EPRDF is a ruling party committed to realize Ethiopia's Renaissance.

Friday, 25 December 2015

የፀረ ልማት ኃይሎች ሴራ በህዝባዊነት ሲከሽፍ!



ከዘመኑ ፈረደ
ከ24 ዓመታት በፊት ሀገራችን የነበረችበት ሁኔታ ብዙ ተብሎለታል፡፡ በፊውዳሉም ሆነ በደርግ ዘመነ መንግስት ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ መብታቸውን ተገፈው፣ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን አጥተው፣ ስር በሰደዱ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውሶች ውስጥ ተዘፍቀው ኖረዋል፡፡ ይህንን ሁኔታ ለመቀየርም ህዝቦች በርካታ መስዋዕትነት ያስከፈሉ አያሌ ትግሎችን አካሂደዋል፡፡ ባካሄዱት መራር ትግልም በ1983 ዓ.ም ድልን ተጎናፅፈዋል፡፡ የድህነት ዘብ የነበረውን ስርዓት ከገረሰሱም በኋላም ሰላማቸውን አስጠብቀው፣ ዴሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብቶቻቸውን አስከብረው እንዲሁም አንገታቸውን ያስደፋቸውን ድህነትን ለመፋለም ብዙ ተንቀሳቅሰዋል፡፡ በጥረታቸውም በየጊዜው ተጠቃሽ ለውጥ የታየባቸውን ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ድሎችን አስመዝግበዋል፡፡ 

የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በስምምነት ባጸደቁት ህገ መንግስት ጥላ ስር ሆነው ተማምነው፣ ተስማምተውና ተቻችለው ላለፉት 24 ዓመታት በጋራ ኖረዋል፡፡ ራስን በራስ የማስተዳደር መብታቸውን ተጠቅመውም አካባቢያቸውን በመረጡት የማስተዳደር፣ ባህላቸውንና ማንነታቸውን የማስተዋወቅ እንዲሁም ፍትሃዊ ተጠቃሚነታቸውን ማረጋገጥ ችለዋል፡፡

ህዝቦች በዚህ ትግል ውስጥ ሲያልፉ ግን ነገሮች አልጋ ባልጋ ሆነው አይደለም፡፡ በተለይ የትምክህት፣ የጠባብና የኪራይ ሰብሳቢ ሀይሎች ህዝቦች የድህነትን ዕድሜ ለማሳጠር የሚያደርጉትን ሩጫ ሲያደናቅፉ ኖረዋል፡፡

ሰሞኑን በኦሮሚያ ክልል የተከሰተው ሁከትም ከዚህ አንፃር የሚቃኝ ነው፡፡  ሁከቱ የኦሮሞ ህዝብ ባደረገው ትግል ያረጋገጣቸውን መብቶቹንና ተጠቃሚነቱን ለመንጠቅ የተደረገ ጥረት ሲሆን በምትኩ የግልና የቡድን ጥቅማቸውን ለማረጋገጥ የሚተጉና ድብቅ ዓላማ ያነገቡ ሀይሎች ከየአቅጣጫው የተሰባሰቡበት መድረክ ሆኗል፡፡ ይህንን ሀቅ የበለጠ ለመገንዘብ ነጥብ በነጥብ ለመመልከት እንሞክራለን፡፡

የኦሮሚያ ህዝብ የ24 ዓመታት ጉዞ
ኦሮሚያና የኦሮሞ ህዝቦች ባለፉት 24 ዓመታት በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካዊና በማህበራዊ ዘርፎች ተጠቃሽ ውጤቶችን አስመዝግበዋል፡፡ በጤና፣ በትምህርትና በሌሎች ማህበራዊ መስኮች ላይ የተቀዳጁት ውጤት ቀደም ባሉት መንግስታት የነበረውን ማህበራዊ ቀውሶች ያስተካከለ ነው ማለት ይቻላል፡፡ በክልሉ የተከናወኑ ሰፋፊ የመሰረተ ልማት ግንባታዎች ኢኮኖሚውን በማሳደግ የህዝብን ተጠቃሚነት እጅጉን ያረጋገጡ ሲሆን ምርትና ምርታማነት እንዲያድግ ከፍተኛ አስተዋፅዖ ያበረከቱ ናቸው፡፡ 

