የሊብራሊዝም
የፖለቲካል ኢኮኖሚ አስተሳሰብ በበለፀጉት አገሮች ከኢንዱስትሪ አብዮት በፊት እንደጀመረና በአብዮቱ ሂደት አስተሳሰቡ እየጠነከረ
እንደመጣም ይገለፃል፡፡ የሊብራሊዝም አስተሳሰብ በበለፀጉት አገራት እየተስፋፋ የሄደ ቢሆንም አገራቱ በየጊዜው ለሚገጥሟቸው የኢኮኖሚ
ቀውስ መፍትሄ ማምጣት ሳይችል በመቅረቱ የአስተሳሰቡ አራማጆችና ባለቤቶች እይታቸውን ጭምር ለማስተካከል የተገደዱበት ሁኔታ ተፈጥሮ
ነበር፡፡ የኋላ ኋላ ደግሞ ከሊበራሊዝም ክስረት በመነሳት ከሁለተኛው የአለም ጦርነት በኋላ የሶሻል ዲሞክራሲና የዌልፌር ስቴት አስተሳሰቦች
በበለፀጉት አገሮች የበላይነቱን ተቆናጠጡ፡፡ ይህ አስተሳሰብም በወቅቱ በአውሮፓውያን ዘንድ ቀላል የማይባል የኢኮኖሚ ለውጥ በማምጣት
ፈጣን እድገት እንዲያስመዘግቡ አስችሏቸዋል፡፡
ይሁን
እንጂ የሶሻል ዴሞክራሲና እና የዌልፌር ስቴት አስተሳሰብም ቢሆን ችግር ሳይገጥማቸው አልቀረም፡፡ እናም ከ1970ዎቹ አጋማሽ ጀምሮ
የአገራቱ የኢኮኖሚ እድገት እየቀነሰ ሄዶ በቀውስ የሚናጥበት ሁኔታ ተፈጠረ፡፡ ከዚህ ቀውስ ጋር በተያያዘ ነው እንግዲህ አዲሱ የሊበራሊዝም
አስተሳሰብ ማገገም የጀመረው፡፡ ይህ አዲሱ ሊበራሊዝም ወይም የኒዮሊበራሊዝም አስተሳሰብ ከነባሩ ጋር የሚጋራው ባህሪያት ቢኖሩትም
የመንግስት ጣልቃ ገብነትን ፍፁም በሆነ ሁኔታ የሚከላከል ሆኖ ነው የመጣው፡፡ መንግስት በኢኮኖሚው ውስጥ ሊኖረው የሚገባው ድርሻ
ህግና ስርዓትን በማስጠበቅ የዘበኝነት ሚና ብቻ እንደሆነ ያስቀምጣል። አስተሳሰቡም በተለይ በእንግሊዝና በአሜሪካ እየገነገነና እየተጠናከረ
መሄድ ችሏል፡፡ የእነዚህ አገራት የኢኮኖሚ ገናናነት ደግሞ ይህንን አስተሳሰብ ወደ ሌሎች አገራት በቀላሉ ለማስፋፋት የሚያስችለው
ዕድል አገኘና በ1980ዎቹ አካባቢ ባልበለፀጉ አገራትም ጭምር መስፋፋት ችሏል፡፡
ኒዮ-ሊበራሊዝም
ባልበለፀጉት አገራት የተስፋፋው በራሱ ልዕልና ሳይሆን በተዘዋዋሪ መንገድ በሚገለፅ ተጽእኖ ነበር። ድሃ አገራት ከገቡበት የኢኮኖሚ
ቀውስ ለመላቀቅ የበለፀጉ አገራትን ድጋፍ የሚፈልጉበት አስቸጋሪ ሁኔታ በመፈጠሩ እጃቸውን ወደእነዚህ አገራት መዘርጋታቸው አልቀረም፡፡
የበለፀጉ አገራት ደግሞ እጅ ለመጠምዘዝ የሚጠቀሙባቸው የአለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅትና የዓለም ባንክ ድጋፋቸውን ከቅድመ ሁኔታ
ጋር በማድረግ የኒዮ-ሊበራሊዝም አስተሳሰብን ለማስፋፋት አጋጣሚውን ሁሉ ተጠቅመዋል፡፡ የእነዚህን ተቋማት እርዳታ የሚፈልጉ ማናቸውም
አካላት ፈለጉም አልፈለጉም በግድ በኒዮ-ሊበራሊዝም የተቀየሱ ፖሊሲዎችን እንዲተገብሩ በማድረግ የእጅ አዙር ተጽእኗቸውን ለማሳረፍ
ችለዋል፡፡
በተለይ
በ1980ዎቹ አካባቢ የአፍሪካ አገራት ላጋጠማቸው የኢኮኖሚ ቀውስ የበለፀጉት አገራት ያገዙበት መንገድ አፍሪካውያን በራሳቸው መንገድ
