EPRDF is a ruling party committed to realize Ethiopia's Renaissance.

Thursday, 29 March 2018

በትውልድ ጅረት ያልተዛነፈ ፍትሃዊ አቋም


(በውብዓለም ፋንታዬ)
በሀገራችን ስነ-ቃል ውስጥ እንደ አባይ ገዝፎ የሚጠቀስ የለም፡፡ ፍቅር፣ ናፍቆት፣ ቁጭትና ብሶትን ለመግለጽ በምንጠቀማቸው ተረትና ምሳሌዎች እንዲሁም ዘፈንና እንጉርጉሮ ውስጥ አባይ የላቀ ስፍራ አለው፡፡ በተረትና ምሳሌዎቻችን ወንዝ ወይም ግዑዝ ፍጡር እስከማይመስል ድረስ አባይ ውሃነቱን ትቶ ሰብዓዊ ማንነት ተላብሶ ሲዳሰስ፣ ሲወቀስና  ሲናገር ይታያል፡፡ ከአይበገሬነቱ፣ አባካኝነቱና አስቸጋሪነቱ በተጨማሪ ለጋስነቱና ውብ ተፈጥሮው በስነ-ቃሎቻችን ውስጥ ይንጸባረቃል፡፡

ከሀገራችን አልፎ በሌሎች ወግና ልማድ እንዲሁም ስርዓተ አምልኮ ውስጥም ይህ ወንዝ የገነነ ቦታ አለው፡፡ የጥንቶቹ ግብጾች ለም አፈር እየተፋ በምርት የሚያንበሸብሻቸውን የወንዝ አምላክ ሃፒ (Hapi) ብለው ሲሰይሙት፤ ለቸርነቱ መስዋዕት ሲሰውለት እንደነበር በወንዙ ዙሪያ የተጻፉ ጽሁፎች ያትታሉ፡፡ እነዚህ ህዝቦች ወንዙ ከሁለት ተራሮች ግርጌ ወደ ምድር ወጥቶ በግብጽ ምድር ላይ እንደሚፈስ እንጂ ትክክለኛ የወንዙ ምንጭ የት እንደሆነ እንኳን አያውቁም ነበር፡፡ 
የወንዙ ምንጭና ለግርጌዎቹ ህዝቦች ፍሰሃ የሆነው የወንዙ ውሃ 86 በመቶው ከእኛ ሀገር ሲሄድ ለታላቅነቱ የንግስና አክሊል ደፍተንለት በእንጉርጉሮ ለዘመናት ለትውልዶች ያለ ልዩነት ስንሸኝ ለእኛ ብቻ የተሰጠን ሳይሆን፤ አባይ ከተፋሰሱ ህዝቦች አልፎ ለሌሎች የሚበቃ የልማት ዋርካ እንደሚሆን ሳንጠራጠር ነበር፡፡ የወንዞች ሁሉ አውራ የሆነው ይህ ወንዝ ልክ በሌለው ድፍረቱ ገመናችንን አሳጥቶ አንገት ቢያስደፋን፤ ለሌላው ሲሳይ ሲሆን ልጓም ለማበጀት እጅ አጥሮን በነበረ ጊዜ እንኳ አባይ ከማንም በላይ ለእኛ ቅርብ ነበር፡፡ ለዚያም ነው ከትውልድ ትውልድ ለአባይ ያለው ስሜት ከስነ-ቃል በቀር የማይለዋወጠው፡፡ የአባይ ማንነት ማንነታችን በመሆኑ ከአጠገባችን እንዳይለይ ልጆቻችንን በስሙ አባይ፣ አባይነሽ፣ አባይነህ ብለን ሰይመናል፡፡
በሺህ ኪሎ ሜትሮች ርቀት ከወንዙ ሸለቆ በማለዳ እሸት ከሚቋደሱ፤ መረብ ዘርገተው የአሳ ምርት ከሚያፍሱ የበለጠ ተስፋው ፊታችንን ሲያወዛ፤ ወዲያ ማዶ በወንዙ ብርሃን ጨለማ ሲረታ፤ እኛ ጨረቃ እየሞቀን ስለ ታላቅነቱ አንጎራጉረናል፡፡ ለሙን አፈር ለማስረከብ ሲጠደፍ፤ ድፍርስ መልኩን እያየን ‹‹ዛሬስ አባይን ከፋው›› ብለን፤ በወንዙ ዳር በሚገላበጠው አዞ ውስጥ የነገዎቹን ጀልባዎች አሻግረን እያማተርን በሌላው ተጠቃሚነት ቅንጣት ታክል ሳንቀና ከአባይ ጋር ኖረናል፡፡ እንደ ወንዙ የውሃ መጠን የሚቀያየር ሳይሆን በትውልድ ዑደት የማይናወጥ ፍቅርን ለግሰን በጣና ካህናት ህብረ ዜማ፤ በሼኮቹ አዛን፤ በወፎቹ ሽብሸባ አጅበን አባይን በእንግዳነት ለሚጠብቁት ሸኝተናል፤ እየሸኘንም ነው፡፡
ሲያሰኘው በዝምታ፣ ሲሻውም እየተነፋረቀ የኛ ጉዳይ ግድ ሳይሰጠው ክረምት ከበጋ የሚገማሸረውን አባይ በአመጸኛ ልጅ መስለን በአዋሽ ስንጽናና ትውልድ በትውልድ ሲተካ የህዳሴው ትውልድ ፍትህን ሳያጓድል፤ መርህን ሳይሸረሽር እንቆቅልሹን እንዲፈታ በታሪክ ሲመረጥ በአንድነት ተሰልፎ አለኝታነቱን አስመስክሯል፡፡ ከትውልድ ትውልድ እተሸጋገረ በስነ-ቃል በልባችን ውስጥ የታተመውን፤ ከእኛ ጋር የተቆራኘውን ማንነት በተግባር ልንኖረው ከአባይ ጋር የልማትና የእድገትን ሀሁ ልንቆጥር ጉባ ላይ ቃል ኪዳን ካሰርን ሰባት ዓመታትን ቆጥረናል፡፡ 
