EPRDF is a ruling party committed to realize Ethiopia's Renaissance.

Saturday, 4 March 2017

አሰራሮቻችንን በማዘመን የወጣቱን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እንረባረብ

(በኤፊ ሰውነት)
በተደጋጋሚ እንደሚገለፀውና ነባራዊ ሁኔታውም እንደሚያስገነዝበው ለአገራችን እድገት መነሻ ሃብቶቻችን የሰው ጉልበትና መሬት ናቸው፡፡ ኢሕአዴግ አገር የመምራት ሃላፊነት በተረከበበት ማግስት የወሰደው እርምጃም ይህን የውስጥ አቅማችንን መጠቀም የሚያስችሉ የህግ ማዕቀፎችንና ፖሊሲና ስትራቴጂዎችን መቅረፅ ነበር፡፡ ከዚህ አኳያ በገጠር አካባቢዎች ድህነት ተኮር የሆነ የገጠር ልማት ፖሊሲን በመተግበር የአርሶ አደሩን ጉልበትና መሬት ማዕከል ያደረገ የልማት ስትራቴጂ ተነድፎ ተግባራዊ ተደርጓል፡፡ በዚህም ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት የአርሶ አደሩ ህይወት በቀጣይነት ከመለወጡ ባሻገር ዓለም አቀፍ አድናቆት የተቸረው ኢኮኖሚያዊ እድገት ማስመዝገብ ተችሏል፡፡

