EPRDF is a ruling party committed to realize Ethiopia's Renaissance.

Thursday, 22 September 2016

ዳግም ተሃድሷችን ጉድለቶቻችንን ብቻ ሳይሆኑ መፍትሄዎቻቸውም ነጥረው የሚወጡበት ይሆናል!!

ያለፈው ዓመት በሀገራችን በርካታ መልካም ነገሮች የተፈጸሙበትና በአንጻሩ ደግሞ አንገትን የሚያስደፉ ክስተቶች የታዩበት ሆኖ አልፏል፡፡ በልማቱ መስክ የአዲስ አበባና የኢትዮ ጅቡቲ የባቡር መስመር የተጠናቀቀበት፤ የታላቁ የህዳሴ ግድብና የሌሎች መሰል ፕሮጀክቶች ግንባታ ተጠናክሮ የቀጠለበት እንዲሁም ላጋጠመን የድርቅ አደጋ በራሳችን አቅም በብቃት ምላሽ መስጠት የተቻለበት ዓመት ነበር፡፡ የተለያዩ ሀገራት መሪዎች ሀገራችንን የጎበኙበትና የሁለትዮሽ ስምምነቶች የተፈረሙበት እንዲሁም ሀገራችን በተባበሩት መንግስታት የጸጥታው ም/ቤት ተለዋጭ አባል ሆና የተመረጠችበት ዓመት ነበር፡፡ ይሁንና በተለያዩ አካባቢዎች የተከሰቱት ሁከትና ብጥብጦች ደግሞ አላስፈላጊ የሰው ህይወትና የንብረት ዋጋ አስከፍለውን አልፈዋል፤ ለሰላም መደፍረስም ምክንያት ሆነዋል፡፡

