EPRDF is a ruling party committed to realize Ethiopia's Renaissance.

Monday, 26 September 2016

“ማን ይናገር የነበረ ማን ያርዳ የቀበረ”

በኤፊ ሰውነት
ኢትዮጵያ በስልጣኔ ማማ የነበረችበት ዘመን ሁሌም ሲታወስ የሚኖር የታሪካችን አንዱ ገፅታ ነው። ከዚህ የከፍታ ማማ ወደ ታች ቁልቁል መውረድ የጀመርንበት ያ አስከፊ ዘመንም ሌላው የታሪካችን አካል ነው። በእነዚህ ሁለት ፅንፍ የታሪክ ውጣ ውረዶች ውስጥ ያለፈችው አገራችን ከሁለት አስርት ዓመታት ወዲህ ደግሞ የቁልቁለት ጉዞዋን ገትታ ዳግም ወደ ከፍታ ማማ ለመሸጋገር በማያቋርጥ የለውጥ ሂደት ውስጥ ትገኛለች።


እኛ ኢትዮጵያውያን እንዲህ ከአንዱ ጫፍ ወደ ሌላኛው ጫፍ እየተላጋን ስንጓዝ ሀገራዊ ሰላም የነበረውን ትርጉምና ፋይዳ በሚገባ ተረድተንዋል። ለእኛ ሰላም ምን ማለት እንደሆነ በተሻለ ለእኛ ሊያስረዳን የሚችልና የሚገባ አካል የለም። የሰላምን ዋጋ ሰላም ባጣንባቸው ክፉ ዘመናትም ሆነ ሰላማችንን ባጣጣምንባቸው የለውጥና የዕድገት ዓመታት በሚገባ መገንዘብና ማመዛዘን ችለናል።

በኢሕአዴግ የሚመራው ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ መንግስት ሰላም፣ ልማትና ዴሞክራሲን የማይነጣጠሉ የለውጣችን ሶስት ማእዘኖች እያለ በተደጋጋሚ ይገልፃቸዋል። ይህ መሰረታዊ እምነት ከሀገራችን ተጨባጭ ሁኔታ የተቀዳ ህዝባዊ አስተሳሰብ ነው። አንዳንድ አገሮች ለዴሞክራሲ ጀርባቸውን ሰጥተው ልማት ላይ ብቻ በማተኮር ስኬታም የልማት ድሎች መቀዳጀት ችለዋል። ሌሎቹ ደግሞ ዴሞክራሲን ብቻ በመዘመር በተጨባጭ ግን ለባለሃብቱ ያዳላ የኢኮኖሚ ስርዓት በመገንባት ደሃውን የበይ ተመልካች አድርገዋል።

በእኛ አገር ነባራዊ ሁኔታ ግን ልማትና ዴሞክራሲን ሳይነጣጠሉ በአንድ ላይ ማረጋገጥ ካልቻልን ብሔራዊ ህልውናችን ጭምር አደጋ ላይ እንደሚወድቅ በግልፅ አስቀምጠን እየተረባረብን እንገኛለን፡፡ ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ መንግስታችን ሰላም፣ ልማትና ዴሞክራሲ ሳይበላለጡና አንዱ የሚቀድም ሌላው የሚከተል ሳይሆን በእኩል መከበር የሚገባቸው የህልውና ጉዳይ አድርጎ በመውሰድም በሁሉም ዘርፎች ወርቃማ ድሎችን አስመዘግቧል፡፡

የአገራችን ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ከ25 ዓመታት በፊት በአገራችን የነበረውን አስከፊ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማሕበራዊ ሁኔታ ከስር መሰረቱ ለማስወገድ ሲታገሉ ሰላማቸውና የመኖር ህልውናቸው ጥያቄ ውስጥ በመግባቱ፣ በነፃነት የመናገር፣ የመፃፍና የመቃወም መብታቸው በመደፍጠጡና በድህነት አረንቋ ውስጥ እየኖሩ የመልማት መብታቸው እንኳን የተገደበበት ሁኔታ ስለነበር ነው። በመሆኑም ሰላምም፣ ልማትም፣ ዴሞክራሲም በአገራችን በእኩል መረጋገጥ እንዲችሉ ነበር ክቡር መስዋዕትነት የከፈሉት። አንዱን ጥሎ ሌላውን አንጠልጥሎ በመሄድ ውጤት ማምጣት የማይቻልና ከነባራዊ ሁኔታችን ጋርም የማይጣጣም የኪሳራ መንገድ መሆኑን ያኔ ገና በውል ተገንዝበውታል።

በእኛ ሁኔታ ሰላም በሌለበት ዜጎች ተረጋግተው ስለልማታቸውም ሆነ ስለዴሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብቶቻቸውና ነፃነቶቻቸው መከበር ማሰብ አይችሉም። ዴሞክራሲያዊ መብትን በመከልከልና በማፈንም ልማትን ማረጋገጥ አይቻልም። ልማት ከሌለም አንዱ እየበላ ሌላኛው የበይ ተመለካች እየሆነ ባለፀጋውና ድሃው በአንድ ላይ ሰላማዊ ህይወት መምራት አይቻላቸውም። በሌላ በኩል ልማትን ማፋጠን የሚቻለው እንደ ህዝብ በአንድ ልብ በአገሩ ጉዳይ ላይ ሰላማዊ በሆነ ሁኔታ ያለገደብ መሳተፍ የሚችል ዴሞክራሲያዊ መብቱ የተጠበቀ ዜጋ ሲኖር ነው፡፡ እናም ሶስቱም በፍፁም የሚነጣጠሉ አይደሉም ማለት ነው።

