ስድስተኛው
የኢትዮጵያ ከተሞች ፎረም “ከተሞቻችን የኢንተርፕራይዞች ማዕከል በመሆን የኢትዮጵያን ህዳሴ ያረጋግጣሉ” በሚል መሪ ቃል የፍቅር፣ የሰላምና
የመቻቻል ተምሳሌት በሆነችው በድሬዳዋ ከተማ ተካሂዷል፡፡
በፎረሙ
የተለያዩ መርሃ ግብሮች የተካተቱ ሲሆን ከተሞቻችን ለኢትዮጵያ ህዳሴ መረጋገጥ እያደረጉት ያለውን ጥረት ያሳየው ከ170 በላይ ከተሞች
የተሳተፉበት ኤግዝቢሽን የዝግጅቱ አንድ አካል ነበር፡፡ በኤግዚብሽኑ ከተሞች ‘እኛን ይገልፀናል’ ያሉትን ባህል፣ የአኗኗር ዘይቤ፣ የእድገት ደረጃ፣ በከተማው ዘርፍ ያስመዘገቡትን ስኬት
በአንድ ትንሽ ስፍራ ላይ ለማሳየት ያደረጉት ጥረት፤ አንዱ ከተማ ከሌላው ልምድ ለመውሰድና ከዚህም ባለፈ አንዱ አንዱን አሸንፎ
ለመውጣት ያደረጉት ጤናማ ውድድር ውቢቷን ድሬዳዋ ይበልጥ አድምቋት ከርሟል፡፡
ከተሞቹ
በተቀናጀ የቤቶች ልማት ዘርፍ፣ በጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራዞች ልማት፣ በቴክኒክና ሙያ ስልጠና፣ በብድርና ቁጠባ አገልግሎት
እና በከተማ ፅዳት ረገድ ያከናወኑት ተግባር በእርግጥም ለሀገራችን ህዳሴ መረጋገጥ ያላቸው ፋይዳ የታየበት ነበር፡፡
ይህ
በፎረሙ የተመለከትኩት ጥቅል የከተሞች ተሳትፎ እንዳለ ሆኖ በዚህ ፅሁፍ ላወሳ የመረጥኩት ግን የፎረሙ አስተናጋጅ ስለሆነችው
ድሬዳዋ ከተማ ነው፡፡ እናም በፅሁፌ የድሬዳዋን ትናንት፤ ዛሬና ነገ ለመቃኘት እሞክራለሁ፡፡
ድሬ በትናንት መስተዋት
የአብዛኞቹ
የሀገራችን ከተሞች አፈጣጠር ከጦርነት ጋር የተያያዘ ሆኖ ለጦር ሰራዊት መስፈሪያነት እንዲያገለግሉ ታስቦ የተከተሙ ናቸው፡፡
ድሬዳዋ ግን ኢትዮጵያ ውስጥ ከተለመደው የከተሞች አመሰራረት ሂደት
በተለየ የባቡር መስመርን ተከትላ የተቆረቆረች ከተማ ናት፡፡ የፍራንኮ-ኢትዮጵያ የምድር ባቡር ሀዲድ መዘርጋትን ምክንያት አድርጋ
በ1895 ዓ.ም የተመሰረተችው ድሬዳዋ የእድገት ፍጥነቷም ከሌሎች ከተሞች የሚስተካከል አልነበረም፡፡ በተመሰረተች አስር ዓመት
ባልሞላ ጊዜ ውስጥ የንፁህ መጠጥ
ውሃ፣ ሆቴሎች፣ ፓስታ ቤት፣ ትምህርት ቤት፣ ሆስፒታል፣ ማተሚያ ቤት፣ የጀኔሬተር መብራት እና የመሳሰሉት መሰረታዊ አገልግሎቶች
ተስፋፍተውባታል፡፡
የባቡር
መስመሩ ድሬን የሀገሪቱ የወጪና ገቢ ንግድ ማዕከል እንድትሆን በማድረግ ለእድገትዋ ትልቅ አስተዋፅዖ አበርክቷል፡፡ ድሬዳዋ
በፕላን የተመሰረተች የመጀመሪያዋ የሀገራችን ከተማ መሆኗና በኢትዮጵያ ውስጥ የመጀመሪያ ሆቴል የተከፈተባት (ፒታኡ ሆቴል
በ1895) መሆኗ ድሬዳዋን በዘመናዊው የኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ጉልህ ስፍራ እንድትይዝ አድርጓታል። በዚህም በአጭር ጊዜ ውስጥ
ከአውሮፓ ከተሞች ጋር መነፃፀር ችላ እንደነበር ለፎረሙ የቀረበ ጥናታዊ ፅሁፍ አመልክቷል፡፡ በአጠቃላይ ድሬዳዋ ከጣሊያን ወረራ