ከችግሮቻቸው እንዲላቀቁ ሳይሆን እርዳታቸውን ስፍር ቁጥር በሌላቸው ቅድመ ሁኔታዎች በማጀብ የራሳቸውን አጀንዳ ለማሳካት ነበር የተረባረቡት፡፡
ይባስ ብለውም በእነሱ ሳንባ የሚተነፍስና በእነሱ የተበጣጠሰ ምጽዋት ብቻ የሚቆም ነፃነት አልባ ኢኮኖሚ እንዲፈጠር አድርገዋል፡፡
አፍሪካ በሞግዚትነት የሚያስተዳድሯት አህጉር እንድትሆንም እኩይ መረባቸውን ለመዘርጋት ሳይታክቱ ሰርተዋል፡፡ በዚህም ምክንያት የኒዮ-ሊበራሊዝምን
አስተሳሰብ ያለምንም መገዳደር በአፍሪካ ላይ በቀላሉ መጫን ችለዋል፡፡
ከ1990ዎቹ
ጀምሮ የአፍሪካ ኢኮኖሚዋ ብቻ ሳይሆን የፖለቲካ ስርዓቷም በኒዮ- ሊበራሊዝም አስተሳሰብ የተቃኘ ሆነ፡፡ የበለፀጉ አገራት የአፍሪካን
የውስጥ ፖለቲካል ኢኮኖሚ ለመቆጣጠር በገንዘብ አቅማቸው የፈረጠሙ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን (መያዶች) በአፍሪካውያን ዘንድ
እንደ አሸን በማፍላት የእጅ አዙር ማስተዳደራቸውን ቀጠሉ፡፡ በምርጫ ሂደት ላይ እንኳን ፈላጭ ቆራጭ ሆነው በመቅረብ የምርጫ ሂደቱን
ትክክለኛነት ለማረጋገጥ የእነሱ በታዛቢነት መገኘት ግድ መሆን ጀመረ፡፡ እነዚህ እንደ አሸን የፈሉት መያዶች ደግሞ በአገር ውስጥ
ያለውን ነባራዊ ሁኔታ በማጤንና ገንዘባቸውን በመጠቀም የእነሱ አጀንዳ ተሸካሚ ኪራይ ሰብሳቢ ሀይል በማሰባሰብ የአገር ውስጥ ፖለቲካል
ኢኮኖሚ አካሄድን እነሱ በሚመቻቸው ልክ ለማሽከርከር ሲጥሩ ተስተውለዋል፡፡
ይህ የኢኮኖሚ
እና የፖለቲካ ተፅዕኖ ታዲያ አፍሪካን ወደ ባሰ ማጥ ውስጥ ከመጨመር የዘለለ ይህ ነው የሚባል ጠቀሜታ ማረጋገጥ አላስቻለም፡፡ አፍሪካ
በበለፀጉ አገራት ላይ ያላት ጥገኝነትም በከፋ ሁኔታ ተባባሰ፡፡ የኢኮኖሚ
ቀውሱም ከድጡ ወደ ማጡ ሆነ፡፡ ገና በእንጭጭ ደረጃ ላይ የነበሩት ኢንዱስትሪዎች በመመናመናቸው አፍሪካ በመሰረቱ መለወጥ አልቻለችም፡፡
የኒዮ-ሊበራል
ሀይሉ የራሱን አስተሳሰብ በሉአላዊ ሀገራት ላይ በመጫን የፖለቲካል ኢኮኖሚ ስርዓቱን በፈለገው መስመር ለማስኬድ እንዲመቸው መያዶችን
ብቻ ሳይሆን በየሀገራቱ ያሉ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን ይጠቀማል። በራሳቸው ልክ የሰፏቸውን የእነሱን ርዕዮት የሚያቀነቅኑ ፖለቲካ ፓርቲዎችን
ያለማመንታት በመደገፍ በአገር ውስጥ አለመረጋጋት እንዲፈጠር የሚቻላቸውን ሁሉ ከማድረግ አይመለሱም፡፡ የኒዮ ሊበራል አስተሳሰብን
ሳይቀበል በራሱ መንገድ ለመንቀሳቀስ የሚፍጨረጨር እና ከእነሱ በተቃራኒ የሚቆም ሀገር በእነዚህ ታዛዥ ተቃዋሚዎች አማካኝነት የትችት
ናዳ ይወርድበታል፡፡ ፀረ ዴሞክራትና አምባገነን፣ የሰብአዊ መብት ረገጣ የሚደረግበት፣ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ የማይካሄድበት፤ ወዘተ…
የመሳሰሉ በርካታ ስያሜዎች በመስጠት ያለመታከት የስም ማጥፋት ዘመቻ ይካሄድበታል፡፡
ኒዮ ሊበራሊዝም
በእነዚህ ሁሉ ጫናዎች የፈለገውን ማግኘት ካልቻለ የቀለም አብዮት ለማካሄድ እስከመንቀሳቀስ ይደርሳል፡፡ የእሱ አጀንዳ ተሸካሚ የሆኑ
የአገር ውስጥ ፖለቲከኞችም ጥቃቅን ችግሮችን ነቅሶ በማውጣትና የተዛባ ስዕል በማስያዝ ሁከት እንዲፈጠር በቁርኝት ሲሰሩ ይስተዋላል፡፡
በአገራችንም በህዝብና መንግስት ጠንካራ ትብብር እየከሸፈ ቢሆንም ይህ ሀይል እኩይ ተግባሩን ከማራመድ አልቦዘነም፡፡
በአገራችን
የኒዮ-ሊበራል ሀይሉ አጀንዳ ከመሸከም ውጭ በራሳቸው አጀንዳ ላይ ለቅፅበትም ቢሆን መቆም የማይችሉት አንዳንድ ጽንፈኛ የተቃዋሚ
ፖለቲካ ፓርቲዎች የኒዮ-ሊበራል ሀይሉ ተላላኪዎች ናቸው ሲባልም ከእውነተኛ ማንነታቸው በመነሳት ነው። የእነዚህ አፍራሽ ሃይሎች
እንቅስቃሴ በተጨባጭ እየታዩ ያሉ ለውጦችን ከመካድና እንዳልተፈጠሩ ከመቁጠር ነው የሚጀምረው፡፡ በሀሰት ፕሮፓጋንዳ ያልሆነውን ሆነ፣
በትክክል ለሆነው ደግሞ አፍራሽ የሆነ መልእክት በመለጠፍና ወደ ህዝቡ በመርጨት ህዝብ በመንግስት ላይ እንዲነሳሳ ፀረ ልማትና ፀረ
ህዝብ የሆነ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ ይስተዋላሉ፡፡ ይህ ጫፍ የወጣ ጨለምተኝነታቸውን ደግሞ ሕገ መንግስቱንና ሕገ መንግስታዊ ስርዓቱን
በመቃወምና ባለመቀበል ይገልፁታል። ህግና ስርዓትን አለማክበር ደግሞ መለያቸው እየሆነ መጥቷል፡፡ ለህገ ወጦች ሽፋን መስጠትም የእለት
ተለት ስራቸው ነው፡፡
በአንድ
ወቅት የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማሕበራት አዋጅ በተለይ ደግሞ በአስተዳደር ወጪ እየተሳበበ የግለሰብ ኪስ የሚደልብበትን የመያዶች
አሰራር በዘጋ መልኩና በትክክል ከተተገበረ ደግሞ የአገር ውስጥ ጥቅምን ሊያጎላ በሚችል መልኩ ሲወጣ “ሆ” ብለው በመነሳት እየተቀባበሉ
ዘመቱበት። አዋጁ በእርግጥም የሀገር ውስጥ ጥገኛው ኃይል እና የኒዮ-ሊበራል ሀይሉን ፍላጎት በመዝጋት የሀገራችንን ልማት የሚያጠናክር
በመሆኑና ኪራይ ሰብሳቢ ፍላጎታቸውንም የሚያጨናግፍ በመሆኑ አዋጁ ከወጣ ጊዜ አንስቶ ያለማመንታት ሲዘምቱበት ይታያል፡፡ የፀረ ሽብርተኝነት
አዋጅ ላይም በተመሳሳይ፡፡ ይህ የተቃዋሚ ሀይል ያሳየው ምላሽ በበርካቶች ዘንድ ትዝብት ውስጥ የከተተው ሲሆን በእርግጥም እነዚህ
ሃይሎች ውግንናቸው ለማን እንደሆነም በግልጽ ያሳየ ነው፡፡
ሌላው
መገለጫቸው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች የቃል ኪዳን ሰነድ በሆነው ህገ መንግስት ላይ ያላቸው የተንሸዋረረ እይታ ነው፡፡
ለዚህ ደግሞ ከሰሞኑ ጽንፈኛ የተቃዋሚ ሀይሉ ህገ መንግስታችን የፀደቀበትን 20ኛውን አመት በሚከበርበት እለት
የፈፀሙት እኩይ ተግባር ከበርካታ ጥፋቶች መካከል አንዱ ማሳያ ይሆናል፡፡ የእነዚህ ፅንፈኛ ሃይሎች ውግንና ለኢትዮጵያ ብሔሮች፣
ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ሳይሆን አፍራሽ አጀንዳውን ላሸከማቸው የውጭ ሀይል በመሆኑ የኢትዮጵያ ህዝቦች በጋራ በደመቀ ሁኔታ በሚያከብሩት
ወቅት የብጥብጥና የአመፅ ተግባራቸውን ለመፈፀም አደባባይ ወጥተዋል፡፡
እነዚህ
ኃይሎች ጫፍ የወጣው ጨለምተኝነታቸውና ከኢትዮጵያ ህዝብ በተቃራኒ እንደቆሙ የሚያረጋግጠው እየተጎናፀፍናቸው ላሉ ግዙፍ የልማት ተግባራት
ያላቸው የተዛባ አመለካከት ነው፡፡ ለዚህም ከፍተኛ የልማት እንቅስቃሴ በሚካሂድበት በመስቀል አደባባይ ሰልፍ ካላደረግን በሚል በግልፅ
ልማቱን ለማደናቀፍ ያላቸውን ምኞት በተግባር አሳይተዋል፡፡ ይህን ህገ ወጥ ድርጊታቸውን ለመፈፀም መነሳሳታቸው ደግሞ ለኢትዮጵያ
ህዝብ ፍላጎታቸው ምን እንደሆነ በቀላሉ ለመረዳት የሚያስችል ሁኔታን ነው የፈጠረለት፡፡ ፀረ ህዝብና ፀረ ልማት የሆነ አጀንዳ እንዳላቸውም
በግልጽ የሚያረጋግጥ ነው፡፡
የሀገራችን
ተቃዋሚዎች አጀንዳቸው ህገ መንግስት መጠበቅ አልያም በአገር ውስጥ የሚከናወን ሁሉን አቀፍ ልማት መደገፍ ሳይሆን የተሰጣቸውን ትእዛዝ
መፈፀም ብቻ ሆኗል፡፡ ይህን ለማድረግ ደግሞ የህዝቡን ፍላጎትና ምኞት ከማዳመጥ ይልቅ በየኤምባሲው ደጅ መቆምን ይመርጣሉ። ሕገ
ወጥ ድርጊት መፈፀማቸው በፍርድ ቤት ተረጋግጦ በማረሚያ ቤት ያሉ እና ጉዳያቸው በፍርድ ቤት በመታየት ላይ ያሉ ተጠርጣሪዎችን እንዲሁም
የኪራይ ሰብሳቢነት መንገድ ስለተዘጋባቸው ያኮረፉ ግልሰቦችን በማሰባሰብ ስርዓቱን ጥላሸት ለመቀባት ይጥራሉ፡፡ ሰሞኑን የተደረጉትን
ሰልፎች የሚነሱ መፈክሮችን በምሳሌነት ብናነሳ በህግ ጥላ ስር ያሉ ዜጎች፣ በህገ ወጥ መንገድ መሬት በመውረር ህገ ወጥ ድርጊታቸውን
መንግስት ያስቆማቸው ግለሰቦች፣ እንደ አገር ደግሞ ድህነትን ለማስወገድ በሚደረግ ሁሉን አቀፍ ርብርብ ውስጥ የሚፈጠሩ አንዳንድ
የመሰረተ ልማት መንጠባጠቦችን እንደ ትልቅ ቀውስ ተጋነው ቀርበዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሕዝብ እነዚህን ፅንፈኛ ተቃዋሚዎች በብዙ ርቀት ቀድሟቸዋል፡፡ እነሱ ግን ዛሬም ከጥንቱ መስመራቸው ላይ እንደቆሙ ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ አጀንዳው ድህነትን ማሸነፍ ነውና የእነሱ አፍራሽ እቅድ ተሸካሚ እንደማይሆን በተግባር ፊቱን ወደ ልማት በማዞር እየገለፀላቸው ይገኛል፡፡ የተቃውሞ ሰልፍ በማድረግ በርካታ ህዝብ ከጎናቸው እንደሚሰለፍ ቢያልሙምም በተግባር ግን እነሱ ብቻ የሚቆዝሙባቸው ሰልፎች ሆነዋል። እነሱ ውግንናቸውንና አሰላለፋቸውን እስካላስተካከሉ ድረስ ከኢትዮጵያ ህዝብ ጋር ዘላቂ ፍቺ መፈፀማቸው አይቀርም።
No comments:
Post a Comment