በአዲሱ ዓመት ላጋጠሙን ችግሮች ዘላቂና ትክክለኛ መፍትሄ ለመስጠትና የተጀመረው ፈጣን ልማት አንዳይደናቀፍ ብሎም ሰላማችንን ወደ ነበረበት እንዲመለስ የችግሮቻችንን ምንጮች ለይቶ ማስቀመጥና አሁን ያለንበትን ሁኔታ መረዳት ያስፈልጋል፡፡ ለዚህም ደግሞ የሀገራችንን የ25 ዓመታት ጉዞ በተለይም የድህረ ተሃድሶ 15 ዓመታት ሂደት በየዘርፉ ምን እንደሚመስል ማየቱ ተገቢ ነው፡፡
በነዚህ ዓመታት አብዛኛውን የሀገራችንን ህዝብ ባቀፈው የገጠርና ግብርና መስክ ሶስቱን የልማት ሃይሎች (ህዝብ፣ መንግስትና ድርጅት) በማስተሳሰር በስኬት ጎዳና ተጉዘናል፡፡ አርሶ አደሩ ጉልበቱን በመጠቀም የሚያመርትበትና መንግስት በግብዓት አቅርቦት፤ የገበያ ትስስር በመፍጠርና በመሰረተ ልማት ዝርጋት ተደጋግፈው በመስኩ ለውጥ ከማምጣትም በላይ በሀገር ደረጃ በምግብ እህል ራሳችንን ለመቻል በቅተናል፡፡ አርሶ አደሩ በትናንሽ ማሳዎች ላይ ከሚያመርተው በተጨማሪ የግብርና ምርቶችን በስፋት ለአለም ገበያ ለማቅረብ እንዲቻል በመስኩ የግል ባለሃብቱ ተሳትፎ እየጎለበት የመጣበት ሁኔታ ተስተውሏል፡፡ በድምሩ ሲታይ በሰፋፊ እርሻዎች ካልሆነ በቀር ለውጥ ማምጣት አይቻልም የሚለውን አስተሳሰብ በመስበር ላለፉት 13 ዓመታት ፈጣንና ተከታታይ እድገት ለማስመዝገብ ችለናል፡፡
በማህበራዊ መስክም የህብረተሰቡ ጤና እንዲሻሻልና መስኩ የሚጠይቀውን የሰው ኃይል ከማብቃት አንጻር ተስፋ ሰጪና ተምሳሌታዊ ስራዎች ተሰርተዋል፡፡ በነዚህ ዓመታት አማካኝ የእድሜ ጣሪያ ከነበረበት 45 ወደ 64 ዓመት ከፍ ሊል ችሏል። በወሊድ ምክንያት ይከሰት የነበረው የእናቶችና የጨቅላ ህጻናት ሞት ቀንሷል፡፡ ሀገሪቱ ያሰበችውን መዋቅራዊ ሽግግር እውን ለማድረግ ይቻል ዘንድም ብቁ የሰው ኃይል ለማፍራት የተኬደበት መንገድ እምርታን አሳይቷል፡፡ ት/ቤቶችን ተደራሽ ማድረግና ግብዓቶችን ማሟላት ከፍተኛ የኢኮኖሚ አቅም የሚጠይቅና ፈታኝ ቢሆንም ረዥም ርቀት የሄድንበትና ተጨባጭ ውጤት ያስመዘገብንበት ነው፡፡ ከህዝባችን 30 በመቶው በተለያዩ የትምህርት ደረጃዎች በመማር ላይ ይገኛል፡፡ በእኛ ሀገር በትምህርት ገበታ ላይ የሚገኘው ህዝብ ብዛት አናሳ የህዝብ ቁጥር ካላቸው 24 የአፍሪካ ሀገራት ህዝብ ቁጥር ድምር ጋር የሚስተካከል ነው፡፡
በፖለቲካው መስክም በህገ መንግስታዊ ፌዴራላዊ ስርዓት የብሄሮች፤ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ጥያቄዎች ተመልሰው፤ የተዛቡ ግንኙነቶች ተስተካክለው አዲስ ስርዓት ተገንብቷል፡፡ ህዝቡ ከልማዳዊ ‘ሰማይ አይታረስ፤ መንግስት አይከሰስ’ አስተሳሰብ ወጥቶ ለጥቅሙና ለመብቱ ተሟጋች፤ በራሱ ጉዳይ እራሱ ወሳኝ መሆኑን አረጋግጧል፡፡ መሰረተ ልማቶች እንዲሟሉለት፤ አጥፊው እንዲቀጣ መናገር ጀምሯል፡፡ በአምስት ሀገራዊና ክልላዊ ምርጫዎች በመሳተፍ ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ያለውን ቁርጠኝነት አሳይቷል፡፡
