አገልግሎት አሰጣጥ ጥራትን ለማሻሻል የሆስፒታል ሪፎርም ትግበራን አጠናክሮ በማስቀጠል የሃኪሞች ስልጠና በብዛትና በጥራት ይቀጥላል፡፡

የተከበራችሁ የህዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባላት፣
ጥሪ የተደረገላችሁ እንግዶችና
መላው የአገራችን ህዝቦች
የመልካም አስተዳደርና የለውጥ ስራዎችን በተመለከተ መንግስት ለዜጎች የሚሰጠውን አገልግሎቶች ቀልጣፋና ከአድልዎ የጸዳ እንዲሆን የሪፎርም እቅድ ተነድፎ ርብርብ ሲደረግ ቆይቷል፡፡ የህዝቡን ተሳትፎ ደረጃ በደረጃ በማጎልበት ተደማሪ መሻሻል እንደመጣ ይታወቃል፡፡ መሻሻሉ እንደተጠበቀ ሆኖ አሁንም ረጅም ርቀት መጓዝ ይጠይቃል፡፡ ሌላው በዚህ ዙሪያ ከምንጊዜውም በላይ ትኩረት ተሰጥቶት መሰራት ያለበት ጉዳይ በሃይማኖት መቻቻል ዙሪያ ህብረተሰቡን ማስተማርና ማንቃት ነው፡፡
በተደራጀ መልኩ የሴቶችንና የወጣቶችን ተሳትፎ በማረጋገጥ የመልካም አስተዳደርና የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ሂደት ላይ በግንባር ቀደምትነት የመሳተፍ ስራ ትኩረት ተሰጥቶት የሚሰራ ይሆናል፡፡ በሌላ በኩል በሀገራችን የሚስተዋለውን ህገወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመግታት በአገር አቀፍ ደረጃና በክልሎች የተጀመረውን እንቅስቃሴ ማጠናከር ያስፈልጋል፡፡ ከዚሁ ባሻገር ህገወጥነትን፤ ሽብርተኝነትን በሁሉም አቅጣጫ ለመመከት መንግስትና ህዝብ እጅና ጓንት ሆነው መስራት ይጠበቅባቸዋል፡፡ በዚሁ ረገድ የሚታዩ አወንታዊ ጅምሮችን በማጠናከር በህዝቡ እምነትና ግንዛቤ ላይ ተመስርተው እንዲስፋፉ ጥረት ይደረጋል፡፡
በኮሚዩኒኬሽን፤ ኢንፎርሜሽንና ሚዲያ ዘርፍም እንደዚሁ ሁለገብ አቅም በመገንባት በሀገራዊ ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ ብሄራዊ መግባባት መፍጠር ያስፈልጋል፡፡ በዚህ ረገድ ብዙሃን መገናኛ የማይተካ ሚና ይጫወታሉ፡፡ በመሆኑም የሚዲያ ብዝሃነት እንዲስፋፋ፤ ሃላፊነት የሚሰማው ሚዲያ በአገራችን እንዲጎለብት ተከታታይ የማበረታቻና የእርምት ስራዎች ይሰራሉ፡፡ ለሚዲያ ብዝሃነት በተለይም በርካታ የግል የይዘት አቅራቢዎችን ለማስተናገድ የሚያስችለው የዲጂታላይዜሽን ስራ በያዝነው አመት ወሳኝ ምዕራፍ ላይ የሚደርስ በመሆኑ የሚዲያ ብዝሃነትን ለማስፋፋት የተያያዝነውን እቅድ ከማሳካነት አንፃር ጉልህ ድርሻ ይኖረዋል፡፡፡ ከዚሁ በተያያዘም 2007 በጀት አመት የህዝቦችን መቃቃር፤ ፅንፈኝነትና ሁከትን የሚሰብኩ ሃይሎችን የምንታገልበት የሰላም፤ የአብሮነትና የመከባበር ድምፆች ይበልጥ እንዲናኙ የምንረባረብበት አመት ይሆናል፡፡
2007 በአገራችን የሚካሄደው አገራዊ ምርጫ ነፃና ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን አስፈላጊው የዝግጅት ስራዎች እንዲሰሩ መንግስት የሚጠበቅበትን ሁሉ ያደርጋል፡፡ ሁሉም ተዋናይ ወገኖችና ዋናው ፈራጁና ወሳኙ ህዝብ በአገራችን የተፈጠረውን ሰፊ የሃሳብ ግብይት እድል በመጠቀም ደረጃ በደረጃ እየጎለበተ የመጣውን ዴሞክራሲያዊ ስርዓታችንን ሃላፊነት በተሞላበት መንፈስ ወደሌላ ከፍታ ማሸጋገር ይጠበቅብናል፡፡

