EPRDF is a ruling party committed to realize Ethiopia's Renaissance.

Friday 5 September 2014

ለተቃዋሚ ፓርቲዎች መዳከም ምክንያቱ ውስጣዊ ችግራቸው ነው



አንዳንድ የአገራችን ተቃዋሚ ፓርቲዎች የውስጣቸውን ችግር ለመሸፈን የሚጠቀሙበት ስልት ‹‹ኢሕአዴግ አዳከመን›› የሚል ነው፡፡ እነዚህ ፓርቲዎች ሰሞኑን በመገናኛ ብዙሃን እየቀረቡ በዚሁ የተለመደ የፈጠራ ክሳቸው ተጠምደዋል፡፡ የፓርቲዎቹ አመራሮችና አባሎቻቸው ሶሻል ሚዲያውን ጨምሮ ባገኙት ሚዲያ ሁሉ የሚወተውቱት በውስጣቸው ላለው መከፋፈል ምክንያቱ ኢሕአዴግ መሆኑን ነው፡፡ ይህ ክስ አዲስ አይደለም፡፡ ይልቁንም ከዘመን ዘመን መልኩን እንኳን የማይለውጥ የተቃዋሚዎቻችን የምርጫ ዋዜማ ፕሮፓጋንዳ ነው፡፡ ሆኖም ለተቃዋሚ ፓርቲዎች መዳከም ኢሕአዴግ ሃላፊነቱን ሊወስድ እንደማይችል አሁንም በድጋሜ ሊያወቁት ይገባል፡፡
እነዚህ ጭፍን ተቃዋሚዎች ሁሌም ኢሕአዴግን ለመውቀስ ከሚያነሷቸው ነጥቦች አንዱ ‹‹ኢሕአዴግ የራሱን አባሎች በውስጣችን በማስገባት በመካከላችን ልዩነት እንዲፈጠር ይሰራል›› የሚል ሲሆን ባስ ሲልባቸውም ‹‹አባሎችንን በገንዘብ እየገዛ በፓርቲያቸው ላይ እንዲያሴሩ ያደርጋል›› የሚል አስተያየትም ይሰነዝራሉ፡፡
በመሰረቱ ኢሕአዴግ የሕዝብ ድምፅም ሆነ ሁለንተናዊ ድጋፍ ማግኘት የሚቻለው ሕዝብን ማዕከል ባደረጉ የፀረ ድህነት ፖሊሲና ስትራቴጂዎቹ ስኬታማ ውጤቶች እንጂ የሚቃወሙትን በማዳከም እንዳልሆነ ጠንቅቆ ያውቃል፡፡ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ድክመት እሱን እንደማያጠነክረውም አበክሮ ይረዳል፡፡ ኢሕአዴግ የጥንካሬው ምንጭ አድርጎ የሚወስደው የሚከተለውን መስመር፤ ህዝባዊነቱንና ውስጠ ዴሞክራሲያዊ አሰራሩን ነው፡፡ ከዚህ ባለፈ ኢሕአዴግ ጠንካራ ተቃዋሚ አለማግኘቱን ይልቁንም እንደ አለመታደል አድርጎ እንደሚወስደው የጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝን ንግግር ማስታወስ በቂ ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ አፍሪካ ሪፖርትከተሰኘው መጽሔት የግንቦት ወር ዕትም ጋር ቃለ ምልልስ  ባደረጉበት ወቅት እንዲህ ብለው ነበር፡፡

“ራሳችንን በእነሱ በኩል ለማየት ጠንካራ ተቃዋሚ ፓርቲዎች እንዲኖሩ እንመኛለን፡፡ ከእኛ ውጪ ያለ አካል ቢተቸን እንወዳለን፡፡ ያለመታደል ሆኖ እንዲህ ዓይነት ጠንካራ ተቃዋሚዎች የሉንም፡፡ ግልጽ የሆነ የራሳቸው ፖሊሲ ያላቸው ፓርቲዎች የሉም፡፡ የዚህን መንግሥት መሠረታዊ እምነቶች ተረድተው ስኬቶቹንና ድክመቶቹን ለመገምገም አልቻሉም፡፡ ኢሕአዴግን የብጥብጥ መንገዶችን ተከትለው ከሥልጣን ማስወገድና ወደ ሥልጣን መምጣት ይፈልጋሉ፡፡ ይኼ የማይሳካ ምኞት ነው፡፡”

