በአሜሳይ ከነዓን
ስለ ትላንቷ ኢትዮጵያ ስናነሳ ከሁለት አስርት
ዓመታት በፊት ስለነበረችው ኢትዮጵያ ነው የምናነሳው፡፡ የትላንቷ ኢትዮጵያ በኢኮኖሚ መስክ ያለማቋረጥ በማሸቆልቆል ላይ የነበረች፤
የዜጎች ዴሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብቶች የሚረጋገጡባት ሀገር ነበረች፡፡ አብዛኛው የሀገራችን ህዝብ በገጠር የሚኖር ቢሆንም
ይህንን ብዙሃኑን ህዝብ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ አሰራር በወቅቱ ባለመኖሩ አርሶ አደሩ ጉልበቱን ለፊውዳሎች ለመገበር ተገዶ
ነበር፡፡ ሀገራችን በተለያዩ ጊዜያት አጋጥሟት የነበረውን የድርቅና የረሃብ ቸነፈር መቋቋም ተስኗት በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎቿ
እንደቅጠል ረግፈውባታል፡፡
የግለሰብም ሆነ የቡድን መብቶች ፈፅሞ በማይከበሩበት
በአጼው ዘመን በተለይ የሀገራችን ህልውና መሰረት የሆኑት የብሔሮች፤ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ህልውና አደጋ ውስጥ የነበረበት ሁኔታ
ነበር፡፡ የሃይማኖትም ሆነ የፆታ እኩልነት ፈፅሞ አይከበሩም ነበር፡፡ ከአጼው የአገዛዝ ዘመን በኋላም ወታደራዊው የደርግ
መንግስት ከድጡ ወደ ማጡ እንዲሉ ሀገራችንን ለ17 ዓመታት በግፍ ቀጥቅጦ በመግዛት ‹‹ኢትዮጵያ ትቅደም›› በሚል መፈክር ከመንግስት
በተቃራኒ ማሰብም ሆነ መቆም እጣ ፈንታው መረሸን እንደነበረ ይታወሳል፡፡
የማሰብ፣ የመናገር፣ የመፃፍ፣ የመደራጀት መብቶች
ሁሉም በይፋ አዋጅ ተከለከሉ፡፡ ዜጎች ሀገራቸውን የመለወጥና የማሳደግ መብት ማንም ሊከለክላቸው እንደማይገባ ሃቅ ሆኖ ሳለ
ደርግ ሃብት ለማፍራት ወሰን በማበጀት ሁሉንም ጠራርጎ በመንግስት ቁጥጥር ስር ማድረጉን አጠናክሮ ቀጠለበት፡፡ ማንኛውም
ኢትዮጵያ ከ500 ሺህ ብር በላይ ካፒታል መያዝ እንደማይፈቀድለት በመደንገግ ፋብሪካዎች፣ ሆቴሎችና መሰል የግል ይዞታዎች
በአዋጅ የመንግስት ንብረት እንዲሆኑ ተደረገ፡፡ የኢትዮጵያ ህዝቦች የሚደርስባቸው የብሄራዊ ጭቆናው እየባሰ ሄደ፡፡ በከተሞችም
ቀይ ሽብር ተፋፍሞ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ታሰሩ፣ ተገረፉ፣ ተሰደዱ እንደቅጠልም ረገፉ፡፡
በአራቱም ማዕዘናት ጭቆናና ግፍ የበዛበት
ህዝብ በወቅቱ የህዝብ ጥያቄ ይዘው ወደ ትግል የገቡ ጥቂት ኃይሎችን በመደገፍ ትግሉ ለድል እንዲበቃ አድርገውታል፡፡ አምባገነኑን
የደርግ መንግስት ለማስወገድ በኢህአዴግ መሪነት የተካሄደው ህዝባዊ ትግልም ለድል በመብቃቱ በኢትዮጵያ የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና
ህዝቦች ዴሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብቶችን የሚያከብር አዲስ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት መገንባት ችሏል፡፡
አምባገነኑ የደርግ ስርዓት ህዝባዊ ድርጅት
በሆነው ኢህአዴግ መሪነት በተካሄደው ህዝባዊ ትግል በተወገደ ማግስት በኢትዮጵያ የተጀመረው የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የማህበራዊ ለውጥ
ዛሬም ድረስ እየተቀጣጠለ ይገኛል፡፡ የደርግ መንግስት መገርሰስን ተከትሎ ከተቋቋመው የሽግግር መንግስት ጀምሮ በአገራችን የነፃ
ገበያ ኢኮኖሚ ስርዓትን በመገንባት የመንግስትና የግል ባለሃብቱ በኢኮኖሚው የሚኖራቸውን ድርሻ የሚያሳይ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ተቀርፆ
ተግባራዊ ተደርጓል፡፡ በዚህም ኢህአዴግ የደርግ መንግስት አግበስብሶ የያዛቸውን ኢንዱስትሪዎች፤ ሆቴሎች እና መሰል ተቋማት ወደ
