ባለፉት
25 ዓመታት በተለይም ኢህአዴግ የመጀመሪያውን ድርጅታዊ ተሃድሶ ማድረጉን ተከትሎ ባሉት 15 ዓመታት ሀገራችን በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊና
በፖለቲካዊ መስኮች አለም የመሰከረለት እድገት አስመዝግባለች። በሁሉም ዘርፎች በሚባል ደረጃ መዋቅራዊ ሽግግር ማምጣት የሚያስችል
ሰፊ መሰረት እየጣለችም ትገኛለች፡፡ እንደ አዲስ በገነባንው ዴሞክራሲያዊ የፌዴራሊዝም ስርዓት ብዝሃነትን በአግባቡ ማስተናገድ በመቻላችን
ከመበታተን አደጋና ከማሽቆልቆል ጉዞ ተላቀን ወደቀደመው የስልጣኔ ማማ የሚወስደንን የሕዳሴ ጉዞ ጀምረናል።
በሌላ
በኩል በየጊዜው ህብረተሰቡ የሚጠይቃቸውን የልማት፣ የመልካም አስተዳደርና ሌሎች ተገቢነት ያላቸውን ጥያቄዎች ከደረስንበት ሀገራዊ
የኢኮኖሚ እድገት አንፃር በሚገባው ደረጃ እንዲመለሱ በማድረግ፣ በመንግስት አመራሩ የሚታዩ የኪራይ ሰብሳቢነት ዝንባሌዎችን በማረም፣
መንግስታዊ ስልጣንን በህዝብ አገልጋይነት መንፈስ በመፈፀም ረገድ ሰፊ ክፍተቶች ይስተዋላሉ። የምንገኝበት ሀገራዊ ሁኔታ በፍጥነት
በማደግ ላይ የሚገኘውን ኢኮኖሚያዊ እድገት ለማስቀጠል አስተማማኝ ዋስትና የሚሰጥ መሆን ሲገባው በተቃራኒው መፍታት ስንችል ባልፈታናቸውና
እየተጠራቀሙ በመጡ ችግሮች የተነሳ ያልተረጋጋ አገራዊ ሁኔታ ተፈጥሯል። ይህ ሁኔታ ለደረስንበት የእድገት ደረጃ በማይመጥን መልኩ
ሃይል በተቀላቀለባቸው ህገ ወጥ የተቃውሞ ሰልፎች ጭምር መገለጥ ጀምሯል።
ይህን
የሀገራችንን ሁኔታ በሚገባ ያጤኑና ከሀገራችን እድገት በተቃራኒው የተሰለፉ ኃይሎች ይህንኑ እንደ ምቹ አጋጣሚ በመውሰድ አጠቃላይ
አገራዊ አመፅ ለማቀጣጠል፣ ብሔርን ከብሔር ለማጋጨትና የልማት ስራዎችን ለማስተጓጎል ተንቀሳቅሰዋል። ባሰቡትና ባቀዱት መጠን ባይሳካላቸውም
የሰው ህይወት እንዲጠፋ፣ የመንግስትና የግለሰብ ንብረት እንዲወድም ማድረግ ችለዋል።
የኢህአዴግ
ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ በዚህ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ከመከረ በኋላ ቁልፉ ችግራችን የመንግስትን ስልጣን የህዝብን ኑሮ ለማሻሻልና አገራዊ ለውጡን ለማስቀጠል እንዲሆን ከማድረግ ይልቅ የግል ኑሮ መሰረት አድርጎ የመመልከትና በአንዳንዶችም ዘንድ የግል ጥቅም ከማስቀደም ጋር የተያያዘ መሆኑን
ተመልክቷል። የኢሕአዴግ ምክር ቤትና የየብሔራዊ ድርጅቶቹ ማዕከላዊ ኮሚቴዎችም ተመሳሳይ ውይይት በማድረግ በተለይ መንግስታዊ ስልጣንን
ለህዝብ አገልጋይነት እንዲውል ካለማድረግ ጋር በተያያዘ የተፈጠሩ የኪራይ ሰብሳቢነት አስተሳሰቦችንና ተግባሮችን ጨምሮ ሙስናና ብልሹ
