በየማነ ገብረስላሴ
ወርሃ መጋቢት 2003ዓ.ም በኢትዮጵያ ታሪክ ልዩ ስፍራ ይሰጣታል፡፡ የዘመናት የህዝቦች ቁጭት ያበቃ ዘንድ በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ጉባ በተባለ አካባቢ በታላቁ መሪያችን የታላቁ ግድባችን ግንባታ የመሰረት ድንጋይ ተጣለ፡፡ በአባይ ጉዳይ ከዘፈንና እንጉርጉሮ አልፈን ተጠቃሚ ለመሆን ተጨባጭ እርምጃ የወሰድንበት ወቅት፡፡
ግድቡ በራስ አቅም የሚገነባ በመሆኑ የህዝብ ያልተቆጠበ ድጋፍ እንደሚያስፈልገውም ተገለጸ፡፡ ህዝቡም ከዳር እስከዳር ሆ ብሎ በመነሳት ለፕሮጀክቱ እውን መሆን በገንዘቡ፤ በጉልበቱና በእውቀቱ እንደሚደግፍ አረጋገጠ፡፡ ኢትዮጵያውያን የውጭ አገር ጠላቶችን ለመመከት ብቻ ሳይሆን በልማቱም በአንድ ድምፅ መዝመት እንደሚችሉ ያሳየ ፕሮጀክትም ሆነ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ፡፡
ለዘመናት ወንዙን በብቸኝነት የመጠቀም መብት አለኝ በሚል የተሳሳተ እምነት ስትመራ የነበረችው ግብጽ ግን ፕሮጀክቱን ተቃውማዋለች፡፡ በአንፃሩ በአባይ ወንዝ ያለው አማራጭ “አብሮ መዋኘት ወይም አብሮ መስመጥ” ብቻ መሆኑን በመግለጽ የግብጽን ተቃውሞ ብዙ ርቀት የሚያስኬድ እንዳልሆነ በመንግስትና የዘርፉ ባለሙያዎች ሲገለጽ ቆይቷል፡፡
ኢትዮጵያ ሌሎች የናይል ወንዝ የላይኛው ተፋሰስ አገሮች ፍትሃዊ ተጠቃሚ እንዲሆኑ የጋራ ማዕቀፍ በማዘጋጀትና በትብብር የመስራት ባህልን ለማሳደግ ጥረት ስታደርግ መቆየቷ ይታወሳል፡፡ ግድቡን ስትጀምር የጋራ ተጠቃሚነት መርህን ባከበረ መልኩ ነው፡፡ ግድቡ በታችኛው የተፋሰስ አገሮች የጎላ ጉዳት እንደማያስከትል ሳይንሳዊ ትንተና በማስቀመጥም ጭምር፡፡ ኢትዮጵያ በራሷ ተነሳሽነት ግድቡ በታችኛው የተፋሰሱ አገሮች የሚያስከትለው ጉዳት ካለ በዓለም አቀፍ ባለሙያዎች እንዲጠና ያደረገችውም በአገራቱ መካከል በመተማመን ላይ የተመሰረተ የጋራ ተጠቃሚነት መንፈስ እንዲሰፍን ካላት ቁርጠኛ ፍላጎት የተነሳ ነው፡፡
ከኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብጽ እንዲሁም ከሌሎች አገሮች የተውጣጡ ባለሙያዎችን ያቀፈው ይህ ቡድን ታዲያ ግድቡ በታችኛው የተፋሰሱ አገሮች ላይ የጎላ ጉዳት እንደማያደርስ በማረጋገጥ ኢትዮጵያ ቀድሞ የያዘችውን አቋም ትክክለኛነት ነበር ዳግም ያረጋገጠው፡፡ ቡድኑ ምክረ ሀሳቦችን ሰጥቶም ነበር፡፡ ይሁንና አሁንም ግብጽ ይህንን ለመቀበል ፈቃደኛ ሳትሆን ቀረች፡፡ የተለያዩ ምክንያቶች በመደርደር ራስዋን ጨምሮ ኢትዮጵያና ሱዳን ተሳታፊ ከሆኑበት የሶስትዮሽ ውይይት አቋርጣ መውጣቷ ይታወሳል፡፡