በፊት በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካዊና በማህበራዊና ዘርፍ በወቅቱ ተጠቃሽ የሚባል የእድገት ደረጃ ላይ ደርሳ ነበር። ይህ በድሬዳዋ
የእድገት ታሪክ የመጀመሪያው የእድገት ጉዞ ተብሎ ይወሰዳል፡፡
ሁለተኛው
የድሬዳዋ እድገት የሚጀምረው ከጣሊያን ወረራ በኋላ ሲሆን እንግሊዞች በከተማዋ ውስጥ የቆዩበትን እስከ 1966ዓ.ም ያለውን ጊዜ
ያጠቃልላል፡፡ ድሬዳዋ ከጣሊያን ወረራ በኋላ ከ1933-1966 ባሉት ዓመታት እንደ ሁለተኛ የኢትዮጵያ ዋና ከተማ ትቆጠር ነበር፡፡
በነዚህ ዓመታት ድሬዳዋ የአየር፣ የመኪና እና የባቡር ትራንስፖርት ስለነበራት የጅምላ ንግድ ማዕከል መሆን ችላለች፡፡ ድሬዎች
ቡና፣ ጫት፣ ጥራጥሬ፣ የቅባት እህሎችና የቁም ከብቶች ወደ ጅቡቲ፣ የአውሮፓ ሀገሮች፣ አሜሪካ፣ ሳዑዲ አረቢያ እና ጃፓን በመላክ
ከአለም ጋር ተሳስረዋል፡፡ ይህም በኢትዮጵያና በውጭው ዓለም መካከል ዋነኛ የመገናኛ መስመር ስላደረጋት ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ ያላት
ከተማ ለመሆን በቃች፡፡
የደርግ
አስተዳደር ስልጣን ላይ ከወጣ በኋላ ግን ስርዓቱ በተከተለው የሶሻሊዝም ስርዓት የተነሳ ከተማዋ ውስጥ የነበሩ ቤቶች ተወረሱ፡፡
ይህም ከተማዋ ውስጥ የነበሩ በኢኮኖሚው ውስጥ ሲሳተፉ የነበሩ ግለሰቦች ኢኮኖሚያዊ ተሳትፎ አንዲቀዘቅዝና በርካቶችም ሀገር
ጥለው እንዲሰደዱ ምክንያት ሆነ፡፡ በሀገር አቀፍ ደረጃም ማንኛውም ባለሃብት ከ500ሺ ብር በላይ ካፒታል እንዳይኖረው የሚያግድ
ህግ እንደነበረውም ይታወቃል፡፡
ከፖለቲካም
አንፃር ከተማዋ ያላትን ህብረ ብሄራዊነትና የአለም አቀፍ ትስስር ስትራቴጂያዊ ሚና ባለመገንዘብ እስከ 1980 ዓ.ም ድረስ
በሐረርጌ ክፍለ ሀገር ስር እንደትቆይ ተገዳ ነበር፡፡ እነዚህ ችግሮች ተዳምረው የድሬዳዋ ከተማ እድገት ወደ ኋላ መመለስ
የጀመረበት ወቅት ነበር ለማለት ይቻላል፡፡ በዚህ የተነሳ የደርግ ስርዓት ለከተማዋ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ እድገት
እንቅፋት የሆነበትና ከተማዋም ወደ ፊት መራመድ አቅቷት ባለችበት እንድትዳክር ይባስ ብሎም ወደ ኋላ እንድትመለስ ያደረገ ትልቅ
መሰናክል ሆኖ አልፏል፡፡
ድሬዳዋ ዛሬ
የአብዛኞቹ
ከተሞች እድገት እንቅፋት የሆነው ዓፋኙ የደርግ ስርዓት በህዝቦች የተባበረ ትግል ከተወገደ በኋላ ድሬዳዋም አዲሱን የእድገት
ምዕራፍ ጀምራለች፡፡ አዲሲቷ ድሬዳዋ አዲሱን የእድገት ምዕራፏን የጀመረችው ራስን በራስ የማስተዳደር ሕገ መንግስታዊ መብቷ
በተግባር ተረጋግጦ፤ ራስን በራስ ማስተዳደር የሚያስችላት የድሬዳዋ ቻርተር በ1996 ዓ.ም አፅድቃ ወደ ስራ በመግባት ነው፡፡
ኢህአዴግ
ደርግን አስወግዶ ሀገሪቷን ማስተዳደር በጀመረበት ጊዜ ልክ እንደሌሎቹ የሀገሪቱ
አካባቢዎች ሁሉ ድሬዳዋም ድህነትና ስራ አጥነት ተንሰራፍቶባት ነበር። የመልካም አስተዳደር እጦት፣ የመንግስት ፋብሪካዎችና