በተመሳሳይ በከተሞች ያለውን ሰፊ ጉልበትና ውሱን ካፒታል ያቀናጀና የከተማውን ህዝብ ኑሮ የሚያሻሽል የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ልማት ስትራቴጂ ተነድፎ ተግባራዊ ከተደረገ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ አነስተኛና ጥቃቅን ተቋማት በውሱን ካፒታል ሰፊ የስራ እድል መፍጠር የሚችሉ ከመሆናቸው ባሻገር በሁሉም ከተሞች ከዚያም አልፎ በገጠር ሊደራጁ የሚችሉ መሆናቸው በተግባር ታይቷል፡፡ ስትራቴጂው በተሟላ መልኩ በተተገበረባቸው ሁኔታዎች በከተሞችም በገጠርም ሰፊ ቁጥር ያለው የስራ እድል በመፍጠር አመርቂ ውጤት ለማምጣት እንደሚያስችል በተግባር ተረጋግጧል፡፡
ይሁንና በአገራችን ወጣቶች አሁንም በተደጋጋሚ ከሚነሱና በቂ ምላሽ ካልተሰጣቸው ጥያቄዎች ዋነኞቹ ከተሳትፎና ከፍትሃዊ ተጠቃሚነት ጋር የተያያዙት ናቸው፡፡ ከጫፍ እስከ ጫፍ በሚባል ሁኔታ የወጣቱ መሰረታዊ ጥያቄ የስራ እድል ፈጠራ ጉዳይ እንደሆነ በግልፅ ይታያል፡፡ የጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማት ከላይ በተቀመጠው ደረጃ ዜጎችን ተጠቃሚ የማድረግ አቅም ያለው በተለይ ሰፊ የስራ እድል ለመፍጠር ትልቅ አቅም ያለው ሆኖ ሳለ አሁንም በበርካታ መሰናክሎች ተከቦ የወጣቱን የስራ እድል ጥያቄ የመመለስ ዓቅሙ ፈተና ውስጥ ሲገባ እንታዘባለን፡፡ ሚሊዮኖችን በማቀፍ ህይወታቸውን ከመቀየር ባሻገር ለህዳሴ ጉዟችን የማይተካ ሚና መጫወት የሚችል የዕድገት ሞተር መሆን ሲገባው አሁንም በተደራራቢ ተግዳሮቶች ተተብትቦ የወጣቱን ተስፋ እስከ መፈታተን ደርሷል፡፡
ኢህአዴግ የሚመራው ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ መንግስት የዘርፉን ልማት የሚያሳልጡና በተግባር ካጋጠሙ ተግዳሮቶች በመነሳት ዘርፉን ለመደገፍ 1994 1999 እና በኋላም 2003 ስትራቴጂ አውጥቷል፡፡ በጥቃቅንና አነስተኛ ስትራቴጂ ትግበራ ዋነኛ ችግር የሆነውን የካፒታል እጥረት ለመፍታት የአበዳሪ ተቋማትን አቅም በማጎልበት፣ ተከታታይነት ያለው ድጋፍ መስጠት እንደሚገባ በስትራቴቻ ተመልክቷል፡፡ የካፒታል እጥረታቸውን መቅረፍ ብቻ ወደ ዘርፉ የሚገባን ወጣት ቁጥር እንደማይጨምር በግልፅ ያስቀመጠው ስትራቴጂው የመስሪያ ቦታዎችን ሰርቶ በማቅረብ ጭምር በዘርፉ የሚገጥመውን ተግዳሮት መፍታት እንደሚገባም ያስቀምጣል፡፡ ከስትራቴጂ በተጨማሪ መሪው ፓርቲና መንግስት ወጣቶች በልማቱ ላይ ንቁ ተሳታፊና ከውጤቱም ፍትሃዊ ተቋዳሽ እንዲሆኑ በየጊዜው አቅጣጫ ያስቀምጣሉ፤ ለተፈፃሚነቱም ይተጋሉ፡፡
አነስተኛና ጥቃቅን ተቋማትን ለማደራጀት የሚያስፈልገው ካፒታል ያን ያህል ከባድ አይደለም፡፡ ዋናው ጉዳይ በተግባር ላይ ለመሰማራት ቆርጦ መነሳትና የተወሰነ ስራ ለመስራት የሚያስችል ክህሎት መጨበጥ ነው፡፡ህን አደራጅቶ በተሟላ መልኩ መተግበር ደግሞ በዋናነት ዘርፉን የሚመራ አካል ድርሻ ነው፡፡ አሁን ያለውፈፃፀም የሚያሳየው ግን አመራሩ ይህን እየፈፀመ ያለመሆኑን ነው፡፡ አሁንም የስራ እድል ፈጠራ ጉዳይ አንገብጋቢና የበርካታ ወጣቶች ጥያቄ እንደሆነ ቀጥሏል፡፡ ወጣቶች ከመደራጀት ጀምሮ በተለያዩ እርከኖች የሚያልፉባቸው መንገዶች ሁሉ ውስብስብ እየሆኑና አሰራሩም ለኪራይ ሰብሳቢነትየተጋለጠ ዘርፉ የወጣቶችን ጥያቄ ስር ነቀል በሆነ መልኩ መፍታት እንዳይችል አድርጎታል፡፡ ይህ ችግር እስካሁን በጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማት የተገኙ ወርቃማ ውጤቶች ሳይቀሩ በአግባቡ እንዳይታዩ አድርጓል፡፡ አሁን ያለው አዝጋሚ ጉዞ በአግባቡ ካልተቀየረ ወደባሰ ውስብስብ ችግር ውስጥ መገባቱ አይቀሬ ነው የሚል የግል እይታ አለኝ፡፡
የስራ እድል ፈጠራን ስንመለከት በታችኛው የመንግስት አስፈፃሚ አካላት አካባቢ ያሉ የአፈፃፀም ጉድለቶች ትኩረት የሚሹ ናቸው፡፡ በወረዳና ክፍለ ከተማ ደረጃ በእጅ ላይ ያሉ ሃብቶችን በተገቢው መንገድና ለሚገባው አካል በማዋል ረገድ ክፍተቶች እንደሚስተዋሉ ወጣቶች ያነሳሉ፡፡ ከማደራጀትና ከስልጠና ጀምሮ የብድር ብሎም የመስሪያና የመሸጫ ቦታ አቅርቦቱን በተደራጀ አኳኋን ለይቶ ከማቅረብ አኳያም እጥረቶች አሉ፡፡ ለመደራጀትና ፍቃድ ለማውጣት የሚወስደው ጊዜና ምልልስ፤ ይህ ሲመለስ ደግሞ ቦታና ብድር ለማግኘት የሚወስደውን ጊዜ በማሰብ ከወዲሁ ዳገትነቱ ታይቷቸው በሌሎች መስኮች ተሯሩጦ መስራት ይሻላል በሚል መንፈስ እንደሚሸሹ ወጣቶች ይናገራሉ፡፡ ከያዝነው ዓመት ነባራዊ ሁኔታ እንኳን ተነስተን ብናይ የስራ አጦች ምዝገባ በሚካሄድበት ወቅት በርካታ ወጣቶች በተደጋጋሚ ምዝገባ መካሄዱን ስለሚያውቁ አፈፃፀሙ ላይ ጥርጣሬያቸውን አንስተዋል፡፡ ከዚህ በፊት በተመዘገበው ልክ ሁሉም ላይ ርብርብ ባለመደረጉና ጥቂቶች ብቻ በሂደቱ ተጠቃሚ ሆነው በማለፋቸው የመጣ ትክክለኛ ጥርጣሬ ነው፡፡
በመሆኑም ዘርፉ ላይ ያለው ችግር የወጣቱን ፍላጎት ታሳቢ ባደረገ መልኩ መታረም ብቻ ሳይሆን በመሰረታዊነት መለወጥ እንደሚያስፈልገው መረዳት አይከብድም፡፡ በእርግጥ አዲሱ የኢትዮጵያ ወጣቶች የልማትና የዕድገት ፓኬጅ እና የወጣቶች የልማትና የዕድገት ስትራቴጂ ሰነዶች እነዚህ አሰራሮችን ለማረም በማሰብ ጭምር የተዘጋጁ ናቸው፡፡ ኢህአዴግም በጥልቅ ተሃድሶው ወቅት እነዚህን ችግሮች ነቅሶ ስላያቸው ቀጣዩ ጉዞ ብሩህ እንደሚሆን አመላካች እንቅስቃሴዎች እንዳሉ መረዳት ይቻላል፡፡ 10 ቢሊዮን ብር የተዘዋዋሪ ፈንድ መቋቋሙ አንዱ ወርቃማ እርምጃ ነው፡፡ ይህ ተዘዋዋሪ ፈንድ በብድር መልክ ከወለድ ነፃ ለተጠቃሚ ወጣቶች የሚተላለፍ ሆኖ ወጣቶቹ አትራፊ ከሆኑ በኋላ ተመላሽ በማድረግ ወደሌሎች ዕድሉ ያላገኙ ወጣቶች እየተዘዋወረ በርካታ ወጣቶችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ይጠበቃል፡፡ በያዝነው ዓመትም 5 ቢሊዮን ብሩ ጥቅም ላይ ይውላል፡፡ በመሆኑም ይህን ጉዳይ የሚያስፈፅሙ የዘርፉ ባለሙያዎች ፍፁም ቁርጠኛ በሆነ መንፈስ ተግባራዊ ሊያደርጉት ይገባል ባይ ነኝ፡፡
ስራ አጦችን ከመለየት ባለፈ በየስልጠና ማዕከሎች የማስገባትና እንደ አገር ደግሞ በምን ዘርፎች ላይ ቢሰማሩ ውጤታማ ይሆናሉ በሚል የመለየት ስራም ከበፊቱ በተሻለ ጥራትና ቁርጠኝነት በመሰራት ላይ ነው፡፡ ይህ በራሱ የሚበረታታ ርምጃ ነው የሚል እምነት አለኝ፡፡ ከወጣቱ ፍላጎትና ጉጉት አኳያ ብናየው ደግሞ ሂደቱ መፍጠን እንዳለበት ይሰማኛል፡፡

በጥቃቅንና አነስተኛ ተደራጅቶ የወጣቱን ህይወት ለመቀየር የሚያስችል ስትራቴጂና መዋቅር አለ፡፡ ይህን ተግባራዊ የሚያደርጉ በየደረጃው ያሉ አካላት ፍፁም አገልጋይ በሆነ ስሜት ውስጥ ሆነው የዘርፉን አገራዊ ጥቅም ጭምር በማጤን ለውጤታማነቱ ከተረባረቡ ዘርፉን አሁን ካለበት ዘገምተኛ አካሄድ ወጥቶ የወጣቱን ፍላጎት ማርካት ወደሚችልበት ሁኔታ ማሸጋገር ይቻላል፡፡ ለመደራጀት፣ ለስልጠና፣ ብድር ለመውሰድም ሆነ የመስሪያና መሸጫ ቦታ ለማግኘት የሚባክነውን ጊዜ በማስቀረት፣ በእጃችን ያለውን ሃብት በአግባቡ በመጠቀምና ዘርፉና የዘርፉ አንቀሳቃሾች ሊያበረክቱ የሚችሉትን አገራዊ ኢኮኖሚያዊ አቅም ተገንዝበን በጊዜ የለንም መንፈስ ከሰራን የወጣቶችንም ፍላጎት ማርካት፣ በአንቀሳቃሹ በኩል ያሉ ተግዳሮቶችን መፍታት እንችላለን፡፡

No comments:

Post a Comment