EPRDF is a ruling party committed to realize Ethiopia's Renaissance.

Wednesday 20 September 2017

ለበለጠ ስኬት የምንተጋበት የከፍታ ዓመት








ከኤፊ  ሰዉነት
አሮጌውን ዓመት ሸኝተን አዲሱን ዓመት ከተቀበልን ቀናት ተቆጥረዋል፡፡ በያዝነው ዓመት ለአገራችን የስኬትና የብልፅግና፤ ለህዝባችንም የለውጥ ዘመን ይሆን ዘንድ መንግስትና ህዝብ ዓመቱን በብሩህ ተስፋ ተቀብለውታል፡፡ የከፍታና የመለወጥ ዘመን ይሆን ዘንድ እጅ ለእጅ ተያይዘው ለመትመም ቃላቸውን አድሰው ተፍ ተፍ በማለት ላይ ይገኛሉ፡፡ የትናንት ስኬታችን ወደላቀ ምዕራፍ የሚሸጋገርበት፤ ዛሬንና የወደፊቱን የምናቅድበት፤ ውጥናችንን ለማሳካት የምንተጋበት ዓመት ነው 2010፡፡ 
 
አገራችን ባለፉት ዓመታት ዘመን ተሻጋሪ በሆኑ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች በመመራት በብዙ መስኮች አበረታች ስኬቶችን ማስመዝገብ ችላለች፡፡ ኢህአዴግ የሚመራው ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ መንግስታችን የመንግስትንና የህዝብ አቅምን በማቀናጀት በልማት፣ በሰላምና በዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ በየጊዜው እየጎለበተ የመጣ ለውጥ ማስመዝገብ ችሏል፡፡ በዚህም አገራችን የህዳሴ ጉዞዋን ለማሳካት በሚያስችላት ትክክለኛ አቅጣጫ ላይ መሆኗን መናገር የሚቻልበት ቁመና ላይ እንደምትገኝ ዓለም ሳይቀር ምስክርነቱን እንዲሰጥ ያስቻለ እድገት በመመዝገብ ላይ ይገኛል፡፡
ባሳለፍነው ዓመት የኢህአዴግ ምክር ቤት የመንግስት ስራዎችን አፈጻጸም በገመገመበት ወቅት የሀገሪቱን ኢኮኖሚ በዓመቱ የተተነበየውን 11ነጥብ1 በመቶ እድገት ሊያሳካ እንደሚችል አስታውቋል፡፡ ለዚህም አገራችን ዓለም አቀፍ ከሆነው የድርቅ አደጋ ባሻገር የተለያዩ ውስጣዊ ፈተናዎች በበጀት ዓመት የገጠማት ቢሆንም የለውጥ ግስጋሴያችን እንዳይገታ ኢህአዴግ የሚመራው ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ መንግስታችን መስራቱ ለዚህ አብይ ምክንያት መሆኑን መግለፅ ይቻላል፡፡ የትናንት የአገራችንን የተመፅዋችነት ታሪክ ተቀይሮ ችግሮችን መቋቋም የሚያስችል አቅም መፍጠር የተቻለውም ህዝብና መንግስት ባደረጉት የጋራ ርብርብ መሆኑ የሚያጠያይቅ አይደለም፡፡

ባሳለፍናቸው ሁለት አስርት ዓመታት በአገራችን የህዳሴ ጉዟችንን የሚሳልጡ ዘርፈ ብዙ የልማት ተግባራት መከናወናቸው እሙን ነው፡፡ ከአገር ውስጥም ይሁን በውጭ የሚገኘው ጥሪት የቋጠረውን የግል ባለሃብት የለውጡ አካል እንዲሆን ምቹ የስራ ሁኔታዎችን በመፍጠር የተፈፀመው ተግባርም የግል ባለሃብቱ በአገሩ ላይ ሃብቱን እንዲያፈስ ለማድረግ አስችሏል፡፡ ይህ በቀጣይም በተለይ የግል ባለሃብቱ እሴት በሚጨምሩ የአምራች ዘርፎች ላይ እንዲሰማራ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን ከመገንባት ባሻገር የፋይናንስና መሰል እንቅፋቶችን የማስወገዱ ተግባር ተጠናክሮ መቀጠል የሚገባው ይሆናል፡፡ ለዚህ ደግሞ በፌዴራልና በክልል ያሉ የስራ ሃላፊዎች የመንግስትን የፖሊሲ አቅጣጫዎች ተከትለው ተፈፃሚ በማድረግ ሃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል፡፡

