EPRDF is a ruling party committed to realize Ethiopia's Renaissance.

Wednesday 28 December 2016

ኢሕአዴግ ደምቆ ለመታየት የቀደሙ መንግስታትን አቧራ ማልበስ አያሻውም!

(በኤፊ ሰውነት)
በግል ከሌሎች ሰዎች ጋር በማደርገው ውይይትና በአንዳንድ አጋጣሚዎች በተሳተፍኩባቸው የውይይት መድረኮች ላይ ኢሕአዴግ ለምን ራሱን ካለፉት ስርዓቶች ጋር ያነፃፅራል? የሚል ጥያቄ ሲነሳ እሰማለሁ፡፡ የጥያቄው መነሻ የተለያየ ገፅታ ያለው የመሆኑን ያክል የጠያቂዎቹም ፍላጎት (motive) የተለያየ ሆኖ ይታየኛል፡፡ በእነዚህ ገፅታዎች ላይ ወደኋላ የምመለስበት ሆኖ አሁን አንዳንድ መሰረታዊ ጉዳዮችን ላንሳ፡፡

ዓለማችን በብዙ ልዩነቶችና አንፃራዊነቶች የተሞላች ነች፡፡ ስለሰለጠኑ አገራት በተለይም ስለ ሃብት መጠናቸውና ስለ ቴክኖሎጂ ምጥቀታቸው ለማውራት የእኛን ሀገር አይነት ታዳጊዎችን ማንሳት ያስፈልጋል፡፡ ስለ ኋላቀርነት ሳታውቅ የእሱ ተቃራኒ የሆነውን ስልጣኔ ልታደነቅ አይቻልህምና፡፡ ስለስንፍና ለማውራት ጉብዝናን መረዳት ግድ ይላል፡፡ ስለ መልካምነት ለማውራትም እንዲሁ የመጥፎነትን ገፅታ መለየት ግድ ይላል፡፡  እናም ንፅፅር ተፈጥሯዊ ነው፡፡ ይህ ሁኔታ የሚያሳየን ግን ንፅፅር ተፈጥሯዊ መሆኑን ብቻ ሳይሆን የተሻለ ግንዛቤ ለመፍጠርም ተፈላጊ ጉዳይ እንደሆነ ነው፡፡ አሁንም ከኢትዮጵያ ሕዝብ 23 በመቶ የማያንሰው ከድህነት ወለል በታች መሆኑን እንድንረዳ፤ ከውስጣችን እንዲያመንና እንዲቆጨን በማሌዥያና ታይዋን ከድህነት ወለል በታች የሚኖረው ሕዝብ 5 በመቶ እንኳን እንደማይሞላ ማወቅ አለብን፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን የደርግ ስርዓት ሲወድቅ 50 በመቶ በላይ የሚሆነው የሀገራችን ሕዝብ ከድህነት በታች ይኖር እንደነበር ማወቃችን እስካሁን ድህነትን ለመቀነስ የተከተልነውን መንገድ የስኬታማነት መጠን ያስገነዝበናል፡፡ ስለዚህ ንፅፅራችን ከመነሻችንም ከመድረሻችንም መሆን አለበት፡፡
በሌላ በኩል ያለፈውን ማወቅ የወደፊቱን ለመተለም አይነተኛ መሳሪያም ነው፡፡ ካለፉ ስህተቶች መማር፣ የቀደሙ ጥንካሬዎችን ጠብቆ መዝለቅ፣ ከተቻለም ጥንካሬዎቹን ይበልጥ ማጎልበት ዛሬን ከትናንቱ የተሻለ ለማድረግ ይረዳል፡፡ ትናንት ዛሬ ለደረስንበት ደረጃ በመልካምም ሆነ በመጥፎ ገፅታው መሰረት ነው፡፡ ያለፈው የሚነሳው የዛሬ እሴቶቻችንን በመጠበቅ የተበላሹ ነገሮች ነገ እንዳይደገሙ በጥንካሬያቸው ምሳሌ መሆን የሚችሉትን ደግሞ ጠበቆ የበለጠ መስራት ስለሚያስፈልግ ነው፡፡ እንደዛማ ባይሆን ኖሮ ስለምን ሰዎች ታሪክን ይማራሉ? ለምንስ ስለታሪክ ይመራመራሉ? ብሎ ራስን መጠየቅም ተገቢ ነው፡፡
