EPRDF is a ruling party committed to realize Ethiopia's Renaissance.

Saturday 29 October 2016

አዋጁን ለመደንገግ የግድ ያሉት ምክንያቶች ምንድን ናቸው?



ሀገራችን ከመስከረም 28/2009 ጀምሮ ለስድስት ወራት የሚቆይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጃ በመተግበር ላይ ትገኛለች። ህገ መንግስታዊ ስርዓቱ በሚፈቅደውና በሚያዘው መሰረት አዋጁ በመጀመሪያ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ታውጆ ስራ ላይ መዋል የጀመረ ሲሆን ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም ቀርቦ በሙሉ ድጋፍ መፅደቁ ይታወቃል፡፡

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከአሁን በፊትም ሆነ በአሁኑ ወቅት በበርካታ የአለማችን ሀገሮች ጥቅም ላይ የዋለ ሲሆን ሀገራት አዋጁን ለማውጣት የየራሳቸው ምክንያቶች ይኖሯቸዋል። በሀገራችን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅን በሚመለከት በኢፌዴሪ ህገ መንግስት አንቀጽ 93 በተደነገገው መሰረት የውጭ ወረራ ሲያጋጥም፣ ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን አደጋ ላይ የሚጥል ሁኔታ ሲከሰትና በተለመደው የህግ ማስከበር ስርዓት ለመቋቋም የማይቻል ሲሆን፣ ማንኛውም የተፈጥሮ አደጋ ሲያጋጥም ወይም የህዝብን ጤንነት አደጋ ላይ የሚጥል በሽታ ሲከሰት የፌዴራሉ መንግስት የሚኒስትሮች ምክር ቤት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የመደንገግ ስልጣን አለው፡፡ በተጨማሪም የክልል መስተዳደሮች በክልላቸው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሊያውጁ ይችላሉ፡፡ ከዚህ በመነሳት አሁን በሀገራችን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲታወጅ መንስዔ የሆኑ ጉዳዮችን በዝርዝር መረዳት ያስፈልጋል።
በሀገራችን አንዳንድ አካባቢዎች የተቀሰቀሰው ሁከት ወደ መላው ሀገሪቱ እየተስፋፋና የሁከቱ ባህሪ እየተቀያየረ መምጣቱ ለአዋጁ መታወጅ እንደ አንድ ምክንያት የሚጠቀስ ነው፡፡ ባለፈው ዓመት ከኦሮሚያ ልዩ ዞን የተቀናጀ ማስተር ፕላን ጋር በተያያዘ ፀረ ሰላም ኃይሎች በፈጠሩት የተዛባ አሉባልታ የተፈጠረው ሁከት በኦሮሚያ የተለያዩ ዞኖች መድረሱ የሚታወቅ ነው፡፡ በተመሳሳይ በአማራ ክልል በሰሜን ጎንደር ዞን የተቀሰቀሰው ሁከት ወደተለያዩ ዞኖች ሊዛመት የቻለ ነበር፡፡ በቅርቡም ከኢሬቻ በዓል ጋር በተያያዘ ፀረ ሰላም ኃይሎች በፈጠሩት ግርግር በሰላማዊ ዜጎች የህይወትና የአካል ጉዳት መድረሱን ተከትሎ በክልሉ የተለያዩ ዞኖች ግጭቶች ተከስተዋል፡፡ በተመሳሳይ በደቡብ ክልል በዲላ ከተማ ግጭት ተፈጥሮ በሰው ህይወትና ንብረት ላይ ጉዳት ደርሷል፡፡ እነዚህ ሁከቶችና ግርግሮች ወደሌሎች የሀገሪቱ አካባቢዎች እየተዛመቱ መሆናቸውና ስፋታቸው እየጨመረና ባህሪያቸው እየተቀያየረ ጠቅላላ ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን ወደ መቀየር የተሸጋገረ ነበር።