አገራችን የታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ጨምሮ ሌሎች የሃይል ማመንጫዎችን በመገንባት ለኢንዱስትሪ መሰረት የሆኑ ተግባራትን በመከወን ላይ ትገኛለች፡፡ የመንገድ፣ የባቡርና ሌሎች የመሰረተ ልማት ግንባታዎችም ኢኮኖሚያዊ እድገቱን መሸከም በሚያስችል ሁኔታ በመስፋፋት ላይ ናቸው፡፡ የመሰረት ልማት የማስፋፋት ጉዳይ በያዝነው ዓመት አንዱ ትኩረት የሚደረግበት ዘርፍ መሆኑን የኢሕአዴግ ምክር ቤት በዓመቱ እቅድ አፈፃፀም ግምገማው ላይ አመላክቷል፡፡ ይህ በቀጣይ አባላት፣ አመራሩን መላው የአገራችን ህዝብ በጥምረት ለሚከውኑት ሁለንተናዊ የልማት እንቅስቃሴ መሰረት እንደሚሆን ግልፅ ነው፡፡

የያዝነው ዓመት ያለፉ ስኬቶቻችን ወደ ላቀ ምዕራፍ የምናሸጋግርበት፣ በድክመቶቻችን ላይ ደግሞ የምንዘምትበት የከፍታ ዘመን ይሆናል ሲባልም መላው የአገራችን ህዝብ የተሻለች ኢትዮጵያን  ለመፍጠር ያለውን ጉጉትና ተስፋ እንዲሁም የመንግስት ቁርጠኝነት ታክሎበት በዓመቱ የተያዙ እቅዶች ሁሉ እንደሚሳኩ ነባራዊ ሁኔታዎች ማሳያ በመሆናቸው ነው፡፡

ሁሉም የአገራችን ህዝብ እንደሚገነዘበው በማህበራዊ ልማት የትምህርት እና የጤና መስኮች ባለፉት ዓመታት የተመዘገቡት ስኬቶች አገራችን በእርግጥም በከፍታ ላይ የምትገኝ አገር መሆኗን የሚያረጋግጡ ናቸው፡፡ የትምህርት ተደራሽነትን ለማረጋገጥ በተደረገው ርብርብ አዳዲስ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትን ጨምሮ በአሁኑ ወቅት አገራችን 50 የሚሆኑ የዩኒቨርሰቲዎች ባለቤት መሆን ችላለች፡፡ በተጨማሪም በጤናው መስክ በመላው የአገራችን አካባቢዎች የጤና ባለሙያዎችን በማሰማራት፣ የጤና ተቋናማትን በማስፋፋትን የቅድመና ድህረ ወሊድ ክትትል በማድረግ በተደረገው ርብርብ የእናቶችና ጨቅላ ህፃንትን ሞት እንዲቀንስ ከማስቻሉ ባሻገር ራሱን ከበሽታ መከላከል የሚችል ህብረተሰብ በመፍጠር ማህበረሰባዊ ለውጥ ማምጣት ተችሏል፡፡ የያዝነው ዓመት ከላይ የጠቀስናቸው መልካም ተግባራት የሚጎለብቱበት የጎደለንን ደግሞ የምንሞላበት ዓመት እንዲሆን ሁሉም የበኩሉን ድርሻ ሊወጣ የገባል፡፡

አገራችን ተስፋ የሚጣልባት እየተለወጠች የመጣች አገር ናት፡፡ ይህ የለውጥ ግስጋሴ ወደ ኋላ እንዳይመለስ መስራት ከሁሉም ኢትዮጵያዊ ዜጋ የሚጠበቅ ነው፡፡ የመልካም አስተዳዳር መስፈን እንቅፋት የሆኑ ጎታች አስተሳሰቦችና ተግባርት የሚደፈቁበት፤ የህዝብ ለህዝብ ትስስራችን ጠብቆ እንደተለመደው የአገራችን ጠላት በሆነው ድህነት ላይ የምንዘምትበት የከፍታ ዓመት እንዲሆን በተለይ አባላት የግንባር ቀደምነት ሚናቻውን መወጣት ይገባቸዋል፡፡  
     