የኦሮሞ ህዝብ ራሱን ማስተዋወቅ፣ ባህሉን፣ ቋንቋውንና ማንነቱን ማሳደግ የቻለ ሲሆን በመረጠው ወኪሎቹ ራሱን ማስተዳደር የቻለ ሉዓላዊ ህዝብ ነው፡፡ ለዚህም ህዝቡ ባለፉት 5 ዴሞክራሲያዊ ምርጫዎች ወኪሎቹን መርጦ የልማትና የዴሞክራሲ ስራዎቹን ማከናወን እንደቻለ ማንሳት ይቻላል፡፡ የኦሮሞ ህዝብ ከሌሎች ኢትዮጵያዊ ወንድሞቹ ጋር በመሆን እንደ ሀገር ለተመዘገበው ሁሉን አቀፍ ስኬት የላቀ ድርሻ ያበረከተ ህዝብ ነው፡፡ በአጠቃላይ ምንም እንኳን ቀሪ በርካታ የቤት ስራዎች ቢቀሩትም የኦሮሚያ ህዝብ ካሳለፈው መራርና የጭቆና ዘመን ጋር ሲነፃፀር ስኬታማ ጉዞ ማከናወኑ ልብ ሊባል ይገባል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርና የኦሮሚያ ፊንፊኔ ልዩ ዞን የጋራ የተቀናጀ የልማት ፕላን አስፈላጊነት
አሸናፊ መሀሪ የተባሉ ፀሀፊ “በአንድ ከተማ የሚካሄድ የልማት ስራ በዙሪያው ለሚገኙት የገጠር አካባቢ እና ሌሎች ከተሞች አዎንታዊ አስተወፅኦ እንደሚያበረክት፤ እንዲሁም በአንድ ከተማ የሚከሰት አሉታዊ ገፅታም እንዲሁ አከባቢውን እንደሚጎዳ መረጃ ማቅረብ ሳያስፈልግ የሚታወቅ ጉዳይ ነው” ሲሉ ያስረዳሉ፡፡ የፕላኑ ዓላማም ከዚህ አንፃር መታየት እንዳለበት ያሳስባሉ፡፡ “በአዲስ አበበ ከተማ የሚከናወኑ ማንኛውም የኢኮኖሚ እና የመሰረተ ልማት ስራዎች ጠቀሜታቸው ከከተማዋ የአስተዳደር ክልል ውጭ ሰፊ ቦታ ስለሚሸፍን ፕላኑ በጋራ መስራቱ አጎራባች ከተሞች ይበልጥ ተጠቃሚ ያደርጋቸዋል” ባይ ናቸው፡፡

የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልል የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ፅ/ቤት ሃላፊ አቶ ፈቃዱ ተሰማም በተመሳሳይ የፕላኑን ዓላማ ያስረዳሉ፡፡ በአንዳንድ ልማትን በማይደግፉ አካላት የክልሉን ህልውና ይገዳደራል በሚል የሚገለፀው ማስተር ፕላኑ፥ የክልሉን ከተሞች ከአዲስ አበባና ከሌሎች የክልሉ ከተሞች ጋር በመሠረተ ልማት፣ በንግድ እና ኢንቨስትመንት ለማስተሳሰር እንዲሁም የተፈጥሮ ሃብቶችን በጋራ ለመንከባከብና በጋራ ለመጠበቅ፣ የአካባቢ ብክለትን ለመቆጣጠር፣ ወንጀለኞችን በጋራ ለመከላከል፣ ያለመ እንደሆነ  ነው የተናገሩት።

በእርግጥም የፕላኑን ዓላማ በሚገባ ከፈተሽን ፋይዳ እንዳለው እንረዳለን፡፡ ከተሞቹ ከአዲስ አበባ ጋር በመንገድና በሌሎች መሰረተ ልማቶች ስለሚተሳሰሩ የከተሞቹ የኢኮኖሚ ዕድገት ፈጣን ይሆናል፡፡ በአካባቢው የሚገኝ አርሶ አደርም ገበያው የሚፈልገውን ተወዳዳሪ ምርት እያጠና በማምረት በዝቅተኛ የትራንስፖርት ወጪ ለገበያ በማቅረብ ተጠቃሚ እንዲሆን ያስችለዋል፡፡ ከተሞች ለነዋሪዎቻቸው እና ለተለያዩ የልማት ስራዎች የሚያስፈልጋቸው የውኃና የመብራት አቅርቦቶች በጋራ ኢንቨስትመንት በማካሄድ የኢንቨስትመንት ወጪያቸውን እንዲቀንሱ ያስችላቸዋል፡፡ ከብክለት የፀዳ የኢንዱስትሪ ልማት ለማስፋፋትም ያግዛል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ እንደ ሀገር አንድ የኢኮኖሚ ማህበረሰብ ለመፍጠር ለምናደርገው ጥረት መልካም ሞዴል የሚሆንበትን ዕድል ይፈጥራል፡፡