ግብፅ ከወራት በፊት አቋርጣው ወደነበረው የሶስትዮሽ የቡድን ውይይት በመመለሷ ውይይቱ ባለፈው ሳምንት በሱዳን ካርቱም ተካሂዷል፡፡ በዓለም አቀፉ የባለሙያዎች ቡድን የቀረቡትን ምክረ ሃሳቦች ለመተግበር ከሶስቱም አገሮች የሚውጣጣ ብሄራዊ የባለሙያዎች ቡድን ለማቋቋም አገራቱ ስምምነት ላይ ደርሰዋል፡፡ ይህ ውይይት ከዚህ በፊት ከተደረጉ ውይይቶች የተሻለ መግባባት የተደረሰበት እንደነበርም ነው የተገለጸው፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ በአሁኑ ወቅት የግድቡ ግንባታ በቀንና በለሊት በመከናወን ላይ ይገኛል፡፡ ከ1.2 ሚሊዮን ቶን በላይ የኮንክሪት ሙሌት የተከናወነ ሲሆን ግንባታቸው በብረታ ብረትና ኢንጅነሪንግ ኮርፖሬሽን እየተከናወኑ ያሉት ውሃውን የሚያስተላልፉ አራት ካልበርት በሮች ግንባታም በመፋጠን ላይ ነው፡፡ እንዲሁም የግድቡን ውሃ የመያዝ አቅም ከፍ ለማድረግ በ50ሜትር ከፍታ የሚገነባው የኮርቻ ምስል ያለው ግድብ (ሳድል ዳም) ግንባታም እየተፋጠነ ነው፡፡ ግድቡ ሃይል ማመንጨት እንደጀመረ ሃይሉን ለማስተላለፍ የሚያስችል የባለ500 ኪሎ ቮልት የሃይል ማሰተላለፊያ መስመር በመዘርጋት ላይ ሲሆን ግድቡ ከጣና በለስ ሃይል እንዲያገኝ የሚያስችል የማተላለፊያ መስመር ግንባታም በመከናወን ላይ ነው፡፡
ከዚህ ጎን ለጎን መላው የአገራችን ሕዝቦች ለግድቡ ግንባታ የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው ቀጥለዋል፡፡ የመንግስት ሰራተኞች፣ ባለሃብቶች፣ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና መላው ህዝብ የተሻለች አገር ለመገንባት በማሰብ በከፍተኛ ቁርጠኝነት በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ፡፡
በቅርቡ ደግሞ ዜጎችን ግንባታውን ከመደገፍ ባለፈ ባለ ዕድል የሚያደርግ የአጭር መልዕክት /SMS/ ጨዋታ ይፋ ሆኗል፡፡ በዚህ ጨዋታ መሰረት ዜጎች በ8100 ላይ A ብለው በመላክ የእድሉ አሸናፊ ከሆኑ ቤት፣ መኪና፣ ላፕቶፕች፣ የሞባይል ስልክና መሰል ዕጣዎች ያገኛሉ፡፡ ግድቡ መላውን ሕዝብ ከጫፍ እስከ ጫፍ ያስተሳሰረ ፕሮጀክት በመሆኑ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ህዝብ በዚህ መርሃ ግብር በመሳተፍ ላይ ይገኛል፡፡ ከመርሃ ግብሩ ከ300ሚሊዮን ብር በላይ ይገኛል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ግድቡ ፋይዳው ብዙ ነው፡፡ የራስ መተማመን አቅምን በማዳበር ለበለጡ የልማት ስራዎች የሚያነሳሳ ቋሚ ሐውልት ነው፡፡ የዚህ ታሪካዊ ትውልድ አባል በመሆናችን እንኮራለን፡፡
ግድቡ ፋይዳው ብዙ ነው፡፡ የራስ መተማመን አቅምን በማዳበር ለበለጡ የልማት ስራዎች የሚያነሳሳ ቋሚ ሐውልት ነው፡፡ የዚህ ታሪካዊ ትውልድ አባል በመሆናችን እንኮራለን፡፡
ReplyDeletewe begin to finish !!!!!!!!!!!!!!!!!!
ReplyDeleteso let us hold our hands and minds,monies and efforts together then we will finish it and show the world how much we are committed to change our peoples life style