EPRDF is a ruling party committed to realize Ethiopia's Renaissance.

Thursday, 1 February 2018

10 የመፍትሄ ሃሳቦች

(በኤስሮም ፍቅሩ)
ኢህአዴግ ተራማጅ እና ሁሌም ለለውጥ ዝግጁ የሆነ ድርጅት ነው፤ የገናና ስልጣኔ ባለቤትነቷ ተዘንግቶ ስሟ በድህነትና ኋላቀርነት የተለወጠውን ሀገር ለመለወጥ የሚተጋ ፓርቲ፡፡
ኢህአዴግ በወሬ ሳይሆን በተግባር፤ በህዝበኝነት ሳይሆን በህዝባዊነት ወኔን ሰንቆ ለኢትዮጵያ ትንሳኤ መላ ኢትዮጵያዊያንን ከዳር ዳር ያነቃነቀ ድርጅት ነው። ምስክር አምጣ ካላችሁኝ ደግሞ ምስክሬ እዚሁ ሀገሩ ላይ ሆኖ ድርጅቱን ጥረት የሚያግዘው፤ ሲሳሳትም በማረም ከጎኑ የተሰለፈው የሀገሬ ህዝብ ነው።
በኢህአዴግ ውስጥ  በችርግ ተተብትቶ መሰናከልም፣ ራስን ለለውጥ ማዘጋጀትም፤ ድክመትም፣ ጥንካሬም፤ ስህተትም፣ ከተግባር መማርም ጎን ለጎን እንዳሉ አምናለሁ። ሆኖም ከነጉድለቱ፣ ከነሙላቱ ለእኔ ኢህአዴግ መተኪያ የሌለው ድርጅት ነው። ዛሬ በሀገራችን አንዳንድ አካባቢዎች የሚታዩ ችግሮችንም ቢሆን ኢሕአዴግ በአፋጣኝ ፈትቶ ሀገሬን ወደ ቀድሞ አስተማማኝ ሰላሟ እንደሚመልሳት በፍፁም አልጠራጠርም።
ይህ እንዳለ ሆኖ በግሌ አውጥቼ አውርጄ ያገኘኋቸውንና በመሪ ድርጅታችን፣ በመንግስትና በህዝቡ ቅንጅት ቢፈፀሙ በአንዳንድ አካባቢዎች የሚስተዋሉ ሁከትና ረብሻዎችን በዘላቂነት በመፍታት ሀገራችንን ወደ ቀደመ አስተማማኝ ሰላሟ ይመልሷታል ያልኳቸውን 10 የመፍትሄ ሃሳቦች እንደሚከተለው አቅርቤያለሁ፡፡
  • አመራሩ ከጥልቅ ተሀድሶ በኋላ በግምገማ የተለዩ ችግሮችን በዝርዝር ነቅሶ በማውጣት ህብረተሰብ አቀፍ የሆኑ ውይይቶችን በማካሄድ የህዝቡን ጥያቄ በአግባቡ ተረድቶ አፋጣኝ ምላሽ መስጠት ይገባዋል።
  • ህብረተሰቡም ያሉትን የመልካም አስተዳደር፣ የፍትሀዊ ሀብት ክፍፍል፣ የልማት ተጠቃሚነትና ተመሳሳይ ይዘት ያላቸውን ጥያቄዎች በተደራጀ እና ሰላማዊ በሆነ መልኩ ሊያቀርብ ይገባዋል።
  • በሰላም ማስከበር ሂደት ላይ ተሳታፊ የሆኑ የፀጥታ አካላት ማለትም የፌደራል ፖሊስ፣ የክልል ፖሊስ፣ የመከላከያ ሰራዊት አባላት ከወትሮ በተለየ መልኩ ሆደ ሰፊነት በተሞላበት እና በህዝብ አገልጋይነት ስሜት ችግሮችን ለመፍታት መንቀሳቀስ ይጠበቅባቸዋል።
  • ህብረተሰቡ ብሄር ላይ ያነጣጠረ ፅንፈኛ ሀሳብ ይዘው የሚንቀሳቀሱ ሀገራችንን ወደለየለት የከፋ እልቂት ውስጥ ለመክተት የሚጥሩ አካላት እንዳሉ ተረድቶ ሀገራችን ኢትዮጵያን በተቆርቋሪነት መንፈስ በጋራ ሊጠብቃት ይገባል።
  • የሀገራችን ሚዲያዎች ኢትዮጵያን እና ኢትዮጵያውያንን ወደ ፍቅር እና ወደ አንድነት የሚያመሩ፣ መቻቻልን መዋደድን አብሮነትን የሚሰብኩ፣ የሚታዩ መልካም እንቅስቃሴዎችን የሚያበረታቱ፣ ችግር አመልካች ብቻ ሳይሆኑ መፍትሄ ጠቋሚ መሆን ይጠበቅባቸዋል።
  • የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሀይማኖት አባቶች የሲቪክ ማህበራት፣ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ሰላም ያለውን ውድ ዋጋ በማስገንዘብ በተገኘው አጋጣሚ ዘላቂ ሰላም በሀገራችን ውስጥ እንዲፈጠር በጋራ መንቀሳቀስ ይጠበቅባቸዋል።
  • ግጭቶችና ሁከቶችን አባብሶ የመሰረተ ልማት አውታሮችን በማውደም ኢኮኖሚዋ ተሽመድምዶ በውስጧ ያሉ የተፈጥሮ ሀብቶችን መጠቀም የማትችል ሀገር ለመፍጠር ሌት ከቀን የሚለፉ የውጪ ሀይሎች መኖራቸውን ህብረተሰቡ ተገንዝቦ አንድነታችንን አጥብቆ በመጠበቅ የሀገራችንን የእድገትና የህዳሴ ጉዞ ማስቀጠል ይጠበቅበታል።
  • መንግስት በተወሰኑ ከተሞች ላይ የሚታዩትን ለውጦች ወደተለያዩ አካባቢዎች በማሰራጨት ለወጣቶች የስራ እድል በመፍጠር አፋጣኝ ፖሊሲዎችን ቀርፆ ወደ ስራ መግባት ይኖርበታል።
  • ምሁራን፣ የፖለቲካ ልሂቃን፣ የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች በሙሉ ለዘላቂ ሰላም መፍትሄ የሆኑ ሀሳቦችን በማመንጨት ከመንግስት ጋር ውይይት ማድረግ ይገባቸዋል።
  • መላ የሀገራችን ህዝቦች ከምንም እና ከማንም በፊት ለኢትዮጵያ አንድነት፣ እድገት፣ ሰላም እና ፍቅር መቆርቆርና ለተግባራዊነቱም የድርሻቸውን መወጣት ይኖርባቸዋል።
ሰላም!!

No comments:

Post a Comment