EPRDF is a ruling party committed to realize Ethiopia's Renaissance.

Friday, 15 August 2014

መለስ፤ በህያው ስራህ ህያው ነህ!




በአሜሳይ ከነዓን
እለተ ማክሰኞ 2004 ዓም ነሃሴ ወር አጋማሽ የዓለም ህዝበ ከባዱንን መራሩን የመርዶ ዜና ሰማ፡፡ ጆሮውን ማመን የተቸገረ የሀገሬው ህዝብ እዚህም እዚያም እየደወለ የሰማሁት እውነት ነው ሲል ሲቃ እየታገለው ያረጋግጥ ጀመር፡፡ የማይታመን ምናልባትም ሁሉም ሰው ሊሰማውና ሊያምነው የማይፈልገው ከባድ እውነት ሆነ፡፡
የኢትዮጵያ ተወዳጅ መሪ! የአፍሪካ አንደበት ብልሁንና አስተዋዩን ሰው ዓለም በዚች እለት ከመዳፏ ተነጥቀች፡፡ ጓድ መለስ ዜናዊ እንደ ዓይኑ ብሌን ይመለከተው ከነበረው የኢትዮጵያ ህዝብ በአካል ተነጠለ፡፡ ይህንን እውነታ ለመቀበል የተቸገረው የሀገሬ ህዝብ ልጅ አዋቂው በእንባ ተራጨ፡፡ ሴቶች ልጃችንን፣ አባታችንን፣ ጠበቃችንን አጣን ሲሉ በምሬት እንባቸውን አዘሩ፡፡ የጓድ መለስ ወዳጅና አድናቂ በሙሉ የተፈጥሮ ህግን አሜን ብሎ ለመቀበል ተቸገረ፡፡ ለምን? ሲል ወደ ሰማይ እያንጋጠጠ ፈጣሪውን ተማፀን፡፡ የሀገራት መሪዎች ከጫፍ እጫፍ ተነቃነቁ፡፡ በእርግጥም ዓለም አንድ ታላቅ ሰው አጣች ሲሉ በየፊናቸው ተናገሩ፡፡
በኢትዮጵያ ታሪክ እልፍ ህዝብ ከዳር እዳር ተሰልፎ በአንድ ልቦና እንባ እየተራጨ የሸኘው ተፅእኖ ፈጣሪ ታላቁ የህዳሴአችን መሀንዲስ ጓድ መለስ ዜናዊ፡፡
ጥቂት የማይባሉ ሰዎች ምን ሊውጠን ነው ሲሉ ስጋታቸውን ገልፀው ነበር፡፡ በሀገር ውስጥም ሆነ በተለያየ የዓለማችን አካባቢዎች የሚገኙ ፀሐፊያን ከመለስ ህልፈት በኋላ የኢትዮጵያ ዕጣፈንታ ምን ሊሆን እንደሚችል በስፋት ማተቱን ተያያዙት፡፡ ኢትዮጵያውያን ግን ያንንም ያንንም ለማለት ጊዜ አልነበረንም፤ ሁላችንም በሀሳብ ባህር ሰጠምን፡፡ ኢትዮጵያ ትፈራርሳለች ብለው ሟርታቸውን ይነዙ ለነበሩ ሟርተኞች ህዝቡ አንድ ሆኖ እንደ ብዙ፣ ብዙ ሆኖ እንደ አንድ በመተጋገዝ ሀገራችን ቁልቁል እንዳትመለስ በመትጋት ፅናቱን ለዓለም በተግባር ለማሳየት ከጠለቀበት ጥልቅ የሃሳብና የሰመመን ባህር ባትቶ ተነሳ፡፡ በአንድ ድምፅም መለስ በህይወት ዘመኑ ተስፋን እንጂ ተስፋ መቁረጥን ያላስተማረ ጀግና መሪ በመሆኑህያውነትህን ስራህን በማስቀጠል እናሳያለንሲል ከመስዋእቱ ማግስት ከዳር ዳር በቁጭት ተነሳ፡፡ ኢትዮጵያውያን ከታጋይ መለስ ዜናዊ የተቀበልነው የህዳሴ ቃልኪዳን አለንና የበለፀገች ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ ቃልኪዳናችንን እንደገና በማደስ ወደፊት መገስገሱን ተያያዝነው።
