EPRDF is a ruling party committed to realize Ethiopia's Renaissance.

Monday 12 December 2016

የመሪ ቃሉ ትንታኔ




  (በእውነቱ ይታወቅ)

11ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን ሕዳር 29 ቀን 2009 ዓ.ም በሃረሪ ክልል ተከብሯል፡፡ የፍቅርና መቻቻል አብነት ተደርጋ የምትጠቀሰውና የጀጎል ግንብን ጨምሮ በፈረስ መጋላና ሌሎች መስህቦቿ የጎብኝዎችን ቀልብ የምትስበው ሃረር “ሕገ መንግስታችን ለዴሞክራሲያዊ አንድነታችንና ለሕዳሴያችን” በሚል መሪ ቃል በተከበረው በዓል ላይ ለመሳተፍ የመጡ እንግዶቿን በፍቅር በመቀበል፣ በመልካም መስተንግዶ አክርማ በልዩ ትዝታ ሸኝታለች፡፡


የዘንድሮው በዓል መሪ ቃል በውስጡ ዴሞክራሲያዊ አንድነት እና ህዳሴ የሚሉ አቢይ መልዕክቶችን ይዟል፡፡ ዴሞክራሲያዊ አንድነት ሲባል የአንድ ሀገር ዜጎች ወይም የተለያየ ፍላጎት ያላቸው ቡድኖች ልዩነታቸውን በዴሞክራሲያዊ አግባብ አቻችለው የሚፈጥሩት ህብረት ነው። የአንዱ ፍላጎት በሌላው ላይ በሃይል ሳይጫን ሁሉም ለሌላው ፍላጎት፣ ጥቅምና መብት እውቅና ሰጥተው በጋራ የሚፈጥሩት አብሮነት ሲሆን በአስገዳጅ ሁኔታዎች ከሚፈጠር የግዛት አንድነት በእጅጉ የተለየ ነው። ከዚህ አንፃር የእኛ የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ አንድነት በምን ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ለመገንዘብ ጥቂት ወደኋላ ተጉዞ ያለፉት ስርዓቶች ልዮነቶቻችንን ሲያስተናግዱ የነበሩበትን ሁኔታ ማወቅ ተገቢ ይሆናል፡፡
በረጅም ጊዜ ታሪካችንም ሆነ በሀገራችን ማዕከላዊ መንግስት ከተመሰረተበት ወዲህ ኢትዮጵያ የብዝሃነት ሀገር ስለመሆኗ አያጠያይቅም፡፡ አሁን ያሉ ብሔር ብሔረሰቦች ጥንተ ጠዋት ጀምረው በየራሳቸው ንጉሶች፣ አባ ገዳዎች፣ ሱልጣኖች፣ ባህላዊ አስተዳደሮች እየተመሩ ኢትዮጵያን ያቀኑ፣ በኢትዮጵያ የኖሩ ናቸው፡፡ በእምነት ረገድም እንደየቅደም ተከተላቸው 4ኛው እና 7ኛው ክፍለ ዘመን ወደ ሀገራችን ከገቡት የክርስትና እና የእስልምና እምነቶች በፊትም ሆነ በኋላ የተለያዩ እምነቶችን ያመልኩ ነበር፡፡
ብዝሃነት ያላቸው እነኚህ ሕዝቦች ብዝሃነታቸውን ያስተናገዱበት አግባብ ሲታይ ግን ሁሉጊዜም ባይባልም እንኳን በአመዛኙ አሉታዊ ነበር፡፡ አንደኛው በሌላው ላይ የበላይ ለመሆን፤ ብሎም አንዱን በአንዱ የማዋዋጥ ፍላጎት የተንፀባረቀበት ታሪክ አሳልፈናል፡፡ ብዝሃነት ባለበት ሀገር የመቻቻልና መፈቃቀድ ፖለቲካዊ ባህል መገንባት የግድ ቢሆንም ያለፉት ስርዓቶች የተከተሉት ስልት ግን አንድነትን በሃይል የመፍጠር ስለነበር ብሄር ብሄረሰቦች የራሳቸውን ቋንቋ፣ ባህል ወይም አምነት የሚጠቀሙበትና የሚያሳድጉበት እድል አልነበረም፡፡ ይህ ሁኔታ በ20ኛው ክፍለ ዘመን ማገባደጃ ላይ የመበታተን ቋፍ ላይ አድርሶን ነበር፡፡ ኢትዮጵያውያን በላያቸው ላይ በግድ የተጫኑ ስርዓቶች ለመጣል ያደረጉት እልህ አስጨራሽ ትግል ፍሬ አፍርቶ የአዲሲቷን ኢትዮጵያ መሰረት የጣሉት ግንቦት 1983 ዓ.