(በውብዓለም ፋንታዬ)
ከ2008
ዓ.ም አጋማሽ ጀምሮ በተለያዩ የሀገራችን አካባቢዎች የጸጥታ መደፍረስ ችግሮች ተስተውለዋል። በዚህም የዜጎች ህይወት ጠፍቷል፤
በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ከቀዬያቸው ተፈናቅለዋል፤ የሀገር ሃብት ወድሟል፤ የጸጥታ አካላትን ኢላማ ያደረጉ ጥቃቶች
ተፈጽመዋል። በዚህ ምክንያትም በ2009 ዓ.ም መጀመርያ ችግሩን ለመቀልበስ በማሰብ ለአስር ወራት የዘለቀ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ
ታውጆ ነበር።
የሰላም
ሁኔታው መሻሻል በማሳየቱ አዋጁ እንዲነሳ ተደርጎ የነበረ ሲሆን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ዳግም ችግሩ ዳግም ተባብሶ ስርዓት
አልበኝነት እየነገሰ መጥቷል። በህዝቦች መካከል መቃቃር እንዲፈጠር፤ አብሮነትና አንድነት እንዲሸረሸር የሚያደርጉ ሁከቶችና
ብጥብጦች ተከስተዋል። ሰላማዊ ዜጎች ከቤት ንበረታቸው ተፈናቅለዋል፤ ከቦታ ቦታ የመንቀሳቀስ ሁኔታ ተስተጓጉሏል።
በመሪው
ድርጅት በኢህአዴግ በኩል የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት የተለያዩ እርምጃዎች እየተወሰዱ ይገኛሉ። ውክልና ያላገኙ ድምጾች
እንዲወከሉና የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋትና ብሄራዊ መግባባትን ለመፍጠር ሲባል የተለያዩ የህግ ታራሚዎች ክሳቸው ተቋርጦ እና
በይቅርታ እንዲፈቱ ተደርጓል።
ይህ
እየተካሄደ በሚገኝበት ወቅት ላይ የሰላምና የጸጥታ ሁኔታ መሻሻል ሲገባው በተቃራኒው ሁከት እየተባበሰ ከመደበኛው የህግ
ማስከበር አግባብ አቅም በላይ እየሆነ በመምጣቱ የህዝቡን ደህንነት ስጋት ውስጥ ከትቷል። ስጋት ብቻም ሳይሆን ከፖለቲካ ምህዳሩና
ብሔራዊ መግባባት ጋር የማይያያዙ ይልቁንም የተጀመሩትን የለውጥ እንቅስቃሴዎች የሚያስተጓጉሉ ድርጊቶችን ስናስተውል ሕገ-መንግስቱንና
ሕግ-መንግስታዊ ስርዓቱን በኃይል ለመናድ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች መኖራቸውን አመላካች ነው።
ለዓመታት
የተገነባውን ልማት ለመናድና ሀገር ስትቃጠል ዳር ሆኖ ለመሞቅ ባሰፈሰፉ አካላት የተደገሰውን ይህንን የጥፋት መንገድ የተገነዘቡ
ኢትዮጵያውያን መንግስት የህግ የበላይነትን እንዲያረጋግጥና ይህንን አካሄድ እንዲያስታግስላቸው በተለያዩ መንገዶች ጥያቄ
አቅርበዋል።
መንግስትም
ይህንን ጥያቄ ተቀብሎ በዜጎች ሕይወትና ሰላም እንዲሁም በሀገር አንድነት ላይ የተቃጣውን አደጋ የመመከት ግዴታና ኃላፊነቱን
ለመወጣት በሕገ-መንግስቱ በተደነገገው መሰረት በሚኒስትሮች ም/ቤት የካቲት 9 ቀን 2010 ዓ.ም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ደንግጓል።
በአሰራሩ መሰረት አዋጁ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦም በአብላጫ ድምፅ ፀድቋል።
