EPRDF is a ruling party committed to realize Ethiopia's Renaissance.

Friday 25 August 2017

እዉን በግሎባላይዜሽን ዉስጥ ማደግ እንችላለን?

 (በስንታየሁ ግርማ)
አሁን ያለንበትን ዘመን ብዙዎች የግሎባይዜሽን ወይም ሉላዊነት ዘመን ሲሉ ይጠሩታል፡፡  ግሎባላይዜሽን (ሉላዊነት) ማለት በአጭሩ በምርት እና በገበያ የተሳሰረች አለም ማለት ነው፡፡ ግሎባላይዜሽን ብሔራዊ ኢኮኖሚን ወደ ተያያዘ እና ተደጋጋፊ (ተመጋጋቢ) አለም አቀፍ ኢኮኖሚ መቀየር ማለት ነው፡፡ ግሎባላይዜሽን ሁለት ዋና ዋና መገለጫዎች አሉት፡፡ እነሱም ግሎባል ምርት እና ግሎባል ገበያ የሚባሉት ናቸው፡፡

ግሎባል ምርት ምን ማለት ነው?
ግሎባል ምርት (global product) ማለት ምርትና አገልግሎትን የተለያዩ ሀገሮች በዋጋና በጥራት ላይ ተመስርተው ከብሔራዊ አዋጭነት አኳያ እየመዘኑ ሲያመርቱት ነው፡፡ ለአንዱ ሀገር የአንድን ምርት የተወሰነ ክፍል ማምረት በዋጋ አዋጭ ሊሆነው ይችላል፡፡ ሌላኛው ሀገር እንዲሁ የተመሳሳይ ምርትን ሌላ ክፍል በማምረት ተወዳዳሪ ሊሆን ይችላል፡፡ አሁን ላይ ኩባንያዎች ይህንን በማድረጋቸው አጠቃላይ ወጪያቸውን በከፍተኛ ሁኔታ እየቀነሱ ይገኛሉ፡፡ የምርት አቅርቦታቸውንና ጥራታቸውንም ለማሻሻል እየረዳቸዉ ነዉ፡፡ ከዚያም በተቀናቃኛቸው ላይ የተሻለ አቅም እንዲኖራቸው ያስችላቸዋል፡፡

ቦይንግ 777ትን ለአብነት ብንወስድ በ545 ያህል የተለያዩ አቅራቢዎች የሚመረቱ 13,500 የተለያዩ ክፍሎች አሉት፡፡ የተለያዩ ክፍሎች በተለያዩ ሀገራት የሚመረቱበት ምክንያት እነዚህ አቅራቢዎች የተለያዩ ክፍሎችን በማምረት አንፃራዊ ብልጫ (relative advantage) ስላላቸውና ይህም የማምረት ሂደቱን አዋጭ ስለሚያደርግላቸው ነው፡፡ ስምንት የጃፓን አቅራቢዎች የቦይንግን የበር ክንፍ ሲያመርቱ ሶስት የጣሊያን አቅራቢዎች ደግሞ የቦይንግን የክንፍ ሊፍት ያመርታሉ፡፡ የምርት ሂደቱ  በሲንጋፖርም በተመሳሳይ መልኩ ይተገበራል፡፡ ስለዚህ ምንም እንኳን ብራንዱ የአሜሪካ ቢሆንም ቅሉ ቦይንግ የአሜሪካ ብቻ ምርት ሳይሆን የአለም ምርት ነው ማለት ነው፡፡
የተለያዩ ምርቶችን በተለያዩ ሀገራት ማምረት ለትላላቅ ምርቶች ብቻ የተወሰነ አይደለም፤ ለአነስተኞቹም ጭምር እንጂ፡፡ ለምሳሌ ሰን ኦፕቲክስ መሠረቱ አሜሪካ የሆነና አመታዊ ሽያጩ ከ20-30 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር የሚደርስ በአለም የታወቀ የአይን መነፅር አምራች ድርጅት ነው፡፡ የሰን ኦፕቲክስ መነፅሮች የተለያዩ ክፍሎች በሆንግ ኮንግ፤ በቻይና፤ በጃፓን፣ በፈረንሳይና በጣሊያን ይመረታሉ፡፡ ይህንን በማድረጉ ሰን ኦፕቲክስ በአለም የመነጽር ገበያ ዉስጥ ብቁ ተወዳዳሪ መሆን ችሏል፡፡ በአጠቃላይ የሰንም ሆነ የቦይንግ 777 ልምድ የሚያሳየን ምርቶች ብሔራዊ ማንነት ቢሰጣቸውም ቅሉ በተጨባጭ (real essence) ግን አለም አቀፍ ምርት እየሆኑ መምጣታቸውን ነው፡፡
ግሎባል ገበያ ምን ማለት ነው?