ግል እንዲዞሩ በማድረግ ገና ከጅምሩ የአገራችን ኢኮኖሚ እንዲያንሰራራ በርካታ አበረታች እርምጃዎችን ወስዷል፡፡
ኢህአዴግ በአርሶ አደሩ ላይ ተጭኖ የነበረው
በኮታና በእርሻ ሰብል ገበያ ድርጅት አስገዳጅነት ሲካሄድ የነበረውን ምዝበራ ከመሰረቱ እንዲወገድ አድርጓል፡፡ የግል ባለሃብቱ
ሃብቱን አምኖ በሀገሩ ላይ ማፍሰስ እንዲችል አሰራሮችን በመፍጠርና በማበረታታት ሀገራችን በጋራ የህዝቦቿ ጥረት የምትቀየር
አገር እንድትሆን ምቹ ሁኔታዎችን ፈጥሯል፡፡ በማሽቆሽቆል ላይ የነበረው ኢኮኖሚ እንዲያገግም በማድረግ አገራችን በዓለም በፈጣን
እድገት ላይ ካሉ ሀገሮች መካከል በቀዳሚነት ተጠቃሽ እንድትሆንም አስችሏታል፡፡
በኢህአዴግ መሪነት በገጠር በከተማ የመሰረት
ልማት ተስፋፍቷል፡፡ የሀገራችንን ህዳሴ ሊያፋጥኑ የሚችሉ ግዙፍ ፕሮጀክቶች ተገንብተዋል፤ እየተገነቡም ይገኛሉ፡፡ በሀገራችን
በመካሄድ ላይ ባለው መጠነ ሰፊ የልማት እንቅስቃሴ የህዝባችን ተጠቃሚነት እየተረጋገጠ የዜጎች ገቢ በፍጥነት እያደገና
ህይወታቸውም በተጨባጭ በመለወጥ ላይ ነው፡፡ ይህ ለውጥ መመዝገብ የቻለው ደግሞ ኢህአዴግ ቀርፆ ተግባራዊ ባደረጋቸው በፀረ ድህነት
ላይ ያተኮሩ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ነው፡፡ ከዚህ ባሻገር በኢህአዴግ የሚመራው ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ መንግስት የሀገራችንን
ሰላም በማረጋገጥ ዜጎች በሰላማዊ መንገድ ወጥተው የሚገቡበት አምርተው የሚጠቀሙበት ሁኔታን በመፍጠሩ ነው፡፡
ህገ መንግስታችን በሀገራችን በማንኛውም ሁኔታ
ሊፈጠር የሚችለውን ውስጣዊ የሃሳብ ልዩነት በዴሞክራሲያና ህዝብን ባሳተፈ መንገድ መፈታት እንዳለባት ደንግጓል፡፡ ይህን መሰረታዊ
መርህ በጥብቅ ተግባራዊ ማድረግ ስንችል ነው ውስጣዊ ሰላማችንን
ዘላቂና አስተማማኝ በሆነ መንገድ ማስቀጠል የምንችለው፡፡ እስካሁን የመጣንባቸው የድልና የስኬት ዓመታት የሚያሳዩትም ይህንኑ
ነው፡፡
በኢህአዴግ የሚመራው ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ
መንግስታችን ለሰላም ያለው ዋጋ ከፍ ያለ መሆኑን ከራሳችን ሰላም አልፎ ለጐረቤት ሀገር ሰላም በመቆም በተግባር አረጋግጧል፡፡ በሩዋንዳ፣
በቡሩንዲ፣ በላይቤርያ፣ በሶማሊያና በሱዳን ሰላምና መረጋጋት ሀገራችን የከፈለችው ዋጋ ለሰላም ያላትን አቋም የሚያረጋግጥ
ነው፡፡
በሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች
ቀጥተኛ ተሳትፎ የፀደቀው ህገ መንግስታችን መሰረታዊ ለሆኑ የዜጎች ዴሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብቶች እውቅና በመስጠቱ ሀገራችን
ሁሉም ዜጋ ወዶና ፈቅዶ የሚኖርባት ሀገር ለመሆን በቅታለች፡፡ አዲሲቷ ኢትዮጵያ የህዝቦች የተናጠል ታሪክ ብቻ የሚነገርባት
ሳትሆን የበርካታ ብሔሮች፤ ብሔረሰቦችና ህዝቦች አኩሪ ታሪክ የሚነገርባትና መላ የሀገራችን ህዝቦች በጋራ በሰሯቸው ታሪኮች የሚኮሩባት
ሀገርም ሆናለች፡፡ ዛሬ የሀገራችን ህዝቦች በጋራ ታሪካቸው የሚኮሩበትና
‹‹ልዩነታችን ውበታችን፤ አንድነታችን ጥንካሬያችን›› በሚል መርህ በጋራ ድህነትን ታሪክ ለማድረግ የሚተጉባት ሀገር ሆናለች፡፡
በመሆኑም በአዲሲቷ ኢትዮጵያ ልማት
ዴሞክራሲና ሰላምን አስተማማኝና ዘላቂ በሆነ ሁኔታ በማስፈን ድህነትን መፋለም ነው ዋነኛ የህዝባችን አጀንዳ፡፡ ትናንትን
ለመመለስ በአንዳንድ የቀድሞ ስርዓት ናፋቂዎች የሚደረግ አፍራሽ እንቅስቃሴ ሁሉ በህዝቦች የተባባረ ክንድ እየተደፈቀ ይሄዳል፡፡
አሁንም የሀገራችን ብሔሮች፤ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በሀገራችን የተጀመረው ልማት፣ ሰላምና ዴሞክራሲ አስተማማኝና ዘላቂ በሆነ
ሁኔታ ለማስቀጠል መትጋታቸውን ይቀጥላሉ፡፡
No comments:
Post a Comment