የህገ
መንግስታችን አንቀጽ 93 ’ሀ’ ስለ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በተመለከተ የውጭ ወረራ ሲያጋጥም ወይም ሕገ መንግስታዊ ሥርዓቱን
አደጋ ላይ የሚጥል ሁኔታ ሲከሰትና በተለመደው የሕግ ማስከበር ሥርዓት ለመቋቋም የማይቻል ሲሆን፤ ማንኛውም የተፈጥሮ አደጋ
ሲያጋጥም ወይም የህዝብን ጤንነት አደጋ ላይ የሚጥል በሽታ ሲከሰት፤ የፌደራሉ መንግስት የሚኒስትሮች ምክር ቤት የአስቸኳይ ጊዜ
አዋጅ የመደንገግ ሥልጣን እንዳለው ያስቀምጣል።
የአዋጁን
መውጣት ተከትሎ አንዳንዶች በማህበራዊ ሚዲያ በሚያሰራጩት መልዕክታቸው አጥብቀው ሲቃወሙትና ምክር ቤቱም አዋጁን እንዳያፀድቀው
ሲወተውቱ ነበር። የህዝብ ጥያቄዎችን መደበቂያ አድርገው ሊፈፅሙት ያሰቡት ሴራ እንደከሸፈባቸው የተረዱት አካላት አቃቂር
ቢያወጡና አዋጁን ቢቃወሙ የሚገርም ሊሆን አይችልም። የእነዚህ አካላት ተልዕኮና ዓላማ በአባቶችና እናቶች ደምና አጥንት
የተገነባችው ይህች አገር ስትወድቅ ማየት በመሆኑና የአዋጁ መደንገግ ደግሞ የጥፋት ተልኳቸውን በመግታት የተወጠነውን የጥፋት
ድግስ መና የሚያስቀርባቸው ነውና።
አንዳንድ
የምዕራባውያን ተቋማትም ህግና ስርዓት ሲከበር ዓይናቸው ደም የሚለብሰው
የመንግስታትን እጅ የመጠምዘዝ ስውር ተልዕኳቸውን ለመወጣት ካልሆነ በቀር የአንድን ህዝብና ሀገር ሰላምና ደህንነት
ለማስጠበቅ ህግና ስርዓትን ሊያስከብር የሚችል የሕግ ስርዓት ሲዘረጋ ‹‹ለሰው ልጆች ደህንነት እሰራለሁ›› በሚል ተቋም ሊነቀፍ
ባልተገባ ነበር።
እነዚህ
ተቋማትና ግለሰቦች አዋጁ በፓርላማው እንዳይጸድቅ የትችት መግለጫ ሲያሽጎደጉዱና አለፍ ሲሉም የፓርላማ አባላትን በተለያዩ
መንገዶችን ሲያስፈራሩ የከረሙት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የእስትፋሳቸው ዋስትና ይመስል ከሶስት አስርተ ዓመታት በላይ በአስቸኳይ
ጊዜ አዋጅ ስር የቆዩ ሀገራት በምዕራቡ ዓለም መኖራቸውን ዘንግተው አይደለም። የምድራችን ልዕለ ሀያሏ አሜሪካ እ.ኤ.አ ከ1976 እስከ 2014 ባለው
ጊዜ ብቻ ብሔራዊ ጥቅሟን ለማስጠበቅና በተፈጥሮ አደጋዎች ምክንያት 52 የአስቸኳይ ጊዜ አዋጆችን ስራ ላይ አውላለች። በዚች
ሀገር ስለ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አንዲት ዘለላ መስመር እንኳን ሳይጻፍ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅን ማወጅ ወይም ማንሳት እስከሚቻል
ድረስ መለመዱን ዩ ኤስ ቱደይ በኦክቶበር 2014 የፕሪስተን
ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰሩን ዋቢ አድርጎ ያሳፈረው ጽሁፍ ያትታል።
ኦባማ
በስድስት ዓመታት የስልጣን ቆይታቸው ብቻ 9 የአስቸኳይ ጊዜ አዋጆችን ስራ ላይ ያዋሉ ሲሆን ከእሳቸው የስልጣን ዘመን በፊት ከተደነገጉ
