(በመሃመድ
ሽፋ)
የኢትዮጵያን አንድነት ከሚፈታተኑ መሰረታዊ ችግሮች
መካከል ጠባብ አመለካከትና ትምክህተኛ አቋሞች ይገኙበታል። ጠባብነትም ሆነ ትምክህተኝነት በህዝብ ዘንድ መቃቃርን የሚፈጥር መልዕክት
በመንዛት ሌት ከቀን የሚሰሩ፤ በኢትዮጵያ ውስጥ ዲሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት እንዳይፈጠር የሚያደርጉ አደናቃፊ አመለካከቶች ናቸው፡፡
በመሆኑም አዲሱ ትውልድ የትግል አጀንዳው ሊያደርጋቸው ይገባቸዋል፡፡
በሀገራችን ተጨባጭ ሁኔታ የጠባብነትና የትምክህተኝነት
አስተሳሰቦች ሰፊ መገለጫዎች አሏቸው፡፡ ሁለቱም የያዙትን አመለካከት ለማስረፅ በርካታ መንገዶችን ይከተላሉ፡፡ ትምክህተኝነት ካለፈው
ስርዓት ከተገኙ ቅሪት አስተሳሰቦች የሚመነጭ ሲሆን አንድን ህዝብ ከሌላው ህዝብ የተሻለ አድርጐ የማየት አባዜ ያለው ነው። የራስን
ብሔር የሀገር ብቸኛ መገለጫ ወይም ወኪል አድርጐ የማቅረብ ፍላጎት ነው ትምክህተኝነት፡፡ ባህል ማለት የኛ ባህል ነው፣ ሀይማኖት
ማለት የኛ ሀይማኖት ነው የሚል የተውገረገረ አጀንዳ የሚያራምድ አስተሳሰብ ነው፡፡ ያለፉ ስርዓቶችን የተዛባ የህዝቦች ግንኙነት
እንደ መልካም ስራ በታሪክ በማጣቀስ እራስን ስልጣኑን የተቀማ ሀይል አድርጐ የማቅረብ ዝንባሌ ይንፀባረቅበታል፡፡ ትምክህተኛነት
የኔ ብቻ ትልቅ ነው በሚል አያበቃም፣ ሌሎችም እኔን መከተል ይገባቸዋል የሚል ፀረ-ደሞክራሲያዊ አቋም ይይዛል።
በሌላ በኩል የጠባብነት አመለካከት በተዛባው የታሪክ
ግንኙነታችን ውስጥ ራስን ብቻ ተጐጂ ሀይል አድርጐ የማቅረብ ዝንባሌ የሚስተዋልበት ነው፡ የእኛ ብሔር ስልጣን አልያዘም፣ የእከሌ
ብሔር በዝቷል፣ የእኛ አካባቢ ሳይለማ ሌላ አካባቢ እየለማ ነው፣
እከሌ የሚባል ባለስልጣን ከዚህ ብሔር ስለመጣ መንገዱ ሁሉ ወርቅ እየተነጠፈ ነው የሚሉና ሌሎችንም ቅስቀሳዎች በማድረግ አዲስ ገዥ መደብ የመሆን ፍላጐት በወለደው
ውዠንብር ውስጥ ሲዋልል የሚውል ሃይል ነው፡፡ በዚህ አስተሳሰብ መሰረት የአንድ ህዝብ ልማት ለሌላው ጥፋት የሚሆን የዜሮ ድምር
ጨዋታ ተደርጎ ይወሰዳል። በጋራ ሰርቶ በጋራ ለማደግ ሳይሆን ተገነጣጥሎ አቅም አልባ ለመሆን የሚዳርግ ክፉ አመለካከት ነው።
ትምክህትና ጠባብነት ተመጋጋቢ ናቸው። የትምክህተኝነት
አስተሳሰብ ጐልቶ በሚወጣበት ወቅት የጠባብነት አመለካከት ይወለዳል፡፡ እኛስ ምን ሆነን ነው? የሚል ጥያቄን በማንሳት ጠባብነት
ይጠነሰሳል፡፡ ጠባብነት ትምክህተኛነት በሞላበት ቦታ ሁሉ አለ፡፡ አንዱ ሲኖር ሌላኛው መኖሩ አይቀርም፡፡ እናም የጠባብነት አስተሳሰብ
እንዲሞት የትምክህተኝነት አስተሳሰብ መሞት አለበት፡፡ ምክንያቱም ትምክህተኛው አስተሳሰብ እየሞተ ሲሄድ ጠባብ ሀይሎች የመፈጠር እድላቸው ይመነምናል።
እነዚህ አመለካከቶች ጥቂት የስልጣን ጥመኞችና በዙሪያቸው
ያሉ ተጋሪዎቻቸው ቢከተሏቸውም ህዝባዊ መሰረት ኖሯቸው አያውቅም። የትኛውም የሀገራችን ህዝብ የእነዚህ አስተሳሰቦች ማህበራዊ መሰረት
ሆኖ አያውቅም። ለዚህም ነው ጠባብነትና ትምክህት የትኛውንም ብሄር ወይም ህዝብ አይወክሉም የሚባለው። አዲሱ ትውልድም አፈር የለበሰውን
ስርዓት ጠራርገው ሊያስነሱ የሚሞክሩ ትምክህተኛ ሃይሎችንም ሆነ በተራቸው በህዝብ ጫንቃ ላይ ለመቆናጠጥ የሚሹ ጠባብ ሀይሎችን እኩይ
ስብከት አዳምጦ የሚሳሳትበት ወቅት ላይ አይደለም፡፡ ይህም ባለመሆኑ አመለካከቶቹ የሚረግጡበት ገዢ መሬት አጥሯቸው፣ በአየር ላይ
ተንሳፈው ቀርተዋል።