በተፈጥሮ ኃብታችን ለመጠቀም ማንንም ማስፈቀድ እንደማያስፈልግ በመገንዘብ አባይን የመገደብ ዜናው በተበሰረ ቅጽበት ህጻን- አዛውንት፣ ተማሪ- ነጋዴ ሳይል ሁሉም ከያለበት የህይወት ፈርጅ ለአባይ ጥሪ ምላሽ የሰጠው ትውልድ፤ ያጋመሰውን የግድቡ ግንባታ ለማገባደድ እየተጣደፈ ይገኛል፡፡  ከዕለት ጉርሱ ቀንሶ ምንም ሳይሰስት ለግድቡ እውን መሆን የተሰለፈው ህዝብ ድህነት ነጋችንን ከመስራት እንደማይገድበን ያረጋገጥንበት ነው - ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ፡፡
ከጉልበትና እውቀት በተጨማሪ እስከአሁን ከ10 ቢሊየን የሚልቅ ገንዘብ ለግንባታው የተበረከተለት ታላቁ የህዳሴ ግድብ ሲጠናቀቅ 6ሺ 450 ሜጋ ዋት ኃይል በማመንጨት ከመብራት ጋር የማይተዋወቀው 70 ከመቶ የሚጠጋው ህዝብ ብርሃን እንዲያገኝ፤ ነባር ፋብሪካዎች አስተማማኝ የኃይል ምንጭ አግኝተው ያለስጋት እንዲያመርቱ፤ የሀገርን ህዳሴ የሚያፋጥኑ አዳዲስ ፋብሪካዎች እንዲተከሉ በማድረግ የህዳሴ ውጥናችንን ሊያሰምር ወደ መገባደጃው እየተንደረደረ ይገኛል፡፡ በአሸዋና ጠጠር ውህደት ታግዞ ብረት በኮንክሪት እየተለበጠ፣ ቁመትና ወርዱ እየተሰደረ ያለው የአፍሪካ ግዙፉ ግድብ የልማታችን ፈርጥ፣ የህዳሴያችን ማማ፤ ከወንድም ህዝብ ጋር ደግሞ የልማት ትስስር ምሰሶ ሊሆን ግንባታው 64 በመቶ ደርሷል፡፡
ይቻላልንና የትውልዱን ቆራጥነት ያጣመረው ይህ ግድባችን ከኃይል ማመንጫነቱም በላይ ከናይል አዞዎች የሚበልጡ ቅንጡ ጀልባዎች የሚርመሰመሱበት፤ ለሰው ሰራሽ ሃይቅና ለ40 ውብ ደሴቶች መፈጠር ምክንያት የሚሆን ግድብ ነው፡፡ ድንበር ተሻግሮ ካሉት የናይል ህዝቦች እኩል መረብ ዘርግተን አሳ የምንዘግንበትና የፍትሃዊ ተጠቃሚነት ምዕራፍ የሚበሰርበትም ነው፡፡ ድፍርስ መልኩን እያየን ለአባይ የምንታመምለት ዘመንን ሸኝተን  በሰማያዊ መልኩና  በሚነፍሰው አየር፤ እንደ ግርጌው ሀገራት ሁሉ በዳሪቻዎቹ ቁጭ ብለን ከተፈጥሮ ጋር የምንነጋገርበት፤ ከአባይም ጋር የምንመሰጋገንበት ምዕራፍ በህዝባችን ትብብር እውን ሊሆን ጥቂት ጊዜ ብቻ ቀርቶታል፡፡
ዛሬም ቦንድ ለመግዛትና ስጦታ ለማበርከት ለዚህ ተግባር በተዘጋጁ ቦታዎችና በባንክ የሚታየው ወረፋ ህዝቡ የጀመረውን ውጥን ሳያገባድድ እንደማይመለስ የሚያሣይ ነው፡፡ በተለያዩ የግድቡ የግንባታ ምዕራፎች ከ20 ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያንን የስራ ባለቤት የሚያደርገው ይህ ግድብ ከ32 ሀገራት የተውጣጡ የመስኩ ባለሙያዎች ለግንባታው ስኬት ደፋ ቀና እያሉ የሚገኙበት ነው፡፡
በኢህአዴግ የሚመራው የኢፌዴሪ መንግስትም ግንባታውን እንዳስጀመረ ሁሉ የግድቡ ግንባታ ለአፍታ እንኳን እንዳይቋረጥና ከወዲያ ‹‹እኛ ልንጠማ…›› ከወዲህ ደግሞ ‹‹ግድብ የለም አትታለል፤ ከሌላ ሊያጋጩህ ነው…›› በሚሉ አሉባልታዎችና መሰረተ-ቢስ ክሶች የህዝቦች ትስስር እንዳይላላ የቤት ስራውን በሚገባ እየተወጣ ነው፡፡ 
አባይ የሚወቀስበት የታሪክ ምዕራፍ ሊዘጋ የውዳሴ ዘመን ተጀምሯል፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብም የጀመረውን ውጥን ቋጭቶ ለዘመናት የተጠማውን የልማት በረከት ለመቋደስ በወሳኝ ምዕራፍ ላይ ደርሷል፡፡

No comments:

Post a Comment