በርካታ ከተሞችን ያካተተ ፕላን (Regional Planning) ለሀገራችን አዲስ ቢሆንም በሌሎች   ሀገራት ግን  ካለው ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ አንፃር ተመዝኖ በስፋት የሚሰራበት ስራ ነው፡፡ በዚህ ፅንሰ ሀሳብ በመታገዝ በአንድ ሀገር ውስጥ የሚገኙ ከተሞችን ብቻ ሳይሆን አህጉርና ክፍለ አህጉሮችን የሚያገናኙ የመሰረተ ልማት አውታሮች እንኳ ሲዘረጉ ማየት የተለመደ ነው፡፡ በተጨባጭም በአፍሪካ ከደቡብ አፍሪካ እስከ ምስራቅ አፍሪካ የሚዘልቁ የመንገድ ስራዎች በሀገራት ትብብር በመሰራት ላይ ናቸው፡፡ የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት በኤሌክትሪክ ኃይል ለማስተሳሰርም በተለይ በሀገራችን ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ ይገኛል፡፡ የእነዚህ መሰል እርምጃዎች መሰረታዊ ምክንያት ልማት ማፍጠን የሚቻለው ሀገራት አቅማቸውን አሰባስበው በጋራ ሲሰሩ እንደሆነ ግንዛቤ የተያዘበት ነው፡፡ በቅርብ ከሚገኙ አጎራባች ሀገራት በንግድና ኢንቨስትመንት ካልተሳሰሩ በተነፃፃሪ ራቅ ባሉ አከባቢዎች ከሚገኙ ሀገራት የሚካሄድ የንግድ ግንኙነት ከፍተኛ ወጪዎችን መጠየቁ የግድ ነው፡፡

‹‹ስለዚህ አዲስ አበባ ከሌሎቹ የሀገሪቱ ከተሞች የተሻለ የኢኮኖሚ አቅም እና ለኢንቨስትመንት ካላት ከፍተኛ ተመራጭነት አንፃር በአከባቢው የሚገኙ የኦሮሚያ ከተሞች ተጠቃሚ ስለሚያደርጋቸው ለጋራ ተጠቃሚነታቸው የሚያጠናክር ነው፡፡ በመሆኑም ይህ የጋራ ዕቅድ እንደ ጠላት የሚታይበት ሁኔታ አሳማኝ ምክንያት አይኖረውም›› ሲሉ አቶ አሸናፊ ይሞግታሉ፡፡
የልማት ባለቤት ማነው?
ልማትም ሆነ ዴሞክራሲ ለህዝብ ሲባል የሚፈፀም፣ ከህዝብ የሚመነጭና በህዝብ ተግባራዊ የሚደረግ ነው፡፡ በህዝብ የተመረጠ መንግስት ሚናው ማስተባበርና የህዝብን ፍላጎት አደራጅቶ ማስፈፀም ነው፡፡ በመሆኑም ህዝብ የፈለገው ብቻና ብቻ ተፈፃሚ ይሆናል ማለት ነው፡፡ ከዛ ውጭ የህዝብ ወኪል የሆነው መንግስት በራሱ ፈቃድ የሚፈፅመው ተግባር አይኖርም፡፡ ልሞክር ቢልም ፈፃሚው ህዝብ ስለሆነ ያሰበውን ማሳካት አይችልም፡፡ በተለይ ዴሞክራሲን የሚከተሉ ሀገራት ዘንድ ይህ ሀቅ ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡
ምንም እንኳን የጋራ እቅዱን ሽፋን በማድረግ የተስተዋለው ሁከትና ብጥብጥ ዓላማው ሌላ ቢሆንም የኦሮሚያ ክልል ባለስልጣናት በእውነት ህዝቡ የማይሻው ከሆነ አንድ ጋት እንደማይራመዱ አሳውቀዋል፡፡ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ክቡር አቶ አባዱላ ገመዳ ከኢቢሲ ቴሌቪዠን ጋር ባደረጉት ቆይታ ይህንኑ አረጋግጠዋል፡፡ “የኦሮሚያ ህዝብ በጉዳዩ ላይ ተወያይቶና በቂ ግንዛቤ አግኝቶ ማስተር ፕላኑን አልፈልግም ይቅርብኝ ካለ ይቀራል፡፡ ከህዝብ ውሳኔ ውጭ የሚፈፀም ምንም አይነት ነገር የለም” ሲሉ ተደምጠዋል፡፡ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሙክታር ከድርም ቢሆን ያረጋገጡት ይህንኑ ነው፡፡