ሰላም ለእኛ ከልማትም ከዴሞክራሲም እኩል አስፈላጊያችን ነው ስንል ጥቅሙንና ጉዳቱን ከሌሎች አይተነው ሳይሆን ኖረንበት በተጨባጭ ስለምናውቅ ነው። ይህን ብንዘነጋ እንኳን ዞር ብለን አለምን ስናያት አሁንም አብነቶች ሞልተውባታል። ሰላም ከሌለ በህይወት መኖር እንኳን እንደማይቻል የጎረቤቶቻችንን እንዲሁም የመካከለኛው ምስራቅን ወቅታዊ ሁኔታ በማየት መረዳት እንችላለን።
ሰላም የሌለበት ከባቢ መልካም ነገሮች ሁሉ ይርቁታል፣ የነበሩ መልካም ነገሮችም ይጠፋሉ፣ ይወድማሉ። በልማት የሞቁና የደመቁ ከባቢዎች በሙሉ እንዳልነበሩ ይሆናሉ። ደስተኛ ፊቶች ተስፋ በቆረጡና ሞትን በሚጠባበቁ ፊቶች ይተካሉ። ዜጎች ወዴት መሄድ እንዳለባቸውና ምን፣ የትኛው ትክክልና የትኛው የተሳሳተ ውሳኔ እንደሆነ ለመለየት እንኳን ይቸገራሉ። ሰላም ከሌለ ነገን እንኳን አሻግሮ ማየት ይከብዳል። ለዚህ ደግሞ ሶሪያና ዜጎቿ ህያው ምስክር ናቸው።

በሶሪያ እየታየ ያለው በሀገራችንም ሆኖ ያለፈ የታሪካችን አንድ ገፅታ ነው። እናም እኛ ኢትዮጵያውያን የሰላምን ዋጋ ከማንም በላይ በተሻለ እንገነዘበዋለን። ለዛም ነው በመነጋገር፣ በመመካከርና በመተራራም አገራችንን ወደ ፊት እንጂ ወደ ኋላ ላንመልስ ከ20 ዓመት በፊት ባፀደቅነው ህገ መንግስት እጅ ለእጅ ተያይዘን ቃል የገባነው። ለዚህም ነበር ልዩነታችንን የሚያከብር፣ መቻቻልን የሚሰብክ፣ በመከባበርና በመፈቃቀድ ላይ የተመሰረተ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት በቃልኪዳናችን ያፀናነው። ለዚህም ነው ለአገራችን ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ያልተሸራረፈ ነፃነትን የሰጠ የህጎች ሁሉ የበላይ ህግ በሆነ ህገመንግስት ጥላ ስር በመሆን አገራችንን ከቁልቁለት ጉዞ ገተን ወደነበረችበት የስልጣኔ ማማ ለመመለስ የሚያስችለንን ጉዞ የጀመርነው።

እናም “ማን ይናገር የነበረ፣ ማን ያርዳ የቀበረ” ነውና ሰላማችን ለእኛ የበዛ ዋጋ እንዳላት ጮክ ብለን እንመሰክራለን፡፡ ከሰላማችን ማንም ሊያናጋንና ሊነቀንቀን እንደማይገባ እንናገራለን። ይህን የምናደርገው ግን ከችግር የፀዳ እንከን የለሽ ስርዓት ስለፈጠርን አይደለም። የኢሕአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል ጓድ ካሳ ተ/ብርሃን እንዳሉት “የጎደለውን በመጨመር እንጂ ያለውን እያፈረስክ የጎደለውን መሙላት እንደማይቻል” ጠንቅቀን ስለምናውቅ ነው። እዚህም እዚያም የሚፈጠሩ ችግሮች እንደ ዓይን ብሌናችን የምንሳሳለትን የህዳሴ ጉዟችንን እየተፈታተኑት ባሉበት ወቅት ላይ መሆናችንን ዘንግተንም አይደለም። መፍትሄው የጀመርነውን ተሃድሶ ይበልጥ በማጥለቅ ወደ ቀደመው ሕዝባዊ ባህሪያችን መመለስ እንደሆነ ስለምንገነዘብ ነው።


የሀገራችንን ህዳሴ እውን በማድረግ አገራችንን ወደ ተሻለ የእድገት ማማ የማድረስ ራዕያችንን ማሳካት የምንችለው ሰላማችንን ጠብቀን፣ ዴሞክራሲያችንን ይበልጥ ስናጎለብትና ልማታችንን እጅ ለእጅ ተያይዘን ማፋጠን ስንችል ነው። ስለሆነም በማንኛውም ጊዜና ሁኔታ ሰላማችንን የሚያናጋ ማንኛውም ሁኔታ ሲፈጠር በሰከነ አኳኋን ቆም ብሎ ማሰብ ተገቢ ነው። ለእነርሱ የቀለለውን ለእኛ ግን ለዘመናት ስንመኘውና በመራራ ትግላችንና በክቡር መስዋዕትነታችን ያረጋገጥነው ሰላም ሊያሳጡን የሚራወጡትን የጥፋት ሃይሎች ነቅቶ የመከላከል ሃላፊነት በኛው ትከሻ ላይ ያረፈ ነው፡፡

No comments:

Post a Comment