EPRDF is a ruling party committed to realize Ethiopia's Renaissance.

Wednesday, 26 November 2014

እኛና አይ ኤም ኤፍ


በእውነቱ ይታወቅ
"የአለም ኢኮኖሚ ቀስ እያለ ነገር ግን በማይቀር መልኩ ከገባበት ቀውስ እየተላቀቀ ባለበት በአሁኑ ወቅት አንዳንድ ታዳጊ ኢኮኖሚዎች ጎልተው እየወጡ ነው" ይላል ዘ ሞትሌ ፉል የተባለ ድረ ገፅ ባወጣው ትንታኔ፡፡
ከአሮጌው ሚሌኒየም መገባደጃ ጀምሮ ስኬታማ የኢኮኖሚ እድገት ስታስመዘግብ ቆይታ አሁን በአለም ሁለተኛውን ግዙፍ ኢኮኖሚ የገነባችውን ቻይናን በአብነት ያነሳል፡፡ እነ ህንድ፤ ብራዚል እና ሩሲያ መካከለኛ ገቢ ያለው ዜጋ ቁጥር በማደጉ፤ በከተሞች መስፋትና በህዝባቸው ብዛት መጨመር ተደግፈው በአለም ግዙፍ ኢኮኖሚ ያላቸውን 10 ሀገራት መቀላቀላቸውንም በምሳሌነት ያክላል፡፡
ይህን ብሎም “አሁን የትኞቹ ሀገሮች ናቸው በመውጣት የኢኮኖሚው ዳገት በፍጥነት በመውጣት ላይ ያሉት?” ሲል ይጠይቃል ዘገባው፡፡ ምላሹንም የአለም አቀፉን የገንዘብ ድርጅት /IMF/ የ2014 የአለም ኢኮኖሚ ትንበያን /World Economy Outlook/ ምክንያት በማድረግ አምስት ሀገሮችን ለይቷል፡፡ አንዷ ሀገራችን ኢትዮጵያ ስትሆን ሌሎቹ ሊቢያ፤ ማይናማር፤ ኳታርና ናይጄሪያ ናቸው፡፡
የአለም አቀፉን የገንዘብ ድርጅት /IMF/ የ2014 የአለም ኢኮኖሚ ትንበያ የኢትዮጵያን የ2014 /እ.አ.አ/ እድገት 10.5 በመቶ እንደሚሆን ተንብያል፡፡ ይህን መሰረት አድርጎ ትንታኔውን የሰራው ዘ ሞትሌ ፉል ድረ ገፅ ደግሞ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በተያዘው ፍጥነት እንዲያድግ ወደ ሃገሪቱ በስፋት እየገባ ያለው የውጪ ኢንቨስትመንት ምክንያት መሆኑን ያስረዳል፡፡
በቻይናና በሌሎች መሰል አምራች ኢንዱስትሪ ባሏቸው ትላልቅ ሀገራት የጉልበት ዋጋ መጨመር ኢትዮጵያን ሁነኛ የኢንቨስትመንት መዳረሻ ያደርጋታል ይላል ዘገባው፡፡ ለማስረጃነትም በቻይና ብቻ በዚሁ የፈረንጆች አመት 85 ሚሊዮን ያክል የሰራተኛ ጉድለት እንደሚኖርና የቻይና የልብስ አምራች ኩባንያዎች በኢትዮጵያ በተነፃፃሪ በዝቅተኛ የጉልበት ዋጋ ሰራተኞችን በመቅጠር ስራ መጀመራቸውን ይጠቅሳል፡፡
"ከ30 አመት በፊት የአንድ ሚሊዮን ዜጎችን ህይወት የቀጠፈ ረሃብ ያስተናገደችው ኢትዮጵያ አሁን ግብርና ላይ በተመሰረተ ኢኮኖሚ እየዘመነች ነው" ይላል ሪፖርቱ፡፡ ሆኖም አሁንም ኢትዮጵያ የመሰረተ ልማቷን ይበልጥ ማስፋትና ለውጭ ኢንቨስትመንት ምቹ ሁኔታን መፍጠር ላይ እንደሚቀራት አሳስቧል፡፡ በዙሪያዋ ያሉ ሀገሮች ያለመረጋጋት በተለይም ከኤርትራ በብዛት የስደተኞች መፍለስ በኢትዮጵያም ያለመረጋጋት ሊፈጥርና ኢንቨስትመንቱን ሊያናጋ እንደሚችል ስጋቱን አስቀምጧል፡፡ ፅሁፉ በማጠቃለያው ታዲያ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የቀጣይ አቅጣጫ ወዴትም ሳይሆን ወደ ላይ /ፈጣን እድገት/ እንደሆነ ደምድሟል፡፡
በዚህ ፅሁፍ መሰረት የኢትዮጵያ ሁኔታ ከሌሎቹ ፈጣን እድገት እንዳላቸው ከተመሰከረላቸው አራ ሀገራትም ይለያል፡፡ በመጀመሪያ ከማይናማር በስተቀር ሶስቱም ሀገራት በነዳጅ ዘይት ላይ ጥገኛ የሆነ ኢኮኖሚ የሚመሩ ናቸው፡፡ ማይናማርም ብትሆን ነዳጅን ጨምሮ ሌሎች የተፈጥሮ ሀብቶችን የሚጠቀም ኢኮኖሚ ያላት ነች፡፡ በሌላ በኩል የኢኮኖሚ እድገቱ መጠንም ሲታይም ከሊቢያ /17.1%/ በስተቀር የትኞቹም ሀገራት ከኢትዮጵያ የተሻለ እድገት አልተተነበየላቸውም፡፡ በሶስተኛ ደረጃ ድረ ገፁ በአራቱ ሀገራት ስጋቶችን በማስቀመጥ የኢኮኖሚ እድገታቸው ቀጣይ የሚሆነው በቅድመ ሁኔታ /ስጋቶች ሲወገዱ/ መሆኑን ሲያነሳ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እድገት ግን ሊቀለበስ እንደማይችል ደምድሟል፡፡