የኦህዴድ ፅ/ቤት ሃላፊ አቶ ዳባ ደበሌ ከአይጋ ፎረም ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ “ቀደም ሲል ኦሮሞ ነን እንኳን የምንልበት ወቅት አልነበረም፡፡ አሁን ከዛ ወጥተናል፡፡ ማንም መብቱን መጠየቅ ይችላል፡፡ በህዝብ የተመረጠው የኦሮሚያ መንግስትም የህዝብን ጥያቄ በጣም ነው የሚያከብረው” ሲሉ ተናግረዋል፡፡ ሰሞኑን ከኢቢሲ ጋር ቃለመጠይቅ ያደረጉት ጠቅላይ ሚንስትር ኃይለማርያም ደሳለኝም የኦሮሚያ ሃላፊዎችን ሃሳብ የሚያጠናክር ሃሳብ ሲናገሩ ተደምጠዋል፡፡ “የኦሮሚያ የፊንፊኔ ዙሪያ ዞንና የአዲስ አበባ የተቀናጀ የልማት ዕቅድ በረቂቅነት ያለ፤ ህዝቡ ተወያይቶበት ሊሻሻል የሚችል የህዝቡን ይሁንታን ካላገኘም እስከመቅረት የሚሄድ ዕቅድ ነው” ሲሉ አረጋግጠዋል፡፡
የሁከቱ መነሻዎችና ያስከሉት ጥፋት
ከላይ ለማየት እንደሞከርነው የማስተር ፕላኑ ዓላማዎች የህዝቦችን ተጠቃሚነትና ዕድገትን የሚያፋጥኑ ናቸው፡፡ ማስተር ፕላኑ ፊንፊኔን የማስፋፋት ዓላማ ያለው ሳይሆን በልማት በማስተሳሰር አንድ የኢኮኖሚ ማህበረሰብ ለመፍጠር የሚደረገውን ጥረት የሚያግዝ ዕቅድ ነው፡፡
ሁከቱን ከመገምገማችን በፊት አንድ ነገር በውል ልንረዳ ይገባል፡፡ ህዝቦች በየትኛውም ጉዳይ ላይ ያላቸውን ተቃውሞ መግለፅ መብታቸው እንደሆነ በህገመንግስቱ ሰፍሯል፡፡ በኦሮሚያ አንዳንድ አካባቢዎች የተስተዋለው ተቃውሞ ውል ተበጅቶለት ለነውጥ፣ ለሁከትና ለጥፋት በር እንዳይከፍት ቢደረግና ህጋዊ መልክ ቢይዝ ምንም አልነበረም፡፡
ከዛ ውጭ የኦሮሞ ህዝብ በጉዳዩ ላይ ግልፅነት እንዲያገኝ መጠየቁ ስርዓቱን ለመጠበቅ ያለውን ተነሳሽነት ነው የሚያመላክተው፡፡ የኢፌዴሪ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ፅ/ቤት ሃላፊ ሚኒስቴር ያስገነዘቡትም ይህንኑ ነው፡፡ “ከህዝቡ የሚነሳው አንዳንድ ጥያቄ ለፌዴራል ስርዓቱ ጥብቅናም ከመቆም የሚመነጭ ነው፡፡ ሆኖም ከዚህ በተቃራኒው አንዳንድ ሁከት ናፋቂ የፖለቲካ ሃይሎች ነገሩን ለፖለቲካ ትርፍ ሊጠቀሙበት ፈልገዋል” ብለዋል።
የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልል የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ፅ/ቤት ሃላፊ አቶ ፈቃዱ እንደገለፁት ከሆነም የልማት ሃሳቡ ፈፅሞውንም የኦሮሞ ማንነትን የሚዳፈር አይደለም፡፡ “በክልሉ ያሉ የገጠር ቀበሌዎችን በዚያው ክልል ካሉ አጎራባች ከተሞች ጋር በልማት ለማስተሳሰር ያለመ እንጂ ፌደራሊዝምን የሚቃረንና የክልሉን ሉዓላዊነት የሚጥስ አለመሆኑን ሁሉም ሊገነዘብ ይገባል” ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

