EPRDF is a ruling party committed to realize Ethiopia's Renaissance.

Thursday, 3 May 2018

ትናንት የዛሬ መሰረት ነው


 

ኤፊ ሰውነት
በተለያዩ የታሪክ አጋጣሚዎች ዓለም ግራ በተጋባበት ወቅት ነገን ዛሬ ላይ አሻግረዉ መተለም የቻሉ ባለ ራዕዮች የማንም አካል ድጋፍ ሳያሻቸው ለአገራቸው ብሩህ መጻኢ እድል መፈንጠቅ ወሳኝ የሆነውን እርምጃ በመውሰድ የተረጋጋችና ለሁሉም የተመቸች አገር መፍጠር ችለዋል፡፡ ይህም በጎ ስራቸው በታሪክ ሲወሳ፤ ትውልድም ሲማርበት ይኖራል፡፡ እንደ ሌሎቹ  ሀገራት ሁሉ መሰል የታሪክ ክስተት በእኛም ሀገር ተፈጥሯል፡፡

ወቅቱ 1983ዓ.ም ነው፡፡ የኢፌዴሪ ህገመንግስት እውን ሲሆን ዓለም በዘመመበት ከመዝመም፤ ዓለም በተነፈሰበት ሳምባ ከመተንፈስ ይልቅ በራሳችን መንገድ ለራሳችን የሚበጀንን መንገድ የቀየስንበት፤ ከአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ጋር የሚሄድ የልማትና የዴሞክራሲ መስመር ለይተን ለመጓዝ በታሪክ ፊት አንድ ያልንበት ወቅት ነው፡፡

ከሩብ ምእተ-ዓመት በኋላ አገራችን ዘርፈ ብዙ ሁለንተናዊ እድገት ላይ የምትገኝ፣ የተረጋጋችና  እንዲህ በርካታ የለውጥ ፍላጎቶችን ማስተናገድ የሚችል ቁመና ላይ ከመድረሷ በፊት ዜጎቿ ህልውናቸዉ በመኖርና ያለመኖር አጣብቂኝ ውስጥ በነበረበት ጊዜ አምባገነንነትን ላይመለስ በመቅበርና ዴሞክራሲያዊ ስርዓት እንዲሰፍን ዋጋ የከፈሉ የቁርጥ ቀን ልጆች ትናንት የከፈሉትን ከባድ መስዋዕት ታሪክ መቼም አይዘነጋውም፡፡ ጥቂቶች ግን ሩቅ ህልም የነበራቸው ወላጆች ገና አፍላ የወጣትነት እድሜያቸውን እንኳን በቅጡ ያላጣጣሙ ያውም ባለ በሌለ አቅሙ አስተምሮ ነገ እንደሚጦረው በተስፋ ይጠብቅ የነበር እልፍ አእላፍ፤ ለፍቶ አዳሪ ቤተሰብ ባለበት ዘመን ነው ዛሬን የተሻለ ለማድረግ አፍላ ልጆቻቸውን ወደ ነበልባል እሳት ለመማገድ የቆረጡት፡፡ ለነገሩ ዛሬን በትናንት ውስጥ ማየት ካልተቻለ ጣእሙን እንዴት ማጣጣም ይቻላል፡፡ ነገንስ ያለትናንትና ዛሬ እንዴት ማሳመር ይቻላል፡፡ እናም ዛሬ ትናንት ከነበረው የተለየው፤ ትናንት በተከፈለው መሪር መስዋዕትነት፤ ትናንት በተረጋገጠው ዴሞክራሲያዊ ስርዓት መሆኑ ግልፅ ነው፡፡

ይህን ለፅሁፌ መነሻ ያህል ካልኩ ኢህአዴግ በአገራችን ባለፉት ሁለት ዓመታት እንደ አገር ተጋርጦ የነበረውን አደጋ ለመመከት የወሰዳቸውን ርምጃዎች በወፍ በረር በመዳሰስ ዛሬ ላይ የደረስንበትን ሁኔታና ለድርጅታችን ያለውን አንድምታ እንመለከታለን፡፡ 