ኢሕአዴግ ከዚህ እምነቱ በመነሳት ሙሉ ጊዜውንና የአመራር ሃይሉን የሚያውለው ፓሊሲና ስትራቴጂዎቹን በመተግበር የህዝቡን ተጠቃሚነተ ለማረጋገጥ ነው፡፡ ፓርቲው ላለፉት 23 አመታት በነበረው አፈፃፀም ኢትዮጵያን ከመበታተን ቋፍ መልሶ በሕዝቦች አንድነትና መፈቃቀድ ላይ የተመሰረተች አዲሲቷን ኢትዮጵያ ገንብቷል፡፡ የረሃብና ኋላቀርነት እንዲሁም የእርስ በርስ ጦርነትና ያለመረጋጋት ምሳሌ የነበረችውን ኢትዮጵያ አሁን ላይ የፈጣን ኢኮኖሚ እድገት ተምሳሌትና የአለም ሰላም ማስከበር ግንባር ቀደም ተዋናይ አድርጓል፡፡ ከውስጥ ተነስቶ ወደ ውጭ የሄደው የሰላም ማስከበር ሚናችን በአገሪቱ ከሰፈነው ዘላቂ ሰላምና ተከታታይ የኢኮኖሚ እድገት ጋር ተዳምሮ ኢትዮጵያን ለውጭ ኢንቨስትመንት ተመራጭ ከሆኑ የአፍሪካ አገራት ተርታ አሰልፏታል፡፡ ለህልውና ሲባል ስንዴ ከመለመን ተላቀን በምግብ እህር ምርት ራሳችንን ችለናል፡፡ መላ የኢትዮጵያ ሕዝቦችም በድርጅታችን መሪነት የተመዘገቡትን እነዚህን ስኬቶችና ፓርቲያችን አገሪቱን ለማድረስ ያሰበበትን ራዕይ በመረዳት በተከታታይ ምርጫዎች አገር እንዲመራ ድምፃቸውን ሰጥተውታል፡፡
ተቃዋሚዎች ግን ከኢሕአዴግ የተሻለ የፖሊሲ አማራጭ ቀርቶ ስም ያለው የፖለቲካ መስመር እንኳን ስለሌላቸው የሕዝብ ድጋፍ ማግኘት አልቻሉም፡፡ ለኢትዮጵያ ሕዝብ መታገል የሚቻለው ከራሱ ከሕዝቡ ጋር በመኖር ነው፡፡ ከሕዝቡ ርቀው በውጭ ሃይሎች ላይ የሚመኩት አንዳንድ የአገራችን ተቃዋሚ ፓርቲዎች ያላቀረቡት ሕዝብ ሲገፋቸው በኢሕአዴግ የተገፉ ይመስላቸዋል፡፡ ይህን መሰረታዊ ችግራቸውን ዘወር ብለው ማየት የተሳናቸው ወይም ማየት የማይፈልጉት እነዚህ ፓርቲዎች በአንዲት ተጨባጭ ማስረጃ እንኳን ማሳየት በማይችሉበት ሁኔታ የውስጥ ችግራቸውን በኢሕአዴግ ላይ ማላከክን ቀጥለውበታል፡፡ ከአመላመል ጀምሮ እስከ አባላት አቅም ግንባታ ድረስ ባሉ ሂደቶች የአባሎቻቸውን ጥራት ማስጠበቅ ሲገባቸው አባሎቻቸው በወጡና በገቡ ቁጥር በኢሕአዴግ እንደተደለሉ ለማስመሰል መሞከራቸው የውስጠ ድርጅት -ዴሞክራሲያዊ አሰራራቸውን አለባብሰው ማለፍ ስለሚፈልጉ ነው፡፡
ፅንፈኛ ተቃዋሚዎች ‹‹ተለጣፊ ፓርቲዎች›› በመፍጠር ኢሕአዴግ ጉልበታቸውን እንዳዳከመውም ይገልፃሉ፡፡ እንደሚታወቀው በአገራችን በፖለቲካ አመለካከት መደራጀት ህገ መንግስታዊ ዋስትና ያለው ነው፡፡ ይህን ህገ መንግስታዊ መብት የማስፈፀም ሃላፊነት የተሰጠው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ መስፈርቱን ለሚያሟሉ የፖለቲካ ድርጅቶች ፍቃድና እውቅና ይሰጣል፡፡ በዚህም መሰረት የተለያዩ ብሔር፤ ብሔረሰቦችና ሕዝቦችን እንወክላለን የሚሉ ብሔራዊና አገር አቀፋዊ የሆኑ 75 ያክል የፖለቲካ ፓርቲዎች አሉ፡፡ ይህ መላ የኢትዮጵያ ሕዝቦች በኢሕአዴግ መሪነት የታገሉለትና መስዋዕት የሆኑለት ትግል ፍሬ ነው፡፡ በዚህ ኢሕአዴግ ይኮራበታል፡፡ ምርጫ ቦርድ መስፈርቱን እስካሟሉ ድረስ ለአንድ ፓርቲ የሚፈቅድበት ሌላን የሚከለክልበት አሰራር የለም፤ ሊኖርም አይገባም ብሎም ኢሕአዴግ ያምናል፡፡
