ክሩቤል መርሃፃዲቅ
የኢትዮጵያ ብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች
የጋራ የቃል ኪዳን ሰነድ የሆነውን ህገ መንግስት ከጸደቀ 22 ዓመታትን ተቆጠሩ፡፡ ህገ መንግሰቱ የዘመናት የህዝቦች ጥያቄ በመመለስ
አገሪቱን ወደ አዲስ ተስፋና ምዕራፍ አሸጋግሯል፡፡ ህገ መንግስቱ የጸደቀበት ቀን ምክንያት በማድረግ ህዳር 29 ቀን የብሄሮች ብሄረሰቦችና
ህዝቦች በዓል ሆኖ እየተከበረ ይገኛል፡፡ በዓሉ ዘንድሮም ‹‹ህገ መንግስታችን ለዴሞክራሲዊ አንድነታችንና ለህዳሲያችን›› በሚል
መሪ ኃሳብ ለ11ኛ ጊዜ በተለያዩ ዝግጅቶች በመከበር ላይ ይገኛል፡፡
ኢትዮጵያ ለበርካታ ዘመናት የቀጠሉ
በርካታ ጦርነቶችና ግጭቶችን በእልህ አስጨራሽ የህዝቦች ትግል በብቃት አልፋ ሰላምዋንና በብዙኃነት ላይ የተመሰረተ ጠንካራ ህገ
መንግስታዊ ስርዓት ገንብታለች፡፡ የህገ መንግስቱ መጽደቅን ተከትሎ የተተገበረው ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት በሁሉም መስክ ወደ
ፊት መገስገስ ከጀመረች እነሆ ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ ተቆጥረዋል፡፡ በእነዚህ የስኬትና የትግል ዓመታት በሰላም፣ ልማትና
ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ አስደናቂ ለውጦችን ተመዝግበዋል፡፡ በዚህም የአገራችንን የዘመናት የኃልዮሽ ጉዞ ተቀልብሶ ቀድሞ ወደ
ነበረችበት የስልጣኔ ማማ ለመውጣት የህዳሴ ጉዘዋን እያቀላጠፈች ትገኛለች፡፡
አዲሱ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት
እውን ከመሆኑ በፊት በነበሩ ዘመናት በኢትዮጵያ ተንሰራፍቶ የነበረውን
ጭቆና ለማስወገድ ብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች መብታቸውንና ነፃነታቸውን ለማስከበር በየፊናቸው ጨቋኞችን ተፋልመዋል፡፡
በኢህአዴግ መሪነት በተደረገው መራራ ትግልና በተከፈለው ክቡር መስዋእትነትም
በብሄሮች፣ ብሄረ ሰቦችና ህዝቦች ላይ ተጭኖ የነበረውን የጭቆናና የዓፈና ቀንበር ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ተገርስሶ በምትኩ በህዝቦች
መፈቃቀድ ላይ የተመሰረተ ህገ መንግስታዊ፣ ዴሞክራሲያዊ ፌደራላዊ
ስርዓት ተገንብቷል፡፡
በኢትዮጵያ ከነበረውና አሁንም ካለው
ተጨባጭ አውነታ የፌደራላዊ የመንግስት አወቃቀር ተግባራዊ መደረጉ
አመራጭ የሌለው ብቸኛ መንገድ ነው፡፡ ቀደም ሲል ሰፍኖ በነበረው
የብሄር ጭቆና ምክንያት በርካታ በብሄር የተደራጁ ኃይሎች ነፍጥ አንስተው መገንጠልን ዓላማ ያደረገ የትጥቅ ትግል ሲያደርጉ እንደነበር
ይታወሳል፡፡ እናም ኢትዮጵያ ተጋርጦባት የነበረው የመበታተን አደጋ ለማስቀረት የብሄሮች፣ ብሄረ ሰቦችና ህዝቦች መብት ሳይሸራረፍ
በእኩልነት እንዲኖሩ ብሎም ባህላቸውንና ቋንቋቸውን እንዲያሳድጉ ለማስቻል የፌደራሊዝም ስርዓት መገንባት እንዳለባቸው ተስመማምተው
አዲሱን የእኩልነትና የመተማመን ምዕራፍ በመክፈት የሀገራችን አስተማማኝ ሰላም ከማረጋገጣችንም በላይ ለአፍሪካውያን ወንድሞቻችንንም
ጭምር መትረፍ ችለናል፡፡
ባለፉት 25 ዓመታት በተግባር እንደታየውም
