(በእውነቱ ይታወቅ)
የኢፌዴሪ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ሚያዚያ 21 ቀን 1998 ዓ.ም
ባካሄደው በሶስተኛ የስራ ዘመን አንደኛ አመት ሁለተኛ መደበኛ ስብሰባው ለዜጎችና ለቡድኖች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች መከበር
ዋስትና የሆነው የኢፌዴሪ ህገ መንግስት የፀደቀበት ህዳር 29 ቀን የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በሚል ስያሜ በየአመቱ
በተለያዩ ዝግጅቶች እንዲከበር ውሳኔ አስተላልፏል።
የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በዓልን የምናከብረው ለዘመናት የቆየው
የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የእኩልነት፣ የዴሞክራሲና የፍትህ ጥያቄ ተገቢ ምላሽና ዘላቂ ዋስትና ያገኘበት እለት በመሆኑ ነው።
በዓሉ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች መልካም እሴቶቻቸውን በማጎልበት በሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ እንዲሰለፉና ህገ መንግስታዊና ዴሞክራሲያዊ
እሴቶችን ጠብቀው ከትውልድ ትውልድ እንዲያስተላልፉ ከማስቻሉም ባሻገር ዜጎች ሃገራዊ አመለካከትና ብሔራዊ መግባባትን እንዲያጎለብቱ
ከፍ ያለ ሀገራዊ ፋይዳ ያለው በመሆኑ በድምቀት ልናከብረው ይገባል። የማንነት፣ የቋንቋ፣ የባህል፣ ወዘተ… ልዮነት ያላቸው ኢትዮጵያውያን
በየራሳቸው ውበት ደምቀው የሚታዩበት፣ እርስ በርስ የሚተዋወቁበትና የጋራ ጉዳዮቻቸውን የሚያጎለብቱበትም በዓል ነው።
በዚሁ መሰረት የመጀመሪያው በዓል ህዳር 1999 ዓ.ም “ህገ መንግስታዊ
ቃል ኪዳን የአብሮነታችን መገለጫ ነው” በሚል መሪ ቃል በአዲስ አበባ ከተማ ተከበረ። ይህን በዓል በዋናነት የፌዴሬሽን
ምክር ቤት ሃላፊነት ወስዶ በወቅቱ ከነበረው የአዲስ አበባ ከተማ ጊዜያዊ ባለ አደራ አስተዳደር ጋር በመሆን ነው ያዘጋጀው። የመጀመሪያው
በዓል የተከበረበት ወቅት ከአለም ልዩ የሚያደርገን የዘመን አቆጣጠራችንን ተከትለን ወደ ሶስተኛው ሚሌኒየም ለመሸጋገር ብሩህ ራዕይና
ተስፋ የሰነቅንበት ወቅት ነበር፡፡
ሁለተኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በሺህ አመት
አንድ ጊዜ የሚገኘውን የሚሌኒየም በዓል መላ ኢትዮጵያውን በአዲስ መንፈስ በድምቀት እያከበሩ ባሉበት በ2000 ዓ.ም የተከበረ መሆኑ
ባለ ልዩ ትውስታ ያደርገዋል። “ልዩነታችን ውበታችን፤ ውበታችን አንድነታችንና ጥንካሬያችን ነው” በሚል መሪ ቃል የተከበረው ይህ በዓል
“የሚሌኒየሙ
የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን” የሚል ስያሜም ተሰጥቶታል። በተለይም ይህ በዓል የብሔሮች ህብር፣ ውበትና አንድነት
ሙዚየም በሆነው በደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል በሃዋሳ ከተማ መከበሩ ልዩ ድምቀት እንዲኖረው ያስቻለ ነበር።
ሶስተኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በኦሮሚያ
