EPRDF is a ruling party committed to realize Ethiopia's Renaissance.

Thursday, 14 August 2014

መለስና ወጣቶች

ታላቁ መሪ መለስ ዜናዊ ከሀገር አቀፍ የወጣቶች ተወካዮች ጋር በተለያዩ ጊዜያት በሀገራዊና ወጣቶችን በሚመለከቱ ወቅታዊ ጉዳዮች የፊት ለፊት ውይይቶችን በማድረግ ጠቃሚ መልዕክቶችን አስተላልፈዋል፡፡ ለአብነትም በ2000 በተካሄደ ሀገር አቀፍ የወጣቶች የውይይት መድረክ ከወጣቶች ተወካዮች የቀረቡ ጥያቄዎችን መሰረት በማድረግ ከወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ጋር በማያያዝ የሚከተሉትን መልዕክቶች አስተላልፈዋል፡፡
‹‹የኃላፊነት ቦታን ከወሰዳችሁ በኋላ እኛ ከሰራነው ስራ በተሻለ መልኩ መስራት አለባችሁ፡፡ ይህን ማድረግ የምትችሉት ሁለት ነገር ስታደርጉ ነው፡፡ አንደኛ የትምህርት ጊዜያችሁን በአግባቡ ስትጠቀሙበትና ማግኘት ምትችሉትን ያህል እውቀት በላቀ ደረጃ ለማግኘት ስትረባረቡ ነው፡፡  እውቀት ትልቁ መሳሪያችሁ ነው፡፡ የድህነትን ተራራ የሚያፈርሰው ዋነኛው ጥይት እውቀት ነው፡፡ ይህን እውቀት መያዝ መቻል አለባችሁ፡፡ ሁለተኛ እውቀት የንድፈ ሃሳብ ጉዳይ ብቻ አይደለም፡፡ የማህበራዊ ኑሮ ብቃትም ይጠይቃል፡፡ በመሆኑም እውቀቱን እንደያዛችሁት ወዲያው ተግባራዊ ማድረግ አለባችሁ፡፡›› 
‹‹ለወጣቱ ቅድሚያ በመስጠት ወጣቶችን በሀገር አቀፍ ደረጃ ለማሳተፍ ፓርቲዎች የራሳቸውን ድርሻ መወጣት አለባቸው፡፡ ወጣቱ ራሱን በማደራጀት በመድረኮች በንቃት ተሳታፊ መሆን አለበት፡፡ ድርሻውንም መወጣት አለበት፡፡  የወጣት ማህበራት ነፃ ማህበራት መሆን ይገባቸዋል፤ ወጣቱ ራሱ ጊዜውን በመስጠትና ያሉትን ትናንሽ ሳንቲሞች መስዋዕት በማድረግ የሚያንቀሳቅሳቸው ማህበራት መሆን አለባቸው፡፡››
‹‹መንግስት ወጣቶች ሊደራጁ የሚችሉበትን ምቹ ሁኔታ በመፍጠር፣ ከተደራጁም በኋላ ከውሳኔ ሰጪ አካላት ጋር የጋራ መድረክ እንዲኖራቸው በማድረግ ድርሻውን ሊወጣ ይገባል፡፡ ይህንን ተግባራዊ እንደምናደርግና በቀጣይ አጠናክረን እንደምንሄድበት ላረጋግጥላችሁ እችላለሁ፡፡ ወጣቱ የለውጥ ኃይል መሆኑን የሚያረጋግጠው ውጤቱ እስኪገኝ ድረስ የማይቀለበስ ቁርጠኝነት ያለው ተግባር ሲያከናውና ሲሳካለት ብቻ ነው፡፡››
‹‹በመረጃ ላይ የተመሰረተ አስተሳሰብ ነው የዴሞክረሲ ምንጭ፡፡ ምክንያታዊ ትንታኔ ነው የለውት ምንጭ የሚሆነው፡፡ ስለዚህ ሁሉን ነገር ምክንያታዊ በሆነ መንገድ ማየት መቻል አለባችሁ፡፡ ወጣት ማለት በስሜት የሚነዳ ማለት አይደለም፤ የለውጥ ጉልበት ያለው ኃይል ማለት ነው እንጂ፡፡››
‹‹ይህንን የወጣቶች ፓኬጅ ፕሮግራም ማንም ሰው እንዲያሰናክልባችሁ መፍቀድ የለባችሁም፤ የራሳችሁ ፕሮግራም ነው፡፡ በራሳችሁ ይህን ፕሮግራም ልትከላከሉት፣ አፈፃፀሙ ላይ ገፍታችሁ ልትሄዱበት ይገባል፡፡ ሁላችንም የየድርሻችንን ከተወጣን የወጣቶቹ ፓኬጅ አፈፃፀሙ በፊት ያጋጥሙ ከነበሩት ችግሮች የተሻለ እንደሚሆን መገመት ይቻላል፡፡››
‹‹መብትና ጥቅማችሁ በማይከበርበት ሀገር ሄዳችሁ ያልፍልናል የሚል አቋም ይዛችሁ መሰደድም የራሱ አደጋ አለው፡፡ ከባርነት  ያልተለየ ኑሮ ውስጥ የተጠመዱ በርካታ ኢትዮጵያውያን እንዳሉም እናውቃለን፡፡ ስለዚህ ዋናው መፍትሄ ሀገርን እያለሙ ከሀገር ጋር አብሮ መልማት ነው፡፡››

No comments:

Post a Comment