EPRDF is a ruling party committed to realize Ethiopia's Renaissance.

Tuesday 19 August 2014

መለስ ዜናዊ- የፀረ- ድህነት ትግል አርበኛ


ረድዔት ልጅ
በርካታ የአፍሪካ፣ የኤስያ እና የላቲን አሜሪካ ሀገራት  የተፈጥሮ ሀብት ሳያንሳቸው ዜጎቻቸውን የድህነት፣ የርሃብና የኋላቀርነት ተምሳሌት ሆነው ለዘመናት የዘላቁት  ትክክለኛ የለውጥ መሪ፤ ትክክለኛ የሆነ ሀገር በቀል ፖሊሲና ስትራቴጂ በማጣታቸው ነው፡፡ ይህ አባባል ይበልጥ ተጨባጭ ማድረግ እንችል ዘንድ እሩቅ ሳንሄድ ሃገራችን ኢትዮጵያን በምሳሌነት ማንሳት ተገቢ ይሆናል፡፡ ሀገራችን ኢትዮጵያ ለዘመናት ትክክለኛ ፖሊሲና ስትራቴጂ ሳይኖራት፤ ከራስ ጥቅምና የስልጣን ቆይታን ከማራዘም በዘለለ ስለ ህዝብ ጥቅም እና የሀገር ብልፅግና የሚቆረቆር ስርዓትና መሪ ባለመማግኘቷ የችግር የረሃብና የኋላ ቀርነት ምሳሌ ሆና ለዘመናት ዘልቃለች፡፡
  
ሀገራችን በአዲስ አስተሳሰብ እና በአዲስ የልማትና የብልፅግና ቅኝት መጓዝ የጀመረችው ባለፉት   ሁለት አስርት ዓመታት ብቻ ነው። በእነዚያን ዓመታት በተካሄደው አዲስ ርብርብ የረሃብና የኋላቀርነት ምሳሌ መሆናችን ቀርቶ ለማደግ የምንጥርና በማደግ ላይ ያለች ሃገር መገንባት ችለናል፡፡ 

በሀገራችን ለህዝባቸው መሻሻል ዕድመልካቸውን ከታገሉ፣ ህዝባቸውን ከድህነትና ከኋላቀርነት ለማላቀቅ ሌት ተቀን ያለዕረፍት ከባተሉ አንድ ግን ደግሞ እንደ በዙ ሆነው በርካታ ስራዎችን ስላከናወኑ ብርቅዬ ኢትዮጵያውያን ስናስብ የቀድሞው ጠቅላይ ሚንስትር ጓድ መለስ ዜናዊ ግናባር ቀደሙ ሆነው እናገኘዋለን ፡፡ ጓድ መለስ እርሱን ባፈራው ድርጅቱ ኢህአዴግ፣ እንደመንግሰት በተቀበለው የስልጣን እርከን ተልእኮውን ያለምንም ማዛነፍ የፈፀመ፤ በዓለም ላይም ተፅዕኖ መፍጠር የቻለ፣ የጭቁን ህዝቦች አንደበትና ልቦና በመሆን ለመብታቸውና ጥቅሞቻቸው በፅናት የታገለ የዘመናችን ታላቅ መሪ ነው፡፡ ጓድ መለስ ያበረከታቸውን አስተዋፅኦዎች  በዚች ፅሁፍ ዘርዝሮ ለመጨረስ ፈፅሞ የማይታሰብ ቢሆንም በጣም ጥቂቶቹን በወፍ በረር እናውሳ፡፡
 
ከግንቦት 83 በፊት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ወደ ፊት መሄድ ቀርቶ ባለበት መቆም ተስኖት ቁልቁል መሽመድመድ የጀመረበት፤ ሀገሪቱም ምስቅልቅል ያለ የፖለቲካ ሁኔታ ውስጥ የተዘፈቀችበት ፈታኝ  ሁኔታ ነበር፡፡ ይህም አብዛኛውን ኢትዮጵያዊ የትጥቅ ትግልን ብቸኛ አማራጩ አድርጎ የወሰደበት አስገዳጅ ሁኔታ ተፈጠረ፡፡ የራሳቸውን ፍላጎት በእጅጉን ገድበው የብዙሃኑን ህዝብ ፍላጎት ለማሟላት  ማቄን ጨርቄን ሳይሉ ወደ በርሃ ከከተሙት ወጣቶች መካከል የትኞቹም የህዝብ ትግሎች ለውጤት የሚበቁት በተደራጀ አኳሃን ሲመሩ እንደሆነ የሚያምነው 19 ዓመቱ ወጣት መለስ አንዱ ነው፡፡ 