በአዲሲቷ ኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በመከባበርና
በመፈቃቀድ ላይ ተመስርቶ በጋራ እንዲኖሩ የሚያደርግ ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል። በዛሬይቱ ኢትዮጵያ ህዝቦች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ
ከአንተ ብሄር የእኔ ይበልጣል የሚል አመለካከትን የሚቀበሉበት ወቅት ላይ አይደሉም፡፡ ጠባብነትም ህዝባዊ ተቀባይነት አጥቶ ይበልጥ
እየተገፋ በጥቂት ተስፈኞች ላይ ብቻ የተንጠለጠለ አመለካከት ለመሆን ተዳርጓል።፡ አሁን የኢትዮጵያን አንድነት በአስተማማኝ መሠረት
ላይ የመገንባት ሂደት እየተሳካ ነው ለማለት በሚያስደፍርበት ወቅት ላይ ደርሰናል፡፡
ይህ በመፈቃቀድና መከባበር ላይ የተመሰረተች አንዲት
ኢትዮጵያን የመገንባት ሂደት ታዲያ የአንድነታችን ፀር በሆኑት የትምክህትና ጠባብነት ሃይሎች በየጊዜው ፈተናዎች ይጋረጡበታል። እነዚህ
የጥፋት አመላከቶች ምቹ ሁኔታ አግኝተናል ብለው ባሰቡ ቁጥር ቀና ማለታቸው አልቀረም። ወቅታዊ የሀገራችን ሁኔታ የሚያሳየንም ይህንኑ
ነው። ስለሆነም አሁንም ህገ መንግስቱ ያስቀመጠውን አንድ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማህበረሰብ የመፍጠር ዓላማን ለማሳካት ማነቆ የሆኑ
የጥፋት አመለካከቶችንና ተግባሮችን አውቆ ርብርብ ማድረግን ይጠይቃል፡፡
ትምክህትና ጥበት አመለካከቶች የተደላደለ ማረፊያ ቢያጡም
ዛሬም ጨርሰው አልጠፉምና የፀረ ኪራይ ሰብሳቢነት ትግላችን ኢላማ መሆናቸው ተገቢ ነው። ትናንት የትግሉ አጀንዳ የብሔር እኩልነት
ጥያቄ፣ የፖለቲካ ስልጣን ጥያቄ፣ የመሬት ጥያቄና የመሳሰሉት እንደነበሩት ሁሉ የአሁን ዘመን የትግል አጀንዳዎች ደግሞ የህዳሴ ጉዟችን
እንቅፋት የሆነው የኪራይ ሰብሳቢነት መገለጫ የሆኑት የጠባብነትና የትምክህተኝነት አስተሳሰብ ናቸው፡፡
ኢትዮጵያዊነትን በፅኑ የህዝብ አንድነት ላይ ለመገንባት
ከተፈለገ እኔ አውቅልሃለሁ ባይ ፀረ ዴሞክራሲያዊነት እየተዳከመ፤ በምትኩ ከስሜታዊነት የፀዳና ከአስመሳይነት የራቀ ዴሞክራሲያዊ
ብሄርተኝነት እየለመለመ መሄድ አለበት። መከባበርና መፈቃቀድ የፈጠራት ገናና ሀገር እንድትኖረን የፀረ አንድነት እና የእኩልነት
ፀር የሆኑ አመላካከቶችንና ተግባሮችን ሁሉ ለይቶ ተከተታይ ትግል ማድረግ ይገባል፡፡ በመሆኑም አዲሱ ትውልድ በፀረ ድህነትና ኋላቀርነት
ትግላችን ላይ እንቅፋት የሆኑትን የጠባብነትና የትምክህተኛ አስተሳሰብን በመዋጋት ወደ ትናንት ገናናነቷ የተመለሰች፣ በዓለም አደባባይ
ቀና ብላ የምትታይ የተባበረች ኢትዮጰያን የመፍጠር የህዳሴ ጉዞውን ማስቀጠል ይገባዋል እላለሁ።
Enter your comment...ይልቁንሥ ትክክለኛ ጥያቄን አንሸዋራችሁ ታግ ከመፈለግ ትክክለኛ ለህዝብ መልሥ ብትመልሡ ዝንታለም መግዛት ትችላላችሁ ።ጥቂቶች.ተላላኪዎች. አሸባሪዋች. ትምክተኞች . ጠባቦች እያላችሁ ሥም ከምታወጡ ቀጥተኛ መልሥ ሥጡ ።
ReplyDeleteትምክህተኛ ማለት የበላይ ነበርኩኝ በድሮ አሁንም የበላይ ነኝ ቀጣይም ከሁሉም ሰው በሁሉም ሁኔታ /በእምነት.በብሄር በዘር በፓለቲካ.../ የበላይ ሆኜ ሆነን እንቀጥላለን ።የሚሉ አስተሳሰብና በተግባር የሚገለፅ ነው። ጥበትም በውስን ሃሳብ ቢለያይም ተመሳሳይ ሁኔታ አላቸው። እንድ ኢህአዴግ የበላይም የበታችም የለም ነው።
ReplyDelete