የአዲስ አበባና ፊንፊኔ ዙሪያ ኦሮሚያ ልዩ ዞን የተቀናጀ ማስተር ፕላንን እና የክልሉን የተሻሻለው የከተሞች አዋጅን ምክንያት በማድረግ አንዳንድ አፍራሽ ተልዕኮ ያነገቡ አካላት የክልሉን ነዋሪዎች ባልተገባ መንገድ በማነሳሳት ለአመፅ እና ብጥብጥ እንደዳረጉ አቶ ፈቃዱ ይፋ አድርገዋል። እነዚህ ሀይሎች የዕቅዱ ተግባራዊ መሆን አርሶ አደሩን ያፈናቅላል፤ የባህል፣ የማንነትና የቋንቋ መደበላለቅን ይፈጥራል የሚል መልዕክት በመንዛት ሁከቱን ለማነሳሳት ተጠቅመውበታል፡፡ ለእያንዳንዱ ምክንያት ተቃርኖዎችን ማንሳት የሚቻል ቢሆንም የዚህ ፅሁፍ ዋና ዓላማ ባለመሆኑ እንለፈው፡፡ 

የሆነው ሆኖ ከላይ ለማየት እንደተቻለው ህዝቡ ላይ ስጋት የሚያሳድር ከሆነና ህዝብ የማይቀበለው ከሆነ ተግባራዊ እንደማይደረግ ተገልጿል፡፡ ሁኔታው ይህ ሆኖ ሳለ ሰነዱምረቂቅ ደረጃ እያለ በኦሮሚያ አንዳንድ አካባቢዎችተከሰተው ሁከት በጸረ ሠላም ሃይሎች የተቀነባበረ በምንም አይነት ተቀባይነት የሌለው እንደሆነ በርካቶችን ያስማማ ጉዳይ ሆኗል፡፡    
ፀረ ልማት ሀይሎች የነዙት አፍራሽ አስተሳሰብ የተወሰነውን ህዝብም ቢሆን ለጊዜው ያደናገረ ነበር፡፡ ለዚህ ችግር በምክነያትነት የሚጠቀስው ደግሞ ህዝቡ ግንዛቤ ባለማግኘቱ እንደሆነ ይነሳል፡፡ የማስተር ፕላኑን እቅድ በተመለከተ ከህዝብ ጋር በርካታ መድረኮች ቀደም ሲል ተዘጋጅተው ውይይቶች የተደረጉ ቢሆንም በቂ ናቸው ግን ተብሎ አይታሰብም፡፡ 

በአንድ መድረክ ላይ የተከበሩ አቶ አባዱላ ገመዳ ተማሪዎችን ሲያወያዩ አንድ ተማሪብዙሀኑን ተማሪ ወክዬ ጥያቄዎቹን ላቅርብ” ብሎ ተነሳ፡፡ ተማሪውም “ማስተር ፕላኑ አሁን ያገኘነውን የራስ አስተዳደር መብታችንን ያሳጣናል፡፡ በታሪካችንና በማንነታችንን አንደራደርም ኢህአዴግ ከነድክመቱም ቢሆን ኦሮሞ ለዘመናት የናፈቀውን ራስን የማስተዳደር እና በአፍ መፍቻ ቋንቋ መማርን አጎናጽፎናል፡፡ ስለዚህ ይህን መብታችንን ማስተር ፕላን እንዲደፈጠጥ አንፈልግም፤ 
ኦሮሚያ ልዩ ዞኖች በአዲስ አበባ ስር ይጠቃለላሉ ይህን ደግሞ ፈጽሞ አንፈልግምየኦሮሞ ገበሬን ሆን ብሎ የሚያፈናቅል ነው” በማለት ጥያቄዎችን አቀረበ፡፡ ክቡር መድረክ መሪውምስጋት የፈጠሩባችሁን ጥያቄዎች ማንሳታችሁ መልካም ነው፡፡ በመረጃ ላይ ተመስርተን ግን እንወያይ” አሉና ለተማሪዎች መልሰው ጥያቄዎችን ያቀርቡ ጀመር፡፡ማስተር ፕላኑ የትኛው አንቀጽ ገጽ ላይ ነው የኦሮሞን ህዝብ የራስ አስተዳደር ስለመደፍጠጥ የሚያወራው? ኦሮሚያ ልዩ ዞኖችስ በአዲስ አበባ ስር ይካተታሉ የሚለው የማስተር ፕላኑ የትኛው አንቀጽ ነው”? ብለው ጥያቄያቸውን አቀረቡና ፋታ ወሰዱ፡፡ አንዳንዱ እርስ በእርስ መተያየት ጀመረ፡፡ ቤቱ ፀጥታ ነገሰበት፡፡ አቶ አባዱላ ቀጠሉና “እነዚህ ጉዳዮች ላይ ግልጽ ውይይት ማድረግ አለብን፡፡ ማስተር ፕላኑ ይህንን የሚል ከሆነ ከኦሮሞ ህዝብ ፍላጎት ውጭ የሆነ ማስተር ፕላን ስለማያስፈልግ ዛሬውኑ ውድቅ ይሆናል” አሉና መለሱ፡፡  የተወከለው ተማሪ የተጠየቀውን እንዲህ መለሰ፡፡ “እኛ በመሰረቱ ማስተር ፕላኑንም ዝርዝሩንም መመርያውንም አላነበብነውም፡፡ እዚህ ቦታ ላይ ይህንን ይላል ብዬ በማስረጃ ማቅረብ አልችልም፡፡ ግን የምናምናቸው የኦሮሞ ምሁራን ይህንን ስላሉን አምነናቸው አጀንዳውን እያራመድን ነው’’
 