ከዚህ በመነሳት ኢሕአዴግ ለምን ራሱን ካለፉት ስርዓቶች ጋር ያነፃፅራል? ወደሚለው ጥያቄ ልመለስ፡፡ ይህን ጥያቄ የሚያነሱ ሰዎች ‹‹የአሁኑና ያለፈው እኮ በጣም የተለያዩ ናቸው›› ‹‹አሁን መመዘን ያለበት በአሁን ባለው ሀገራዊና ዓለማዊ መመዘኛ ነው›› የሚሉ መከራከሪያዎችን አብረው ያነሳሉ፡፡ ‹‹ኢሕአዴግ ራሱን ካለፉት ስርዓቶች ጋር የሚያነፃፅረው ካለፉት የተሻልኩ ነኝ በሚል ሰበብ ድክመቱን ለመሸፈን ነው›› ብለው የሚደመድሙም አሉ፡፡
በእኔ አረዳድ አሁን አገራችንን እየመራ ያለው ዴሞክራሲያዊና ልማታዊ መንግስት ላለፉት 25 ዓመታት ያስመዘገባቸውን እሴቶች ካለፈው ታሪካችን ጋር በማነፃፀር ለውጦችን ለመረዳት መሞከሩ ጉድለቱ አይታየኝም፡፡ አሁን ባለው ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ መንግስት ህዝባዊ ባህሪ የተነሳ ለአገራችን ህዝቦች የተረጋገጡ ዴሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብቶችና ነፃነቶችን ጠብቆ ማቆየት እንዲቻል ያለፉትን ነባራዊ ሁኔታዎች ማስጨበጥ ተገቢ እንጂ ሌላ ትርጓሜ የሚሰጠው ሊሆን አይችልም፡፡
ውድ አንባብያን ሁላችንም መመዘን እንደምንችለው አገራችን ባለፉት ዓመታት ባስመዘገበችው ሁለንተናዊ እድገት የቁልቁለት ጉዞዋ ተገትቶ አሻግሮ ማየት የሚያስችል ቁመና መገንባት ችላለች፡፡ ባለፉት ዓመታት አገራችንን በሚመራው ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ መንግስታችን ልማት እንዲረጋገጥ፣ ሰላም እንዲሰፍንና የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታችን እንዲያብብ የሚያስችሉ ዘርፈ ብዙ ተግባራት ተፈፅመዋል፡፡ ከህገ መንግስቱ ጀምሮ የተለያዩ ህጎች፣ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ሁሉ ነገን የተሻለ ማድረግ የሚችሉ፣ የህዝባችንን የመልማት ነፃነት ጭምር የሚያጎናፅፉ ሆነው ተቀርፀዋል፡፡ ይህ ያለፉት ዓመታት አንድ ተጨባጭ ስኬት ተደርጎ ነው የሚወሰደው፡፡ በአገራችን እንኳንስ እኛ በውስጧ ያለነው ዜጎች ይቅርና ዓለም የሚመሰክርለት ለውጥ መመዝገብ የተቻለው ኢህአዴግና ኢህአዴግ የሚመራው ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ መንግስታችን ከህዝብ ጋር በመሆን ልማትን የሞት የሽረት ጉዳይ አድርገው በመረባረባቸው ነው፡፡