ሁከቱ በህዝቦችና በሃይማኖቶች መካከል ዘላቂ መቃቃር እንዲፈጠር የሚያደርግ እየሆነ መምጣቱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እንዲታወጅ በምክንያትነት የሚወሰድ ሌላ መነሻ ነው። በአማራ፣ በኦሮሚያና በቅርቡ በዲላ ከተማ በተቀሰቀሱ ግጭቶች የተወሰኑ የህብረተሰብ ክፍሎች በጠላትነት ተፈርጀው ንብረታቸው የተዘረፈ ከመሆኑ ባለፈ የሰው ህይወት ጠፍቷል፡፡ በተመሳሳይ የእምነት ቦታዎችን በማቃጠልና በመዝረፍ በሃይማኖቶች መካከል መቃቃር እንዲፈጠርና ግጭቱን ሃይማኖታዊ መልክ ለማስያዝ ጥረት ተደርጓል፡፡
በአማራና በኦሮሚያ የተለያዩ ዞኖች የተካሄዱ ህገ ወጥ ሰልፎች የጦር መሳሪያ የያዙ አካላት የተሳተፉባቸው ናቸው። በአንዳንድ አካባቢዎች የግልና የመንግስት ተቋማትና ንብረቶች ዝርፊያና ቃጠሎ የተካሄደበት፣ መንገድ በመዝጋት ትራንስፖርት እንዲቋረጥና የሰላማዊ ዜጎችና የፀጥታ ኃይሎች ህይወት እንዲጠፋ የተደረገበት ነው። በአንዳንድ አካባቢዎች ደግሞ ከመከላከያ ሰራዊት፣ ከፌዴራልና ከክልል ፖሊስ ጋር በተደራጀ መልኩ ውጊያ የማድረግ ሁኔታዎች በማጋጠማቸው ለአዋጁ መውጣት ምክንያት ሆኗል።
አመፁ የሚመራበት ስልት ተለዋዋጭ እየሆነ መሄዱም ሌላኛው ምክንያት ነው፡፡ በአንድ በኩል አመፁን ወደትላልቅ ከተሞች ለማስፋፋት ጥረት መደረጉ፣ በሌላ በኩል ደግሞ አነስተኛ ቡድኖችን በማቋቋምና ግለሰቦችን በመጠቀም ወደተለያዩ ቦታዎች በመንቀሳቀስ ጨለማን ተገን በማድረግ ቁልፍ ተቋማት ላይ አደጋ በማድረስ ስርዓት አልበኝነት የማስፈን አቅጣጫ የያዙ መሆናቸውና በተመረጡ ግለሰቦችና የመንግስት ባለስልጣናት ላይ ግድያ የመፈፀም ፍላጎት የታየበት መሆኑ የሚታወቅ ነው።
በዚህ ሁከትና ግርግር የውጭ ኢንቨስትመንትን ኢላማ ያደረጉ ጥቃቶች ተሰንዝረዋል። በበርካታ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ሀገራችን መጥተው ኢንቨስት ያደረጉ የውጭ ባለሃብቶች ተቋማት ላይ ዝርፊያና ቃጠሎ ተከናውኗል፡፡ በአማራና በኦሮሚያ ክልል ንብረትነታቸው የውጭ ባለሃብቶች በሆኑ ፋብሪካዎች፣ የእርሻና የአበባ ልማቶች ላይ እንዲሁም በግልና በመንግስት የልማት ተቋማት ላይ ጉዳት ደርሷል፡፡ ይህን አይነት ተግባር እየቀጠለ ከሄደ ሀገራዊ ገፅታችንን ከማበላሸት አልፎ በቀጣይ በሀገራችን የኢኮኖሚ እድገትና የውጭ ኢንቨስትመንት ለመሳብ እየተደረገ ባለው በጎ ጅምር ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ የሚያሳርፍ በመሆኑ ይህ ሁኔታ በሀገራችን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲታወጅ ተጨማሪ ምክንያት ሆኗል፡፡
በሌላ በኩል በሀገራችን በተስተዋሉት ሁከትና ግርግሮች ህዝቡ ሰላሙና ደህንነቱ አደጋ ላይ እየወደቀ መሆኑን በመረዳት መንግስት አስቸኳይ እርምጃ እንዲወስድ የሚያደርገው ግፊት እየጨመረ መሄዱ በምክንያትነት የሚጠቀስ ነው። ህዝቡ ህገ መንግስታዊ ስርዓቱ አደጋ ላይ እየወደቀ በሄደ ቁጥር ሰላሙ እየደፈረሰ ችግሩ ወደ ሁሉም ቤት ቀስ በቀስ በመድረስ ላይ እንደሆነ በመረዳት መንግስት የዜጎችን ሰላምና ደህንነት በአስተማማኝ ሁኔታ ለማስጠበቅ እርምጃ እንዲወስድ የሚያቀርበው ጥያቄ በስፋት እየተነሳ ተስተውሏል፡፡
በተጨማሪም ሁከቱ ከሚገባው ጊዜ በላይ መቆየቱ ሌላው መነሻ ነው። ሁከቱ የተለያዩ አካባቢዎችን በተለያዩ ጊዜያት የሚያካልል ቢሆንም በአጠቃላይ ከተጀመረ ከስድስት እስከ ዘጠኝ ወራት በላይ እልባት አለማግኘቱና የፀጥታ ኃይሉ ሁከቱን ለመቆጣጠር የሚያደርገው ጥረት አድካሚና ትዕግስትን የሚፈታተን መሆኑ ተስተውሏል፡፡ በሌላ በኩል የውጭና የሀገር ውስጥ ኃይሎች ህዝቡ ያነሳቸውን የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች በመጥለፍ ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን በኃይል የማፍረስ ግብ ይዘው፣ ቅንጅት ፈጥረው እንቅስቃሴ ማድረጋቸው በምክንያትነት የተወሰደ ነው፡፡ የኒዮ ሊበራል ኃይሉ፣ ግብፅና የኤርትራ መንግስት ፀረ ሰላም ኃይሎችን በገንዘብ በመደገፍ በአንዳንድ ቁልፍ ተቋማት ላይ የተለያዩ አደጋዎች በማድረስና እንዲሁም በህዝቦችና በሃይማኖቶች መካከል መቃቃር የሚፈጥር ግጭት በማድረስ እንቅስቃሴ ውስጥ ገብተው ተስተውለዋል፡፡
በአጠቃላይ ከላይ በምክንያትነት የተቀመጡ ስምንት ጉዳዮችን በዝርዝር ለማየት እንደተሞከረው በአሁኑ ወቅት በሀገራችን  ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን አደጋ ላይ በሚጥል ሁኔታ ውስብስብና አደገኛ ችግሮች መከሰታቸውንና መንግስት በተለመደው ህጋዊና አስተዳደራዊ አካሄድ ብቻ እነዚህን በርካታ ችግሮች በፍጥነት እንዲቀረፉ ለማድረግ የማይችልበት ሁኔታ መፈጠሩን መረዳት ይቻላል፡፡ በመሆኑም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከላይ በዝርዝር የተጠቀሱትን ችግሮች በፍጥነት እንዲቀረፉና ህገ መንግስታዊ ስርዓቱንም ከአደጋ ለመከላከል የሚያስችል ህገ መንግስታዊ መፍትሄ መሆኑ ታምኖበት በመተግበር ላይ ነው፡፡ እስካሁን ያሉት ውጤቶችም የዚህኑ እምነት ትክክለኛነት የሚያረጋግጡ ናቸው።
በሌላ በኩል ድርጅታችን ኢህአዴግና መንግስት የጀመሩት በጥልቀት መታደስ በህዝቡ ለተነሱ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችና ቅሬታዎች በተሟላ ሁኔታ ምላሽ በሚሰጥ አግባብ ለማስኬድ ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ምቹ ሁኔታን የሚፈጥር ነው። የእነዚህ ምክንያቶች ድምር አዋጁን ሀገራችን የጀመረችውን የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታና ፈጣን፣ ቀጣይና ፍትሃዊ የሆነ የኢኮኖሚ እድገት ከአደጋ ጠብቆ በማስቀጠል በኩል ወቅታዊና አስፈላጊ እንዲሆን ያደርገዋል፡፡

No comments:

Post a Comment