ከሁሉም በላይ ደግሞ እየተናወጠ በሚገኘው የአፍሪካ ቀንድ ውስጥ ሆነንም ለዓመታት በሀገራችን የሰፈነው አስተማማኝ ሰላም ከፍተኛ ዋጋ የሚሰጠው ድላችን ነው፡፡ ራሳችን ሰላም መሆን ብቻ ሳይሆን በተለያዩ ምክንያት ሰላም ለራቃቸውና ሰላማዊ ህይወት ለናፈቃቸው አፍሪካዉያን ወንድሞቻችንና ለሌሎችም ሰላማቸው እንዲመለስ አጋርነታችንን አሳይተናል፡፡ በዚህም በአለም አቀፍ ደረጃ በሰላም ማስከበር ተሳትፎ ግንባር ቀደም ሚና ካላቸው ሀገራት ተርታ አሰልፎናል፡፡
በአጠቃላይ ሲታይ በአንድ ወቅት እርዳታን ለመጠየቅ አምባሳደሮቿን የምታሰማራ፤ ያለውጭ እርዳታና ብድር በራሷ በጀት ልማትን ማቀድና መከወን ተስኗት የነበረች ሀገር የራሷን አቅም በማጎልበቷ ልመናን ማስቆምና በሀገር ውስጥ ሃብት ልማትን ማስኬድ ችላለች፡፡ ከዚህም በላይ በአለም አቀፍ ደረጃ ያለን ገጽታ ተቀይሯል፡፡ ህዝባችንም ያለፉትን ስኬቶች ሰንቆ ለቀጣይ ለውጥ ያኮበኮበ፤ ድህነትን ታሪክ ለማድረግ የቆረጠ ሲሆን እንደ አጠቃላይ ወደ መካካለኛ ገቢ ለመቀላቀል የቋመጠች ሀገርና ህዝብ መፍጠር ችለናል፡፡
እናም እንዲህ በተስፋ የተሞላች፤ በፈጣን የእድገት ግስጋሴ ላይ ያለችውን ሀገር በተለይም ላለፈው አንድ ዓመት ገዳማ የሚፈታተኗት ችግሮች “ከወዴት መጡ?” ብሎ መጠየቅ ተገቢ ነው፡፡ በተለይ ደግሞ ህዝባዊ ድርጅት መሆኑን በተግባር ያስመሰከረው ኢህአዴግ ገዢ ፓርቲ ሆኖ መንግስትን በሚመራበት ሁኔታ እነዚህ ችግሮች መፈጠራቸው ቆም ብለን ራሳችንን እንድናይ የሚያስገድዱ ናቸው።
ካለው ነባራዊ ሁኔታ በመሳት ስንገመግመው የችግሮቹ ምንጮች በዋናነት በሁለት ተከፍለው ሊታዩ የሚችሉ ናቸው፡፡ በአንድ በኩል ሀገራዊ ለውጡ በራሱ ያመጣቸው ችግሮች ሲሆኑ በሌላ በኩል ደግሞ ከአመራር ጉድለት የመነጩ ናቸው፡፡ በርግጥ በተፈጥሮ ሃብታችን እንዳንጠቀም የሚፈልጉና የዚህች ሀገር ሰላምና ለውጥ እረፍት የሚነሳቸው የውጪ አካላትም ችግሮችን በማባባስና በማቀጣጠል በተለያዩ መንገዶች የራሳቸውን ሚና ተጫውተዋል፡፡ ሆኖም ዋነኛ ችግራችን ውስጣዊ በመሆኑና መፍትሄውም ሙሉ በሙሉ በእጃችን ያለው ለዚሁ ችግር በመሆኑ የዚህ ፅሁፍ ትኩረት የቀደሙት ሁለት ምንጮች ናቸው፡፡
በሀገራችን እየተገነባ የሚገኘው የካፒታሊዝም ስርዓት እንደመሆኑ መጠን ህግና ስርዓቱን ተከትሎ የሚሰራና በገበያ ውድድር ውስጥ ነጥሮ ለመውጣት የሚጥር እንዳለ ሁሉ በአቋራጭ ከገበያ ስርዓት ውጭ ለመክበር የሚደረግ ሩጫም ይኖራል፡፡ ለስልጣን ባለው ቀረቤታ ወይም ከባለስልጣን ጋር ባለ ዝምድና አማካኝነት ያልተገባ ጥቅም ለማግኘት የሚሯሯጡ አካላት እየተበራከቱ መጥተዋል፡፡ እነዚህ አካላት በሚፈጥሩት ኔትዎርክ የህዝብን ኃብት ለመበዝበዝ፣ ከዚያም ከተጠያቂነት ለማምለጥና እድሜያቸውን ለማራዘም ከተለያዩ አፍራሽ አካላት ጋር በመተባባር በስርዓቱ ላይ አደጋ ለማድረስ ጥረት ማድረጋቸው አልቀረም፡፡ በነዚህ ኪራይ ሰብሳቢዎች ጥቅሙ የተነካበት ህዝብ መንግስት መብቱን እንዲያስከብርለት ሲጠይቅ እነዚህ አካላት የህዝቡን ጥያቄ በመጠምዘዝ ወዳልተፈለገ አቅጣጫ እንዲያመራ ሲያደርጉ ታይተዋል። በተጠናቀቀው አመት በህዝብና በመንግስት ንብረት እንዲሁም በሰው ህይወት ላይ ጉዳት ሊደርስ የቻለበት አንዱ መንስዔም ይሄው ነው፡፡