የህዝብን ትግል በተደራጀ አኳኋን የመምራት ጉዳይ ጥራት ባለው አስተሳሰብ ከመመራት ውጭ ሊሳካ እንደማይችል ታሪክ ደጋግሞ አሳይቶናል፡፡ ህዝብን በትክክል መርቶ ለውጤት ለማብቃት ይቻል ዘንድ በጠራ አስተሳሰብ የሚመራ ግንባር ቀደም ድርጅት ባለቤት መሆን አማራጭ የሌለው የትግል መንገድ ነው፡፡ ይህን የተረዱት ጓድ መለስም ድርጅቱን ከተቀላቀለ በኋላ ለድርጅቱ በርካታ ስራዎችን በማከናወን በየምዕራፉ የተሰጠው ተልዕኮ በስኬት መወጣት ችሏል፡፡ ጓድ መለስ ከህውሓት እስከ ኢህአዴግ በአመራርነት ታግሎ እያተገለ ሲንቀሳቀስ ሁሌም ቢሆን ድርጅቱን ከዴሞክራሲ አኳያ ይበልጥ የሚያጎለብቱ፣ ከትግል ፕሮግራም አኳያም ይበልጥ ተራማጅ የሆኑ ሃሳቦችን በማፍለቅ እና በተግባር ላይ በማዋል የበኩሉን ቁልፍ ሚና ተጫውቷል። 

ጓድ መለስ ድርጅቱ በተለያዩ ጊዜያት ፈታኝ ሁኔታዎችች በገባባቸው ወቅቶች ሁሉ ችግሮችን ለመፍታትና ለማስተካከል በስፋት ታግሏል፡፡ ለአብነትም 1993 ድርጅቱ የመከፋፈል አደጋ ሲጋረጥበት ጓድ መለስ ችግሮቹን ለማስተካከል እጅግ የላቀ ሚና ተጫውቷል።ጓድመለስ የትግሉን የጉዞ አቅጣጫ፣ ግቦችና መዳረሻዎች በጠራ ሁኔታ አልፎም በአውሮፓ፣ በኤስያ በአፍሪካ የተካሄዱ አብዮቶችን ባህርይና አካሄድ፣ በድል የተጠናቀቁትም ሆነ የተሰናከሉትና የተኮላሹት ለድሎቻቸውና ለውድቀቶቻቸው የነበሩትን ምክንያቶች በማጥናት፣ በመመርመር፣ ያወቀውንም የለውጥ መሳሪያ በማድረግ ድርጅቱን ከተጋረጠበት አደጋ በብቃት ለማውጣት ሰፊ ትግሎችን አድርጓል፡፡
  
የድርጅት እንቅስቃሴ በድርጅታዊ ህገ-ደንብ እንዲመራ የመንግስትንና የድርጅት ሚና ግልፅ ድንበር በማበጀት አንዱ በሌላኛው ስራ ውስጥ ጣልቃ ገብነትን ያስወገደ የመንግስትና የህዝብ አስተዳደርም በህግ ማዕቀፍ ውስጥ እንዲከናወን አበክሮ የታገለና የህግ የበላይነት የሰፈነባት ሃገር ለመፍጠር ሌት ተቀን የደከመ መሪ ነው፡፡

አንድ  መሪ  ከሁሉ በፊት የአካባቢ ችግሮችን በትክክል የመለየትና ለእነዚህም የሚሆን ተጨባጭ  መፍተሄ የማመንጨት ችሎታና ብቃት ያለው ሲሆን የታላቅነት ሚዛኑን ከፍ ያደርገዋል፡፡ ከትንሽ ቀበሌ እስከ ፌደራል ድረስ ያለውን መዋቅር  ችግሮችን ማየትና ማስተዋል ችግሮች ሲገኙም ለመፍታት የሚያስችል ብቃት ብሎም የመፍተሄ አቅጣጫ ከሁሉ በፊት ማግኘት የጓድ መለስ መገለጫዎች ናቸው፡፡ 