ም ነው፡፡ አዲሲቷ ኢትዮጵያ እውን ስትሆን ጥቅማቸውን፣ መብታቸውንና ነፃነታቸውን በጋራና በተደጋጋፊነት ለማሳደግ ብሎም አንድ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማህበረሰብ ለመገንባት ቆርጠው ተነስተዋል። ከዘመናት የዴሞክራሲ እጦት በኋላ የአላማዎቻቸውና የእምነቶቻቸው ማሰሪያ የሆናቸውን ህገ መንግስትም አፅድቀዋል፡፡
ህገ መንግስቱ ራስን በራስ፤ ሀገርን ደግሞ በጋራ በማስተዳደር መርህ ዜጎችና ቡድኖች የጋራ ጉዳያቸውን በሚመለከት በፌዴራል መንግስት እንዲተዳደሩና በየአካባቢያቸው ደግሞ ራሳቸውን የሚያስተዳድሩበትን ነፃነት ያቀዳጀ ነው፡፡ ማንኛውም የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰብና ሕዝብ በቋንቋው የመናገር፣ የመፃፍ፣ ቋንቋውን የማሳደግ እና ባህሉን የመግለፅ፣ የማዳበርና የማስፋፋት እንዲሁም ታሪኩን የመንከባከብ መብት አለው፡፡ ማንኛውም የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰብና ሕዝብ የራሱን እድል በራሱ የመወሰን እስከመገንጠል ያለው መብቱ በማናቸውም መልኩ ያለገደብ የተጠበቀ መሆኑን በአንቀጥ 39 በመደንገግ ስር ነቀል በሆነ ሁኔታ የቀድሞውን አሃዳዊ ስርዓት በፌዴራላዊ ስርዓት፤ የቀድሞውን የሃይል አንድነት በዴሞክራሲያዊ የሕዝቦች አንድነት ተክቷል፡፡ ይህ የጋራ ልማትና ተጠቃሚነት የአገራችንን ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ አንድነት እያጠናከረ ለበለጠ ልማት እያነሳሳቸው ያለ የእድገት ሞተር ነው ማለት ይቻላል።
ሆኖም ዴሞክራሲያዊ አንድነትን መፍጠር በራሱ የመጨረሻ ግባቸው አይደለም፡፡ ይልቁንም ዴሞክራሲያዊ አንድነታቸውን አፅንተው በመፈቃቀድ ላይ የተመሰረተ ዲሞክራሲያዊ ስርአትና መልካም አስተዳር የሰፈነባት፣ ማህበራዊ ፍትሕ የነገሰባት፣ ከድህነት ተላቃ መካከለኛ ገቢ ያላት ኢትዮጵያን እውንማድረግ ራዕይ አንግበዋል፡፡ የሀገራዊ ራዕያችን ሌላ ከፍታ የሆነውን የኢትዮጵያን ሕዳሴ ማረጋገጥን የጋራ ፕሮጀክታቸው አድርገው በመረባረብ ላይ ናቸው፡፡ ይህ እውን የሚሆነው ታዲያ ህገ መንግስታዊ መብቶቻቸው ተረጋግጠው አንድ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ማህበረሰብ መፍጠር ሲችሉ መሆኑ የማያሻማ ነው፡፡ ለዛም ነው የዘንድሮው በዓል ህገ መንግስታችን ለሕዳሴያችን የሚል ፅንሰ ሃሳብንም በውስጡ የያዘው፡፡