ይህ ታሪክ የሚያስገነዝበን ነገር ቢኖር ህዝቡ በአንድ ጉዳይ ላይ ግልፅነት ካላገኘ አፍራሽ አስተሳሰብ ሊሰልበው እንደሚችል ነው፡፡ ምንም እንኳን ረቂቅ ቢሆንም በማስተር ፕላኑ የተካተቱ ይዘቶችን፣ ዓላማውንና ግቦችን ይበልጥ ማስተዋወቅ ይገባ ነበር፡፡ ክልሉም ይህን ክፍተት አምኗል፡፡ የኦሮሚያ ሃላፊዎች ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ጋር ባደረጉት ቆይታ በአዲስ አበባ እና ፊንፊኔ ዙሪያ የተቀናጀ የልማት ረቂቅ አቅድ ላይ በተደራጀ መልኩ የግንዛቤ ማስጨበጥ ስራ በበቂ ሁኔታ አለመሰራቱም ህብረተሰቡ በመነሻነት ያነሳው ጥያቄ ተገቢ መሆኑን የሚያሳይ መሆኑን ጠቅሰዋል። ይህንን የግንዛቤ ክፍተት እንደ መልካም አጋጣሚ የተጠቀሙ ፀረ ሰላም ሃይሎችም ሁከቱ እንዲጫር ማድረጋቸውንና ጥቂት ወጣቶችና ተማሪዎችንም  ለአላማቸው መጠቀማቸውን ነው የገለፁት።
በክልሉ በተከሰተው ሁከት ሳቢያ የሰው ህይወት አልፏል፣ ከፍተኛ ግምት ያላቸው የህዝብና የመንግስት ንብረቶችም ወድመዋል። የፀረ ሽብር ግብረ ሀይል ባወጣው መግለጫም የሚከተለውን ነው ያለው፡፡
“ካለፈው ህዳር ወር 2008 . ጀምሮ በኦሮሚያ ክልል በሚገኙ በአንዳንድ የከፍተኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የሚገኙ ውስን ቁጥር ያላቸው የኦሮሞ ብሄር ተወላጆች የሆኑ ተማሪዎች ከፊት ለፊት የአዲስ አበባ ማስተር ፕላንን በመቃወም ከበስተጀርባ ከውጭ ዘወትር ለሀገራችን ህዝቦች ሠላምና ዕድገት እንቅፋት መሆናቸውን በገሃድ ካስመሰከሩ የሽብር ቡድኖች የሚሰጣቸውን ተልዕኮ አንግበው ከሚንቀሳቀሱ ሃይሎች ጋር ቀጥተኛ ትስስር በመፍጠር ሠላማዊ የመማር ማስተማር ሂደቱን አስተጓጉለዋል፡፡ እንዲሁም ከትምህርት መዋቅሩ ውጭሚገኘውና ከፍ ሲል ከተገለጸው የሽብር ቡድን ቀጥተኛና ቀጥተኛ ያልሆነ ግንኙነት በመፍጠር የነውጡና ረብሻው አድማስ ወደ ከተሞችና ወደተለያዩ የመንግስትና የግል ተቋማት እንዲስፋፋ በማድረግ በርካታ የመንግስት፣ የግል ባለሃብቱና የደሃው አርሶ አደር ንብረትና ሃብት እንዲወድም አድርጓል፡፡ የህብረተሰቡን ሠላምና ደህንነት ለመጠበቅ በተሠማራው የፌደራልና የኦሮሚያ ክልል ፖሊስ አባላትና ጀግናው መከላከያ ሃይላችን አባላት ላይ የሞትና የአካል መጉደል አደጋ አድርሷል፡፡

በተለያዩ አካባቢዎች የደረሰው ጥቃት ህዝብን የጎዳና ልማትን ወደኋላ የሚመልስ ነው፡፡ የልማት አውታሮችን ማውደምም በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የህዝብን ጥቅም መጉዳት ተደርጎ ይወሰዳል፡፡  ለዚህም ነው በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኘው የኦሮሚያ ህዝብና ሌላው ህብረተሰብ ክስተቱን ያወገዘው፡፡
ማስተር ፕላኑ ወይስ ሌላ…
ከማስተር ፕላኑ ጋር ተያይዞ የተነሳው ምክንያት በምክንያትነት እንዳይጠቀስ የሚያደርገው ምላሽ ከመንግስት እስከተሰጠ ድረስ ሁከቱ መልኩን እየቀየረ ለምን ቀጠለ? የሚለው ጥያቄ በሁላችንም ዘንድ መጫሩ አይቀሬ ነው፡፡ መልሱ እጅግ ቀላል ነው፡፡ በእኔ እይታ አጀንዳው የህዝብ አይደለም ነው ምላሹ፡፡
ህዝብ የመልማትና የመለወጥ ፍላጎት አለው፡፡ ባለፉት 24 ዓመታት ያደረገው ሁሉን አቀፍ እንቅስቃሴ ለዚህ ዋቢ ምስክር ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ህዝብ በተለወጠ፣ ድህነት በከሰመ፣ አንድነታችን በተጠናከረና ገፅታችን ይበልጥ በተቀየረ መጠን እየከሰሙ የሚሄዱ ሀይሎች አሉ፡፡ እነዚህ ሀይሎች የጠባብ፣ ትምክህትና ኪራይ ሰብሳቢ ሀይሎች ናቸው፡፡ የሁከቱ ባለቤቶችና አንቀሳቃሾችም እነዚህ ሀይሎች ናቸው፡፡ አጀንዳውም የእነርሱ ነው፡፡ የተወሰኑ የጠባብ ሀይሎች ከአሜሪካ ድምፅ ራዲዮ ጋር ባደረጉት ቆይታ መጀመሪያም የተነሱለትን ዋና ፍላጎታቸውን አፍረጥርጠው ተናግረዋል፡፡ “ኢህአዴግ ስልጣን ያጋራን” ሲሉ አፋቸውን ሞልተው ተናግረዋል፡፡ የህዝብ ወገንተኝነት የሚሰማቸው ሀይሎች ቢሆኑ ስልጣን የሚሰጠው ከህዝብ እንጂ ከማንም እንዳልሆነ በተረዱ ነበር፡፡ ከዚህ አባባላቸው የምንረዳውም ነገር ቢኖር የህዝብን ጥቅም ማስከበር ሳይሆን የግል የስልጣን ጥማታቸውን በህዝብ ደም ማሳካት ነው፡፡ 