በድሃና ኋላ ቀር አገሮች የስብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብት ጥያቄዎች  ምላሽ ለማግኘት የኢኮኖሚ ጥያቄዎችን በትክክል ለመመለስ ልዩ ተፈላጊነት አለው፡፡ ማለትም ልማት ባልተረጋገጠበት ሁኔታ ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብት ብሎ ነገር የይምሰል ብቻ ሆኖ ይቀራል። በተለይ እንደኛ በመሳሰሉ አገሮች ከኢኮኖሚያዊ ጥያቄዎች በማይተናነስ ሁኔታ ምላሽ ማግኘት ያለባቸው በርካታ የፖለቲካ ጥያቄዎች አሉ፡፡ የስብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች መነፈግ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት እድል መነፈግን ማስከተሉ አይቀርም፡፡ ጓድ መለስ የሀገራችን የልማት፣ የሰላም እና የዴሞክራሲ ጥያቄዎች ሳይበላለጡና ሳይቀዳደሙ ተገቢውን ምላሽ እንዲያገኙ ዕድመ ልኩን የታገለ ታላቅ መሪ ነበር። 

ከግንቦት 1983 በፊት የብዙሃኑን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በቅድሚያ የዜጎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች መከበር አማራጭ የሌለው ነበር፡፡ ከግለሰብ መብት አኳያ የዜጎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ባልተከበሩበት አንዳችም የህዝብ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ሊኖር እንደማይችል ታሪካችን በራሱ ምስክር ነው፡፡ በዚህም ጓድ መለስ የዜጎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ ጥያቄዎች መልስ እንዲያገኙ የብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች እኩልነት፣ ሃሳብን በነፃ የመገለፅና የመያዝ፣ የእምነት ነፃነት፣ የህዝብ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ፣ የህዝብ የስልጣን ባለቤትነት እና የመሳሰሉት ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ህገ-መንግስታዊ ዋስትና እንዲያገኙ በማድረግ ሂደት ውስጥ ግንባር ቀደሙን ሚና ተጫውቷል፡፡

ጓድ መለስ የሀገራችንን ብዙሀነት በአግባቡ የሚያስተናግድ ሁሉንም ፓለቲካዊ ሀይሎች የሚያሳትፍና የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ፈቅደው በመዋሀድ አዲሲቱን ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ እንዲገነቡ በብቃት የሚያዘጋጅ የሽግግር መንግስት ካልመሠረትን ሌላ የእልቅት ዘመን ሊያስከትል ይችላል በማለት የሞገተና አገራችን ዛሬ ለደረሰችበት የእድገትና ትራንስፎርሜሽን መድረክ እንድትበቃ   መሠረት የጣለ ባለ ራዕይ መሪ ነው፡፡
  
ሰላም በሌለበት ሀገር ልማት አይኖርም፤ ልማትን ለማፋጠን ዴሞክራሲና መልካም አስተዳደር ማስፈን ወሳኝ ጉዳይ ነው፡፡ ስለ ሆነው ልማት፣ ሰላም እና ዴሞክራሲ ለኛ የምርጫ ጉዳይ ሳይሆኑ የህልውናችን መሰረቶች ናቸው በማለት ሳይታክትና ሳይሰለች ታግሏል። ዋንኛውና ትልቁ የመለስን ባህሪ የቀረፀው በድህነት ላይ ያለው የመረረ ጥላቻ ነውይላሉ ጓድ መለስን በቅርብ የሚያውቋቸው፡፡ 

ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሃብት ደሃ ሳትሆን ለዘመናት የድርቅና የርሃብ ምሳሌ መሆኗ ለሁሉም ዜጎች የሚያስቆጭ ቢሆንም ለታላቁ መሪ መለስ ዜናዊ ደግሞ የከፋ ነበር፡፡ ታላቁ መሪም ሀገሪቱ ባላት ሃብትም መለወጥ እንደምትችል ነገር ግን ያላትን የተፈጥሮ ሃብት ተጠቅሞ ልማትን በማፋጠን ከድህነት ለመውጣት በአጭር ጊዜ ውስጥም መካከኛ ገቢ ካላቸው ሀገራት ተርታ ለማሰለፍ ትክክለኛ ፖሊሲና ስትራቴጂ እንደሚያስፈልጋት የተረዳው ጓድ መለስ በኢህአዴግ ማዕቀፍ ውስጥ በመሆን ለተግባራዊነቱ በስፋት ሰርቷል፡፡ በትጥቅ ትግሉ ወቅት የተደረገውን ተጋድሎ ድህነትን ለማጥፋት በሚደረገው ትግል የድህነት ዘበኛ ያህል የነበረውን ስርዓት ለማስወገድ የተደረገ ጥረት አድርጎ የሚቆጥረው ጓድ መለስ ከደርግ መደምሰስ በኋላም ዋናው የድህነት ጠባቂ የሆነው ስርዓት በመደምሰሱ ዋነኛ የትግል አውድማ የሆነውን ድህነት መታገል እንደሚገባ አጥብቆ አስተምሯል፡፡   ከድህነት መውጫ ቀዳዳ ሲያማትርም እድሜ ዘመኑን ሙሉ ገብሯል፡፡