ግሎባል ገበያ (global market) ማለት በታሪክ የተለያዩ እና የተነጣጠሉ ገበያዎች ወደ አንድ ትልቅ ገበያ የተለወጡበት መንገድ ማለት ነው፡፡ በአለም ላይ የሸማቾች የምርት ፍላጐታቸው እና ምርጫቸው እጅግ እየተቀራረበ በመምጣቱ ግሎባል ምርት እንዲፈጠር ምክንያት ሆኗል፡፡ ይህ ሂደት ተቀራራቢና የተሳሰረ አለም አቀፍ ገበያ እንዲፈጠር ምክንያት ሆኗል፡፡ በግሎባል ገበያ ተቀባይነት ካገኙ ምርቶች መካከል ኮካ ኮላ፣ ማክዶናልድ፣ ጅንስ እና የመሳሰሉት ይገኙበታል፡፡ የምርቶች፣ የኢንዱስትሪ እቃዎችና የፋይናንስ አገልግሎት ዋነኛው ገፅታቸው ከሀገር ሀገር ከፍተኛ ውድድር ማጋጠሙ ነው፡፡ ኮካ ኮላ ከፔፕሲ፣ ፎርድ ከቶዮታ፣ ቦይንግ ከኤየር ባስ፣ ወዘተ.. በምት ሽረት የገበያ ወድድር ዉስጥ ናቸው፡፡ ይህ በግሎባላይዜሽን የግብይት ሂደት ዉስጥ የተፈጠረው ከፍተኛ ውድድር ደግሞ ሸማቾችን ተጠቃሚ አድርጓቸዋል፡፡
በርካታ መረጃዎች እንደሚያሳዩት በአሜሪካ ምርታቸውን ለዉጭ ገበያ ምርት ከሚያቀርቡ ኩባንያዎች መካከለ 97 በመቶ ያህሉ ጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማት ናቸው፡፡ እ.ኤ.አ በ1987 እና በ1997 መካከል በአሜሪካ ከ100 በታች ሰራተኛ ያላቸው ፋብሪካዎች በእጥፍ አድገው ነበር፡፡ ይህ ደግሞ በዘመነ ግሎባላይዜሽን በግዙፍ ካምፓኒዎች ብቻ ሳይሆን በአነስተኛ አምራች ተቋማትም ጭምር መወዳደር እንደሚቻል ያመላከተ ነው፡፡ ከ1990ዎቹ ጀምሮ እስከ አሁን ወደ ቻይናና ሆንግ ኰንግ ኤክስፖርት ከተደረጉት ምርቶች ዉስጥ 40 በመቶ ያህሉን እነዚህ ጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማት ሸፍነውታል፡፡
ይህ የሚያሳየው ብሔራዊ ገበያዎች ለግሎባል ገበያ ቦታቸውን እየሠጡ መሆናቸውን ነው፡፡ ይሁንና በተጠቃሚዎች ምርጫ እንዲሁም በባህል ላይ በተመሠረተ የእሴት ልዩነቶች የተነሳ አሁንም ቢሆን የብሔራዊ ገበያዎች ተፈላጊነት አልጠፋም፡፡ አለም አቀፍ አምራቾችም በማርኬቲንግ ስትራቴጂያቸው እነዚህን የሚያጣጥም አቅጣጫ ይከተላሉ፡፡ ለምሳሌ የመኪና ፋብሪካዎች የአካባቢውን የነዳጅ ዋጋ፣ መልክዓ ምድር፣ የትራፊክ ፍሰት እና የባህል እሴቶችን ከግምት ውስጥ በማስገባት የተለያዩ ሞዴል መኪኖችን አምርተው ለብሔራዊ ገበያዎች ያቀርባሉ፡፡ እዚህ ላይ ቻይና ለአፍሪካ እና ለአሜሪካ የምታቀርባቸው ምርቶች በሸማቹ የመግዛት አቅም ላይ የተንተራሱና እጅግ የተለያዩ መሆናቸውን ልብ ይሏል፡፡