የሀገራችንን ህዝብ ከድህነት ቀንበር ነፃ ለማውጣት የሀገር በቀል ፖሊሲና ስትራቴጂ መሀንዲሱ በጓድ መለስ ሃሳብ አመንጭነት የተቀየሱት ፖለሲና ስትራቴጂዎች በላቀ ሁኔታ በመተግበራቸው የጀመርነው የህዳሴ ጉዞ በተያዘው አቅጣጫና ፍጥነት ቀጥሏል። የሀገራችን ዜጎች የነፍስ ወከፍ ገቢ 550 የአሜሪካን ዶላር ከፍ በማድረግም ከድህነት ወለል በታች ያሉ የሀገራችን ዜጎች 2005 ዓም ወደ 26 በመቶ ዝቅ ማድረግ ተችሏል፡፡ የባለራዕዩን አደራ ጠብቀን መገስገሱንም ተያይዘነዋል።
ጓድ መለስ ድህነትን ከጫንቃችን እስከምናወርድ ድረስ እረፍት ሊኖረን አይገባም የሚል አቋም በተደጋጋሚ ሲያሰማ የነበረ የእድሜ ልክ ታጋይ ነበር፡፡ ድህነትን ታሪክ ለማድረግ ደግሞ የመላው ህዝባችን ርብርብ ወሳኝ መሆኑን ሳይጠቅስ አያልፍም፡፡ በተለይ ወጣቶች አፍላው ጉልበታቸውንና እውቀታቸውን ለሀገራቸው ልማት ማዋል እንዳለባቸው ደጋግሞ ይመክር ነበር፡፡ ከወጣቶች ጋር በተደረጉ የተለያዩ መድረኮችም ሁሉንም እንደየደረጃው እና እንደየአመጣጡ መቅረብና ማስተናገድ የሚያውቀው ጓድ መለስ ወጣቶችን ከጎናችን አድርገን መጓዛችን ግዴታችን ነው፣ ያለእናንተ ሁሉን አቀፍ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ሃገር አትለማም፣ እናንተ የነገ ሃገር ተረካቢ የኢትዮጵያ ብሩህ ተስፋ ናችሁ በማለት ያለወጣቱ ተሳትፎ ልማት ፍፁም ማሰብ እንደማይቻል በተደጋጋሚ ሲናገር ይደመጥ ነበር፡፡ ለጓድ መለስ አርቆ አሳቢነትና የተሟላ ብስለት ሁሌም አክብሮት ያላቸው ወጣቶች ታዲያ ተደራጅተው ሃብት በማፍራት፣ አርሰውና አዘምረው ጥሪት በማከማቸት በከተማም ሆነ በገጠር የመሪያቸውን ራዕይ በማሳካት አኩሪ ተግባር መፈፀሙን ባህል እያደረጉት  ነው፡፡
አገር የምትለወጠው ያለማመንታት ተግቶ በመስራት በመሆኑ ዛሬ ዛሬ በሀገራችን የማይሰሩ እጆች እየተመናመኑ ሄደዋል፡፡ የሀገራችን ወጣቶች በተፈጠረላቸው ምቹ የስራ እድል ተሰማርተው የሀገራችንን ህዳሴ የሚያበስሩ የለውጥ ሃዋርያ እየሆኑ ነው፡፡ መልካምነትንና ልማትን፤ ለሀገር ሰርቶ ለዘመናት ሲያሸማቅቀን ከነበረውና ብሔራዊ ክብራችንን ዝቅ በማድረግ ሲያዋርደን የነበረውን ድህነት በመፋለም አዲስ ታሪክ መስራት እንዳለብን ያስተማረንን ታጋይ መለስ ዜናዊን በስራችንና በመለወጣችን ሁሌም እንደዘከርነው እንኖራለን፡፡
ወጣቶች የተረጋጋች፣ አስተማማኝ ሰላሟ የተረጋገጠባትና በወጣት ላይ እምነትና ክብር ያላት ሀገር እንድትሆን የታገለላቸውን መሪ ራዕይ ለማሳካት ከመስዋእቱ ማግስት በቁጭት ተነስተዋል፡፡ በተግባርም ድህነትን ታሪክ ለማድረግ በየተሰማሩበት እየታገሉ ይገኛሉ፡፡
