(በኤፊ ሰውነት)
ካሳለፍነው ሳምንት ጀምሮ በአገራችን በተለያዩ አካባቢዎች ውይይቶች በመካሄድ ላይ ናቸው፡፡ እንደአገር
በተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የተነሱ የተሳትፎና የተጠቃሚነት እንዲሁም መሰል የመብት ጥያቄዎችን በተገቢውና አፋጣኝ በሆነ
መንገድ ከመመለስ አኳያ ባለፉት ዓመታት ችግሮች መስተዋላቸውን
ለይቶ ኢህአዴግ የሚመራው ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ መንግስት ይህንን መፍታት በሚቻልበትና በቀጣይ የህዳሴ ጉዞአችንን ለማሰላጥ የሚያግዘን
የጥልቅ ተሃድሶ እንቅስቀሴ ውስጥ ይገኛል፡፡ በዚህም ኢህአዴግና ህዝቡ በጋራ ችግሮችን የመለየትና በቀጣይም መፍትሄ በማስቀመጥ
ወደፊት መራመድ የሚችሉበትን ምክክር በማድረግ ላይ ናቸው፡፡ ባለፉት ዓመታት በነበሩ ስኬቶችና ተግዳሮቶች ውስጥ መላው
የአገራችን ህዝብ ጨምሮ የመንግስት አስፈፃሚ አካላት ሚና ከፍተኛ መሆኑ ይታወቃል፡፡
ውድ አንባብያን ካሳለፍነው ሳምንት ጀምሮ የመንግስት ሰራተኛው፣ መላው ህዝብና፣ ወጣቶች ከመንግስት ጋር
የሚያደርጉት የጋር ውይይት ተጀምሯል፡፡ እነዚህ አካላት ባለፉት ዓመታት እንደአገር በነበሩ ሁለንተናዊ እንቅስቃሴዎች ላይ
ኃላፊነት የነበራቸውና የድርሻቸውን የተወጡ በመሆናቸው ያለፉ ስኬቶቻቸውንና የቀጣይ አቅጣጫዎችን በጋራ መምከራቸው ተገቢና
ወቅታዊ መሆኑ አያጠያይቅም፡፡
የዚህ ጽሑፍ ዓላማም በተለይ የመንግስት ሰራተኛው ወይም ፐብሊክ ሰርቫንቱ ባለፉት ዓመታት እንደአገር
በተመዘገቡ ስኬቶችና በገጠሙ ተግዳሮቶች ላይ የነበረውን ሚና ቀንጭቦ ማሳየት ይሆናል፡፡ ሁላችንም እንደምናውቀው ለአንደ አገር
ከሁሉም ነገር በላይ የሚቀድመው አገሪቱ የምትመራበትን ህግና የህግ ማዕቀፍ ማዘጋጀት ነው፡፡ ከዚህ አኳያ ባለፉት 25 ዓመታት
ከህገመንግስቱ ጀምሮ የተለያዩ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች፣ መመሪያዎች፣ አዋጆችና ደንቦች ተቀርጸዋል፡፡ በተለያዩ ጊዜያት እየተሻሻሉና
እየዳበሩ የሚሄዱ ደንብና መመሪያዎች እንደተጠበቀ ሆኖ አገሪቷ ልትመራበት የምትችለውን መስመር ከመንደፍ አኳያ ኢህአዴግ ህዝብ
የማስተዳደር ስልጣን ከተረከበ ጊዜ ጀምሮ ይበል የሚያሰኝ ስራ ተሰርቷል፡፡ ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ ከሰነድ ባለፈ ይህንን ስልት
ሊያስፈፅም የሚችል መዋቅር በመዘርጋትና ያንን መፈፀም የሚችሉ ባለሙያዎችን ከመመደብ አኳያም አበረታች ተግባር ተፈጽሟል፡፡ ከዚህ
አኳያ ባለፉት ዓመታት የአገራችንን መጻኢ እድል የሚወስኑ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎችን መሬት ከማውረድና ለህዝብ ከማድረስ አኳያ
ሲቪል ሰርቪሱ የነበረው ሚና የአንበሳውን ድርሻ ይወስዳል፡፡
በፖለቲካ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ መስክ የተቀመጡ ራዕዮችን ለማሳከት መዋቅር ከመዘርጋት ባለፈ ያንን
የሚያስፈፅም አካል መኖሩ ግድ ነው፡፡ አንገት ያለ ራስ፤ ራስም ያለ አንገት የማይታሰብ ነውና፡፡ በመሆኑም የህዝብ ኃላፊነት