አገልግሎቶች ምርታማነትና ትርፋማነት መዳከም፤ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ አበረታች አለመሆን፤ ወዘተ… ዋና ዋናዎቹ የከተማዋ
ችግሮች ነበሩ፡፡ በተጨማሪም የንግድ እንቅስቃሴዋ በህገ ወጥ የኮንትሮባንድ ንግድ ተተብትቦ ህጋዊ ንግድን በማደከምና የአገር
ውስጥ ምርቶች ተወዳዳሪ እንዳይሆኑ በማድረግ፣ መንግስት ገቢ በማሳጣትና አምራቾችን በማሸሽ፤ ወዘተ… ኢኮኖሚውን በመጉዳት
እድገት እንዳይመጣ አግዶ ከያዘው ትልቅ መሰናክል ጋር ነበር በኢሕአዴግ የሚመራው መንግስት ድሬዳዋን የተረከበው፡፡
በመሆኑም
ህገ ወጥ ንግድን በመቆጣጠር ኢኮኖሚውን ለማሳደግ ከፍተኛ ጥረት ማድረግ ወቅቱ የሚጠይቀው ዓብይ ተግባር ነበር፡፡ ለተከታታይ
ዓመታት በተደረገው ጥረትም
አበረታች ውጤቶች ተመዝግበዋል፡፡ ድሬዳዋ በሁሉም ዘርፎች ማለትም በግብርና፣ በኢንዱስትሪና በአገልግሎት ዘርፎች በ2004 ዓ.ም
11 ነጥብ 5 በመቶ እድገት ማስመዝገብ ችላለች፡፡ በ1997 ዓ.ም 32 ነጥብ 3
በመቶ የነበረውን የድህነት ደረጃ በ2004 ዓ.ም ወደ 27 ነጥብ 3 በመቶ ዝቅ ብሏል፡፡ በ1996 ዓ.ም የድሬዳዋ ነዋሪዎች የነፍስ
ወከፍ ገቢ 314 ዶላር የነበረ ሲሆን በ2004 ዓ.ም 706 ዶላር ደርሷል፡፡
ድሬዳዋ
በማህበራዊ መስክም እንዲሁ
ስኬታማ ውጤቶችን በማስመዝገብ ላይ ትገኛለች፡፡ በትምህርት መስክ የድሬዳዋን የትምህርት ጥቅል ተሳትፎ በ2006 ዓ.ም 85 ነጥብ
4 በመቶ ማድረስ ተችሏል፡፡ በጤናው ዘርፍ የመጀመሪያ ደረጃ የጤና አገልግሎት ሽፋንን መቶ በመቶ ማድረስ የቻለች ሲሆን
የእናቶችን ሞት በመቀነስ ረገድ ከ2004 ዓ.ም በፊት ከ100ሺ እናቶች መካከል 871 የነበረውን የሞት ምጣኔ በ2006 ወደ
470 ዝቅ በማድረግ እና የህፃናት ሞትን ደግሞ ከ2004 ዓ.ም በፊት ከ1000 ህፃናት መካከል 77 ህፃናት ይሞቱ የነበረበት
ሁኔታ በተደረገው ሁሉን አቀፍ ርብርብ በ2006 ዓ.ም ወደ 31 ዝቅ በማድረግ ከፍተኛ ስኬቶችን አስመዝግባለች፡፡
ድሬዳዋ
የነዋሪዎቿን የመኖሪያ ቤት ችግር ለመፍታት በ1996 ዓ.ም የጋራ መኖሪያ ቤቶች ልማት ፕሮግራም በመጀመር ከ1996-2006
ባሉት ዓመታት ውስጥ 2 ሺህ 898 የጋራ መኖሪያ ቤቶችና 306 የንግድ ቤቶች በጠቅላላው 3ሺህ 204 ቤቶችን በመገንባት
ለነዋሪዎች ማስተላለፍ ችላለች። በሂደቱም ለ123 ተቋራጮች፣ ለ270 ኢንተርፕራይዞችና ለ25ሺህ ወጣቶችና ሴቶች የስራ እድል
በመፍጠር ነዋሪዎቿን የዕድገቱ ፍትሐዊ ተጠቃሚ ማድረግ ችላለች፡፡
በጥቃቅንና
አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ልማት ዘርፍም እንዲሁ ከ1996-2002ዓ.ም በነበሩት ዓመታት ለ515 ሺህ 90 ዜጎች ጊዜያዊና ቋሚ
የስራ እድል መፍጠር ተችሏል፡፡ በእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዘመኑ ያለፉት አራት አመታት 367 ማህበራት ተደራጅተዋል፡፡ ለ61