ጓድ መለስ ሀገራችን ከግብርና መር ኢኮኖሚ ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ መሸጋገር የምትችልበት መደላድል እንዲፈጠር ቀን ተሌሊት ሰርቷል፣ ለፍቷል፡፡ እድገታችንን የሚመጥን ፈጣንና አስተማማኝ የኤሌክትሪክ ሃይል የማመንጨት አቅማችንን ለማሳደግ በእኛ አቅም የማይታሰቡ የሚመስሉ ግዙፍ ፕሮጀክቶችን እውን በማድረግ በአመራርነት ዘመኑ ያስተማረን የይቻላል ባይነት እና የአይበገሬነት አርማችን ጭምር ነው፡፡  
የማይታሰብና ተረት ተረት የነበረው የአባይ ወንዝ ለልማት የሚውልበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ በአባይ ወንዝ ላይ እየተገነባ ያለው የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድብ ለሀገር ከሚያበረክተው ኢኮኖሚያዊ፣ ማሕበራዊና ፖለቲካዊ አስተዋፅኦ አልፎ የአካባቢውን አገራት ህዝቦች ኢኮኖሚያዊ ትስስር ጭምር የሚያጠናክር ነው፡፡
ኢትዮጵያውያን ለዘመናት ሲመኙት ነገር ግን በምኞች ብቻ ታጥሮ የኖረው የህልም ዳቦም ዛሬ ላይ እውን ሆኗል፡፡ ህዝቡ ለአባይ ያለውን ቁጭት እንጉርጉሮ በመደርደር ከመግለጽ ወደ ተግባር ምዕራፍ በመሸጋገር አባይን ለልማት እንዲተባበር እያስገደደው ነው፡፡ አሁን ዜማው፣ ቅዳሴውና ሶላቱ ሁሉ ልማት ሆኗል፡፡ ለሩቅ አሳቢው መሪያችን ምስጋና ይጋባውና ኢትዮጵያ የራሷን ህዝብ ጥቅም የሚያስከብሩ በርካታ ዓበይት ፕሮጀክቶችን የምትተገብርበትን አቅም ገንብታለች፡፡ ይህም ጓድ መለስ በበርካቶች ልብ ውስጥ በማይፋቅና በማይደርቅ የህይወት ቀለም ታትሞ እንዲኖር አድርጎታል፡፡ አሁንም መላው የሃገራችን ህዝብም ከዳር እዳር በመነቃነቅ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድብን ጨምሮ በታጋይ መለስ የተጀመሩትን ታላላቅ ፕሮጀክቶች ለማጠናቀቅ በትጋትና በከፍተኛ ወኔ እየሰራ ይገኛል፡፡ ህዝቡ በሚያስገርም ሁኔታ በጉልበቱ፣ በእውቀቱና በገንዘቡ ግድቡን እየደገፈ ይገኛል፡፡ የግድቡ ግንባታም ዛሬ ላይ 38 በመቶ መድረስ ችሏል፡፡
ጓድ መለስ ለሀገሩ ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካም ታማኝ አንደበት በመሆን ሳይታከት አገልግሏል፡፡ አፍሪካውያን ልዩነታቸውን ወደ ጎን በመተው ለአህጉራቸው ዘላቂ ልማትና ተሰሚነት በአንድነት መነሳት እንደሚገባቸው በፅናት በመታገሉ የአፍሪካውያን የወንድማማችነት መንፈስ በቀጣይነት ማደስ የሚያስችል መሰረት መጣል ችሏል፡፡ ዛሬም ድረስ ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡ ኢትዮጵያ ጎረቤት ሃገራት ከጎናቸው የማይነጥሏት ለሰላማቸው በእጅጉ የሚፈልጓት ቀዳሚ ተመራጭ ሃገር መሆን ችላለች፡፡ ለጎረቤት ሃገር ሱዳንና ሶማሊያ ዘላቂ መረጋጋት ዋጋ እየከፈለች ያለች ሃገር ናት፡፡ በአህጉራዊ ድርጅቶች ላይ ያላት ተደማጭነት አሁንም እንደቀጠለ ነው፡፡