አሰራርሮችን ተገቢነት ባለው መልኩ እንዲታረሙ የማድረግና አጠቃላይ ድርጅታዊ በጥልቀት የመታደስ ንቅናቄ ተግባራዊ እንዲሆን ወስነዋል፡፡
የኢፌዴሪ
ጠቅላይ ሚኒስትርና የኢሕአዴግ ሊቀ መንበር ጓድ ኃይለማርያም ደሳለኝ የተለዩት ችግሮች ጥልቀት እንዳላቸው የገለፁ ሲሆን የችግሮቹ
ባለቤትም ኢህአዴግና አመራሩ መሆናቸውን አስምረውበታል፡፡ በመሆኑም ችግሮቹንም ለመፍታት በሚደረገው እንቅስቃሴ ኢህአዴግ በቀዳሚነት
በውስጡ ከሚያደርጋቸው ትግሎች ተነስቶ ህብረተሰቡን በስፋት ተሳታፊ እንዲሆን ማድረግ አለበት ማለት ነው፡፡
የአሁኑ
ውሳኔ 10ኛው የኢህአዴግ ጉባኤ መልካም አስተዳደርን ስለማስፈን ካስቀመጠው አቅጣጫ ጋር ተመሳሳይነት ያለው ቢሆንም ቅሉ መፍትሄው
ጥልቀት ያለው ተሃድሶ ማድረግ መሆኑ ደግሞ ለየት ያደርገዋል። ኢህአዴግ ያስቀመጠው በጥልቀት የመታደስ እንቅስቃሴ በከፍተኛ ድርጅታዊ
ቁርጠኝነት ተግባራዊ እየተደረገ በመሆኑ በርካታ ችግሮችን የሚያስተካክል እንደሚሆን ይጠበቃል።
በመጀመሪያ ደረጃ ለበርካታ ችግሮች
መፈጠርና መደራረብ ጭምር ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዳለው በታመነበት ከድርጅትና ከመንግስታዊ ስልጣን አጠቃቀም አኳያ ባለው መባለግ
ላይ ፅኑ ትግል ይደረግበታል። በየደረጃው የሚገኘውን የመዋቅር አመራር ህብረተሰቡን ባሳተፈ አግባብ በመፈተሽ የማስተካከልና መልሶ
የማደራጀት እርምጃም ይወሰዳል፡፡
ሆኖም
ችግሩ በአጭር ጊዜ በሚደረግ የአመራር ማስተካከያ ብቻ የሚፈታ ስላልሆነ በተለይ በከተሞች አካባቢ የሚታየው የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከት
እንዲከስምና በሀገር ደረጃ ልማታዊ አስተሳሰብ የበላይነቱን ይዞ እንዲወጣ የሚያስችል ዘለቄታዊ የአመለካከት ግንባታ ማካሄድን ያካትታል።
በተጨማሪም የተቋማትን አቅም የማጎልበት አቅጣጫን መከተልን መሰረት ያደረገ ጥልቀት ያለው ተሃድሶ ነው የሚደረገው፡፡
ኢህአዴግ
ከመጀመሪያው አንስቶ ለሚፈጠሩ ችግሮች ውጫዊ ባለቤት በመፈለግ ሳይሆን ችግሮችን ውስጣዊ አድርጎ በማየትና መፍትሄ በመስጠት የሚታወቅ
ድርጅት ነው። አሁን ላጋጠሙ ችግሮችም እንዲሁ ዋነኛው ባለቤቱ እራሱ መሆኑንና ለችግሮቹም መፍትሄ አስቀምጦ ወደ ተግባር መግባቱ
ለተሻለ ሀገራዊ ለውጥ አዲስ ምዕራፍ የሚከፍትበትን ሁኔታ ለመፍጠር ያስችለዋል፡፡ በተለይ በጥልቀት ለመታደስ በምናደርገው እንቅስቃሴ
ውስጥ መላ ህብረተሰቡን በሚገባ ማሳተፍ ከቻልንና የተሃድሶ ሂደቱና ውጤቶቹ ሳይቀዛቀዙ እንዲቀጥሉ ማድረግ ከቻልን የእስካሁኑን የእድገት
ጉዞ አጠናክረን በማስቀጠል የሕዳሴ ጉዟችንን ከታለመለት ምዕራፍ ማድረስ እንችላለን፡፡
No comments:
Post a Comment