የመሰረት ልማት ዝርጋታ የአገራችንን ታሪክ በቀየረ ሁኔታ መፋጠን ችሏል፡፡ በመብራት፣ በመንገድና በውሃ እንዲሁም በሌሎች የመሰረት ልማት አውታሮች ከከተማ ለከተማ ትስስር ተሻግሮ አህጉር አቀፍ ትስስር እየተፈጠረ መጥቷል፡፡ የምርታማነት ደረጃችን አድጓል፡፡ ምንም እንኳን ዛሬም ስራ የሚፈልግና ሁሉንም ወደ ተመሳሳይ ደረጃ ማድረስ የሚገባ ቢሆንም ቀላል ቁጥር የሌለው አርሶ አደር በማይታመን ለውጥ ውስጥ ይገኛል፡፡ ዛሬ አገራችን በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠር ሃብት የሚንቀሳቀስባት፤ ግለሰቦች ያለምንም መሳቀቅ ሃብታቸውን በአገራቸው ላይ የሚያፈሱባት፣ የውጭ ባለሃብቶችም ለኢንቨስትመንት የሚመርጧት አገር መሆን ችላለች፡፡ ይህ ትናንት ያልነበረና ኢህአዴግ አገር የመምራት ስልጣን ከተረከበበት ጊዜ ጀምሮ እየሆነ ያለ ተጨባጭ ታሪክ ነው፡፡ ይህን እውነታ በሚዛኑ መውሰድ ግድ ይላል፡፡ በዓይን የሚታይ ተጨባጭ ሃቅ በመሆኑ፡፡
በእኔ እምነት ይህ እውነታ ኢሕአዴግን ከማናቸውም የቀደሙ ገዥዎች ጋር ሳናነፃፅረው እንኳን በራሱ ታሪክ ሆኖ የሚነገርለት አንፀባራቂ ድሉ ነው፡፡ ይህ ድል ከስኬታቸው ጉድለታቸው ከበዛው የእኛ ነገስታትና አምባገነኖች አንፃር ይቅርና ሕዝባቸውን በአጭር ጊዜ ከድህነት አዙሪት አውጥተው ወደ ብልፅግና ካሸጋገሩ የኤሺያ ነብሮች ጋር ተወዳድሮም በመልካም አብነቱ የሚጠቀስ መሆኑ አለም አቀፍ እውነታ ነው፡፡ እናም ኢሕአዴግ ደምቆ ለመታየት የቀደሙ መንግስታትን አቧራ ማልበስ አያሻውም፡፡
በተመሳሳይ ኢሕአዴግ ራሱን ከቀደሙት ስርዓቶች ጋር የሚያነፃፅረው ጉድለቶቹን ለመደበቅ ነው የሚለው መከራከሪያ መሰረት የሌለውና ማሳመኛ ነጥብ የማይጠቀስለት ድምዳሜ ነው፡፡ የመጀመሪያው ተሃድሶና በየወቅቱ ድርጅቱ የተጋረጡበትን ፈተናዎችና ፈተናዎቹን የተጋፈጠበትን አካሄድ ትተን በቅርቡ ያለውን ሀገራዊ ሁኔታ ብንመዝን እንኳን ኢህአዴግ ባለፉት ስርዓቶች ድክመት ጥላ ስር የመደበቅ ፍላጎት እደሌለው ያሳየናል፡፡
እንደምናውቀው 2008 ዓም ማገባደጃ ጀምሮ በተከሰተው አለመረጋጋት ፍትሃዊና ተገቢ የህዝብ ጥያቄዎች ሳይቀሩ ህጋዊ ባልሆነ መልኩ የተገለፁበት ሁኔታ አጋጥሞ ነበር፡፡ ይህ ኢሕአዴግ 15 ዓመታት የተሃድሶ ጉዞውን በጥልቀት እንዲገመግምና በሰፊ እይታ እንዲመለከተው እድሉን አስፍቷል፡፡ እዚህም እዚያም የተከሰቱ ችግሮች በእርግጥም አገራችንን ለአደጋ ያጋለጡና የመጣንባቸውን የለውጥ ምዕራፎች ቀላል በማይባል ደረጃ ያበላሹ እንደነበሩም አይዘነጋም፡፡ በአገራችን የተከሰተው አለመረጋጋት መነሻ የውስጥ ችግሮች በመሆናቸው ኢህአዴግ ላለፉት ዓመታት በተመዘገቡ ስኬቶች ሳይኮፈስና ድሎቹ በቂ ናቸው የሚል ከንቱ ስሌት ውስጥ ሳይገባ ወደራሱ አስጠግቶ በመመልከት የችግሩ መንስኤ ራሱን መሆኑን ገምግሞ ለህዝብ ይፋ አድርጓል፡፡ አስፈላጊ ነው ብሎ ያሰባቸውን እርምጃዎችም