ህገ መንግታዊና ፌደራላዊ ስርዓቱ አስተማማኝ ሰላም እንዲሰፍን ልማት እንዲፋጠንና የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታን ከጊዜ ወደ ጊዜ
እንዲጠናከር የማይተካ ሚና ተጫወቷል፡፡ በእርግጥ ህገ መንግስቱንና ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን የሚፈታተኑ ጉዳዮች የሉም ወይም የፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ጉዞው አልጋ በአልጋ ነው ማለት አይደለም፡፡
ቀደም ባሉ ዓመታት በአንዳንድ አካባቢዎች አልፎ አልፎ እንደታየውና በቅርቡም በአንዳንድ አካባቢዎች የትምክህትና የጥበት አስተሳሰቦች የወላዳቸው አፍራሽ ተግባራት መከሰታቸው አልቀረም፡፡
የትምክህት ኃይሉ ከ25 ዓመታት በፊት የነበረችውን ኢትዮጵያ አሁን ካለችው አዲሲቷ ኢትዮጵያ በጣም የተሻለች እንደነበረች
አድርጎ በማቅረብ በመፈቃቀድ ላይ የተመሰረተው ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ
ስርዓት በማጥላላትና “ከፋፋይ” የሚል ስም በመስጠት አዲስ በመገናባት ላይ ባለው ስርዓት ላይ የተለያዩ የማጥላላት ዘመቻዎችን
ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ እውነታው ግን ከ25 ዓመታት በፊት የነበረው ሁኔታ በሁሉም መልኩ እጅግ አስከፊ ከመሆኑ የተነሳ ዜጎቿ እንኳን
በሀገራቸው ከመኖር ይልቅ በደመነፍስ እግሮቻቸውን ወደመሩባቸው የሚሰደዱበት የጨለማ ዘመን እንደነበር ዓለም ጭምር የሚያውቀው እውነታ
ነው፡፡ ሀገራችን “የብሄሮች ብሄረ ሰቦችና ህዝቦች እስር ቤት” እስከመባል ደርሳ የነበረችበት ምክንያትም ለዘመናት ተንሰራፍቶ በነበረው
ግፍና ጭቆና መሆኑን እየታወቀ አዲስ የተገነበውና በእኩልነት ላይ የተመሰረተና ለብዙኃነት ተገቢ የሆነ ዕውቅና የሰጠ ስርዓት ለማጣጣል
ሲባል እነዚህ ኃይሎች የትናትናውን አስከፊ ስርዓት እያሞካሹ ባለፉት ስርዓታት በዜጎች ላይ የደረሰውን ስቃይና እንግልት በመካድና
ጨቋኞችን በማወደስ ይሞግታሉ፡፡
የጠባብነት አስተሳሰብ የተጠናወታቸው
ኃይሎችም እንዲሁ ባለፉት ስርዓቶች የተፈጸሙ በደሎች ዛሬም እንዳልተወገዱ አስመስለው በማቅረብ ዴሞክራሲያዊ ፌደራላዊ ስርዓቱን ጥላሸት
ለመቀባት ብዙ ጥረት አድርገዋል፡፡ ይህ ግን ለማደናገርና ለማውገርገር የተመሰረተ እንጂ በህገ መንግስቱና በፌደራል ስርዓታችን ቀደም ባሉ ዓመታት የነበሩ በደሎች እንዳይደገሙ አድርጎ አስከፊውን የታሪክ
ምዕራፍ ላይመለስ መዘጋቱ አጥተውት አይደለም፡፡
በኢህአዴግ የሚመራው መንግስትና ህዝብ
ህገ መንግስቱንና ፌደራላዊ ስርዓቱ የፈጠሩላቸው ምቹ ሁኔታ እየተጠቀሙ እጅ ለእጅ ተያይዘው ባለፉት 25 ዓመታት አመርቂ ድሎችን
ተጎናጽፈዋል፡፡ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ልዩነታቸው ጌጥና ውበት ከመሆኑም በላይ የጥንካሬአቸው ምንጭና ምሶሶሰ መሆኑን በተግብር
ተቀብለው አከባቢቸውና ክልላቸው እንዲሁም የጋራ ጎጆአቸው የሆነች ሀገራቸውን ለማልማት እጅ ለእጅ ተያይዘው ባካሄዱት ዘርፈ ብዙ
ርብርብ ኢትዮጵያ ብዙዎችን ያስገረመ ፈጣንና ተከታታይነት ያለው የኢኮኖሚ ዕድገት ለማስመዝገብ ችላላች፡፡ በተለይም ከተሃድሶ ማግስት