ሺህ 215 ዜጎች የስራ እድል ተፈጥሯል፣ ለማህበራትና ኢንተርፕራይዞች የገበያ ትስስር በመፍጠር 240 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር
ማስገኘት ተችሏል፡፡ በብድርና ቁጠባ መስክም ለ46 ማህበራትና ለ5ሺህ 117 የግል አንቀሳቃሾች የ78 ነጥብ 04 ሚሊዮን ብር
ብድር ተሰጥቷል፡፡ 58 ነጥብ 35 ሚሊዮን ብር ደግሞ በቁጠባ መልክ መሰብሰብ ተችሏል፡፡
የድሬ ሕዳሴ
ቀድሞ
የምስራቁ የሀገሪቱ ክፍል የንግድ ማዕከል ከመሆን ባለፈ የአለም አቀፍ ትስስር እምብርት በመሆን ያገለገለችው ውቢቷ ድሬዳዋ
ዛሬም ወደ ቀድሞ ገናናቷ ለመመለስና ለነዋሪዎቿ የተመቸች ከተማ ለመሆን በትጋት እየሰራች ትገኛለች። እስከ አሁን ድረስ ድሬዳዋ
ካስመዘገበቻቸው ተጨባጭ ስኬቶች በተጨማሪ ውብና ምቹ፤ መልካም አስተዳደር የሰፈነባት፤ በንግድ፣ በኢንዱስትሪና በአገልግሎት
ዘርፍ ላይ ያተኮረ፤ የዳበረ ዘላቂ ኢኮኖሚ ያላትና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ሆኖ ለመገኘት በዕድገት ጎዳና እየገሰገሰች
ትገኛለች፡፡
የውጭ
ንግድና የሀገር ውስጥ ፍላጎትን የሚያሟሉ እና እርስ በእርሳቸው ተደጋጋፊ የሆኑ የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪዎች በብዛትና
በጥራት መገንባትና የስራ እድል መፍጠርን ቀዳሚ አጀንዳዋ አድርጋ እየተጋች ነው፡፡ የከተማዋን ኢኮኖሚ በማሳደግ ራዕዬን
ያሳኩልኛል ያለቻቸውን አቅጣጫዎች ነድፋ የዕድገት ጉዞዋን እያፋጠነች ትገኛለች።
ድሬዳዋ በሀገሪቱ የኢንዱስትሪ ልማት ፈር ቀዳጅ በመሆን የመጀመሪያዎቹ የሲሚንቶ እና የጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካዎች የተመሰረቱባት
ከመሆኗ በተጨማሪ
በአሁን ሰዓትም
ከፍተኛ የኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ልማት ከተስፋፋባቸው ከተሞች አንዷ ለመሆን በቅታለች፡፡ በፌዴራል ደረጃ በኢንዱስትሪ
ማዕከልነት ከተመረጡት ከተሞችም አንዷ ናት፡፡
የያኔው
ውበቷ የነበረው የጅቡቲ ኢትዮጵያ የባቡር መስመር ከዘመኑ ጋር መዘመን ተስኖት ከአገልግሎት ውጪ ቢሆንም አሁን የዘመናዊ ባቡር መስመር
ባለቤት ለመሆን ጥቂት አመቶች ብቻ ቀርተዋታል፡፡ ይህም ለሀገሪቱ የህዳሴ ጉዞ ድሬዳዋ የተጣለባት ሃላፊነትን ከፍ ያደርገዋል፡፡
ከግብርና መር የኢኮኖሚ ልማት ወደ ኢንዱስትሪ መር የኢኮኖሚ ልማት ለምናደርገው መዋቅራዊ ሽግግር ድሬዳዋ የምስራቁ የሀገሪቱ
ክፍል የኢንዱስትሪ፣ የማኑፋክቸሪንግና የአገልግሎት ማዕከል የሚያደርጋትን ስራ በብቃት ለመወጣት ከወዲሁ ሽርጉድ እያለች መሆኗን
በተግባር እያሳየች ነው። ሕዳሴዋን ለማረጋገጥ በሚያስችላት ትክክለኛ መስመር ላይ መሆኗንም የስድስተኛው የኢትዮጵያ ከተሞች
ፎረም ተሳታፊዎች አረጋግጠውላታል፡፡
No comments:
Post a Comment