በአንፃሩ እነሱ ያገኙት መብት ለሌሎች ዝግ እንዲሆን የሚሹ ፅንፈኛ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ይህን አይደግፉም፡፡ ‹‹እኛ ብቻ ተቃዋሚ›› ከሚል ራስን አግዝፎ ከማየት የተዛባ አመለካከት በመነሳት ሌሎችን ያጣጥላሉ፡፡ ለዚህም የሚያነሱት እነዚህን ፓርቲዎች ‹‹የኢሕአዴግ ተለጣፊ›› ናቸው የሚል ነው፡፡ ይህ ግን እርስ በእርሳቸው ያላቸው የመጠላለፍና የዜሮ ድምር ፖለቲካ መገለጫ ነው፡፡ የትኛውም ፓርቲ ለሌላው እውቅና ሲሰጥ ሳይሆን እርስ በርስ ሲናቆሩ ማየት የተለመደ ነውና፡፡
ተቃዋሚዎቻችን ምርጫ በደረሰ ቁጥር የፖለቲካ ልዩነታችንን ለጊዜው እናቻችለው ወይም ወደ ጎን እንተወው ብለው ህብረት ይፈጥራሉ፡፡ በምርጫ ማግስት ሊታረቅ የማይችለው ባህሪያቸው ፈጦ ይወጣና ያለመግባባት ሲፈጠር ኢሕአዴግ ላይ ያመካኛሉ፡፡ ለጊዜያዊ አላማ የተሰባሰቡት አመራሮች ለሁለት ሲከፈሉም ማሳበቢያው ኢሕአዴግ ነው፡፡ እርስ በርሳቸው ተደባድበው ሲያበቁ እንኳን ኢሕአዴግ ነው ያጣላን ከማለት ወደኋላ አይሉም፡፡ በህገወጥ መንገድ የሚሰበስቡትን የውጭ ገንዘብ ሲከፋፈሉ በሚፈጠረው ፀብም ኢሕአዴግን ተጠያቂ ለማድረግ ይዳዳቸዋል፡፡
የአገራችን ተቃዋሚ ፓርቲዎች አሁንም በአገሪቱ የልማትና ዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ አፍራሽ ሚና ከመጫዎት ወጥተው በጎ ሚና እንዲኖራቸው ከፈለጉ ራሳቸውን ወደ ውስጥ መፈተሸ ይገባቸዋል፡፡ ሕዝብና አገር ሊመሩ ከፈለጉ መጀመሪያ ራሳቸውን መምራት አለባቸው፡፡ የጥላቻ ፖለቲካ ከማራመድ ይልቅ ገንቢ በሆነ ትችትና የፖሊሲ አማራጭ ላይ ቢያተኩሩ እንደሚሻላቸውም ኢሕአዴግ ያምናል፡፡
ይህ እንዳለ ሆኖ ኢሕአዴግ በሰላማ ህጋዊ መንገድ ከሚንቀሳቀሱ ሁሉም ፓርቲዎች ጋር ያለው የፖለቲካ ልዩነት እንደተጠበቀ ተባብሮ መስራት እንዳለበት ያምናል፡፡ የአገሪቱን የምርጫ ስነ ምግባር ህግ አክበረው በጋራ /ቤቱ ከገቡ ስምንት አገራዊ ፓርቲዎች ጋርም በዚሁ አግባብ እየሰራ ይገኛል፡፡ በየክልሎቹ ያሉ የምክር ቤቱ አባል ፓርቲዎችም ተመሳሳይ ሚና እንዲጫዎቱ ከፓርቲዎቹ ጋር በመሆን እየሰራ ይገኛል፡፡ ወደፊትም ለመድብለ ፓርቲ ስርዓት መጎልበት ሲል በአገራዊ ጉዳዮች ላይ በጋራ መስራቱን ይቀጥላል፡፡ ለመድበለ ፓርቲ ስርዓት መዘርጋት እንደታገለው ሁሉ አሁንም ስርዓቱ እንዲጎለብት በፅናት ይቆማል፡፡ በዚህ ረገድ እንደ ገዥ ፓርቲ ያሉበትን ሃላፊነቶችም ይወጣል፡፡ ከዚህ ውጭ ውስጣዊ ችግሮቻቸውን መፍታት ተስኗቸው ለሚዳከሙ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ማሳበቢያ ሊሆን አይችልም፡፡

No comments:

Post a Comment