EPRDF is a ruling party committed to realize Ethiopia's Renaissance.

Sunday, 7 August 2016

የሀገራችን እድገት የሁሉም ዜጎች የጋራ ፕሮጀክት ነው!

(በአደም ሐምዛ)
መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገራት ተርታ ለመሰለፍ ያስቀመጥነውን ሀገራዊ ግብ ለማሳካትም ሆነ ረጅሙን የህዳሴ ጉዟችንን ከግብ ለማድረስ በድህነትና ኋላቀርነት ላይ የጀመርነውን ጦርነት አጠናክሮ መቀጠል ለምርጫ የማይቀርብ ብቸኛው መንገድ ነው፡፡ ይህንን ተግባራዊ ለማድረግ ሀገራችን ያሏትን ሁሉንም የልማት አቅሞች በውጤታማነት መጠቀም ይኖርባታል፡፡ ከዚህ አንፃር ዜጎች በተለያዩ የልማት ዘርፎች ተሰማርተው ራሳቸውንና ሀገራቸውን ተጠቃሚ ለማድረግ የሚያከናዉኗቸው ተግባራት ከፍተኛ ሚና የሚጫወቱ ሲሆን ይህም ለአንድ ሀገር እድገት ወሳኙና ትልቁ ሃይል የሰው ሃብቷ ነው ከሚለው ትክክለኛ ትንታኔ የሚነሳ ነው፡፡