ይህ በዝርዝር ሲታይም የናይጄሪያ ኢኮኖሚ ሊያድግ ከሆነ እየወደቀ ያለው አለም አቀፍ የነዳጅ ዋጋ ሊያንሰራራ እና በሀገሪቱ የተንሰራፋው ሽብርተኝነትና ያለመረጋጋት ሊቀረፍ እንደሚገባው አንስቷል፡፡ በኳታርም እድገቱ ዘለቄታዊ እንዲሆን በነዳጅ ላይ ጥገኛ ከሆነ ኢኮኖሚ ተላቆ ዘርፈ ብዙ የኢኮኖሚ ልማት ማምጣት እንደሚገባ ጠቁሟል፡፡ በማይናማር ደግሞ የሰብዓዊ መብት አያያዝን ማሻሻልና ኢኮኖሚውን መሰረት የሚያሲዝ የፖለቲካና የህግ ማዕቀፍ ማበጀት ግድ እንደሆነ አሳስቧል፡፡ በሊቢያ የእርስ በርስ ጦርነቱን ማቆም ካልተቻለና የፖለቲካ መረጋጋት ካልሰፈነ ኢኮኖሚው በታሰበለት ልክ እንደማያድግ ስጋቱን ገልጧል፡፡
እንግዲህ የአለም አቀፉን ገንዘብ ድርጅት መረጃ ተጠቅሞ የተሰራው ትንታኔ ጥሬ ትርጉም ይህን ይመስላል፡፡ ትንታኔው ግን ቢያንስ ሁለት ነገሮችን ያሳያል፡፡ አንደኛው የአለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት የዘንድሮው እድገታችንን መጠን ትንበያው እኛ ካስቀመጥነው /11.4%/ ጋር ከሞላ ጎደል ተመሳሳይ መሆኑ ነው፡፡ በተለመደው ሁኔታ እኛና አለም አቀፍ የኢኮኖሚ ተቋሞች የምንግባባው በበጀት አመቱ መጨረሻ ያስመዘገብነው ውጤት ሲመዘን እንጂ እንደርስበታለን ብለን በምናስቀምጠው እቅድ ላይ አልነበረም፡፡ 2014 ላይ ግን እኛና አይ ኤም ኤፍ ትንበያችን ሳይቀር ተቀራራቢ ሆኗል፡፡ ይህም ላለፉት 12 አመታት ያስመዘገብነው እድገት በእቅድ ዲሲፒሊን የምንመራና ያቀድነውን የመፈፀም ብቃት እንዳለን ማሳመን የቻለ መሆኑን ያረጋግጣል፡፡
ሌላው ተንታኞቹ ለሀገራችን ኢኮኖሚ እድገት ስጋት ናቸው በሚል ያስቀመጧቸው ነጥቦች ኢሕአዴግና በኢሕአዴግ የሚመራው መንግስትም ቀድመው የተረዷቸውና መፍትሄ ያስቀመጡላቸው መሆናቸው ነው፡፡ አንደኛው የመሰረተ ልማት ጉዳይ ሲሆን ይህ መንግስት ከትራንስፖርት እስከ ሃይል ማመንጨት፤ ከማህበራዊ ተቋማት እስከ ቴሌኮም ከፍተኛ በጀት መድቦ መሰረተ ልማትን እያፋጠነ የሚገኝበት ነው፡፡
ከሁሉም አቅጣጫ ወደ ሀገራችን ኢንቨስትመንትን መሳብ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቁልፍ ተግባር በማድረግ ብቻ ሳይወሰን ከመጡ በኋላ ያለውን አያያዝ ለማስተካከልም መንግስት እየሰራ ይገኛል፡፡ ይህም የተንዛዛ ቢሮክራሲን ከማሳጠር ጀምሮ የህግ ማዕቀፎችን ማስተካከልንም ያካተተ ነው፡፡
በአካባቢ መረጋጋትም እንዳለመታደል ሆኖ ቀጠናው ሰላም የራቀው ቢሆንም የጎረቤቶቻችን ሰላም ለመመለስ በሰላም ማስከበርና በአደራዳሪነት ግንባር ቀደም ተሳትፎ እያደረግን እንገኛለን፡፡

በአጠቃላይ ሲታይ ዘገባው የምንከተለውን መስመር ትክክለኛነት ያረጋገጠ፤ እያስመዘገብነው ያለውን የኢኮኖሚ እድገት አለም አቀፍ ተቀባይነት ያሳየና የጀመርናቸውን የማሻሻያ እርምጃዎች ማጠናከርና ማፋጠን እንዳለብን የጠቆመ ተደርጎ የሚወሰድ ነው፡፡

2 comments:

  1. አቅማችን አማጥጠን የቤት ስራችን ከሰራን ከዚህ በላይም ማደግ እንደምንችል እናውቃለን፤ በዚህ አንዘናጋም፡፡
    ውሻው ይጮኋል ግመሉ መንገዱ ቀጥሏል!!!!
    ታላቅ ነበርን ታላቅ እንሆናለን!!!!!
    ቀጣዩ ዘመን ከኢህአዴግ ብሩህ ነው!!!

    ReplyDelete