የማይስማሙ ጋብቻዎች

የሰሞኑን ጋብቻ
ያለአቻ ጋብቻ!
መርህ የለሽ ጡንቻ
የሻዕቢያ ኮረቻ፣
የግብፅ ቃልቻ
የትም ፍጭው ዱቄቱን በስልቻ፣
ፀንቶ የሚቆየው ለሳምንታት ብቻ

ይህ ከፌስቡክ ገፅ የተገኘ ግጥም ሰሞኑን በኦሮሚያ አንዳንድ ከተሞችና በትምህርት ተቋማት የተከሰተው ሁከት ሁሌም ውሻው እስኪቀደው ድረስ የሚጠባበቁ ጅቦች የተሰባሰቡበትን መድረክ አጉልቶ ስለሚያሳይልኝ ተጠቅሜዋለሁ፡፡ በዚህ መድረክ ላይ ጠባቡም፣ ትምክህቱም ሀይማኖትን በሽፋንነት የሚጠቀሙ ፅንፈኞችና ሌሎች ኪራይ ሰብሳቢ ሀይሎች ሲራኮቱበት ታይተዋል፡፡ የሁሉም ማሊያና ግብ ለየቅል ቢሆንም ለጊዜውም ቢሆን ሜዳው ላይ በሚፈልጉት ልክ ተሰልፈዋል፡፡ ጠባቡና ትምክህቱ የሚያራምደውን አቋም እንኳን ካየን መቼውንም የሚገናኝ አይደለም፡፡ ባጭሩ ሆድና ጀርባ ነው፡፡ ሆኖም የትምክህት ሀይሉ ክስተቱን እንደ መልካም አጋጣሚ ለመጠቀም ሲተጋ ተስተውሏል፡፡ አዛኝ ቅቤ አንጓች ለመሆን ጥሯል፡፡ ትምክህተኛው ግንቦት ሰባት “………..አብረን ወያኔን እንጣለው!!!......” በማለት የኦነግን ጠባብ ቡድን ሲለማመጥ ትዝብት ውስጥ ወድቋል፡፡

ሁለት እግር አለኝ ተብሎ ሁለት ዛፍ ለመውጣት እንደማይቻል ቢያውቁትም ባልበላውም ልፈሰው፤ ባልጠጣውም ላፍስሰው አይነት አካሄድ ሰሄዱ እየተመለከትን ነው፡፡ ትላንት "ያንተ ከተማ ነው" "ሌላ ብሔር ሊኖርበት አይገባም" የተባለው ህዝብ አሁን ደግሞ "አዲስ አበባ የተባለ ጭራቅ ባዕድ መጣብህ ተነስና ጦር ምዘዝበት" የሚሉ ተቃራኒ አጀንዳዎች እያስተጋቡ ነው፡፡ አቶ አሸናፊ የነዚህን ሀይሎች ሴራ ሲያጋልጡ ተልዕኳቸው የህዝብን ጥቅም ማስጠበቅ ሳይሆን በምርጫ ያልተሳከላቸው የሚጠቀሙት ሰበብ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል” ይላሉ፡፡


በቀጣይ ከህዝብና ከመንግስት ምን ይጠበቃል?
የትኛውም የልማት፣ የዴሞክራሲና የመልካም አስተዳደር ስራ በህዝብና በመንግስት የተባበረ ክንድ የሚፈፀም ነው፡፡ በአሁኑ ወቅትም የተከሰተውን ሁከት በማረጋጋት ወደ ልማት ስራችን በተሟላ አቅም ለመግባት ከህዝብም ሆነ ከመንግስት ብዙ ይጠበቃል፡፡