ክልል አዘጋጅነት በአዲስ አበባ ከተማ “ዴሞክራሲያዊ አንድነታችንን በማጠናከር ልማታችንን እናፋጥናለን”
በሚል መሪ ቃል ነው የተከበረው። ከትግራይ ክልል በስተቀር ከሁሉም የሀገራችን ክልሎች ጋር የሚዋሰነው የኦሮሚያ ክልል በሁሉም የአዲስ
አበባ መግቢያ በሮች ወደ አዲስ አበባ የሚገቡ ተሳታፊዎችን በመቀበል ከሁሉም የኢትዮጵያ ሕዝቦች ጋር በፍቅር፣ በመከባበርና በዴሞክራሲያዊ
አንድነት ለመኖር ያለውን ፅኑ ፍላጎት ያሳበት ነው፡፡
አራተኛውን የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን ልዩ የሚያደርገው
የምስራቅ ኢትዮጵያ ተጎራባች ክልሎች በጋራ ያዘጋጁት መሆኑ ነው። የኦሮሚያ፣ አፋር፣ ሀረሪ ክልሎችና የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር
በጋራ በመሆን የፍቅር ከተማ በሆነችው ድሬዳዋ ከተማ በዓሉን “መቻቻል ለዴሞክራሲያዊ አንድነትና ልማት” በሚል መሪ ቃል
በድምቀት አክብረውታል። እነዚህ ክልሎች ያላቸውን የታሪክ፣ የባህል፣ የመልክዓ ምድርና የሕዝቦች ትስስር መሰረት በማድረግ መልካም
እሴቶቻቸውን አስተባብረው የተመጣጠነ ልማት ለማስፈንና አስተማማኝ አካባቢያዊ ሰላም ለማረጋገጥ በ2001 ዓ.ም ኮንግረንስ አካሂደው
የመተዳደሪያ ቻርተር ባፀደቁ ማግስት ነው ይህን በዓልም በጋራ ያከበሩት።
“የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች እጅ ለእጅ ተያይዘን
የሀገራችንን ህዳሴ ወደ የማይቀለበስበት ደረጃ እናደርሳለን” በአዲስ አበባ ከተማ ለሶስተኛ ጊዜ
በሀገር አቀፍ ደረጃ ደግሞ ለአምስተኛ ጊዜ የተከበረው የኢትዮጵያ
ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን መሪ ቃል ነው። ይህ በዓል በአህጉራችን ለመጀመሪያ ጊዜ እዚህ መዲናችን ከተካሄደው አለም አቀፍ
የፌዴራሊዝም ጉባዔ ጋር ተቀናጅቶ የተከበረ ነው። ለብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በዓል ከተዘጋጁት መርሃ ግብሮች ዋና ዋናዎቹ በጉባዔው
መክፈቻ ላይ እንዲቀርቡ ተደርጓል። እናም ኢትዮጵያውያን ይህን በዓል ያከበሩት በአለም የፌዴራሊዝም ስርዓት ከሚከተሉ አገሮች ጋር
በመሆን ነው ማለት ይቻላል።
ይህ በዓል የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ማንነት፣ ውበት፣
አንድነትና ብዝሃነት ለአለም የተዋወቀበት፤ የሀገራችንም መልካም ገፅታ የተገነባበት ተደርጎ ይወሰዳል። የፌዴራሊዝም ስርዓትን የተመለከቱ
ተሞክሮዎቻችንን ለሌሎች ያካፈልንበት፤ ከሌሎችም ልምድ የቀሰምንበት ነው። በተጨማሪም ወቅቱ የመጀመሪያው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን
እቅድ ተቀርጾ ሰፊ ውይይት ከተደረገበት በኋላ መተግበር በጀመረበት የመጀመሪያዎቹ ወራት ነበር። እናም ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች
ይህን የተለጠጡ ግቦችን ይዞ የወጣ እቅድ ለመፈፀም ቃላቸውን ያፀኑበት ነው።
የትግራይ ብሔራዊ ክልል ርዕሰ መዲና የሆነቸው መቀሌ ስድስተኛውን
የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን “ህገ መንግስታችን ለብዝሃነታችን፣ ለአንድነታችንና ለህዳሴያችን”