ከሀገራት ጋር ያለን ግንኙነት አሁንም የውጭ ጉዳይና የብሔራዊ ደህንነት ፖሊሲያችንን መርህ የተከተለ ነው፡፡ የሀገራችን ዋነኛ ጠላት ድህነት መሆኑን አንጥሮ የሚያስቀምጠው ፖሊሲያችን የምንዋጋውም የምንረባረበውም ድህነትን ለማስወገድ በመሆኑ በማንኛውም ሁኔታ የራሳችንን አቋም በግልፅ ማራመድ የሚያስችለን ፖለቲካዊ ስብዕና መገንባት ችለናል፡፡ ዛሬም ፀረ ሰላም ሃይሎችን በማያዳግም መልኩ መመከትና ማምከን የሚችል ስብዕና እንዳለን በተደጋጋሚ እያሳየን እንገኛለን፡፡ ሰላም በሌለበት ሁሉ የምናስበው ልማት፣ ዴሞክራሲና ብልፅግና በፍፁም አይታሰብምና!
በፀረ ድህነት ትግላችን ላይ የተጋረጠውን የሀይማኖት አክራሪነትና የአሸባሪነት አደጋ መመከት የሚችል ህዝብ ሆነናል፡፡ በጠንካራ መሰረት ላይ የገነባነው በመፈቃቀድ ላይ የተመሰረተው ዴሞክራሲያዊ አንድነታችን የእግር እሳት የሆነባቸውና የመሪያችን ሞት ሀገራችንን ወደ ቀውስና ሁከት የሚወስዳት አድርገው በመመኘት ያልሙ የነበሩትን ህልማቸውን ቅዠት አድርገን ዛሬም አንድነታችንን ጠብቀን አብበን እየቀጠልን ነው፡፡ የህዳሴ ጉዞአችንን በማፋጠንም የታላቁ መሪያችንን አደራ ለመወጣት በከፍተኛ መነሳሳት እየተረባረብን ነው።
የሀገራችን እድገት ደምቆና ጎምርቶ ወደ ፊት እየተምዘገዘገ፣ ሰላማችንን መላው ህዝባችን ዘብ ሆኖ እየጠበቀ፣ የመንገድና የባቡር ግንባታ፣ የመኖሪያ ቤት ግንባታ በተጠናከረ ሁኔታ በማስቀጠል የህዘቦች ተሳትፎና ተጠቃሚነት በቀጣይነት በመሻሻል ላይ ነው፡፡ በገጠር የተፋሰስ ልማቱ ባሰብነውና ባቀድነው ልክ እየተጠናከረ ሄዷል፡፡ የአረንጓዴ ልማት ስራችን ላፍታም ከግባችን ሳይነጠል እየተተገበረ ይገኛል፡፡ የሰብል ምርትና ምርታማነታችን ጨምሯል፡፡ ሀገራችን ብሩህ ተስፋ ያላት ሃገር ሆናለች፡፡ ጓድ መለስ፣ ድህነትን ከእግራችን ስር የማድረግ ህልምህ በእኛ በልጆችህና በጓዶችህ እውን የሚሆንበት ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡
ትፈራርሳለች የተባለችውን ሃገር ወጣትነትህ ሳይገድብህ ከጥቂት ቆራጥ የህዝብ ልጆች  ጋር በመሆን መስዋዕት ከፍለህ በሁለት እግሯ አቁመሃታልና ሁሌም ስምህ ከመቃብር በላይ ዘላለም ሲነሳ ይኖራል፡፡ በህያው ስራህም ህያው ሆነህ በልቦናችን እናኖርሃለን። እኛም አደራህን በመወጣት የበለፀገች ዴሞክራሲያዊት ሀገር ለመገንባት በአንተና በእነዚያ አእላፍ ቆራጥ የህዝብ ልጆች ስም ቃል ገብተናልና ቃላችንን በተግባር እንጠብቃለን፡፡

No comments:

Post a Comment