የኢሕአዴግ ችግሮችን ነቅሶ የማውጣት ብስለት 

ኢሕአዴግ የ15 የተሃድሶ ዓመታትን አሁን ከደረስንበት ሁለንተናዊ ለውጥ ጋር በማቆራኘት እየገመገመ ባለበት ማግስት በአገራችን የተከሰተው ሁለንተናዊ የለውጥ ፍላጎትን መሰረት ያደረገ ንቅናቄ ሂደቱን በበለጠ ትኩረትና ፍጥነት እንዲካሄድ እድል የሰጠው መሆኑ ይታወሳል፡፡ ሁሌም ቢሆን ችግሮችን ወደ ውስጥ የመመልከት ተፈጥሯዊ ባህሪ ያለው ኢሕአዴግ በወቅቱ የተፈጠሩት ችግሮችን ኢሕአዴጋዊ በሆነ አካሄድ ለመፍታት ያላሳለስ ጥረት አድርጓል፡፡ ለዚህም በግምባሩና በብሄራዊ ድርጅቶች በተናጥል የተለያዩ አካባቢዎች የተነሱ ግጭቶችን መነሻ በማድረግና ከህዝቡ ይነሱ የነበሩ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችንና ማስተካከያዎችን ጭምር በጥልቀት ሲገመግም መቆየቱ ግልፅ ነው፡፡ በወቅቱ ኢሕአዴግ የተሃድሶ እንቅስቃሴውን በተመለከተ ሲሰጥ በነበረው ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳመላከተው ኢህአዴግ ባለፉት የተሃድሶ ዓመታት በስኬት የሚገለፁና ድክመቶቼ ናቸው በሚል ችግሮችን ነቅሶ በማውጣት እርምጃዎችን መውሰድ የጀመረበት ሁኔታ ውስጥ መግባቱ ይታወሳል፡፡ 

በድርጅታችን የተለያዩ ሰነዶች ላይ በግልፅ እንደተመላከቱት የኪራይ ሰብሳቢነት ፖለቲካል ኢኮኖሚ በልማታዊ ፖለቲካል ኢኮኖሚ እስካልተደፈቀ ድረስ አገራችን ልማቷም ሆነ ሰላሟ ብሎም የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ሂደቷ ተሸመድምዶ የመወድቁ ጉዳይ አጠያያቂ አይደለም፡፡ ባለፉት ጊዜያት የተደረጉ የተሃድሶ ግምገማዎችም በአገራችን የተከሰቱት ግጭቶች በተለይ ህገመንግስታዊ የሆነው የሰዎችን ተዘዋውሮ የመስራትና የመኖር መብትን ጭምር የነካ በዚህም በርካታ ዜጎች ለመፈናቀል የተዳረጉበት መሆኑ መነሻው የኪራይ ሰብሳቢነትን ችግሮች መድፈቅ ባለመቻሉ፤ ገና በማደግ ላይ ያለውን የፌዴራሊዝም ስርዓት አዛብቶ በመተርጎም የተለያዩ ሃይሎች ለግጭት መነሻ እንዲሆን ስለተጠቀሙበት መሆኑ ግልፅ ነው፡፡   

ኢሕአዴግም በተሃድሶ ግምገማው እንዳስቀመጠው የኪራይ ሰብሳቢነት፣ የሙስናና የብልሹ አሰራሮች ከዚህ ጋር ተያይዞ ህገ ወጥነት እንዲስፋፋ እያደረጉ ያሉ የኮንትሮባንድ ትስስሮች መሆናቸውን በግልፅ በመስቀመጥ ከእነዚህ ችግሮች ጋር በተያያዘ የሚከሰቱ ህገ ወጥነቶችን ለማስታገስ አስፈላጊውን ትግልና እርምጃ እንደሚወሰድ አፅንዖት ሰጥቶ እንደሚሰራ ማስታወቁ የሚታወስ ነው፡፡ ከዚህ በተመሳሳይ የኢሕአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ባድረጋቸው ስብሰባዎች የወጭ ንግድ፣ የወጣቶች የስራ እድል ፈጠራ አለመጠናከር፣ የመልካም አስተዳደር እጦትና የስልጣን እይታ ብልሽቶች ችግሮች መስተካከል እንደሚገባቸውና ለዚህም መላው አባላትና አመራሩ መስራት እንደሚገባው ማመላከቱ ሁላችንም የምናስታውሰው ነው፡፡ ይህ እንግዲህ ኢህአዴግ እንደ መሪ ድርጅት በአገሪቱ የተጋረጠውን አደጋ እልባት ለመስጠት የወሰደው የመጀመሪያ እርምጃ እንደሆነ መገንዘብ ይቻላል፡፡