ከድህንት ጋር የሚደረገው ትግል በፍጥነት መከናወን እንዳለበት ለማስገንዘብ ጊዜ የማያጠፋው ታላቁ መሪ ከድህነት ጋር የሚደረገው ትግል ከተራራ ጫፍ ከሚወርድ ናዳ ጋር ያመሳስለዋል። ከላይ ከሚወርደው ናዳ ለማምለጥ የሚሮጥ ሰው ከናደው የላቀ ፍጥነት ከሌለው ናዳው በጀመረበት የመጀመሪያም ሆነ በመጨረሻው ሰዓት ላይ ቢሞት ያው ሞቷል። በመጀመሪያም ሆነ በመጨረሻ ሰዓት መሞቱ ትርጉም የለውም፤ ስለዚህም ሀገራችንን ሊበታትን ከሚችለው ናዳ እጅግ በላቀ ሁኔታ መፍጠን እንደሚገባ ያለውተወተበት ጊዜና ቦታ የለም፡፡ ድህነት ቶሎ ካልፈታነው በቀር ይበታትነናል የሚል ፅኑ አቋም ያራምድ ነበር፡፡ 

ያን ሁሉ ድንጋይ ፈልፍሎ ያን የመሰለ ቅርፅ ማውጣት የቻለ ሕዝብ በምን ሂሳብ አሁን ድንጋይ መፈልፈል ቀርቶ አርሶ መብላት አቅቶት የርሃብና ችግር ምሳሌ ይሆናል የሚል ቁጭት በየመድረኩ በማስተጋባት ህዝብን  ለልማት አነሳስቷል፡፡

ጠላታችን የሆነውን ድህነትን በማጥፋት ዜጎቻችንን ሰብዓዊ ክብር ማላበስ፣ ሀገራችንንም ከተስፈኞች ጎራ ማውጣት አለብን የሚል ፅኑ አቋም  ነበረው፡፡ የሀገራችን እድገት ጎልቶ እንዲታይ ያደረጉት ፖሊሲዎቻችንና ስትራቴጂዎቻችን ምስክሮቻችን ናቸው፡፡ የከተማና ኢንዱስትሪ ልማት፣ የገጠር ልማትና የውጭና የደህንት ፖሊሲዎቻችን ሁሉ መነሻና መድረሻቸው ደህነትን ከማስወገድ፤ ልማት ከማፋጠን አንፃር መቃኘት እንደሚገባቸው መለስና ድርጅቱ ኢህአዴግ በስፋት የታገሉበትና ተጨባጭ ውጤት የተገኘባቸው ናቸው፡፡ ጓድ መለስ ዋነኛ ጠላታችን ድህነት ነው የሚል አቋም በመያዝ ከድህነት በላይ የምናካሂደው ጦርነት አይኖረም በማለት በድህት ላይ ጦርነትን ያወጀና በድህነት ላይ  ድል የተጎናፀፈ የፀረ- ደህነት ትግል አርበኛ ነው፡፡ምርጥ የተባሉትን ውጤታማ ተሞክሮዎችን ለቅሞ በማያዝና እነርሱንም በማስፋት ከዛሬ 23 ዓመታት በፊት የአገሪቱ ህዝብ 45 ነጥብ 5 ያህሉ በፍፁም ድህነት ውስጥ ሲኖር የነበረበትን ሁኔታ በመቀየር በአሁኑ ስዓት በድህነት ላይ የሚኖር ህዝብ  ወደ 26 በመቶ ዝቅ ማድረግ  ተችሏል፡፡