መንግስት የጀመረውን በማስተር ፕላኑ ዙሪያ ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራ አጠናክሮ መቀጠል ይገባዋል፡፡ ሁከት በማነሳሳት ህዝብን የሚረብሹትንና የህዝቡን ልማት የሚያደናቅፉ ሀይሎችን ህብረተሰቡን አሳትፎ ማጋለጥና የማያዳግም እርምጃ በቁርጠኝነት መውሰድ ይጠበቅበታል፡፡ በየጊዜው ያሉ ለውጦችንም በወቅቱ ለማሳወቅ በመድረኮችም ሆነ በሚዲያዎች ከህዝቡ ጋር ሊገናኝ ይገባዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የመልካም አስተዳደር ችግሮች እንዲቀረፉ፣ የዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ እንዲጎለብትና ድህነት እንዲከስም ጠንክሮ መስራት የቀጣይ ወሳኝ ስራው ይሆናል፡፡ አቶ ዳባ እንደተናገሩት ከሆነ በገጠርም በከተማም ያለው የኦሮሞ ህዝብ አሁን ላይ እንደ ሃገር እየተቀጣጠለ ባለ ልማትና እድገት ተጠቃሚ መሆን መጀመሩ ማንም የማይክደው ነው። “ይሁንና  ከዚህ እየተቀጣጠለ ባለ ኢኮኖሚያዊ ልማት በሰፊው እንዳይጠቀም ደንቃራ የሆኑበት ችግሮች ተጠራርገው እንዲወገዱለት የክልሉ ህዝብ በተደጋጋሚ እያነሳ ይገኛል” ሲሉ አስታውሰዋል። ይህን ታሳቢ በማድረግም የክልሉ መንግስት የመልካም አስተዳደር ችግርን ለመፍታት እንቅስቃሴ መጀመሩን ነው የተናገሩት።

ሁልጊዜም ቢሆን ድህነትና ኋላቀርነት እንዲሁም ብልሹ አሰራሮች የሁከትና ብጥብጥ እርሾዎች ናቸው፡፡ በመሆኑም ክልሉ የጀመረውን የፀረ ድህነትና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን የማስወገድ ትግል አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል፡፡ ህዝቡም በበኩሉ የሚጠበቅበትን ሊወጣ ይገባል፡፡ በእርግጥም  ኦሮሚያ የሚገኙ ነዋሪዎች በተለያዩ አካባቢዎች የተነሱ ሁከትና ብጥብጦችን በማውገዝ ላይ ይገኛሉ፡፡ ይህንን ሁኔታ ግን አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል፡፡ የተጎናፀፈውን ሰላም፣ ዴሞክራሲና ልማት ለማደናቀፍ የሚሹ ሀይሎችን ከመንግስት ጎን ቆሞ ሊታገላቸው ይገባል፡፡ አቶ አባዱላ ህዝቡ በምን አግባብ ጥቅሙን አስጠብቆ ሊቀጥል እንደሚችል ሲያስረዱ "ሕብረተሰቡ የትኛውንም አይነት የልማት ጥያቄ ለመረጠው መንግሥት የማቅረብ መብቱን እየተጠቀመ ልማቱን የሚያደናቅፉ ኃይሎችን በመከላከሉ በኩል ያለውን የቆየ ልምድ የበለጠ ሊጠቀምበት ይገባል" ብለዋል፡፡ ጠቅላይ ሚንስትር ኃይለማርያም በበኩላቸው መንግስት ከህብረተሰቡ ጋር ሆኖ ሁከት የተከሰተባቸው አካባቢዎችን የማረጋጋት ስራውን እንደሚያጠናክርና በጥፋተኞች ላይም የማያዳግም እርምጃ እንደሚወስድም አረጋግጠዋል፡፡
በተለይ በውል ባልተረዳው ሀሳብ ለጥፋት እየተማገደ ያለው ወጣት በሰከነ ሁኔታ ማሰብ ይኖርበታል፡፡ ይህንን ነውጥ ከውጭ ሆነው እያቀጣጠሉ ያሉ ወገኖች በመቃወማቸው ብቻ ጥቅምን የሚያገኙ፣ የሌላ ሀገር ዜግነትን ያገኙና በጨለምተኝነት የተነሳሱ እንደሆነ መረዳት ያስፈልጋል፡፡  እናራምደዋለን ለሚሉት ሀሳብም መስዋዕትነት ከመክፈል ይልቅ በድሃውና በታዳጊው ደም ወደ ስልጣን ለመውጣት የቋመጡ ናቸው፡፡ የትኛውንም ጥያቄ ለመንግስት በማቅረብ ተገቢ የሆነ ምላሽ ማግኘት የሚቻልበት ሁኔታ ሁሌም ቢሆን ክፍት እስከሆነ ድረስ በሰላማዊና በሰከነ ሁኔታ ማቅረብ ብቸኛ አማራጫችን ሊሆን ይገባል፡፡ አፍራሽ አስተሳሰብ ሰንቀው ወደ ህብረተሰቡ በመንዛት ሰለማችንን ለማደፍረስ ልማታችንን ለማደናቀፍ እረፍት ያጡ ፀረ ህዝብ ሃይሎችን በቃችሁ!! አቁሙ!! ልንላቸው ይገባል፡፡

1 comment: