በፈድሉ ጀማል
በሀገራችን ከገጠር እስከ ከተማ በሁሉም ዘርፎች
እድገት በመመዝገቡ በዜጎች የአኗኗር ሁኔታ ላይ ዘርፈ ብዙ ለውጦች በመታየት ላይ ናቸው፡፡ በለውጡ ሂደት ስፋትና ጥልቀት ላይ በሚሰጡ
ምስክርነቶች ልዩነት መታየቱ ካልሆነ በስተቀር ይህን እውነታ ከሀገሪቱ ዜጎች አልፎ የተለያዩ አለም አቀፍ ተቋማት መመስከር ከጀመሩ
ሰንብተዋል፡፡ ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ ቁጥራቸው ትንሽ ቢሆንም “ምንም ለውጥ አልመጣም” የሚል አቋም የያዙ አካላትም አልታጡም፡፡
ሰፊውን ቁጥር የያዘውና ለውጡ መሰረታዊና
ትልቅ ነው የሚለው ወገን ተጨባጭ ለውጦችን በማንሳት <<ለተመዘገው እድገት ተገቢው እውቅና ሊሰጠው ይገባል>>
ከሚል አልፎ የለውጡ የመጨረሻ ደረጃ ላይ ተደርሷል ብሎ ስለማያምን ለውጡ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ያስቀምጣል፡፡ በአንፃሩ የለውጡን
አቅጣጫና ሂደት ለመቀበል ፍቃደኝነቱ የጎደላቸውና በአብዛኛው የትላንቷ ኢትዮጵያ ትሻል ነበር ብለው የሚያምኑ ወገኖች ለውጡ መቀጠል የለበትም ወይም መቋረጥ ይገባዋል ወይም ሌላ አቅጣጫ መቀየስ
አለበት ብለው ያምናሉ፡፡
በእኔ እምነት የዛሬይቱን ኢትዮጵያ ከሁለት አስር አመታት በፊት ከነበረችው
ጋር ማነፃፀር ለቻለ ሰው ለውጡን ለማረጋገጥ አይሳነውም፡፡ በንጉሳውያኑ እና በአምባገነኑ ስርዓት ስር በከፋ የእርስ በእርስ ጦርነትና
የመበታተን አደጋ ውስጥ የነበረችው ሀገራችን አሁን በታሪኳ ረጅሙን ከእርስ በርስ ጦርነትና ግጭት የፀዳ ጊዜ እያሳለፈች ነው፡፡
የደርግ መንግስት በተገረሰሰ ማግስት የነፃ ገበያ የኢኮኖሚ ስርዓት በመገንባቱ በማሽቆልቆል ላይ የነበረው ኢኮኖሚ ከመጀመሪያዎቹ
አመታት ጀምሮ በእድገት አቅጣጫ እንዲራመድ ተደርጓል፡፡ በተለይ ባለፉት 12 ዓመታት በተመዘገበው ከፍተኛ የእድገት ምጣኔ ሀገራችን
በአለም ፈጣን እድገት አላቸው ከሚባሉ ሀገሮች በቀዳሚነት የምትጠቀስ መሆን ችላለች፡፡
በግብርናው መስክ በ1994/95 ከ83 ሚሊዮን ኩንታል የማይበልጠው
አመታዊ የሰብል ምርት በአሁኑ ወቅት 254 ሚሊዮን ኩንታል ደርሷል፡፡ ከጥቃቅንና አነስተኛ እስከ ከፍተኛ ኢንዱስትሪዎች መስፋፋት
ችለዋል፡፡ ከትናንሽ እስከ ግዙፍ የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች ተነድፈው ተግባራዊ ተደርገዋል፡፡ ከታላቁ የህዳሴ ግድብ እስከ ባቡርና
ሰፋፊ አውራ ጎዳናዎች፤ ከገጠር ኤሌክትሪፊኬሽን እስከ መሰረተ ሰፊ የቴሌኮም አውታር ዝርጋታ ድረስ በተካሄዱ የልማት ፕሮጀክቶች
በኢህአዴግ የሚመራው መንግስት በርግጥም ልማታዊ መሆኑን አፍ አውጥተው የሚመሰክሩለት ናቸው፡፡
በሀገራችን እየተመዘገበ ያለው መጠነ ሰፊና ፈጣን እድገት የመላው ህዝብ
ተጠቃሚነት በየደረጃው እየተረጋገጠ የመጣበት ነው፡፡ በእዚህም ሀገራችን በርካታ ሃብታሞችን መፍጠር የቻለች ሲሆን ከዚህ ጎን ለጎን
ዜጎች ከዝቅተኛ ወደ መካከለኛ ገቢ በፍጥነት መሸጋገር የጀመሩባት ሆናለች፡፡ አርሶ አደሩ ምርትና ምርታማነቱ እንዲያድግና የምርቱ
ነፃ ተጠቃሚ እንዲሆን በመደረጉ ከድህነት እየተላቀቀ ሃብት በማፍራት ላይ ነው፡፡ በከተሞች በዝቅተኛና መካከለኛ ገቢ የሚተዳደሩ
በርካታ ዜጎችን በጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማት ልማት ተጠቃሚ እንዲሆኑ በማድረግ በድህነት የሚኖሩ ዜጎችን ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ መቀነስ
ተችሏል፡፡ በግል ባለሃብቱና በመንግስት የሚከናወኑ የልማት ፕሮጀክቶች በእጅጉ በመስፋፋታቸው ሰፊ የስራ እድል ተፈጥሯል፡፡
ይህ እድገት በማየት ብቻ በቀላሉ የሚረጋገጥ መሆኑ እንደተጠበቀ
ሆኖ አለም አቀፋዊ ተቀባይነቱም እያደገ የመጣበት ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ አለም አቀፍ የኢኮኖሚና የፋይናንስ ተቋማት እድገቱንና ከዚሁ
ጋር ተያይዞ በሀገራችን ያለውን የኢንቨስትመንት አዋጭነት መመስከራቸው ለዚህ ዋነኛ ማሳያ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ሀገራችን አለም
አቀፉን የፋይናንስ ገበያ መቀላቀል የቻለችው የተወዳዳሪነት አቅሟን በማሳደጓ ነው፡፡
ሀገራችን የጦርነት አደጋን በማስወገድ ዘላቂ ሰላም የሰፈነባት ሀገር
ልትሆን መቻሏም ባለፉት 23 ዓመታት ከተመዘገቡ አኩሪ ድሎች ይጠቀሳል፡፡ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መገለጫ ከሆነው የብጥብጥና የጦርነት
ቀጠናነት በተለየ ሁኔታ ሀገራችን ዘላቂ ሰላም የሰፈነባት ልትሆን በቅታለች፡፡ የኤርትራን መንግስት ወረራ ለመመከት ተገደን ከገባንበትና
አልሸባብ የደቀነብንን አደጋ ለማስወገድ ካደረግነው ጦርነት በስተቀር ያለፉት 23 አመታት ዘላቂ ሰላም የሰፈነባቸው ናቸው፡፡ ከጎረቤቶቻችን
ጋር በሰላም፤ በመልካም ጉርብትናና በጋራ ተጠቃሚነት መንፈስ ተያይዘን መጓዛችንን ቀጥለናል፡፡ ከዚህም አልፈን የቀጠናውንና የሌሎች
ሀገሮችን ሰላም ለማስከበር በመትጋታችን አለም አቀፍ እውቅና ተሰጥቶናል፡፡ ይህ ሊሆን የቻለው በሰላም፣ በእኩልነትና በውስጥ ጉዳይ
ጣልቃ ባለመግባት መርህ በሚገዛ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ስለምንመራ ነው፡፡
ሀገራችን የሃሳብ ልዩነት በዴሞክራሲያዊና ህጋዊ መንገድ መፈታት እንዳለበት
በሚደነግግ ህገ መንግስት መመራት በመቻሏ ውስጣዊ ሰላሟ ዘላቂና አስተማማኝ ሆኖ ቀጥሏል፡፡ በህዝብ ነፃ ምርጫ በተመሰረተው ህገ
መንግስታዊ ጉባኤ ከብዙ ክርክር በኋላ በአብላጫ ድምፅ የፀደቀው የሀገራችን ህገ መንግስት ለዜጎች ዴሞክራሲያዊና ሰብአዊ መብቶች
የተሟላ እውቅና የሚሰጡ ዴሞክራሲያዊ ባህሪያትን ያሟላ ነው፡፡ በተባበሩት መንግስታት ቻርተር የፀደቁ መሰረታዊ መብቶችን በመቀበል
ሳይወሰን በሀገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ለህዝቦች ቀጥተኛ ዴሞክራሲያዊ ተሳትፎ መጎልበት፤ ለብሔሮች እኩልነት መከበር፤ ለቡድንና የግለሰብ
መብቶች የተሟላ እውቅና በመስጠት አለም አቀፉን የዴሞክራሲ ማዕቀፍ ይበልጥ አስፍቶ የደነገገ ህገ መንግስት ነው፡፡ በዚህም ህገ
መንግስታችን የሉዓላዊነት ባለቤትነትን ከነገስታቱና አምባገነኖቹ እጅ አውጥቶ ወደ ሕዝቡ የመለሰ ተደርጎ ይወሰዳል፡፡
በተግባርም ሀገራችን ባለፉት 23 ዓመታት
የግልና የቡድን መብቶችን በሰፊ ህዝባዊ ተሳትፎና እንቅስቃሴ በመታገዝ ተግባራዊ የተደረጉባት ሆናለች፡፡ ዜጎች ሃሳብን የመግለፅ
መብታቸውን ተጠቅመው ማንኛውንም ሃሳብ ህጋዊ በሆነ መንገድ መግለፅ ችለዋል፡፡ መንግስትን ከመቃወም ጀምሮ በማንኛውም ጉዳይ ላይ ያላቸውን
የተለየ ሃሳብ በነፃነት አራምደዋል፡፡ ማሰብም ሆነ ያሰቡትን መግለፅ የሚያስጠይቅበት ዘመን ታልፎ በማንኛውም ህጋዊና ሰላማዊ መንገድ
የማሰብና ሃሳብን የመግለፅ ነፃነት ተግባራዊ ተደርጓል፡፡ ይህን ሃቅ የሀገራችን የግል ሚዲያዎች የሚፅፏቸውን መሰረተ ቢስ የተቃውሞ
ሃሳቦች በመመልከት ብቻ ማረጋገጥ ይቻላል፡፡ የመደራጀት መብት በመከበሩ በርካታ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተፈጥረውና በህጋዊነት ተመዝግበው
ይንቀሳቀሳሉ፡፡ የሲቪክ፣ የሙያና የብዙሃን ማህበራት በብዛት ተፈጥረዋል፡፡
ከዚህ በፊት የአንድ ብሔር ባህልና ታሪክ
ብቸኛ መታወቂያዋ እንዲሆን ተፈርዶባት የነበረችው ሀገራችን የባህልና የታሪክ እኩልነትን በተግባር ላይ አውላለች፡፡ አዲሲቷ ኢትዮጵያ
ህዝቦች በባህላቸው የሚታወቁባትና የሚኮሩባት ነች፡፡ ብዝሃነት ያላቸው ህዝቦቻችን በልዩ ልዩ ባህላዊ እሴቶቻቸው ደምቀው በአደባባይ
የሚታዩባት እንጂ ተሸማቅቀው የሚደበቁባት ሀገር አይደለችም፡፡ የኢትዮጵያ ብሔሮች፤ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ታሪኮች ባለፉት ሁለት ተኩል
አስርት አመታት በሰፊው እየተጠኑና እየተገለፁ መጥተዋል፡፡ እነዚህ ፖለቲካዊ እርምጃዎችና ያስገኙት ውጤት በርግጥም ኢሕአዴግ ልማታዊ
ብቻ ሳይሆን ዴሞክራሲያዊ ድርጅት መሆኑን የሚያሳዩ ናቸው፡፡
አዲሲቷ ኢትዮጵያ ለልማትና ለዴሞክራሲ፣
ለሰላምና ለጤናማ የውጭ ግንኙነት በተካሄዱት የጋራ ትግሎች የብሔር ብሔረሰቦች የተናጠል ገድል ብቻ ሳይሆን የመላ ሕዝቦቻችን የጋራ
ተጋድሎ በ21ኛው ክፍለ ዘመን ተጠናክሮ የቀጠለባት ሆናለች፡፡ የሀገር ግንባታ ፕሮጀክታችን ሁሉንም በባለቤትነት የሚያሳትፍ፣ ሁሉንም
በመስዋዕትነትና በጋራ የሚያስተሳስር ጠንካራ ሀገራዊ ፕሮጀክት ሆኗል፡፡ ይህንንም የሀገራችን ህዳሴ መሃንዲስ ታላቁ መሪ ጓድ መለስ
ዜናዊ ባዘጋጀው ፅሁፍ እንዲህ ሲል ገልፆታል፡፡
“የሀገራችንን የህዳሴ ጉዞ እንደ አንድ የጋራ
ፕሮጀክት ግንባታና የእድገት ጉዞ ልናየው እንችላለን፡፡ አዲሲቷን ኢትዮጵያ ‘ሀ’ ብለን ከመጀመሪያ ጀምረን ለመገንባት ሁሉም የኢትዮጵያ
ህዝቦች በፕሮጀክቱ ባለቤትነትና መስራችነት እንዲሳተፉ አድርገናል፡፡ እንደማንኛውም ጥሩ የጋራ ፕሮጀክት ሁሉ ሁሉም ህዝቦች እኩል
የመሳተፍ ዕድል ተሰጥቷቸው እንደየአቅማቸው ድርሻቸውን እንዲያበረክቱ ተደርጓል፡፡ አንዱ መስራች ሌላው ተጋባዥ ሆነው ሳይሆን ሁሉም
በመስራችነት እኩል አስተዋፅኦ የማድረግ እድል ባገኙበት ሁኔታ ሁሉም ያላቸውን ሁሉ እንደአቅማቸው፣ ቋንቋቸውን፣ ባህላቸውን፣ እውቀታቸውን፣
ጉልበታቸውንና ንብረታቸውን አዋጥተዋል፡፡ በዚሁ አማካኝነት የጋራ ፕሮጀክቱ የሁሉንም አቅሞች አጣምሮ ስራ ከጀመረ በኋላ ሁሉም ባበረከተው
አስተዋፅኦ ልክ ከጥቅሙ ተጋሪ ይሆናል፡፡ ያለፈው ሂደት ተሽሮ አዲሲቷ ኢትዮጵያ በአዲስ መሰረት ላይ ስትጀምር የዞሩ እዳዎችን ሁሉ
አራግፋ ነው እየጀመረች ያለችው፡፡ ካለፈው ታሪክ በመነሳት ባዕድና ቤተኛ የሚባሉ ህዝቦች የሉንም፡፡ በዚህ ምክንያት ካለፈው የውርደትም
ሆነ የገናናነት ታሪክ በተለየ ሁኔታ የኢትዮጵያ ህዳሴ የሁሉም ህዝቦች ህዳሴ፣ የሁሉም ህዝቦች የጋራ ፕሮጀክት ነው፡፡”
በመሆኑም የአዲሲቷን ኢትዮጵያ የህዳሴ ፕሮጀክት
እውን ለማድረግ በልማታዊና ዴሞክራሲያዊ ጉዟችን ፊት የሚደቀኑ የመልካም አስተዳደር፣ የትምክህትና ጠባብነት እንዲሁም በሃይማኖት
ሽፋን የሚራመዱ የአክራሪነት አደጋ ችግሮችን በጋራ ርብርብ መመከትና ማስወገድ ይጠበቅብናል፡፡
No comments:
Post a Comment