ኢሕአዴግ አገር የማስተዳደር ስልጣን በተረከበበት ማግስት አገራችን ለሁሉም ብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች እኩል መብትና እውቅና የሰጠ ህገመንግስት እውን ከማድረግ ባሻገር አገራችን ህግና ስርዓት ባለው መንገድ እንድትመራ ማድረግ ችሏል፡፡ ምንም እንኳ የወጣቶችም ሆነ የሌላው የህብረተሰብ ክፍል የለውጥ ፍላጎትና የፍትሀዊ ተጠቃሚነት ጥያቄ እየጨመረ የመጣ ቢሆንም በአገራችን ዘርፈ ብዙ የለውጥ ስራዎች ተከናውነዋል በዚህም ወጣቶችን ጨምሮ መላው የአገራችን ህዝብ ተሳታፊነቱንና ተጠቃሚነቱን ማረጋገጠ ተችሏል፡፡  እኔ በግሌ ትላንት ከመጣነበት ውስብስብ አገራዊ ሁኔታ አንፃር የተመዘገበው ሁለንተናዊ ለውጥ ከነችግሩም ቢሆን ለነገ መዳረሻችን መሰረት ነው የሚል መረዳት አለኝ፡፡


ዛሬ ላይ አገራችንን ወደፊት ሊያሻግር ይችላል የሚል ውሳኔ ኢህአዴግ እንደከዚህ ቀደሙ ሁሉ አሳልፏል፡፡ ኢህአዴግ ከፅንሰቱም አንአስቶ በጠረጴዛ ዙሪያ ተወያየቶ፣ በሀሳብ ተፋጭቶ፣ ተከራክሮ የጋራ ድምዳሜ ላይ በመያዝ ለአገርና ለህዝብ የሚጠቅም ውሳኔ እያሳለፈ ዛሬ ላይ የደረሰ ድርጅት ነው፡፡ ይህ ባህሉና እሴቱ ዛሬ ጠንክሮና ዳብሮ እየቀጠለ ለመሆኑ ያለፉት ዓመታት ሂደቶች ማሳያዎች ናቸው፡፡ ዛሬም ኢህአዴግ ከህዝብ የተሰጠውን አደራ መሸክም የሚችል የአብዮታዊ ዴሞክራቶች መፈልፈያ ፤ተራማጅ ድርጅት መሆኑን በተግባር እያረጋገጠ ይገኛል፡፡ በዚህ ሂደቱም ህዝብ ሁሌም ቢሆን በድርጅቱ ተስፋ ሳይቆርጥ ድርጅቱን እየደገፈና እያስተካከል የሚሄድ መሆን በተግባር አሳይቷል፡፡

አገራችን ካሳለፈቻቸው በርካታ ውጣ ውረዶች በኋላ አመራሩ መስመራችን እንዲቀጥል በከፈለው መስዋዕትነት ዛሬም አብዮታዊ ዴሞክራሲ በድል አድራጊነት አሸንፎ ወጥቷል፡፡ ዛሬም የመጀመሪያችን መስመራችን ለመዳረሻችን መሰረት መሆኑን ለዓለም ማሳየት ተችሏል፡፡ ኢህአዴግ ህዝብን የማገልገል ብቃትና ሃላፊነትን መውሰድ የሚችል ድርጅት መሆኑንም ህዝባችን ከመቼውም በላይ መተማመን እንዲኖረው ማድረግ ተችሏል፡፡

የኢሕአዴግ ሊቀመንበርና የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚንስቴር ዶክተር አብይ አሕመድ ሰሞኑን በተለያዩ ክልሎች ተዘዋውረው ከህዝብ ጋር ባደረጉት ውይይት አፅንዖት ሰጥተው እንደተናገሩት በአገራችን ለሚመዘገበው ሁለንተናዊ ለውጥ የሁሉም ህዝብ ሁለንተናዊ ተሳትፎ ወሳኝ ነው፡፡ ኢህአዴግ በሰነዶችም በግልጽ ያስቀመጠው ይሄንኑ ነው፡፡ እንደ ትላንቱ ዛሬም በኢሕአዴግ ቤት ህዝብ የድርጅታችን አለቃ ነው፡፡ ትናንት የጨለማውን ጊዜ ማለፍ የተቻለው ከህዝብ ጋር ነው! ዛሬንም የምንሻገረው፤ ነገንም በስኬት ማጀብ የምንችለው ከሀገራችን ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ጋር ነው፡፡ የዚህ የትግል ምእራፍ አንዱ አካል ለመሆን እና አገራችንን ወደተሻለ ምዕራፍ ለማሸጋገር መትጋት የግድ የሚል ይሆናል እላለዉ፡፡ ሰላም!!

 








No comments:

Post a Comment