በፈጣን እድገት ላይ የሚገኘው የሀገራችን ኢኮኖሚ ያለን የሰው ሃብት በሚገባ ተሳታፊና ተጠቃሚ እንዲሆን በተደረገው ጥረት እየመጣ ያለ መሆኑን መረዳት ይቻላል፡፡ በገጠር ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ የአንበሳውን ድርሻ በሚይዘው የግብርናው ዘርፍ መላ አርሶ አደሩን በተደራጀ ሁኔታ በማነቃነቅ እንዲሁም በከተሞች በርካታ የህብረተሰብ ክፍሎችን በጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዝ ልማት ዘርፎች ተሳታፊ በማድረግ የተከናወኑት ተግባራት የዚህ ማሳያ ናቸው፡፡ ሀገራዊ ባለሃብቱን በመደገፍ የልማቱ አንቀሳቃሽ ሞተር እንዲሆን ለማብቃት የተፈፀሙ ተግባሮችም ትርጉም ያለው ለውጥ ያመጡ ናቸው፡፡
በሀገር ውስጥ ያለውን ህብረተሰብ ዋነኛ ተዋናይ ማድረግ የግድ አስፈላጊ እንደሆነው ሁሉ በተለያዩ ሀገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን በተመሳሳይ የዚሁ ጉዞ ተዋናዮች በመሆን በሀገሪቱ ሁለንተናዊ እድገት ላይ ተሳታፊና ተጠቃሚ መሆን ይጠበቅባቸዋል፡፡ ምክንያቱም ዲያስፖራው የትም ሀገር ይኑር፣ የቱንም ያህል ሀብትና ንብረት እንዲሁም የትምህርት ደረጃና እውቀት ይኑረው ወይም የትኛውንም አይነት ፖለቲካዊ አስተሳሰብ ያራምድ ሊኖረው የሚችለው አንድ ሀገር ብቻ ነው፡፡ ስለዚህ ማንኛውም ሰው በሀገሩ ጉዳይ አይመለከተኝም ሊልም ሆነ አይመለከትህም ሊባል አይገባውም፤ አይችልምም፡፡ በተመሳሳይ ዲያስፖራው ለሀገሩ ሊያበረክት የሚችለውንና የሚገባውን ተሳትፎ እንዳያደርግ ማደናቀፍም ሆነ መከልከል ተቀባይነት የለውም፡፡
በበርካታ የአለም ሀገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ያካበቱትን የእውቀት፣ የገንዘብ፣ የቴክኖሎጂና የተለያየ የልምድ አቅም በሀገሪቱ እድገት በግብዓትነት ለመጠቀም የተደረገው ጥረት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከፍተኛ መሻሻል እየታየበት ቢሆንም በአጠቃላይ የዘገየና ሰፊ ክፍተት የነበረበት ነው፡፡ ለአብነት ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በተለያዩ ሀገራት ከሚኖሩ ዲያስፖራዎች ጋር ሀገራችንን በሚመለከት ትክክለኛና ወቅታዊ መረጃ ከመስጠት ጀምሮ በበርካታ የልማት፣ የዴሞክራሲና የመልካም አስተዳደር ጉዳዮች ላይ በሰፊው ውይይት ማድረግ በመጀመሩ በተለያየ መንገድ በሀገሪቱ እድገት የራሳቸውን አሻራ እንዲያኖሩ ማስቻሉ ሲታይ ቀደም ብሎ ያልተጀመረና የዘገየ ወሳኝ ስራ እንደነበር አመላካች ነው፡፡
ዘግይቶም ቢሆን የተጀመረው ይህ ስራ ዲያስፖራው አሁን ላይ በሀገሪቱ ሁለንተናዊ እድገት ተሳታፊና ተጠቃሚ እንዲሆን እያስቻለ ነው፡፡ በተለያዩ ዘርፎች ላይ በኢንቨስትመንት በመሰማራት፣ በሀገር ውስጥ ቁጠባ በመጀመር ለሀገሪቱ ልማት የፋይናንስና የውጭ ምንዛሪ አቅም በመፍጠር፣ በቦንድ ግዢ፣ በእውቀትና ቴክኖሎጂ ሽግግርና በመሳሰሉት ላይ ንቁ ተሳታፊ እንዲሆኑ ለማስቻል ከዲያስፖራው ማህበረሰብ ጋር ውይይቶች እየተካሄዱ ነው፡፡ በተግባር ወደ ስራ የተገባባቸውን በርካታ ዘርፎችም ስናይ መልካም የሚባሉ ውጤቶች በመታየት ላይ ናቸው፡፡ ሆኖም ካለን ሰፊና ያልተነካ እምቅ አቅም አንፃር በቀጣይ በስፋት መስራት ይጠይቃል፡፡
በሌላ በኩል የዴያስፖራ ማህበረሰብ አባላት በሀገራቸው እድገት ላይ በሚያደርጉት ተሳትፎ ልክ ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚያስችሉ አሰራሮችን መዘርጋትም ይገባል፡፡ በሀገራቸው በሚያደርጉት ኢንቨስትመንት መጠን እራሳቸውን በመጥቀም እግረ መንገዳቸውን ሀገራቸውንና ማህበረሰቡን የሚጠቅሙበት ሁኔታ መፈጠር አለበት፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ በመንግስት በኩል ከዲያስፖራዎች ጋር በሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ተቀራርቦ በመስራት በርካታ መድረኮችን ፈጥሮ ትክክለኛና ወቅታዊ መረጃዎችን በመስጠት በኢንቨስትመንት ያላቸውን ድርሻ ማሳደግ ይጠበቃል፡፡ በመሆኑም አሁን ላይ በጅምር ደረጃ ያሉ ተግባራትን አጠናክሮ ማስቀጠል ቁልፍ ተግባር ሊሆን ይገባል፡፡ በመንግስት የተጀመሩ በተለይ ዲያስፖራው ቢሰማራባቸው ውጤታማ የሚሆንባቸውንና አዳዲስ የኢንቨስትመንት አማራጮችን በአግባቡ መለየትና በመንግስት በኩል የሚደረጉ ድጋፎችን ለይቶ በማስቀመጥ በየጊዜው በመደበኛነት የማስተዋወቅና ሌሎች ተጓዳኝ መረጃዎችን ተደራሽ የማድረጉ ስራ ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል፡፡
በተመሳሳይ በውጭ ሀገር በሚኖሩ የዲያስፖራ አካላት ሀገራቸውን በሚመለከት በተለያዩ አጋጣሚዎችና አካላት አማካኝነት በሚደርሳቸው የተሳሳተና መሰረተ ቢስ መረጃ የተፈጠረውንና በቀጣይም ሊፈጠር የሚችለውን ውዥምብር በማስቀረት ትክክለኛውን መረጃ ማድረስ ላይ መንግስት በሰፊው ሊሰራ ይገባል፡፡ ሀገራችን ከምትገኝበት የእድገት ደረጃና የህዳሴ ጉዞ በተቃራኒው በተሰለፉ ጥቂት ፅንፈኛ ኃይሎች ተፈብርከው በሚሰራጩ በሀሰትና በአሉባልታ የተሞሉ መረጃዎች በርካታ ቁጥር ያላቸው የዲያስፖራ አባላት በሀገራቸው እድገት የበኩላቸውን ድርሻ እንዳይወጡ እየተደረጉ ነው፡፡ አንዳንዶቹ ከትክክለኛ መረጃ ከመራቃቸውና የአሉባልታ ሰለባ ከመሆናቸው የተነሳ ኢትዮጵያ ያለችበትን ሁኔታ 1983. በፊት ከነበረው ጋር እስከማመሳሰልና አንዳንዴም በባሰ ሁኔታ ላይ እንዳለች አድርገው የሚረዱበት ሁኔታ እንዳለ ማየት ይቻላል፡፡ ለዚህም ነው ዲያስፖራው ሚዛናዊና እውነተኛ መረጃዎችን የሚያገኝበትን ስልት መቀየስ የሚያስፈልገው፡፡
ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ የዲያስፖራው አባላት በሀገራቸው አጠቃላይ የልማትና የዴሞክራሲ እንቅስቃሴዎች ላይ ሊከተሉት የሚገባው በትክክለኛ መርህ ላይ የተመሰረተ አካሄድ ሌላው ሊታይ የሚገባው ጉዳይ ነው፡፡ አንድ ያለቻቸው ሀገራቸው ኢትዮጵያ ብቻ ነችና እሷን በሚመለከት ከሚፈጠሩ ማንኛቸውም ጥሩም ሆነ መጥፎ ሁኔታዎች ፈልገውትም እንኳን ቢሆን ሊነጠሉና አያገባኝም ሊሉ እንደማይችሉ በደንብ ሊያጤኑት ይገባል፡፡ በሀገራቸው ማንኛውም የእድገትና የዴሞክራሲ ጉዳይ ተሳታፊ የመሆንና የመጠቀም መብት አብሯቸው ያለና የሚቀጥል በመሆኑ ይህንኑ እድል ለራሳቸውና ሀገራቸው እድገት ሊያውሉት ይገባል፡፡ ስለዚህ የሀገራቸውን እድገትና ማንኛውን ጉዳይ ከውጭ ሆነው የሚመለከቱት ሳይሆን የራሳቸውን የነቃ ተሳትፎ ጭምር የሚጠይቅ መሆኑን በሚገባ ግምት ውስጥ ያስገባ በቂ ተሳትፎ ማድረግ ይኖርባቸዋል፡፡ በሀገራቸው አሉ የሚሏቸውንና ሊቀረፉ የሚገባቸውን ችግሮች ከሚመለከተው የመንግስት አካላት ጋር ተቀራርቦ በመወያየት እንዲፈቱ ከማድረግ አንስቶ የሀገራቸውን እድገት በተለያየ መንገድ የመደገፍ የዜግነት ሃላፊነታቸውን መወጣት ይገባቸዋል፡፡

No comments:

Post a Comment