ጀምሮ ለ15 ዓመታት በተመዘገበው ፈጣን ልማት በበርካታ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎቸ ከድህነት ወለል ለማውጣት ተችሏል፡፡ በዚህም የድህነት
መጠን በግማሽ ለመቀነስ ተችሏል፡፡ በአገሪቱ ከዚህ በፊት ሊታሰቡ የማይችሉ ትላልቅ የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች ጨምሮ በአገሪቱን
የመንገድ፣ የባቡርና የመገናኛ የመሰረተ ልማት አውታሮች በማስፋፋት የህዝቦቻችን ተጠቃሚነት በቀጣይነት ማሻሻል ተችሏል፡፡
በማህበራዊ ልማት ዘርፍም እንዲሁ
ማንኛውም ለትምህርት የደረሰ ህጻን ከትምህርት ገበታ ውጭ እንዳይሆን ለማድረግ የሚያስችሉ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን ከማስፋፋት
ጀምሮ የሙያና ቴክኒክና የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በብዙ እጥፋ ማስፋፋት ተችሏል፡፡ በዚህም በሁሉም የትምህርት ደረጃዎች 30
ሚሊዮን የሚሆኑ ዜጎች ማስተናገድ የሚችል የትምህርት መሰረተ ልማት መገንባት ተችሏል፡፡ በዚህም የዜጎቻችን የትምህርት ተጠቃሚነት
ትርጉም ባለው መልኩ ማረጋገጥ ተችሏል፡፡
መከላከልን ማዕከል ያደረገ የጤና
ፖሊሲ በመከተልም የጤና መሰረተ ልማቶችን በማስፋፋትና ባለ ሙያዎችን በመመደብ በጤና መስኩ ላይ አመርቂ ውጤቶችን መመዝገቡ ሌላው
ሀገራችን ያስመዘገበችውን አስደነቂ ስኬት ነው፡፡ ይህ ስኬትም በዓለም አደባበይ ጭምር ሀገራችን የጤናው ዘርፍ የስኬት ተመሳሌት
ተደርጋ የሚትወሰድበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡
የፌደራል ስርዓቱ አስተማማኝ ሰላም
እንዲሰፍን በማድረጉ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ሂደታችን ለማጠናከርም አስችሏል፡፡ የግልና የቡድን መብቶች ሳይነጣጠሉና አንዱ ሌላኛውን
ሳይደፍቅ እንዲሁም በሁለቱ መብቶችና ነፃነቶች መበላለጥ ሳይኖር በእኩል በማክበር፣ ፖለቲካዊ ስልጣን በምርጫ ብቻ እንዲያዝ በማድርግ
እንዲሁም መንግሰትና ሃይማኖት እንዲነጣጠሉና አንዱ በሌላኛው ላይ ጣልቃ እንደዳይገባ ሕጋዊ ክልከላ በማበጀት ዴሞክራሲያችንን በቀጣይነት
ማጠናከር ችለናል፡፡
የጠባነትና የትምክህት አስተሳሰብ
የተጠናወታቸው ኃይሎች የፌደራል ስርዓቱን ለመናድ የሚያደርጉት ጥረት በመሰረቱ የህዝቡን ጥያቄዎች ተገን በማድረግ ካልተነሱ በየትኛውም
ሁኔታ ወደ ህዝቡ ዘልቀው የሚገቡበት ዕድል እንደማይኖር ይገነዘባሉ፡፡ ለዚህም ነው ሕዝቡ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች
ባነሳበት ሁሉ እነሱም የማይጠፉት፡፡ ካሳለፍነው ዓመት ጀምሮ ደግሞ መንግስት ህዝቡ ለሚያነሳቸው ጥያቆች በወቅቱ ተገቢውን ምላሽና
በማይሰጥባቸውና የህዝቡ የመልካም አስተዳደር እሮሮዎች ዘላቂ መፍትሔ
መስጠት ካለመቻሉ ጋር ተያይዞ የፌደራላዊ ስርዓቱን የሚፈታተኑ ተግዳሮቶች መከሰት ጀምረዋል፡፡ እነዚህ ኃይሎች የፌደራል ስርዓቱን
ለመናድ በሚያደርጉት ጥረትና የድርጅታችን የህዝብ አገልጋይነት ባህል እየተሸረሸረና የመንግስትን ስልጣን የግልን ጥቅም ማስከበሪያ
መንገድ አድርጎ የማሰብ ዝንባሌ እያደገ በመምጣቱ ምክንያት በህዝቡ ዘንድ በተፈጠሩ ቅሬታዎች አማካይነት በኢህአዴግ መሪነትና በህዝቦች
