EPRDF is a ruling party committed to realize Ethiopia's Renaissance.

Sunday, 10 May 2015

ስኬታማው የጤና ፖሊሲያችንና አተገባበሩ


ኢህአዴግ የተከተለው መከላከል ላይ የተመሰረተው የጤና ፖሊሲ የህዝብን ተጠቃሚነት ያረጋገጡ ከፍተኛ ስኬቶች ተመዝግበውበታል!!
የተከበራችሁ የአገራችን ህዝቦች፣
ኢህአዴግ ባለፉት ሁለት አሰርት አመታት የነደፈውን መከላከልን መሰረት ያደረገ የጤና ፖሊሲ ከመላ የአገራችን ህዝቦች ጋር በመሆን ተግባራዊ በማድረግ በጤናው ዘርፍ የነበሩትን ስር የሰደዱ ዘርፈ ብዙ ችግሮች ደረጃ በደረጃ በመቅረፍ እመርታዊ ስኬቶችን አስመዝግቧል፡፡ የህዝባችንን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ከጊዜ ወደ ጊዜ በማሳደግ በአገራችን ፍትሃዊ የጤና ተደራሽነትን ያረጋገጡ ተጨባጭ ስኬቶች ተመዝግበዋል።
እንደሚታወቀው አገራችን ኢትዮጵያ ከ1983 ዓ.ም በፊት በግልና በአካባቢ ጤና ጉድለት፤ በተላላፊ በሽታዎች ምክንያት ዜጎቿ በህመም ሲማቅቁባትና በሞት ሲቀጠፉባት ነበር። የጤና አገልግሎቱ በጣም ዝቅተኛና በአፍሪካ የመጨረሻው ጭራ ላይ የሚገኝ ነበር፡፡ በወቅቱ  የነበሩ የጤና ተቋማት ቁጥራቸው እጅግ አነስተኛ ከመሆናቸውም በላይ የነበሩትም በዋና ዋና ከተሞች አካባቢ የታጠሩ ስለነበር ሰፊውንና ድሃውን የገጠርና የከተማ ህዝብ ተጠቃሚ የሚያደርጉበት ሁኔታ አልነበረም፡፡
ኢህአዴግ የጤና ፖሊሲውን ሲቀርጽ ዋነኛ መነሻው የጤና ዘርፉን መሰረታዊ ችግር በመቅረፍ የአገራችንን ዜጎች ጤንነት ማስጠበቅ ላይ ያተኮረ ነበር፡፡ አብዛኛዎቹ ህዝቡን ለህመምና ሞት ሲዳርጉት የነበሩ በሽታዎች በመከላከል ሊወገዱ የሚችሉ በመሆናቸው ኢህአዴግ የተከተለው የጤና ፖሊሲ በሽታን መከላከልን ማእከል አድርጓል፡፡ መከላከልን ማእከል ያደረገው የጤና ፖሊሲያችን ለህክምናም አስፈላጊውን ትኩረት የሰጠ ነው፡፡ 
ኢህአዴግ ላለፉት ሁለት አሰርት ዓመታት በሽታን በመከላከል ላይ ባተኮረ ፕሮግራምና ፖሊሲው አማካኝነት ጤናማና አምራች ዜጋ ማፍራትን ዋነኛ ግቡ አድርጎ መጠነ ሰፊ ስራዎችን በማከናወኑ ዘርፈ ብዙ ስኬቶች ተመዝግበዋል። በሂደቱም ህዝባዊ ንቅናቄን በመፍጠር ለረጅም ጊዜ ሰፍኖ የቆየውን ኋላቀር አመለካከት፣ አሰራርና አደረጃጀት በትክክለኛ ፖሊሲና አደረጃጀት በመቀየር ህብረተሰቡን የመከላከሉ ስራ ባለቤትና ግንባር ቀደም ተዋናይ አድርጓል። ከግለሰብ ጀምሮ በቤተሰብና ማህበረሰብ ብሎም በአገር አቀፍ ደረጃ ስኬታማ ተግባራትን አስመዝገቧል።
በጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራማችን የገጠሩና የከተማው ህዝብ በበሽታዎች ተጠቂ እንዳይሆን ከህብረተሰቡ የተውጣጡ የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎችን በማሰልጠንና የአመለካከትና ግንዛቤ ስልጠናዎች እንዲስፋፉ በማድረግ ውጤታማ ስራ ተሰርቷል፡፡ ይህም ህብረተሰቡ በቀላሉ ሊከላከላቸው በሚችላቸው በሽታዎች ተጋላጭ እንዳይሆን በማድረግ ከፍተኛ ጠቀሜታ አስገኝቷል።
ተላላፊ በሽታዎችን ለመከላከል የሚያስችል ስራ ትኩረት ተሰጥቶት በመሰራቱ ተጨባጭ ስኬቶች ተመዝግበዋል፡፡ አምራቹን ኃይል ከምርት ተግባሩ እንዲፈናቀልና የአልጋ ቁራኛ እንዲሆን ሲያደርግ የነበረውን የወባ በሽታ ስርጭት በመግታትም ተጨባጭ ውጤት ተገኝቷል። በወባማ ቦታዎች የወባ ትንኝ የሚያራቡ ቆሻሻዎችን በህብረተሰብ አቀፍ የተቀናጀ አገልግሎት በማስወገድ፣ እርጥበታማ ቦታዎችን በማድረቅና በቂ አጎበር በማቅረብ ውጤታማ ተግባር ተከናውኗል። ይህም በወባ ምክንያት የሚከሰተው ሞት በ1983 ዓ.ም ከነበረበት አንፃር ሲለካ በ73 በመቶ የቀነሰው ሲሆን በወባ በሽታ ሳቢያ ተኝተው የሚታከሙ ህሙማን ቁጥርም በ83 በመቶ  ሊቀንስ ችሏል፡፡
ኢህአዴግ ኤች አይቪ ኤድስን ለመከላከልና ለመቆጣጠር አገራዊ የንቅናቄ ስትራቴጂ ነድፎ በመንቀሳቀሱ ውጤታማ ተግባር አከናውኗል፡፡ በአስተሳሰብና አመለካከት ዙሪያ ከተሰራው ወሳኝ ተግባራት ባሻገር የታመሙ ወገኖች የፀረ- ኤች አይቪ ኤድስ መድሓኒቶችን በነፃ የሚያገኙበት ሁኔታ ተመቻችቶላቸዋል። በአጠቃላይ በህዝብ ንቅናቄ በተሰራው ስራ በኤች አይ ቪ አዲስ የሚያዙ ሰዎችን ቁጥር በ90 በመቶ መቀነስ የተቻለ ሲሆን በኤች አይ ቪ ምክንያት የሚከሰት ሞት ደግሞ ከ50 በመቶ በላይ ለመቀነስ ተችሏልበሽታ መከላከልን ማእከል ያደረገው የጤና ፖሊሲያችን የህጻናትና የእናቶችን ሞት በመቀነስም ስኬቶች የተመዘገቡበት ነው፡፡ ዕድሜያቸው ከ5 ዓመት በታች የሆናቸውን ህፃናት ሞት በ1983 ከነበረበት ስሌት ከ67 በመቶ በላይ በመቀነስ የዕቅድ ጊዜው ከመጠናቀቁ  ቀድሞ ለማሳካት የተቻለ ሲሆን የእናቶችን ሞት በ69 በመቶ በመቀነስ መልካም ለውጥ ተመዝግቧል፡፡