ሌላው ከህዝብ ቁጥር መጨመር ጋር የተያያዘ ነው። ኢህአዴግ ሀገሪቷን ማስተዳደር ከጀመረ ወዲህ የህዝብ ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል። ይህ በራሱ ሃብትና የልማት አቅም ቢሆንም ወጣቱ አብዛኛውን የህብረተሰብ ክፍል በሚሸፍንበት ነባራዊ ሁኔታ የስራ እድል መፍጠር ፈተና መሆኑ የማይካድ ሀቅ ነው፡፡ በርግጥ በኢህአዴግ የሚመራው መንግስት የስራ እድሎችን በመፍጠር ረገድ ወሳኝ ተግባራትን ሲያከናውን ቆይቷል፡፡ ሆኖም ግን ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚመረቁ ወጣቶችን በተገቢው ሁኔታ ወደ ስራ በማሰማራት ረገድ ውስንነቶች ተስተውለዋል፡፡ በዚህም ለሰላምና ህጋዊነት በጽናት የቆመ ወጣት እንዳለ ሁሉ በርካታ ቁጥር ያለው ወጣት በተስፋ መቁረጥ ውስጥ ሊገባ ችሏል፤ በቀላሉ የጸረ ሰላም ኃይሎች መጠቀሚያም ሆኗል፡፡
በሀገሪቱ የመጣው እድገት ለከተሞች መስፋፋትና ለኢንቨስትመንት ፍላጎት መጨመር ምክንያት ሆኗል። ይህም የነዋሪዎችና የአርሶ አደሮች መፈናቀልን አስከትሏል፡፡ በአንዳንድ ቦታዎች ላይ አመራሩና የመንግስት ሰራተኞች ያልተገባ ጥቅም ለማግኘት ከባለሃብቱ ጋር በመመሳጠር ለአርሶ አደሮች ተገቢ ካሳ ሳይሰጣቸው እንዲነሱ አድርገዋል። በተጨማሪም በአንዳንድ ቦታዎች የልማት ተነሺዎችን መልሶ የማቋቋም ሁኔታ በተገቢው ሁኔታ ባለመከናወኑ የቅሬታ ምንጭ ሆኖ ይታያል።
በሌላ በኩል ከእድገቱ ጋር ተያይዘው የተከሰቱ አዳዲስ የህዝብ ፍላጎቶችና ይህንን ለማሟላት ወይም በቂ ምላሽ ለመስጠት አለመቻላችን የህዝብ ቁጣ እንዲቀሰቀስ አይነተኛ መንስዔ ሆኗል። ህዝብ ላነሳቸው ጥያቄዎች በወቅቱ ምላሽ ያለመስጠታችን እንዲሁም በየአገልግሎት ተቋማት የሚከሰቱ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በአግባቡ ያለመፍታታችን ህዝቡ በድርጅታችን ላይ ያለው እምነትና ተስፋ እንዲሸረሸር አድርጓል።
እነዚህን ስር የሰደዱ ችግሮች ለመቅረፍ ኢህአዴግ ዳግም ተሃድሶ በማካሄድ በውስጡ ያሉ ኪራይ ሰብሰቢዎችን የማጥራት እንቅስቃሴ ጀምሯል። አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ለህዝቡ ተገቢውን አገልግሎት እንዲሰጡ፣ የህዝብ ጥያቄዎች ፈጣን ምላሽ እንዲያገኙና ህዝቡ ቅሬታውን የሚያቀርብበትና ተገቢውን ምላሽ የሚያገኝበት እንደ እምባ ጠባቂና ሰብዓዊ መብት ያሉ የዴሞክራሲያዊ ተቋማት እንዲጠናከሩ ማድረግ የተሃድሶው ፍሬዎች እንደሚሆኑ ይጠበቃል።
ለወጣቱ የስራ እድል በመፍጠር ረገድም እስካሁን የተሰሩ ስራዎች ተጠናክረው የሚቀጥሉበትና በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ ወጣቶች አዲስ የስራ እድል የሚፈጥር የወጣቶች የእድገት ፓኬጅ ከመጪው ጥቅምት ወር ጀምሮ ስራ ላይ ለማዋል በመንግስት በኩል ዝግጅቱ ተጠናቋል፡፡
በልማትና በኢንቨስትመንት ምክንያት ለሚነሱ አርሶ አደሮችና የከተማ ነዋሪዎች ተገቢው ካሳ እንዲሰጥና የመልሶ ማቋቋሚያ ማዕከላት ተጠናክረው የህዝቡ ጥያቄ በአግባቡ እንዲመለስ ለማድረግና የሌሎችን ጥቅም በማይነካ መልኩ ያለንን የተፈጥሮ ሃብት የመጠቀም መብታችንን ማስከበርና የተጀመሩ ፕሮጀክቶችን አጠናክሮ መቀጠል ሌላው የመፍትሄው አካል ነው፡፡ በተጨማሪም የማስፈጸም አቅም ለማሳደግና የተሳለጠ ለማድረግ በዚህ ዓመት አዳዲስ አደረጃጀቶች ይፋ ይሆናሉ፡፡