የግሎባላይዜሽን መንስኤዎች
ለግሎበላይዜሽን ማደግ እና መስፋፋት ምሁራን የተለያዩ ትንታኔዎችን ይሰጣሉ፡፡ በአብዛኛው ግን ስምምነት የተደረሰባቸው ምክንያቶች ሁለት ናቸው፡፡ አንደኛው ከ2ኛው የአለም ጦርነት በኋላ በምርቶች እና በአገልግሎቶች ላይ ተጥሎ የነበረው ቀረጥ፣ ኰታ እና መሰል የንግድ መሰናክሎች በከፍተኛ ሁኔታ እየቀነሰ መምጣቱ ነው፡፡ ከዚሁ ጋር በከፊል የሚያያዘው ሌላው ምክንያት ደግሞ የቴክኖሎጂ እድገት በተለይም በኮሚኒኬሽንና በኢንፎርሜሽን ፕሮሰሲንግ እና በትራንስፖርት ዘርፍ ላይ የታየው የቴክኖሎጂ እምርታ ነው፡፡
እ.ኤ.አ በ1920ዎቹ እና በ1930ዎች ብዙ ሀገራት የሀገር ውስጥ ምርትን ከውጭ ኩባንያዎች ውድድር ለመከላከል ሲሉ በአለም ንግድ እና ኢንቨስትመንት ላይ ከፍተኛ ቀረጥ እና በኰታ መልክ የሚገለፁ ከባድ መሠናክሎችን ጥለው ነበር፡፡ በእነዚህ መሰናክሎች የተነሳ የዋጋ ንረት ተከስቶ በአለም ላይ ከፍተኛ የፍላጎት መቀነስን በመፍጠር የ1930ዎቹን የኢኮኖሚ ውድቀት አስከትሏል፡፡
ሀገራት ከዚህ የኢኮኖሚ ድቀት በመማር በአሜሪካ መሪነት የንግድና የኢንቨስትመንት እንቅፋቶችን በሂደት ለመቀነስ ተስማሙ፡፡ እ.ኤ.አ በ1993 በኡራጓይ የአለም የንግድ ድርጅትንም አቋቋሙ፤ 125 ሀገሮችም ድርጅቱን ለመቀላቀል ተስማምተዉ ነበር፡፡ ድርጅቱ የአለም ንግድን በተመለተ ፖሊሲዎችን ያወጣል፤ በሀገራት መካከል ያሉ የንግድ አለመግባባቶችንም ይፈታል፡፡ ከአለም ንግድ ድርጅትም በተጨማሪ በተለያዩ ወቅቶች ሀገራት በመካከላቸው ያሉ ንግድና ኢንቨስትመንትን የሚገድቡ ተግባራትን ለመቀነስ ወይም ለማስወገድ ስምምነት አድርገዋል፡፡ እነዚህ እንቅስቃሴዎች የአለም ምርቶችን ብሎም የአለም ገበያን እድገት አፋጥነውታል፡፡ በውጤቱም ግሎባላይዜሽን ሀገራትን በጥብቅ እያስተሳሰረ ነው፡፡
የግሎባላይዜሽን ተግዳሮቶች
ዛሬ ላይ ግሎባላይዜሽን ምርትንና አገልግሎትን በከፍተኛ ሁኔታ እያሳደገ ቢሆንም በጥርጣሬ የሚያዩት አልጠፉም፡፡ ጥቂቶች ይበልጥ እየበለፀጉ፣ ብዙዎች ይበልጥ እየደኸዩ የሚሄዱበት በመሆኑ ግሎባላይዜሽን ስርዓት ሳይሆን ስርዓት አልበኝነት ነዉ ይሉታል፡፡ በሌላ በኩል ግሎባላይዜሽን ማለት አሜሪካናይዜሽን ማለት ነው የሚሉትም አልጠፉም፡፡ ለዚህ መነሻቸው አዲሱ የአለም ስርዓት አሜሪካ የፈጠረችውና የምትመራው ስርዓት ነው የሚል ነው፡፡ ይሁንና በዚሁ ስርዓት አሜሪካ ብቸኛ ተጠቃሚ ናት ብሎ መደምደም ግን አስቸጋሪ ነው፡፡ ምክንያቱም ከግርጌ ተነስታ በአለም ግዙፉንና በሁለተኛ ደረጃ የሚቀመጥ የጠንካራ ኢኮኖሚ ባለቤት የሆነችው እና በመቶ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጐችን ከድህነት ወለል ላይ ያነሳችዉ የዘመናችን ሀያሏ ሀገር ቻይናም የዚሁ የግሎባለይዜሽን ውጤት ናትና፡፡
ምንም እንኳን ዛሬ የምንኖርባት አለም በምርቶችና በገበያዎች በጥብቅ እየተሳሰረች ቢሆንም ዛሬም ድረስ የሚያጋጥሙ ፈተናዎች እና ተግዳሮች አሉ፡፡ መደበኛ የሆኑና ያልሆኑ የንግድ መሰናክሎች አሁንም በሀገራት መካከል ይታያሉ፡፡ የትራንስፖርት ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ መዋዥቅ፣ የአለም ኢኮኖሚው ቀውስ መሠረታዊ ምክንያቶች አለመፈታት፣ ከፖለቲካ ጋር የተያያዙ ስጋቶች፣ እንደ ትራምፕ ዓይነት ብሄርተኛ መሪዎች ወደ ስልጣን መምጣታቸዉና በተለያዩ የአውሮፓ ሀገራት የቀኝ እና የግራ ዘመም ፓርቲዎች በፓርላማ ወንበር የበላይነት ማግኘታቸው፣ በበለፀጉት ሀገራት እና በድሃ ሃገራት መካከል ያለው የገቢ ልዩነት እንደታሰበው እየጠበበ አለመምጣቱ፣ በምዕራቡ አለም በሚገኙ ድሆች እና በሀብታሞች መካከል ያለው የገቢ ልዩነት እየሠፋ መሄዱ ሁሉ የግሎባላይዜሽን ተግዳሮቶች ናቸው፡፡
ያም ሆነ ይህ ግሎባልይዜሽን የአለማችን እውነታ ሆኗል፡፡ ታላቁ መሪ መለስ ዜናዊ እንዳሉት የምርጫ ጉዳይ ሳይሆን የህልውና ጉዳይ ነው፡፡ እርሳቸው እንደሚሉት ከግሎባላይዜሽን ስርአት ውጭ መሆን ከእግር ኳስ ሜዳ ቀርቶ በፎርፌ መሸነፍ እንደ ማለት ነው፡፡ ከግሎባለይዜሽን ውጭ መሆን ተመጽዋች መሆን ነው፡፡ 
ግሎባላይዜሽንና ሀገራችን
ታላቁ መሪ መለስ ዜናዊ እንዳሉት እዉን ታዳጊና ኋላቀር ሀገራት በግሎባላይዜሽን ዉስጥ ሆነው ማደግ ይችላሉ ወይ? የሚለው ጥያቄ እንዲያው ለፅንሰ ሃሳብ ውይይት ካልሆነ በቀር በተግባር የተመለሰ ነው ብለዋል፡፡ በርግጥ እንደ ቻይና ያሉ ያንቀላፉ ዝሆኖችን አንቅቶ ያሳደገ ስርዓት ኢትዮጵያን የማያሳድግበት ምንም ምክንያት አይኖርም፡፡ ስለዚህ በግሎባይዜሽን ውስጥ ያለን አማራጭ አንፃራዊ ብልጫችንን በመለየት በውድድሩ መሳተፍ ብቻ ነው፡፡ የ”ኤስያ ነብሮች” ከሚባሉት የምንማረውም ይሄንኑ ነው፡፡