እነዚህ በጤናው መስክ የተመዘገቡ ውጤቶች ህዝባችንንና አገራችንን ተጠቃሚ ከማድረጋቸው በተጨማሪ ኢትዮጵያን በዓለም አቀፍ መድረኮች ከፍ ያደረጉና እውቅና ያሰጡ ናቸው። ኢትዮጵያ በዘርፉ ባገኘቻችው እውቅናዎችና ሽልማቶች በፖሊሲ አቅጣጫዋ ስኬት ብዙዎች የአገራችንን ሞዴል ለመከተል እንዲነሳሱ አስችላለች።
በኢህአዴግ አመራር ለህዝቡ የጤና አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ የጤና ተቋማትን በማስፋፋትና የጤና ባለሙያዎችን በማፍራት የተሰራው ስራ እመርታዊ ለውጥ የተመዘገበበት ነው፡፡ በአገራችን በ1983 ዓ.ም የነበሩትን 72 ሆስፒታሎች በአራት እጥፍ በማሳደግ 311 አድርሰናል፤ በዚሁ ወቅት የነበሩትን 153 ጤና ጣቢያዎችንም ከሃያ ሁለት እጥፍ በላይ በማሳደግ 3 ሺህ 541 ማድረስ ችለናል። ከ16ሺ251 በላይ የጤና ኬላ ግንባታም ተካሂዶ አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛሉ። በህክምና ተቋማት ማስፋፋቱ ላይ ከመንግስት በተጨማሪ የግል ባለሃብቱ የሚሳተፍበት ምቹ ሁኔታ በመፈጠሩ በግል ባለሃብቶች የተቋቋሙ የህክምና ተቋማት በርካታ ናቸው።
በ1983ዓ.ም 3 ብቻ የነበረዉ የጤና ባሙያዎች ማሰልጠኛ ተቋማትና ዩኒቨርስቲዎች ቁጥር በአሁኑ ወቅት ወደ 30 ደርሷል፡፡ በመሆኑም በየዓመቱ ከ23ሺህ ባለይ የጤና ሙያ ሰልጣኞች ቅበላ የሚደረግ ሲሆን ከነዚህ ዉስጥም 3560ዎቹ የህክምና ዶክተሬት ተማሪዎች ናቸዉ። በዚህም መሰረት በየዓመቱ ከ16ሺህ በላይ ባለሙያዎች እየተመረቁ ወደ ስራ በመስማራት ላይ ናቸዉ። ከ10 ዓመታት በፊት ከ150 የማይበልጥ የነበረዉ የህክምና ዶክተሮች ምረቃና ወደ ስራ የማሰማራት ቁጥር በዚህ ዓመት ብቻ የተመረቁ ሃኪሞች ቁጥር 1257 ማድረስ ተችሏል፡፡ የዚህ ድምር ውጤት የጤና ባለሙያዎችን ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ አሳድጎታል።
በአጠቃላይ የጤና አገልግሎትን ለማስፋፋትና ለህዝቡ ተደራሽ ለማድረግ በተሰራው ስራ እጅግ ዝቅተኛ የነበረውን የመሰረታዊ ጤና አገልግሎት ሽፋን አሁን 100 ፐርሰንት ማድረስ ተችሏል። የዜጎች አማካይ በሕይወት የመኖር ዕድሜም ከ45 ወደ 64 አመት ከፍ እንዲል የጤና አገልግሎት መሻሻሉ ከፍተኛዉን ድርሻ አበርክቷል፡፡።