ከተሸከመው ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጀምሮ እሰከታችኛው መዋቅር ድረስ ያለው ፐብሊክ ሰርቪስ የመንግስትን አገልግሎት ለህዝብ ከማድረስ
አኳያ ብቸኛውና አይነተኛ መሳሪያ መሆኑን መገመት አያዳግትም ፡፡
በተደጋጋሚ ለማመላከት እንደተሞከረው በአገራችን ባለፉት 25 ዓመታት በተከናወኑ አበረታች ተግባራት
አገራችን ተከታታይና ፈጣን የሆነ ልማት ማስመዝገብ ከመቻሏ ባሻገር ተስፋ የሚጣልባት ባለራዕይ አገር ለመሆን በቅታለች፡፡
ዴሞክራሲ እንዲያብብ፣ የዜጎች እኩል ተሳትፎና ተጠቃሚነት እንዲጎለብት፣ ዜጎች በአገራቸው ሰርተውና ሃብት አፍርተው የሚለወጡባት
አገር እንድትሆን ከማድረግ አኳያ እንዲሁም በተለይ መንግስት በአገራችን የመሰረት ልማት ለማስፋፋት፣ የማህበራዊ ልማትን
ለማፋጠን በሚነድፈው ስትራቴጂና እሱን ለማስፈፀም በሚያደርገው እንቅስቃሴ ውስጥ የመንግስትን ፕሮግራም በማስፈፀም በኩል የመንግስት ሰራተኛው ሚና ከፍተኛ ነበር፡፡ መላው የአገራችን ህዝብ ደግሞ
ከመንግስት አስፈፃሚዎች ጋር እጅና ጓንት ሆኖ በመደገፍና በጋራ ለመንቀሳቀስ በተጨባጭ ያሳየው ቁርጠኝነት በቀላሉ የሚገመት አይደለም፡፡
የመንግስትን አገልግሎት ለህዝቡ ተደራሽ ለማድረግ በሚከናወን ተግባር ሁሉ የመንግስት ሰራተኛው ደከመኝ
ሰለቸኝ ሳይል ህዝቡን ሲያገለግል መቆየቱ አይዘነጋም፡፡ በከተማም ሆነ በገጠር ቤት ለቤት ከማስተማር ጀምሮ በተለያዩ መድረኮች
በመወያየትና ግንዛቤ በማስጨበጥ ህዝቡ በሚከናወኑ የልማት ስራዎችና መሰል ተግባራት ቀጥተኛ ተሳታፊ እንዲሆን ከማስቻል አኳያ
የመንግስት ሰራተኛው በቁርጠኝነት ሰርቷል፡፡ በገጠር አኗኗሩም ከከተማ ነባራዊ ሁኔታ ጋር ፈፅሞ የተለየ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ
አሁን አገራችን ለደረሰችበት የለውጥ ደረጃ መሰረት የሚሆን ተግባር በመንግስት ሰራተኛው ተፈፅሟል፡፡ ስለግብርና ምርትና
ምርታማነት፣ ስለተፈጥሮ ሃብትና መስኖ ልማት ስራችንና የተመዘገበውን ስኬት ስናወራ በገጠር አርሶ አደሩን በቀጥታ ስለሚደግፈውና
ቀን ከሌሊት ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይል ተራራ ገደሉ ሳይበግረው ከአርሶ አደሩ ጋር አብሮ የሚታትረውን የግብርና ባለሙያ አብረን
እናነሳለን፡፡ ስለጤና ስናወራም እንዲሁ፡፡ የጤና ፖሊሲያችን መከላከልን መሰረት ያደረገ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኑ ከዚህ ባሻገር
ያሉ አገልግሎቶችም ቀላል የሚባሉ አይደሉም፡፡ የጤና ኤክስንቴንሽን ባለሙያን ለአብነት አንስተን ብንነጋገር እናቶችን በቀጥታ
ከመደገፍና በተለይ ሁሉም በገጠሪቱ የአገራችን ክፍል የሚኖር ዜጋ ከዘልማዳዊና ኋላ ቀር የአኗኗር ዘይቤ እንዲወጣ፣ በመንግስት
የቀረቡ የጤና አገልግሎቶችን እንዲጠቀም በመስተማርና መተግበራቸውንም በቀጥታ በመከታታል ጭምር ዘርፈ ብዙ ተግባራትን
ይከውናሉ፡፡ እናቶች ልጆቻቸውን ከጤና ተቋም ውጭ እንዳይወልዱ በጤና ተቋማ ያለመውለድ ጉዳትን በማስተማር፣ ያለእድሜ ጋብቻን