በሚል መሪ ቃል አክብራለች። በዓሉ በህገ መንግስቱ ላይ የተሻለ ግልፀኝነት የማስያዝ ልዩ አላማ አንግቦ የተከበረ እንደመሆኑ ህገ
መንግስትን በስፋት ማስተዋወቅ ያስቻሉ ልዩ ልዩ ሲምፖዚየሞች ቀርበውበታል። የትግራይ ክልል በወቅቱ 4.6 ሜትር ቁመት ያለውና
16 ቶን የሚመዝን ግዙፍ ጀበና በመስራት እንግዳ ነገር ይዞ ቀርቦ ነበር። ይህ ጀበና ኢትዮጵያ መላው አለም በየቀኑ የሚጠጣውን
ቡና ለአለም ያበረከተች ሀገር መሆኗን የሚመሰጥር ነው። ከዚህም በላይ ግን ቡናን ተጠራርቶ የመጠጣት ሀገራዊ ባህላችን በብሔር፣
ብሔረሰቦችና ሕዝቦች መካከል ያለው መቀራረብና ህብረት መገለጫ ነው። የጀበናው 11 መቅጃ ቧንቧዎችም ዘጠኙን ክልሎችና ሁለቱን የከተማ
አስተዳደሮች የወከሉትም ለዚህ ነው።
ሰባተኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል “ብዙም አንድም
ሆነን በመለስ ራዕይ በህገ መንግስታችን ለህዳሴችን” በሚል መሪ ቃል በአማራ ብሔራዊ ክልል አዘጋጅነት በባህር ዳር
ከተማ ተከብሯል። ይህ በዓል በሀገራችን ብዝሃነትን ያስተናገደ፣ ሁሉንም የፖለቲካ ሃይሎች ያሳተፈ፣ ብሔር ብሔረሰቦችን ያስተሳሰረና
ዴሞክራሲያዊ ኢትዮጵያን ለመገንባት ያስቻለን ህገ መንግስታዊ ስርዓት እውን እንዲሆን አንፀባራቂ ሚና የተወጡትን ታላቁን መሪ መለስ
ዜናዊ ባጣንበት ማግስት የተከበረ መሆኑ ልዩ ትውስታ ያለው ነው። ታላቁ መሪ መለስ ዜናዊ ከወጣትነታቸው ጀምሮ ለብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና
ሕዝቦች እንዲሁም ለሀይማኖቶች እኩልነት፣ ለፍትህና ለዴሞክራሲ መረጋገጥ ሩቅ አልመው ወደ ትግሉ ተቀላቅለዋል። ድርጅታቸውን በበሳል
አመራር በመምራትም የህዝቦችን ትግል ለፍሬ አብቅተዋል። በሀገር መሪነት ጊዜያቸውም ሀገራችንን ከተዘፈቀችበት የድህነትና ኋላቀርነት
አረንቋ ለማውጣት የሚያስችል የጠራ መስመር እንዲሁም ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች በመቅረፅ ብቃት ያለው አመራር ሰጥተዋል። ይህ በዓል
የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የመለስን ራዕይ ለማሳካት ቁርጠኝነታቸውን ዳግም ያደሱበት ሲሆን መታሰቢያነቱም ለታላቁ
መሪ እንዲሆን ተደርጓል።
በዚህ በዓል ላይ አዘጋጁ ክልል 5 ሜትር ዲያሜትር ያለው በጣም
የገዘፈ መሶብ ይዞ ቀርቦ ነበር። ይህ በኢትዮጵያ ለዘመናት ፀንቶ የቆየውን በጋራ የመመገብና የቤተሰብ አብሮነት ባህል የሚያመለክተው
መሶብ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በዴሞክራሲያዊ አንድነት መኖር የሚያስችላቸው ህገ መንግስት ከቀረፁ በኋላ እየተገነባ
ካለው አንድ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማህበረሰብ የሚገኘውን ሀብት በእኩልነት የመቋደስ አብሮነታቸውንና ፍቅራቸውን አመላካች ነው።
ስምንተኛውን የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል
ያዘጋጁት የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ሕዝቦች ናቸው። በዓሉ የክልሉን ሕዝቦች ባህል፣ ታሪክና ማንነት በሌሎች እንዲታወቅና በዓሉ በክልላዊ
የልማት ክንዋኔዎች እና በሕዝብ ለሕዝብ ትውውቅ እንዲከበር በማድረግ ረገድ ልዩ ቦታ የሚሰጠው ነው። በዚህ በዓል የተነሳ ባለፉት
ስርዓቶች በነበሩ ጭቆናዎችና በፀረ ሰላም ሃይሎች ተፅዕኖ ምክንያት የኢትዮጵያ ሶማሌ ሕዝቦች በሌሎች ሕዝቦች ላይ ያኖሩትን የተሳሳተ
ጥርጣሬ መቅረፍ የተጀመረበት ነው። የክልሉ ሕዝቦች ለኢትዮጵያ አንድነት የከፈሉት መስዋዕትነትም ጎልቶ የወጣበት ነው።
የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል 400 ሊትር ወተት መያዝ የሚችል ጎረፍ
(ለግመል ወተት ማቅረቢያነት የሚያገለግል ባህላዊ ቁስ) በማዘጋጀት የበዓሉ ተሳታፊዎች (የዘጠኙ ክልሎች ተወካዮች) ከአንድ የወተት
ማቅረቢያ በጋራ ጠጥተዋል። ክልሉ ይህን ሲያደርግ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ፍቅርና አንድነት እንዲሁም መተሳሰብ
ከመቼውም ጊዜ በላይ እየጎመራ ስለመምጣቱ ማሳያ ነው። በተጨማሪም ክልሉ በሚታወቅበት የግመል ሃብት ውጤት በሆነው የግመል ቆዳ ላይ
ህገ መንግስቱን በመፃፍ ለመታሰቢያነት አበርክተዋል። በክልሉ ዋና ከተማ ጅግጅጋ “ህገ መንግስታችን ለህዳሴያችን” በሚል መሪ
ቃል ከተከበረው በዓል ቀደም ብሎ በአዲስ አበባ ሸራተን ሆቴል አርቲስቶች ከፌዴሬሽን ምክር ቤት ጋር ያዘጋጁት የካሊ ምሽት የክልሉን
ገፅታ ለሌሎች የኢትዮጵያ ሕዝቦች በማስተዋወቅ ረገድ ከፍተኛ እገዛ አድርጓል።
ዘጠነኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል የቃል
ኪዳናችን ሰነድ የሆነውና ሀገራችንን ከቁልቁለት ጉዞ የታደገው የኢፌዴሪ ህገ መንግስት የምልዓተ ህዝቡን ይሁንታ አግኝቶ በፀደቀበት
20ኛ አመት ላይ የተከበረ ነው። በመሆኑም “በህገ መንግስታችን የደመቀ ኢትዮጵያዊነታችን ለህዳሴያችን”
በሚል መሪ ቃል የተከበረው በዓል ማዕከል ያደረገው በህገ መንግስቱ ትሩፋቶች፣ ተግዳሮቶችና በህገ መንግስት አስተምህሮ ላይ ነው።
ህገ መንግስቱ ከፀደቀ ወዲህ ባሉት 20 አመቶች መላ ኢትዮጵያውያን በሁሉም መስኮች አያሌ ድሎችን አስመዝግበዋል። ይሁንና ለዘመናት
ከኖርንበት ድህነትና ኋላቀርነት ለመውጣት ከፊታችን ረጅምና አድካሚ ጉዞ አለብን። የቀረፅነውን ሀገራዊ ራዕይ ለማሳካትና ህዳሴያችንን
ለማረጋገጥ ህገ መንግስታችን የሚኖረው ፋይዳ በ9ኛው በዓል ላይ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት ውይይት ተደርጎበታል።
በሌላ በኩል በዓሉ የተከበረው የሁሉም የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና
ሕዝቦች አሻራ ያረፈበት ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ በሚካሄድበት የቤንሻንጉልና ጉሙዝ ክልል መሆኑ ለበዓሉ ልዩ ድምቀትና
ስኬት ሰጥቶታል። በርካታ የበዓሉ ተሳታፊዎችም ግድቡ ካረፈበት ጉባ ድረስ በመሄድ ለ24 ሰዓታት ያለማቋረጥ የሚካሄደውን የግንባታ
ሂደት ለመጎብኘት ችለዋል።
ባለፈው አመት በጋምቤላ ብሔራዊ ክልል አዘጋጅነት “የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና
ሕዝቦች ተሳትፎ ለላቀ እድገትና ትራንስፎርሜሽን” በሚል መሪ ቃል በጋምቤላ ከተማ የተከበረው 10ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና
ሕዝቦች ቀን የክልሉን የቱሪስት መስህቦች ይበልጥ የተዋወቁበት፣ ኢንቨስተሮች በከፍተኛ ቁጥር የልማት ጥያቄ እንዲያቀርቡ በር የከፈተና
የክልሉ ህዝብ አዳዲስ የመሰረተ ልማትና የማህበራዊ ተቋማት ባለቤት እንዲሆኑ ያስቻለ ነው። በሌላ በኩል ሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን
እቅድ ወደ ትግበራ የገባበት በመሆኑ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ከመጀመሪያዊ እቅድ ያገኟቸውን መልካም ልምዶች በመቀመር፣ ጉድለቶቻቸውን
ደግሞ በመቅረፍ ለላቀ ስኬት የተነሳሱበት በዓል ነበር።
በዚህ አመት የተከበረው አስራ አንደኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና
ሕዝቦች በዓል “ሕገ መንግስታችን ለዴሞክራሲያዊ አንድነታቸንንና ለህዳሴያችን” የሚል መሪ ቃል የያዘ ሲሆን በሃረሪ ክልል
መዲና ሃረር ከተማ በድምቀት ተከብሯል፡፡ የክልሉ መንግስትና ነዋሪዎች ሁሉንም የሀገራችንን ሕዝቦችና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን
የሚወክሉ እንግዶቻቸውን በፍቅር ተቀብለው፣ በአክብሮት ሲያስተናገድ ከከረሙ በኋላ በልዩ ትዝታዎች አጅበው ሸኝተዋል፡፡ በሀረር ከተማ
የተከበረው በዓል ልክ እንደ ከዚህ በፊቶቹ ሁሉ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በእለቱ ተገናኝተው የየአካባቢያቸውን ባህል የሚያንፀባርቁ
ትርዒቶችን ያቀረቡበት ብቻ አይደለም። በበዓሉ ዋዜማ ቀናት የተካሄዱ ውይይቶች የፌዴራል ስርዓቱንና ህገ መንግስቱን አስመልክቶ የተሳታፊዎችን
ግንዛቤ ያሳደጉ ናቸው። የክልሉ መንግስት የአው አባድር ስታዲየምን ግንባታ ከማፋጠን ጀምሮ የእንግዶች ማረፊያ፣ ባህላዊ ቤቶችን፣
ፓርኮችንና ሌሎች መሰረተ ልማቶችን በመዘርጋት ሕዳር 29ኝን ለዘላቂ ልማት መሳሪያነት ተጠቅሞበታል።
የሀረሪ ክልል የበዓል አዘጋጆች ለበዓሉ ድምቀትና ልዩ ትርጉም በሚሰጥ
መልኩ ያዘጋጁት የጉፍቲ ሙዳይ በክልሉ ባህልና ወግ ላይ ተንተርሰው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦችን አንድነት የመሰጠሩበት ነበር፡፡
ሙሽሪት ውድ የስጦታና የግል እቃዎቿን የምታስቀምጥበትን ጉፍታ ሙዳይ መስለው የሰሩት ግዙፍ ቅርፅ 12 ሜትር ርዝመትና 6 ሜትር
ስፋት ያለው ሲሆን ከብረትና እንጨት የተሰራ ነው፡፡ በጉፍታ ሙዳዩ ውስጥ 5 መደቦች ሲኖሩ የመደቦቹ ቀለም ቀይ ነው፡፡ ይህም በምስራቅ
ሃረርጌ ለጨለንቆ ሰማዕታት መታሰቢያነት የተደረገ ነው፡፡ የሁሉም ክልሎች ርዕሰ መስተዳድሮች በውስጡ በመግባት ከአንድ ማዕድ እንዲቋደሱ
አድርገዋል፡፡
በቀጣይ አመት የሚከበረውን 12ኛውን በዓል የሚያዘጋጀው የአፋር
ክልላዊ መንግስት ነው፡፡ የአፋሯ ሰመራ ከተማ ደግሞ በሚቀጥለው አመት አከባበር ላይ ይዛ ብቅ የምትለውን አብረን የምናየው ይሆናል፡፡
No comments:
Post a Comment