በአጠቃላይ ሲታይ የተከሰቱት ችግሮች ድርጅቱ ራሱን እንደ አዲስ ቆም ብሎ እንዲያይና እንዲያርም እድል የሚሰጡ ናቸው። ኢሕአዴግ ችግሮችን ተቋቁሞ የማለፍ ብቻ ሳይሆን ተግዳሮቶችን እንደ መልካም አጋጣሚ ወስዶ ራሱን የማረምና ለላቀ ውጤት የመብቃት ልምድና ብቃትን ያካበተ በመሆኑ መጪው ጊዜም አሁንም ከኢሕአዴግ ጋር ብሩህ እንደሚሆን ለመገመት አይከብድም፡፡

5 comments:

  1. ጥሩ ነው ግን ተወርቶ እንዳይቀር አደራ

    ReplyDelete
  2. ጥሩ ነው ግን ተወርቶ እንዳይቀር አደራ

    ReplyDelete
  3. This comment has been removed by the author.

    ReplyDelete
  4. This comment has been removed by the author.

    ReplyDelete
  5. በርግጥ ኢህአዴግ ጉድለቶችን ብቻ ሳይሆኑ መፍትሄዎቻቸውም አንጥሮ በማውጣት በኩል በአፍሪካ ተወዳዳሪ የሌለው ድርጅት ነው ቢባል ማጋነን አይደለም፡፡ ችግሩ ኢህአዴግ መፍተሄ ብሎ የሚያስቀመጣቸው መፍትሔዎች በተግባር በመቀየር ህዝብ ለሚያቀርባቸው ወቅተዊ ጥያቄዎች በቃሉ መሠረት በወቅቱ መልስ አለመስጠቱና ለአደርባዮችና ሙሰኞች ምቹ ሁኔታ የሚፈጥሩ ለሙሰኛ ባለስልጣናት ምቹ መድረክ መፍጠሩ ነው፡፡
    ግምገማው አሁንም ውጤታማ ለማድረግ ኢህአዴግ ቁርጠኝነቱ ካለው በመጀመሪያ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ማድረግ ያለበት ከጠቅላይ ሚንስትሩ ጀምሮ እሰከ ቀበሌ ያሉትን የባለስልጠናትና ቤተሰቦቻቸው ሃብትና ንብረት ከነ ምንጪ ለህዘብ ይፋ በማድረግ ቁርጠኝነቱን በተግባር ማሳየት ይገባል፡፡ ሁለተኛ በአገሪቱ የሚደረግ የጥሬ ገንዘብ ክፍያ መጠን (cash payment limit) በህግ በመወሰን የመቆጣጠሪያ ስርአት መተግበር ለሙስና አመቺ የማይሆን ስርአት መፈጠር ካልቻለ ግምገማው እንደ ተለመደው ለሚድያ ፍጆታ ብቻ የሚጠቅም ጉንጭ አልፋ ይሆናል፡፡ ስለዚህ ኢህአዴግ እነዚህ የሙስና በሮች ጥርቅም አድርጎ በመዝጋት ከህዝብ ጋር ይታረቅ፡፡ በርግጥ የኢህአዴግ አመራር ቁርጠኝቱ ካለውና ከሙስና የፀዳ ከሆነ ይችላል፡፡ ካልሆነ ግን???????

    ReplyDelete