በመውሰድ ላይ ይገኛል፡፡ እውነቱን ለመነጋገር የትኛውም የተደራጀ የተቃውሞ ሃይል ካደረገው በላይ ኢሕአዴግና አባል ፓርቲዎቹ የራሳቸውን ችግር ነቅሰው በማውጣት ራሳቸውን አምርረው ወቅሰዋል፡፡ ለዚህም ነው ኢሕአዴግ የወደቁትን ስርዓቶች ድክመት የሚያነሳው የራሱን ችግሮች ለመደበቅ ነው የሚለው ድምዳሜ ራሱን በራሱ የማረም የቆየ ድርጅታዊ ባህል ካለው የኢሕአዴግ ታሪክ ጋር ሚዛን ላይ ሲቀመጥ ውሃ መቋጠር የማይችል መከራከሪያ ነው ብዬ የማምነው፡፡
በመጨረሻም መጀመሪያ ላይ ወዳነሳሁት ጉዳይ ስመለስ ኢሕአዴግ ላይ በዚህ መልክ የሚነሱ ትችቶች ገፅታና መነሻቸው ሲታይ በአንድ በኩል ኢሕአዴግ ካለፉት ስርዓቶች ፍፁም የተለየና ሊወዳደር የማይችል መሆኑን በእምነት በመውሰድ ኢሕአዴግ፣ በእሱ የሚመራው መንግስትና ሀገራችን እራሳቸውን ከእነሱ በላቀ ሁኔታ ከበለፀጉ አቻዎቻቸው አንፃር እየመዘኑ ይበልጥ ወደፊት እንዲሮጡ ከመፈለግ የሚመነጭ ገንቢ አስተያየት ነው። በርግጥም ታሪክ የሚነሳው የወደፊቱን ለማቃናት ነውና ከዚህ አይነቱ የተሻለ ነገን ከሚመኝ አመለካከት ጋር ልዩነት የለኝም፡፡ እንደውም የእኔ ልዩነት ይህን የሚያስጎመጅ (ambitious) አላማ ሳይይዙ ዛሬን ከሞተ ትናንት ጋር ከሚያነፃፅሩ ወይም ዛሬን ለማንቆለጳጰስ ብቻ ትናንትን ከሚያንቋሽሹት ጋር ነው፡፡
የዚህ ትችት ሌላው ገፅታና መነሻ ደግሞ ያለፉ ስርዓቶች ድክመት ፈጽሞ እንዳይነገር ከመፈለግ የሚመነጭ ነው። ያለፈ ታሪክ ነው በሚልና የዘመን ልዩነትን በማስታከክ ከቀደሙ ስህተቶች ለመማር ያለመፈለግ የወደፊቱን መንገድ ብሩህ አያደርግልንም። አሁን ከምንመራበት ህገ መንግስታዊ ስርዓት በፊት የነበሩት መንግስታዊ አስተዳደሮች ተፈጥሯዊ የሆነውን ብዝሃነታችንን ባለመቀበላቸው ለረጅም ጊዜ በግጭትና ደም መፋሰስ ውስጥ አልፈናል። የሕዝቦች ዴሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብቶች ባልተረጋገጡበት ልማት አይታሰብምና ሰላማችን ብቻ ሳይሆን እድገታችንም ታንቆ ነበር፡፡
ለዚህም ነው ያን ጊዜ ዓለማዊ ሁኔታው የነበረበት የስልጣኔ ደረጃ ለወቅቱ የሀገራችን መሪዎች ከዛ ውጪ የመፈፀም አማራጭ አልሰጣቸውም የሚሉትን ወገኖች በዛው ተመሳሳይ ወቅት በየሀገራቸው የኢንዱስትሪ አብዮት ያፋፋሙትን፣ የመሩትን ሀገርና ህዝብ ወደ መካከለኛና ከፍተኛ የገቢ ደረጃ ያሸጋገሩትን መሪዎች ተመልከቱ የምንለው። ለዚህም ነው አሁን ያለው የስልጣኔ ደረጃና ዓለማዊ ሁኔታ ብቻውን ኢትዮጵያን ወደ ፈጣን እድገት የሚያስገባ ነው የሚሉትን ከኤርትራ ተነስታችሁ፣ በሶማሊያ በኩል አልፋችሁ በርካታ የአፍሪካ ሀገራትን፣ ከዛም ሶሪያንና ሰሜን ኮሪያን ተመልከቱ የምንለው።

3 comments: