EPRDF is a ruling party committed to realize Ethiopia's Renaissance.

Saturday, 11 October 2014

ብዙ ሆኖ እንደ አንድ የተመመ ሕዝብ


በአሜሳይ ከነዓን

የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች አቢዮታዊ ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ /ደኢሕዴን/ 22ኛ ዓመት የምስረታ በዓልን ለማክበር ወደ ሃዋሳ ያመራነው ማልደን ነበር፡፡ በርካታ መንደሮችንና ከተሞችን አቋርጠን ሃዋሳ ከተማ ረፋድ ላይ ደረስን፡፡ ሃዋሳ ከተማ ከወትሮው በተለየ ደመቅመቅ ብላለች፡፡ ከተማዋ በፍጥነት እያደገች በመሆኗ ከእለት እለት ገፅታዋ እየተቀየረና እያማረች መጥታለች፡፡ በዘንባባ የተሽቆጠቆጡ መንገዶች፣ ዘመናዊ ሆቴሎችና የመዝናኛ ስፍራዎች ተፈጥሮ ከለገሳት ሃይቋ ጋር ተዳምረው ልዩ ውበት አላብሰዋታል፡፡

የመስከረም ወር የመጨረሻዋ ቀን በክልሉ የነፃነት ጎህ እንዲፈነጥቅ ያደረጉ ጀግኖች የሚዘክሩባት እለት በመሆኗ ለክልሉ ህዝብ ልዩ ቀን ሆናለች፡፡ “በደኢህዴን/ኢህአዴግ መሪነትና በህዝቦች የነቃ ተሳትፎ የክልላችን ህዳሴ ተጠናክሮ ይቀጥላል” በሚል መሪ ቃል በክልሉና ከክልሉ ውጭ ሲከበር የከረመው የደኢህዴን 22ኛ ዓመት የምስረታ በዓል ከመስከረም 29 – 30/207 ባሉት ቀናት በደማቅ ስነ ስርዓት ታጅቦ ሊጠናቀቅ ቀን ተቆርጦለታል፡፡ እኛም የበርካታ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቱባ ባህል ባለቤት የሆነው ክልል ታሪካዊ በዓል አካል በመሆናችን ልዩ ስሜት ፈጥሮብናል፡፡


‘የደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች የፀረ ጭቆና ትግልና የደኢሕዴን የ22 ዓመት የድል ፍሬዎች’ በሚል የተካሄደው የፓናል ውይይትና የክልሉን ብሔሮች፤ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቱባ ባህል ፍንትው አድርጎ ያሳየው ትዕይንት ለበዓሉ ልዩ ድምቀት አላብሶት አልፏል፡፡ በፓናል ውይይቱና በማጠቃለያ መርሃ ግብሩ የደኢሕዴንና የኢሕአዴግ ሊቀመንበር ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝን ጨምሮ ሚኒስትሮችና ከፍተኛ የመንግስትና የድርጅት የስራ ሃላፊዎች ተሳትፈዋል፡፡

በፓናል የንቅናቄው ነባር ታጋዮች፤ እህትና አጋር ድርጅቶች የተሳተፉበት ሲሆን በርካታ ሃሳቦች ተንሸራሽረው የድርጅቱ ታሪክ ሁሉም ሊገነዘበው በሚችለው ልክ ግልፅ ሆኗል፡፡ የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች በባህላቸው፤ በቋንቋቸውና በማንነታቸው ኮርተው ራሳቸውን ማስተዳደር በማይችሉበት ሁኔታ ውስጥ ዘመናትን አሳልፈዋል፡፡ በሌላው ክልል ከሚገኘው የኢትዮጵያ ሕዝብም በባሰ ሁኔታ የመሬት ባለቤትነትና የዲሞክራሲ መብት ጥያቄዎቹ ያልተመለሱለት፣ የብሔርና የሃይማኖት እኩልነት ያልተረጋገጠለት፣ ብሄራዊና መደባዊ ጭቆና ያንገላታው ሕዝብ እንደነበር በፓናል ውይይቱ ተጠቅሷል፡፡   

ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ግን ኢትዮጵያ እንደ ሀገር የድህነት ታሪኳን በመፋቅ ማደግ የምትችልና ብሩህ ተስፋ ያላት ሃገር መሆኗን አስመስክራለች፡፡ የክልሉ ህዝቦችም በደኢሕዴን/ኢሕአዴግ አመራር በክልሉ ሁለንተናዊ ለውጥ ማስመዝገብ ችለዋል፡፡ በክልሉ የተመዘገቡ ስኬቶች በቀጣይነት ለማረጋገጥም ከደኢሕዴን ጋር መስራት እንደሚገባ በፓናሉ  ተመላክቷል፡፡ 
   
የበዓሉ ማጠቃለያ በግንባታ ላይ ባለው ግዙፉ የሃዋሳ ህብር ስታዲየም የተካሄደ ሲሆን ልዩና ደማቅ ነበር፡፡ የክልሉ አባቶች ባሸበረቁና በጌጥ በተንቆጠቆጡ ፈረሶች ትርዒት በማሳየት ፍፁም ማራኪ የሆነ አቀባበል ለእንግዶቻቸው አድርገዋል፡፡ በደቡብ ክልል የሚገኙ በርካታ ቁጥር ያላቸው ብሔረሰቦች የመጡበትን አካባቢ በሚወክል መልኩ የአልባሳትና የሙዚቃ ትርዒት ያሳዩ ሲሆን ውበታቸው የታዳሚዎችን ቀልብ መግዛት ችሏል፡፡ ከየብሔረሰቦቹ ባህላዊ የሙዚቃ መሳሪያዎች የሚወጣው ድምፅ የማይጠገብና ከአዕምሮ የማይጠፉ ትውስታን የሚያጭር ነው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝብ ህገ መንግስታዊ መብቱ ተረጋግጦለት፣ ጭቆናና አድሎ ተወግዶለት እንዲሁም ልዩነቱ ውበት ሆኖት በእድገት ጎዳና ላይ እንደሚገኝ በወቅቱ ባደረጉት ንግግር ጠቅሰዋል፡፡ በክልሉ ስራ አጥነትን በመቅረፍ፣ የአርሶ አደሩን ምርትና ምርታማነት በመጨመር፤ መልካም አስተዳደርን በማስፈን በርካታ ስራዎች እንደተሰሩ የገለፁት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ሃዋሳን የኢንዱስትሪ ልማት መዳረሻ በማድረግ በአመቱ 30 ሺህ ለሚደርሱ ሰዎች የስራ አድል እንደሚፈጠር ተናግረዋል። አቶ ኃይለማሪያም አያይዘው እንደገለፁት ኪራይ ሰብሳቢነትን፣ ጠባብነትንና የሃይማኖት አክራሪነትን በመዋጋት በክልሉ እየታዩ ያሉ የልማት ትሩፋቶችን ማስቀጠል ይገባል።

የክልሉ ሕዝብ በተለያዩ የልማትና የመልካም አስተዳደር እንቅስቃሴዎች ላይ በመሳተፍ የልማት ሠራዊትነቱን እያሳየ መሆኑን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም 2007 አገራዊ ምርጫ የሚካሄድበት በመሆኑ የክልሉ ህዝብ ምርጫው ፍትሃዊ፣ ዴሞክራሲያዊና ተዓማኒ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ከደኢሕዴን/ኢሕአዴግ ጎን በመሰለፍ የበኩሉን ድርሻ መወጣት እንደሚገባው አሳስበዋል፡፡


ደኢሕዴን ክልሉን ማስተዳደር ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ብቃት ያለው አመራር በመስጠት ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት፣ የፆታና ሃይማኖት እኩልነት መረጋገጥ ችሏል፡፡ ዛሬ ትግሉ ከምን ጋር እንደሆነ የክልሉ ሕዝብ በውል ተገንዝቦታል፡፡ ብዝሃነቱን ጠብቆ ተቻችሎ መኖርን የለመደ ሕዝብ ተባብሮ መስራትና ማደግ አይቸግረውምና የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝብ በእርግጥም የማይቻል የሚመስለውን ችሎ ያሳየ ህዝብ ሆኗል፡፡ ብዙው እንደ አንድ ሆኖ ለልማትና ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታው የተመመ ህዝብ መሆኑን አረጋግጧል፡፡ 

No comments:

Post a Comment