የተከበራችሁ የህዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባላት፣
ጥሪ የተደረገላችሁ እንግዶችና
መላው የአገራችን ህዝቦች
ያሳለፍነው ዓመት በዲፕሎማሲ እና የውጭ ግንኙነት መስክ የተሳካ አፈጻጸም የተመዘገበበት ነበር፡፡ የሀገራችን ልማትና ሰላም ከጎረቤቶቻችን ሰላም ጋር በእጅጉ የተቆራኘ መሆኑን በመገንዘብ በአካባቢ እና በአህጉራዊ መድረኮች የአለም አቀፍ ፎረሞችን በመጠቀም ሰፊ ርብርብ አድርገናል፡፡ ከዚህ አኳያ በሶማሊያ ያለው ሁኔታ በእጅጉ እየተሻሻለ እንዲመጣ የመከላከያ ሰራዊታችን ያደረገው አስተዋጾ በአለም ደረጃ ምስጋናና እውቅና ተችሮታል፡፡ በደቡብ ሱዳንተፈጠረውን ቀውስ ለማርገብና የህዝቡን እልቂት ለማስቆም አስፈላጊውን ጥረት በማድረግ ጉዳቱን ለመቀነስ ችለናል፡፡ በያዝነው ዓመትም በአካባቢያችን ሰላም እንዲሰፍን የበኩላችንን ጥረት እንቀጥላለን፡፡
ከዚሁ ባሻገር ከሁሉም አህጉሮች በሀገራችን የተፈጠረውን የኢንቨስትመንት ዕድል ለመጠቀም በርካታ የአለም መሪዎችና ኩባንያዎች ጉብኝት ያደረጉ ሲሆን ቀላል የማይባሉ ኢንቨስተሮች ስራ የጀመሩበትና በጥናት ላይ የሚገኙበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ በያዝነው ዓመትም ፍላጎት ካሳዩት ውስጥ ምርጦቹን ለማግባባትና አዳዲስ እንቨስተሮችን ለመሳብ ጥረት ይደረጋል፡፡
ከታላቁ የህዳሴ ግድባችን መጀመር ጋር ተያይዞ በናይል ተፋሰስ ሀገሮች በአጠቃላይ እና ከግርጌ ተፋሰስ ሀገሮች ጋር በተደረገው የማይናወጥ የጋራ ተጠቃሚነት መርህ ላይ የተመሰረተ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትና በግብጽ በኩል የተፈጠረው ለውጥ ሳብያ ሁኔታዎች ፈር ይዘው መሄድ ጀምረዋል፡፡ በያዝነው ዓመትም ይኸው ጥረት ተጠናክሮ ይቀጥላል፡፡ እነዚህ ዲፕሎማሲያዊ ድሎቻችን እንደተጠበቁ ሆኖ በሰላም የዘረጋነውን እጅ በእብሪት የገፋው የሻዕብያ መንግስት ሀገራችን ብቻ ሳይሆን ቀጠናውን በሙሉ ከማተራመስ አልተቆጠበም፡፡ በዘረኝነትና ጭፍን የጥላቻ ፖለቲካ ተለክፈው የሽብር ተግባርን ሥራዬን ብለው የተያያዙትን የግንቦት 7 ጀሌዎችን፣ ኦነግና ኦብነግን የመሳሰሉ የሽብር ድርጅቶች በማስከተል ያደረጋቸውን ሙከራዎች በሙሉ ባለፈው ዓመት በብቃት መክተናል፡፡ በተያዘው ዓመትም ሻዕብያ ለሚቃጣው ትንኮሳ ሁሉ ተመጣጣኝ የአጸፋ ምላሽ የመስጠት ፖሊሲያችን ይቀጥላል፡፡
በድጋሚ ለሁለቱ /ቤቶችና ለመላው የሀገራችን ህዝቦች መልካም የስራና የስኬት ዓመት እንዲሆንላችሁ እመኛለሁ፡፡

አመሰግናለሁ!!
መስከረም 26/2007
አዲስ አበባ

No comments:

Post a Comment