አምርሮ በመታገልና የስነ ተዋልዶ ጤናንም በማስተማር የመንግስት ሰራተኛው የሚፈፅመው በገንዘብ የማይተመን ተግባር ለአገልግሎት
ከሚከፈል ደመወዝ የዘለለ የዜግነት ኃላፊነትን መወጣት ጭምር እንደሆነ መገንዘብ እንችላለን፡፡ በመጀመሪያው የእድገትና
ትራንስፎርሜሽን እቅድ ትግበራ የጤናና የትምህርት ልማት ስኬትን ስናወሳ የመንግስት ሰራተኛው ይሄን ለማሳካት የተጓዘበትን ውጣ
ውርድ አብረን እናወሳለን፡፡ እንደአገር አንድም ህፃን ከትምህርት ገበታው እንዳይቀር በሚደረገው ሁሉን አቀፍ እንቅስቀሴ
የመንግስትን ረጅም ዓላማን የሚያሳኩትና በተጨባጭም ባለፉት ዓመታት የተገኙትን ስኬቶች ስናነሳም የስኬቱ ባለቤቶች እነዚሁ
በመስኩ የተሰማሩ ፐብሊክ ሰረቫንቶች እንደሆኑ መገንዘብ ያስፈልጋል፡
በከተማም ያለው ሁኔታ ተመሳሳይ ነው፡፡ ስለጥቃቅንና አነስተኛ፣ ስለጤና አገልግሎት፣ ስለ መሰረተ
ልማትና በመንግስት የሚቀርቡ የተለያዩ አገልግሎቶችን ስናነስ የመንግስት ሰራተኛው አብሮ ይነሳል፡፡ እንደአገር በሚከናወኑ
ማናቸውም እንቅስቀሴዎች ውስጥ የመንግስት ሰራተኛው ሚና ተነጥሎ የሚታይ አይደለም፡፡ ይህ የሚያመላክተው የመንግስት ሰራተኛው
ጥንካሬና ቁርጠኝነት እንደ አገር ለሚከናወኑ ማናቸውም ተግባራት መጻኢ እድል ወሳኝ መሆኑን ነው፡፡ በአጠቃላይ የመንግስት
ሰራተኛው በአገራችን ለተመዘገበው ተከታታይ እድገት ያበረከተው አስተዋፅኦ የላቀ መሆኑን ማየት ይቻላል፡፡ ይህ እውነታ
እንደተጠበቀ ሆኖ ባሳለፍነው ዓመት እንደ አገር በገጠሙ ፈተናዎች ፐብሊክ ሰርቪሱ የመልካም አስተዳደር መርሆዎች ላይ ቆሞ
ከመስራት አኳያ የገጠመው መሸራረፍ በህዝብ ዘንድ ከፍተኛ ቁጠን መቀስቀሱ ይታወሳል፡፡
ህዝባችን ከሚያነሳቸው አብይ ጥያቄዎችና ኢህአዴግ በጥልቅ ተሃድሶ ከለየው አንገብጋቢ ጉዳይ አንዱ የአድሎአዊ
አሰራር መኖርና ኃላፊነትን ለራስ ጥቅም የማዋል ጉዳይ ነው፡፡ ከዚህ ባሻገር በፐብሊክ ሰርቪሱ የአገልጋይነት ስሜት መጥፋትና
ኪራይ ሰብሳቢነት መንገስም ይጠቀሳል፡፡ ይህ ደግሞ ዞሮ ዞሮ
መጠኑ ይለያይ እንጂ የመንግስት ሰራተኛው መውሰድ ያለበት ኃላፊነት ጭምር ነው፡፡ በታማኝነት በቅንነትና በህዝብ አገልጋይነት
ስሜት የመንግስት አገልግሎትን ለህዝብ የሚያቀርቡ የመንግስት ሰራተኞች የመኖራቸውን ያህል በቅድመ ሁኔታ፣ ማባበያ በመጠየቅና ለህዝብ
የተሰጠን ጊዜ በመሸራረፍ ፈፅሞ ህዝባዊነትን ባልተላበስ ስሜት ውስጥ ሆኖ ስራውን ባልተገባ ሁኔታ የሚጠቀም ሰራተኛም ቁጥር
ቀላል የሚባል አይደለም፡፡ በእጅ መንሻ ካልሆነ አንድ ገፅ ፋይል ገልፆ የማያይ ሙስና መቀበልን እንደግዴታ ቆጥሮ በድፍረት
በመንግስት አገልግሎት ኪራይ የሚሰበስብ ፈፃሚ ለጉድ መሆኑ የአደባባይ ምስጢር ነው፡፡ በአጠቃላይ ፐብሊክ ሰርቪሱ በባለፉት
ዓመታት እንደ አገር በተመዘገቡ በርካታ ስኬቶች ውስጥ የጎላ ድርሻ ያለውን ያህል የተመሰቃቀሉ ሁኔታዎች እንዲፈጠሩና የህዝብ
ቁጣም እንዲገነፍል ያበረከቱት አሉታዊ አስተዋጽኦ ቀላል አይደለም፡፡ በመሆኑም ስለ አለፈው ችግራችን ስናነሳ ፐብሊክ ሰርቪሱ
የነበረውን ስኬትና ተግዳሮት በልኩ መውሰዱ የግድ ይላል፡፡ ስለቀጣይ ረጅሙ የህዳሴ ጉዟችንም ስናነስ እንዲሁ ፐብሊክ ሰርቪሱ
ራሱን ለዛ ማዘጋጀትና ራሱን ከአገራዊ ተልዕኮና ዓላማ አንፃር መመዘን እንደሚገባው ማስቀመጥ ግድ ይሆናል፡፡
ውድ አንባብያን ሁላችንም እንደምናስታውሰው የኢሕአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ባደረገው መደበኛ ስብሰባው የመንግስት ሰራተኞች፣ የህዝብና የወጣት ባለድርሻ አካላት ውይይቶች እንዲከናወኑ አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡
እንደ አገር የተጀመረውን ጥልቅ ተሃድሶ መሬት ማስነካትና በውጤት ማጀብ የሚቻለውም ሁሉም የራሱን መልካም ጎኖች በማጎልበትና
መሻሻል የሚገባቸውን ችግሮች ደግሞ ያለርህራሄ መመልከትና የመፍትሄ አካል መሆን ሲችል በመሆኑ ይህን ማስጨበጥ የሚችል ውይይት
ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር ካሳለፍነው ሳምንት ጀምሮ ተጀምሯል፡፡ የመንግስት ሰራተኛው የጥልቅ ተሃድሶ ሂደት አንዱ
ሲሆን ውይይቱ መልካም በሚባል ደረጃ የተለያዩ ገንቢ ሃሳቦች እየተንሸራሸሩበት የተጀመረ ሲሆን ሂደቱ በተለያዩ ተቋማትም
ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል፡፡
በእኔ እይታ ውይይቱ ተገቢና ወቅቱን የጠበቀ መሆኑ አያጠያይቅም፡፡ ኢህአዴግና ኢህአዴግ የሚመራው
ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ መንግስታችን እንደአገር ባለፉት ዓመታት የታዩ ችግሮችን በመለየት የተሃድስ እንቅስቃሴ ውስጥ ገብቷል፡፡
ይህ አገራችንን ከሩቅ ለማድረስ ካለው ፍላጎትና ቁርጠኝነት መሆኑን መገመት አያዳግትም፡፡ የመንግስት ሰራተኛውም በዚህ
የህዝባዊነት መንፈስ ነገሮችን መመልከት የሚገባው ይሆናል፡፡ የመንግስት ሰራተኛው ከራስ ጥቅም በላይ የህዝብ አጀንዳ ይበልጣል
የሚል እምነት መያዝ አለበት፡፡ መንግስት በተለያየ አጋጣሚ ሲገልፅ እንደተሰማው የመንግስት ሰራተኛው ያልተሳተፈበት ልማት
ሰላምና ዴሞክራሲ በውሃ ጠብታ ግዙፍ ድንጋይን እንደመስበር በመሆኑ የመንግስት ሰራተኛው እያንዳንዱ መልካም ተግባሩ አገርን
የሚያለማ፤ አንድ ቅንጣት የጥፋት አካሄዱ ደግሞ በህዝብ ሁለንተናዊ ለውጥ ላይ እንደመቆም መሆኑን ከልብ መቀበል ይኖርበታል፡፡ የፐብሊክ
ሰረቫንቱ ህዝባዊ ወገንተኝነት መላበስ ዞሮ ዞሮ ለራስ ጥቅም እንደመስራት አድርጎ መውሰድ ይገባል፡፡ ፐብሊክ ሰረቫንቱ ከህዝብ
በተሰበሰበ ገቢ የሚከፈለው ከመሆኑ ባሻገር የራሱን ወገን የሚያገለግል መሆኑ ደግሞ በራሱ የሞራል ግዴታም ጭምር ያለበት መሆኑን
ተገንዝቦ በዛ መንፈስ መስራት ይገባዋል፡፡ ፐብሊክ ሰርቪሱ እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል አይነት አስተሳሰብ ውስጥ ከገባ
አገራችንን ወደ ቁልቁለት የሚወስድ በመሆኑ ፐብሊክ ሰርቪሱ ችግሮችን ወደራሱ አስጠግቶ በማየትና አሉ የሚባሉ ችግሮችንም ጭምር
ለቅሞ በማሳየት የህዳሴ ጉዟችንን ለማሳለጥ በሚከናወኑ ተግባራት ውስጥ የራሱን ማዕተም ማሳረፍ ይኖርበታል ባይ ነኝ፡፡ ፐብሊክ
ሰርቪሱ የአገልጋይነት መንፈስን በማጎልበት ለህዳሴያችን መሰረት መሆን ይገባዋል፡፡ ሰላም፡፡
No comments:
Post a Comment