ህገ መንግስቱ ኢትዮጵያውያን ፊታቸውን ወደ ድህነትና ኋላቀርነት ትግል እንዲያዞሩ ምቹ ሁኔታዎችን ፈጥሯል፡፡ በዚህም ለሁለት አስርት አመታት በላይ በተለይ ላለፉት 13 አመታት ዘርፈ ብዙ ድሎች ተመዝግበዋል። የደርግ ስርዓት ሲወድቅ አብዛኛው ህዝብ በድህነት ሲማቅቅ የነበረበት ሁኔታቀይሮ በ2007 ዓ.ም መጨረሻ የድህነት መጠን ወደ 23.4 በመቶ ወርዷል። በግብርናው ዘርፍ በተደረገ ርብርብ በአመት ከ250 ሚሊዮን ኩንታል በላይ እህል በዋና ዋና ሰብሎች በማምረት በምግብ እህል ራሳችንን ችለናል፡፡ የዛሬይቱ ኢትዮጵያ ድርቅ ባጋጠመ ቁጥር ዜጎቿ በረሃብ የሚረግፉባት አለመሆኗን በወሳኝነት በራሳችን አቅም ተቋቁመን የወጣነው ያለፈው አመት ከባድ ድርቅ ማረጋገጫ ነው።
በ1983 ዓ.ም 70 ዶላር የነበረው የዜጎች ዓመታዊ አማካይ የነፍስ ወከፍ ገቢ በ2007 መጨረሻ 691 ዶላር ደርሷል፡፡ ትላንት ሀገራችንን በድህነቷና ኋላቀርነቷ ሲዘባበቱ የነበሩ አሁን ተስፋ ያላትና በእድገት እየገሰገሰች ያለች ሀገር መሆኗን መመስከር ጀምረዋል። ሀገራችን ፈጣን እድገት እያስመዘገቡ ካሉ ጥቂት ሀገራት አንዷ ስለመሆኗ፤ ለኢንቨስትመንትና ለቱሪዝም መዳረሻነት ከተመረጡ ተርታ ስለመሰለፏ ኒዮ ሊበራል ተቋሞችና ምዕራባውያን መገናኛ ብዙሃን ሳይቀሩ የሚመሰክሩት ሃቅ ሆኗል። በኢኮኖሚ ዕድገት፣ በማህበራዊ ልማት፣ በመልካም አስተዳደርና በዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ከተመዘገቡ ስኬቶች እና በጅምር ላይ ካሉ ሥራዎች በመነሳት የኢትዮጵያ ሕዳሴ እውን እንደሚሆን የሀገራችን ህዝቦች በተጨባጭ ማየት ጀምረዋል፡፡
እነዚህ ወርቃማ ድሎች ቢመዘገቡም በሂደቱ ያጋጠሙ ተግዳሮቶችና ያልተፈቱ ችግሮችም አሉ፡፡ የሴቶችና ወጣቶች ተሳታፊነትና ተጠቃሚነትን በበቂ መጠን ያለመረጋገጡ፣ ባለ ዝቅተኛ ገቢ የህብረተሰብ ክፍሎች የኑሮ ደረጃ ትርጉም ባለው መልኩ ያለመሻሻሉ፣ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን በወቅቱ ያለመመለስ፣ የልማታዊነት ፖለቲካል ኢኮኖሚ የበላይነት አለመያዙ በውስንነት የሚገለፁ ናቸው፡፡ ከህዝቦች ያልተገደበ የመልማት ፍላጎት የሚመነጩ ጥያቄዎችም እየተበራከቱ ናቸው፡፡ በመሆኑም ራሱኑ ህዝቡን በማሳተፍ እነዚህን ተግዳሮቶች እየፈቱ መሄድ ይገባል።
የዘንድሮው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን “ሕገ መንግስታችን ለዴሞክራሲያዊ አንድነታችንና ለሕዳሴያችን” በሚል መሪ ቃል መከበሩም ህገ መንግስታችን በብዝሃነት ላይ ለተመሰረተው አንድነታችን የተጫወተውን ወሳኝ ሚና ለማሳየትና በዚሁ ላይ ተመስርተን ህዳሴችንን ከዳር ለማድረስ ቁርጠኝነታችንን እንድናድስ ለማነሳሳት ነው፡፡

No comments:

Post a Comment