የጋራ ጥረት ሰፍኖ የነበረውን አስማማኝ ሰላም ቀላል የማይባል አደጋ ገጥሞት ነበር፡፡ በዚህም የሀገራችንን ሰላም በማደፍረስ አገርን የማፈራረስ ግልፅ ተልዕኮ ይዘው የሚንቀሳቁ አፍራሽ አካላት ከዚህም
ከዚያም እየተጠራሩ መሰረት አልቦ ጋብቻ እሰከመፈፀም የደረሱበት ሁኔታ ለማየት ችለናል፤፡ ይህም እኛ በማንኛውም ምክንያት የመዘናጋት
ሁኔታ ካሳየንና በሆነ ጉዳይ ከተዳከምን የሀገራችን ህልውና አደጋ ላይ የሚወድቅበት ጊዝ ሩቅ እንዳልሆነ ከማስረዳቱም በላይ የአንዚ
አፍራሽ አካላት ህልውናም በእኛው ድክመት ላይ የተመሰረተ እንደሆነ የሚያስገነዝቡ ክስተት ሆኗል፡፡
ከቅርብ ጊዜ ጀምሮ እየተከሰቱ ያሉ
ግጭቶች የፌደራል ስርዓቱ ያስከተላቸው ችግሮች ናቸው ብለው የሚከራከሩ አንዳንድ የዋህ ወገኖችም አሉ፡፡ አገሪቱ አሃዳዊ የመንግስት
አወቃቀር ብትከተል ኖሮ አሁን ሚታዩ ችግሮች መከላከል ይቻል እንደነበርም ይሞግታሉ፡፡ ይህ ሃሳብ የፌደራል ስርዓቱን ጥላሸት ለመቀባት
ሲደረግ የነበረውን ዘመቻ አንዱ አካል እንጂ ውሃ የሚቋጥር ቁምነገር የለውም፡፡ አሃዳዊ ስርዓት የሀገራችን አንድነት የሚያረጋግጥ
እማ ቢሆን ኖሮ ቅደመ 1983 የነበረችው ኢትዮጵያ ዜጎቿ በመከባበርና በመቻቻል የሚኖሩባት እንዲሁም በመንግስታቱና በህዝቦች መካከል ጠንካራ አንድነት መፍጠር በቻለች ነበር፡፡ እወነታው
ግን ከዚህ በተቃራኒ እንደነበር ለማስረዳት ምርምር አያሻውም፤ ምክንያቱም ሁሉም የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በውል
የሚገነዘቡትና የኖሩበት የሰቆቃ ዘመን ስለሆነ አሁን እንኳን መለስ ብለው ስለዚያ የጨለማ ዘመን ማሰብ አይፈልጉም፡፡
በመሰረቱ በአሁኑ ወቅት እየተከሰቱ
ያሉ ችግሮች ፈጣን ልማቱን በማስቀጠል እና ትክክለኛ ለሆኑ የህዝቡ ጥያቆችም አፋጣን ምላሽ በመስጠት እንዲሁም መልካም አስተዳዳርን
በማስፈን የህዝቡን እርካት በቀጣይነት እረጋገጡ በመሄድ የሚቃለሉ እንጂ ከፌዴራል ስርዓቱ ጋር የሚያገናኝ አንዳችም ተጨባጭ ምክንያት
እንደሌለው ሁላችን የምንገነዘበው እውነታ ነው፡፡
በእርግጥ አሁን አዚህም እዚያም እየተከሰቱ
እንዳሉ መለስተኛ ግጭቶች ወትሮም የፌደራል ስርዓቱን ለሚያጥላሉና ለድሮ ስርዓት ናፋቂዎች የምስራች መሆናቸው የማይቀር ጉዳይ ነው፤
በእስካሁን ጉዞአችን ያረጋገጥነው እውነታም ይህ ነውና፡፡ እነዚህ ኃይሎች የፌደራል ስርዓቱ ያስገኛቸውን ትርፉቶች ድብን አድርገው
በመካድ መነሻቸው ሌላ የሆኑ ችግሮች የፌደራል ስርዓቱ የፈጠራቸው ሳናካዎች ናቸው በማለት ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ ስርዓቱን የማጥላላት
ዘመቻቸው ትናንትም የነበረና ነገም የሚቀጥል ሲሆን ውንጀላቸው ግን በምክንያት የማይደገፍ በሸፍጥ ላይ የተመሰረተ ጥላቻ የወለደው
የጣረሞት ዘመቻ እንደሆነ ግልፅ ነው፡፡
በዓሉን ስናከብር ታድያ ህገ መንግስታችን ያስገኘልን ቱርፋቶች በሚገባ ጠብቀን የህገ መንግስት አስተምህሮና
ስርጸት በማጠናከር የጀመርነውን የልማት፣ የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታና የህዳሴ ጉዞ ከዳር ለማድረስ ለመረባረብ ቃል በመግባት
መሆን አለበት፡፡ የልማታችንና የሰላማችንን ዋስትና የሆነውን ህገ መንግስታችን ከማንኛውንም አደጋ ለመጠበቅ ቃላችንን ማደስም ግድ
ይለናል፡፡
No comments:
Post a Comment