ኢህአዴግ ከጤና ተቋማት ግንባታና ማስፋፋት እንዲሁም ከጤና ባለሙያዎች ስልጠና ጎን ለጎን የመድሃኒትና የህክምና መገልገያዎች አቅርቦትን የማሻሻል፣ የጤናና ጤና ነክ ግብአቶች ቁጥጥር፣ በዘርፉ የቴክኖሎጂ ሽግግር የማምጣትና የህብረተሰቡን የጤና ችግሮች ለመፍታት የሚካሄዱ የምርምር ሥራዎች አጠናክሮ የማስቀጠል ተግባሮችን ፈፅሟል። ሁሉም በጤናው ዘርፍ የተመዘገቡ ስኬቶች መላ የአገራችን ህዝቦች ባደረጋችሁት ርብርብ የተገኘ እንደሆነ ኢህአዴግ ይገነዘባል፡፡ ህዝባቸውን በሙያቸው በማገልገል ላይ የሚገኙ የጤና ባለሙያዎች እያበረከቱት ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑም ኢህአዴግ እውቅና ይሰጠዋል፡፡
ባለፉት ሁለት አሰርት አመታት በጤናው የተመዘገቡ ስኬቶች ከፍተኛ ቢሆንም ሊፈቱ የሚገባቸው ችግሮች እንዳሉም ኢህአዴግ ተገንዝቦ የመፍትሄ አቅጣጫዎችን አስቀምጦ በመንቀሳቀስ ላይ ነው፡፡ አሁንም የጤና አገልግሎቱ ጥራትና ፍትሃዊነት በከፍተኛ ሁኔታ መሻሻል አለበት፡፡ የሰው ሃይል ፍላጎትን ለሟሟላት የተደረገው ጥረት እንደተጠበቀ ሆኖ አሁንም የሰው ሃይል ስብጥር፣ የሞያ ብቃት፣ የማትጊያ ስርዓትና ውጤታማነት ላይ ክፍተቶች ይታያሉ፡፡ እንዲሁም የጤናው ዘርፍ የሚያስፈልጉትን የመድሀኒት፣ ህክምና መገልገያ መሳሪያዎችና ሌሎች ግብዓቶችን ያለማቋረጥ የማቅረብና የጥራት ደረጃቸውን አስተማማኝ የማድረግ መጠነ ሰፊ ስራ መሰራት እንዳለበት በማመን ሰፊ ስራ እየሰራ ይገኛል፡፡ በጤናዉ ዘርፍ የሚታዩ የመልካም አስተዳደር ችግሮችና በአገልግሎት አሰጣጥ ዙሪያ ከህብረተሰቡ የሚነሱ ቅሬታዎችን ለመፍታትም የተቀናጀ የመልካም አስተዳደር ዕቅድ ተዘጋጅቶ በየደረጃው ተግባራዊ በመደረግ ላይ ነው፡፡
በአንጻሩ የአገራችን ተቃዋሚዎች እንደ ሌሎች ልማቶች ሁሉ በጤና ዘርፍ ያስመዘገብናቸው ስኬቶችን ጥላሸት መቀባታቸውን ቀጥለዋል፡፡ አንዳንዶቹ መከላከልን ማእከል ያደረገውን ፖሊሲም ሲቃወሙ ይታያሉ፡፡ አማራጭ ብለው የሚያቀርቡትም ለጥቂቶች ብቻ አገልግሎት የሚሰጡ የጤና ተቋማትን መገንባት ላይ ያተኮረ ነው፡፡ ይህ አማራጭ ደግሞ አብዛኛውን ህዝብ የበይ ተመልካች የሚያደርግ ህዝባዊ ውግንና የሌለው እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡
ምንጊዜም ለአብዛኛው ህዝብ ተጠቃሚነት ቅድሚያ የሚሰጠው ኢህአዴግ የተከተለው ፖሊሲ ግን በተጨባጭ የህዝብ ተጠቃሚነትን እያረጋገጠ ይገኛል፡፡ የእስካሁን ስኬቶችን በማጠናከርና የሚታዩ ችግሮችን በመቅረፍ ኢሕአዴግ አሁንም ሊያገለግላችሁ ተዘጋጅቷል፡፡ 
ለህዝብ ተጠቃሚነትና ቀጣይነት ላለው ለውጥ ኢህአዴግን ይምረጡ!!
ምልክታችን ጣፋጩን ማር የምታመርተው ታታሪዋ ንብ ነች!!

No comments:

Post a Comment