ሀገራችን ኢትዮጵያ ለአባይ ወንዝ ከእንጉርጉሮ ባለፈ ወደ   ልማት ለመለወጥ ዘመናት አስፈልጓታል፡፡ ለዘመናት በርካታ ኢትዮጵያውያን ሲቆጩበት የነበረው የአባይ ወንዝ ዛሬ በሩቅ አሳቢው መሪያችን አባይም ከዜማ ማድመቂያነት አልፎ ዳቦ ሆኖ  ልንጎርሰው፤ ብርሃን ሆኖ ቀን ሊያወጣልን ተቃርቧል፡፡ ኢትዮጵያም የህዝቦቿን ጥቅም የሚያስከብሩ በርካታ ዓበይት ፕሮጀክቶችን የምትተገብርበትን አቅም ገንብታለች፡፡ የስኳር ፕሮጀክት፤ የባቡር ፕሮጀከት፣ ሌሎች የሐይድሮ ኤሌክትሪክና የንፋስ ሀይል ማመንጫዎች በመገንባት ላይ ናቸው፡፡ እነዚህ ፕሮጀክቶች መላው የሃገራችን ህዝቦች ያስተሳሰሩና  የይቻላል መንፈስንም ያጎለበቱ የህዳሴአችን ጮራዎች ናቸው፡፡

ሌላው የጓድ መለስን የልማት አርበኝነት ስንዘክር የማንዘነጋው በአረንጓዴ ልማት ላይ ያራምድ የነበረው አስተሳሰብ ነው፡፡  ላለፉት በርካታ ዓመታት የደን መጨፍጨፍ እንጂ የደን ማልማት ስራ ተዘንግቶ የቆየ ቢሆንም በተግባር በጓድ መለስና በኢህአዴግ ግንባር ቀደም ተዋናይነት   ምሳሌ መሆን የሚችል ተግባር ተፈፅሟል፡፡ የሀገሪቱ የደን ሽፋንም 3 በመቶ ወደ 13 በመቶ እያንሰራራ እንደመጣ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ጓድ መለስ አፍሪካን ወክሎም በዓለም አደባባይ ስለ አለም አየር ንብረት ለውጥ ብሎም አፍሪካ ሊኖራት ስለሚገባ ካሳ አጥብቆ ተከራክሯል፡፡

ጓድ መለስ በሀገር ውስጥ እንደ ድርጅት እንዲሁም እንደ መንግስት ካበረከተው አስተዋፅዖ ባልተናነሰ ሁኔታ ለአፍሪካና ለአለም ህዝቦች በርካታ አርአያ የሆኑ ስራዎችን አከናውኗል፡፡ ከሶማሊያ እስከ ላይቤሪያ፣ ከሱዳን እስከ ቡሩንዲ፣ ከአፍሪካ ሰላም ማስከበር እስከ አፍሪካ ንግድ ለአፍሪካዊ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሄ ያፈላለገ፣ ያፈለቀና በተግባር እንዲተረጎም በማድረግ ተጨባጭ ለውጥ ያመጣ የዕድመ ልክ ታጋይ  ነው፡፡

የአፍሪካውያን ጥቅም የሚረጋገጠው በተናጠል በሚደረግ መፍጨርጨር ሳይሆን በመሰረታዊ የጋራ ጥቅም ጉዳይ ላይ የጋራ አቋም በመያዝ፣ በዓለምአቀፍ መድረኮች በአንድ ድምፅ በመሰለፍ መሆኑን መለስ ያምናል፡፡ ለዚህም ተግባራዊነት ከአፍሪካውያን መሪዎች ጋር በመመካከርና ጠቃሚ ሃሳቦችን በማቅረብ ዓለም አቀፋዊ ተቀባይነትንና አክብሮትን አትረፏል፡፡ መለስ የአካባቢው ሀገሮች ያለንን እድል ተሳስረንና ተባብረን መልማትና ማደግ ነው የሚል ፅኑ እምነት አለው፡፡ አገራችንና የአካባቢውን አገሮችን በመሰረተ ልማት ለማስተሳሰር ቆራጥ እርምጃዎችን ወስዷል፡፡

የአፍሪካ ምርቶች እንዲሻሻል፤ ወደ አፍሪካ የሚፈሰው ኢንቨስትመንት፤ ብድርና የልማት ድጋፍ በቀጣይነት እንዲጨምር፤ አፍሪካውያን በአየር ንብረት መዛባት ለሚደርስባቸው ጉዳት ማካካሻ እንዲያገኙ እንዲሁም የዓለም የንግድ ስርዓት ለአፍሪካ እድገት የሚያመች እንዲሆን ለማድረግ በተገኘበት መድረክ ሁሉ ታግሏል፡፡

ታላቁ መሪ አፍሪካን ወክሎ በቀረበባቸው ዓለም አቀፍ መድረኮች ለአፍሪካዊያን ጥብቅና ቆሞ ተጨባጭ ውጤት በማስገኘት የአፍሪካዊያን ድምፅ እስከመባል ደርሷል፡፡ በኮፐንሃገን አፍሪካ ወክሎ በቀረበበት የድርድር መድረክ  አፍሪካ ላቀረበችው ሀሳብ ዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ድጋፉን እንዲሰጥ፤ የካርቦን ልቀትን መጠንን በመቀነስ በኩል የዓለም ሙቀት 2 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ እንዳይበልጥ በሚከላከል መልኩ ገደብ ሊቀመጥለት እንደሚገባ  የአፍሪካ አቋም መሆኑን በግልፅ አንፀባርቋል፡፡
 
አፍሪካ በአየር ንብረት መዘባቱ እጇ የሌለበት ግን ደግሞ ላላፉት በርካታ ዓመታት ፍትሃዊ ባልሆነ መልኩ ሰቆቃና ስቃዩን እንድትሸከም የተገደደችበት ሁኔታ መቀጠል የለበትም። በአፍሪካ ላይ እየደረሰ ያለው ችግር ብእሳከሁኑ ተባብሶ የሚቀጥል ከሆነ ግን ዘር ከማጥፋት ወንጀል ተለይቶ የሚታይ አይሆንም ሲል ለአፍሪካውያን ጥብቅና ቆሞ ተከራክሯል፤ በድርድሩም አፍሪካ የተሻለ ተደራዳሪነቷን ከማሳየት ባለፈም የታሰበውን ውጤት ማግኘት ችላለች፡፡ በዚህ አስደናቂ ተግባሩ ለዘመናት አፍሪካ በእንደዚህ አይነት መድረኮች የነበራትን የተስፈኝነት ሚና የቀየረና አፍሪካን ወደ ተደራዳሪነት ያሸጋገረና ለአፍሪካ አዲስ የአጋርነት ምዕራፍን የከፈተ ፋና ወጊ መሪ ነበር፡፡

በአፍሪካ ውስጥ የተከሱት ግጭቶችን ለመፍታትና መግባባትን ለመፍጠር የተጫወተው የአደራዳሪነትና የግጭት አፈታት የመሪነት ሚና በእጅጉ የሚደነቅ ነው፡፡ መለስ በአፍሪካ ደረጃ በሶማሊያ፣ በሱዳን፣ በሩዋንዳ፣ በቡሩንዲና ባላይቤሪያ ሰላም እንዲሰፍን አገራችን የድርሻዋን እንድትወጣ በአፍሪካውያን ወንድሞቻችን ዘንድ የሚወደስ ሰላም የመፍጠርና የሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች በፍፁም አፍሪካዊ መንፈስ ሲመራ የኖረ ታላቅ አፍሪካዊ መሪ ነበር፡፡ ለዚህም ነው ለብዙ አፍሪካውያን የጓድ መለስ ህልፈት ያልጠበቁትና ሀዘናቸው ከሬት የመረሪ የሆነባቸው፡፡

ጓድ መለስ   አንድ ሰው በህይወት ዘመኑ ማድረግ ከሚችለው በላይ ሰርቶ አደራውን ጥሎልን አልፏል፡፡፡ በተወልን የተመቻቸ መንገድ የሀገራችንን ብልፅግና ማስቀጠል ከእኛ የሚጠበቅ የወቅቱ ተልዕኮ ነው፡፡ እኛም መሪያችንን፣ አባታችንን ተስፋችንን ብናጣም ሌጋሲውን በማስቀጠል በአካል እንጂ መንፈሱ ሁሌም ከእኛ ጋር መሆኑን በተግባር ማሳየት ይገባናል፡፡ የመለስን ሞት ድል የምናደርገውም የተወልንን የህዳሴ ጉዞ በፍጥነት በማስቀጠል የበለፀገች ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ ለመገንባት በምንከፍለው ክቡር መስዋእትነት በመሆኑ ዛሬም የመለስን ራዕይ ለማሳካት በቁርጠኝነት ቆመናል። 

No comments:

Post a Comment