በአለም አስደማሚ የሆነ እድገት ያስመዘገቡ የኤስያ ሀገራት ለእድገታቸው ከፍተኛ አስተዋጽኦ ካደረገላቸው መካከል ኤክስፖርት መር ፖሊሲ መከተላቸው ነው፡፡ እንደ ኮሪያ የመሳሰሉት ሀገራት ለባለሀብቱ በየአመቱ የኤስክፖርት ኰታ ይሰጡት ነበር፡፡ ኮታውን ካሳካ የተለያዩ ማበረታቻዎችን ይሰጡታል፡፡ አንዳንዶቹ ሀገራት ለሀገር ዉስጥ ምርቶች የተፈቀዱትን ጭምር ለኤክስፖርት አድራጊዎች ሰጡ፡፡ ይህን ካደረጉ በኋላ ኰታውን ባላሳኩት ላይ የማያወላዳ ከፍተኛ የሆነ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ቅጣቶች ተገበሩ፡፡ ኮሪያ ስኬታማ ሆነች፤ እነ ታይዋንና ሌሎችም እሷን ተከትለው አደጉ፡፡ ኢትዮጵያም ይህንን ፈለግ መከተል ትችላለች፡፡ ነገር ግን አሰሱን ገሰሱንም ወደውጭ መላክ ሳይሆን በጥናት ላይ ተመስርቶ አንፃራዊ ብልጫችንን በመለየትእና በመወዳደር ብቻ ነው ሊሆን የሚችለው፡፡
ለምሳሌ በአለም ላይ 90% የሚሆነውን ጤፍ እናመርታለን፡፡ ጤፍ በንጥረ ነገር የበለፀገ እንደሆነና የተለያዩ የጤና ጥቅሞች እንዳሉት በምዕራባውያን ተመራማሪዎች ጭምር ሳይቀር ተረጋግጧል፡፡ በአንፃሩ በምዕራቡ ዓለም የሚገኙ ዜጎች በሚመገቡት ምግብ ምክንያት ከልክ ላለፈ ወፍረት በመጋለጣቸው ለሀገራቱ የጤና፣ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ችግር እየሆነ ነው፡፡ ሸማቹ ስኳር በበዛባቸው ምግቦች ምክንያት የእራሱና የልጆቹ ጤንነት አደጋ ላይ እየወደቀ ስለሆነ መንግስት በማስታወቂያ ላይ አዲስ ሕግ እንዲያወጣ እየወተወተ ነው፡፡ ከፍተኛ ቀረጥም በእነዚህ ምርቶች ላይ እንዲጣል የመብት ተሟጋቾች እየታገሉ ናቸው፡፡ እነ ቪክቶሪያ ቤከምን የመሳሰሉት የመዝናኛዉ አለም ፈርጦች ደግሞ በብረት ማዕድን የበለፀገው ጤፍ ካለው የጤና ጠቀሜታ አንፃር ምርጫቸው እየሆነ ነው፡፡
በመሆኑም በዚህ ለማንም በማይቀር አለም አቀፍ የገበያ ስርአት ዉስጥ ለመቆየትና ይበልጥ ዉጤታማ ለመሆን በጥናት ላይ የተመሰረቱ ስራዎችን መተግበር ረጅሙን የሉላዊነት መንገድ ያለምንም መንገራገጭ ለመጓዝ ያስችለናል እላለሁ፡፡
ሰላም!

1 comment:

  1. ...የኤዢያ ነብሮች ከእድገታቸው በስተጀርባ ከሚያወጡት ፓሊሲዎችና ካሳኩት ሜጋ ፕሮጀክቶቻቸው ጀርባ በጣም ኤፊሸንት በክህሎት ብቁ የሆነ የሱፐርቪዠን ሲስተም ነበራቸው ፡፡ ሀገራቸን የነሱን ፈጣን እድገት አንዳትደግም ትልቁ እንቅፋት የሱፐርቪዠን አቅሟ እጅግ ደካማ መሆኑ ነው፡፡ እንደውም በባለስልጣን ወይምበሚንስቴር መስራቤት ደረጃ መቋቋም የሚገባው ጉዳይ ነው .....

    ReplyDelete