አዋጆች መካከል 22ቱን እንዲራዘሙ አድርገዋል። እ.ኤ.አ የ1979ኙን በኢራን የአሜሪካ ዲፕሎማቶች እገታን ተከትሎ በጂሚ
ካርተር የታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለ38ኛ ጊዜ ተራዝሟል። የአሁኑ ፕሬዝዳንት አዋጁን በማራዘም 7ኛው ሰው ሆነዋል። ሌላው
የ9/11 የሽብር ጥቃትን ተከትሎ የታወጀው አዋጅም 17 ዓመታትን ያስቆጠረ ሲሆን በቡሽ የአስተዳደር ዘመን ብቻ 6 ጊዜ ተራዝሞ
ስራ ላይ ሲውል ይህ ድንጋጌ አሁንም በስራ ላይ ይገኛል። በአሜሪካ ታሪክ ክሊንተን፤ ቡሽ እና ኦባማ በስልጣን ዘመናቸው በርካታ የአስቸኳይ ጊዜ
አዋጆችን ስራ ላይ በማዋል ቀዳሚውን ስፍራ የሚይዙ መሪዎች ናቸው።
በዚህ
እያተጋመሰ ባለው ወርሃ የካቲት በጃማይካ በቱሪስት ማዘውተሪያ ቦታ ላይ በደረሰው ጥቃት ምክንያት ለ3 ወር የሚቆይ የአስቸኳይ
ጊዜ አዋጅ ጸድቋል። በደቡብ ኤስያዊቷ ማልዲቭስ አለመረጋጋት መከሰቱን ተከትሎ ለ30 ቀናት የሚቆይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ
ሲታወጅ በኒውዚላንድ በጎርፍ አደጋ ምክንያት በአራት ግዛቶች የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተደንግጓል። እ.ኤ.አ በ2016 የመንፈንቅለ
መንግስት ሙከራ የተደረገባት ቱርክ ለ18 ወራት በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ውስጥ ቆይታለች።
ይህም
የሚያሣየው በሀገርና ህዝብ ላይ የተቃጣ ሰው ሰራሽም ሆነ የተፈጥሮ አደጋን ለመመከት ይህ የህግ አግባብ የእድገትና የቆዳ ስፋት
ስፋት ደረጃ ሳይለይ በትኛውም ሀገር ስራ ላይ ሊውል እንደሚችል ነው። ድንጋጌው እንደ ሁኔታው በመላው ሀገር ወይም በተወሰኑ
አካባቢዎች በሰዓታት ጭምር ተገድቦ ሊደነገግም ይችላል።
ይህ
አለማዊ ነባራዊ ሁኔታ ባለበት በሀገራችን ለ6 ወራት የሚቆይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መታወጁን ተከትሎ አዋጁ አንዳይጸድቅ ዘመቻ
የከፈቱት አካላት ውጥናቸው ስለተቋረጠባቸው ስጋት ውስጥ የገቡ መሆናቸውን የሚያሣይ ነው። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል
ሳይንስና የአለም አቀፍ ግንኙነት አንጋፋው መምህር የሆኑት ዶ/ር ታፈሰ ኦሊቃ ይህንኑ ሃሳብ ይጋራሉ። ቢቢሲ በድረ-ገጹ
ባሰፈረው የምሁሩ አስተያየት ላይ የኢትዮጵያ ጉዳይ የሚያስጨንቃቸው አካላት ለህዝቡ አስበው ሳይሆን ጥቅማቸው ሲነካባቸው ወይም
የሚነካባቸው ሲመስላቸው ብቻ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ትርምስን
በማንገስ ሀገራችን የጀመረችውን የህዳሴ ጉዞ ለመቀልበስ የሚደረግ ጥረት በሕግ አግባብና በህዝቡ ትብብር ይከሽፋል። ለአዋጁ
ተፈጻሚነት ህዝቡ የተለመደውን ትብብርና ድጋፍ በማድረግ እነዚህን አካላት ዳግም እንዲሚያሳፍር ጥርጥር የለውም።
No comments:
Post a Comment