የቱንም ያህል የገዘፉ እንቅፋቶች ቢፈጠሩ ከህዝብ ጋር በሚደረግ የጋር ርብርብ እንደሚፈቱ የመንግስት ፅኑ እምነት ነው፡፡ ይህ እምነት የመላው የድርጅቱ አባላት እምነት እንደሚሆን መገመት አያዳግትም፡፡ በመሆኑም የያዝነው ዓመት መንግስት ያቀደውን መሬት ላይ በማውረድ ሁሉም አገራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት የሚረባረብበት ዓመት እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡ 
አዲሱ ዓመት ተጨማሪ ስኬቶችን በማስመዝገብ  አገራችን ከድህነት ለመውጣት የጀመረችውን እልህ አስጨራሽ ትግል አንድ ምዕራፍ ወደ ፊት ለማራመድ የምንተጋበት ዓመት መሆን መቻል አለበት። ባለፉት ዓመታት አገራችን ዓለምን ያስደመመ ፈጣን ዕድገት ማስመዝገብ ችላለች። ይህ ለውጥ ችግሮቻችንን ለማቃለል የሚያስችል እንጂ ከድህነት ያቆራረጠን አይደለም። ድህነትን ማሸነፍ በሚያስችለን ትክክለኛ መስመር ላይ ሆነን ከረጅም ጊዜ እንቅልፋችን ያነቃንን ለውጥ መሰረት አድርገን በያዝነው ዓመትም ወደ ፊት ለመስፈንጠር ርብርብ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ 

የሰላም ተምሳሌትነቷ በተደጋጋሚ የሚነገርላት አገራችንን ስሟን አስጠብቆ የመቻቻልና የመከባባር መንፈሱ እንዳይበረዝ ሁሉም በየፈርጁ ርብርብ ማድረግ ይጠበቅበታል የሚል እምነት አለኝ፡፡ አገር ሲታመስ መታመስ የሚጀምረው ከቤት ነው፡፡ ቤቱን ከሁከትና ከብጥብጥ መጠበቅ የማይፈልግ የለምና ሁሉም የህዝብ ሰላም የአገር ሰላም፤ የአገር ሰላም የራስ ሰላም መሆኑን በመገንዘብ ሁሌም ቢሆን ለሰላሙ ዘብ ሊቆም የገባዋል፡፡ ከሁሉ የሚቀድመው የጋራ ጥረታችንን የሚፈልገው ድህነትን የማስወገድ አጀንዳ ነው፡፡ በዚህ አጀንዳ ላይ ሁሉም በመዝመት ለበለጠው ነገር መትጋት የሚገባን ይሆናል፡፡

የትናንት ሁለንተናዊ ስኬታችን የዛሬ ለውጥ መሰረታችን ነው፡፡ በመሆኑም አዲሱ ዓመት የመለወጥ ዓመት የሚሆነው ሁሉም በራሱ መንገድ በሚያደርገው ርብርብ ነው፡፡ ሁሉም የበኩሉን ድርሻ መወጣት ሲችል ነው፡፡ አገራችን የእኛ ናት የእኛን አገር ደግሞ ማንም መጥቶ ሊሰራት፣ ሊለውጣት፣ ሰላሟን ሊጠብቅላት፣ ስለልማቷ ሊጨነቅላት አይችልም፡፡ እኛው በራሳችን መንገድ በምናደርገው ትግል የምትሰራ አገራ ናትና ለራሳችን ቤት መለወጥ የምንተጋበት ዓመት እንዲሆን መስራት ያስፈልጋል፡፡

ዓመቱ በእርግጥም የከፍታ እንዲሆን ሁሉም ኢትዮጵያዊ በቁጭት ለስራ የሚነሳበት ዓመት እንዲሆን እንትጋ፡፡
ሰላም

No comments:

Post a Comment