EPRDF is a ruling party committed to realize Ethiopia's Renaissance.

Monday, 3 April 2017

ከህዳሴው ግድብ ጠንካራ የህዝብ ተሳትፎ የምንማረው




በክሩቤል መርኃጻድቅ
መጋቢት 24ቀን 2003 ዓም አንድ ድንቅ ዜና በሁሉም ዘንድ ተሰማ፡፡ መገናኛ ብዙሃንም ማረፊያቸው የዜናቸው ማድመቂያ ይኽው ዜ ሆነ፡፡ በዚህ ባለንበት 21ኛው ክፍለ ዘመን ኢትዮጵያ አዲስ የታሪክ ባለቤት ለመሆን እየሰራች እንደሆነ በበርካቶች ዘንድ እምነት ተያዘ፡፡ ኢትዮጵያውያንም ያለፉት አያት ቅድመ አያቶቻችን በሰሩት ታሪክ መኩራት ብቻ ሳይሆን መጪው ትውልድ የአሁኑን ትውልድ የሚያደንቅበትና የሚዘክርበት ታሪክ ለመስራት የሚቻልበት ዕድል በመፈጠሩ በፌሽታ ዘለሉ፡፡ በቤሻንጉል ክልል ጉባ ተራሮች መሃል አዲስ ታሪክ ተፃፈ፡፡ የመተባበራችን ተምሳሌት፤ የአንድነታችን ምልክት፤ ድህነትን መስበሪያ መሳሪያችን የሆነው የኢትዮጵያውያን ህዳሴ ግድብ ከዛሬ ስድስት ዓመት በፊት በያዝነው ወር እውን ሆነ፡፡ 

ወርሃ መጋቢት  በልማትና በህዳሴ ዘመንን ትዘበራለች፡፡  በዚህች ወር ከስድስት ዓመታት በፊት በቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ታላቁ መሪ መለስ ዜናዊ የህዳሴው ግድብ የመሰረት ድንጋይ ተጣለ፡፡ ለዘመናት ከኪነ ጥበብ ማድመቂያነት ያልዘለለው የአባይ ወንዝን ታሪክ የሚቀይር የመሰረት ድንጋይ!

የግድቡን ግንባታ ካለ ጠንካራ የህዝብ ተሳትፎ ከዳር ማድረስ አይቻልምና ታላቁ መሪ መለስ ዜናዊ መላው የሀገራችን ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ለህዳሴው ግድብ ግንባታ እውን መሆን የአቅማቸውን አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ ጥሪቸውን አቀረቡ፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብም በአንድ ድምጽ ‹‹ሆ›› ብሎ  በመነሳት ለታሪካውዊ ጥሪ ፈጣን ምላሽ ሰጠ፡፡ የውጭ ወራሪዎችን  በጀግንነት ተዋግቶ በመመከት የደማቅ ታሪክ  ባለቤት የሆነው ህዝብ በሰላም ጊዜ አዲስ የብልጽግና ጀብድ ሊሰራ ተነሳ፡፡

እንደሚታወቀው ቀደምት አያትና ቅድመ አያቶቻችን የሀገራችንን ሉአላዊነት ጠብቀው በማቆየት ደማቅ ታሪክ አውርሰውናል፡፡ በ19ኛው ክፍለ ዘመን አውሮፓውያን አፍሪካን በቅኝ ግዛት በሚቀራመቱበት ወቅት ኢትዮጵያን በቅኝ ለመግዛት የመጣው ወራሪው የጣሊያን መንግስት እንደሌሎች የአውሮፓ ሀገሮች እድል አልቀናውም፡፡ ኢትዮጵያውያን ሉአላዊነታቸውን ለድርድር የሚያቀርቡ አልነበሩምና ወራሪውን ጣሊያን በዓድዋ ላይ ከባድ ሽንፈት አከናነቡት፡፡ እናም የአድዋ የኢትዮጵያውን የአይበገሬነት ዝና በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍ ብሎ እንዲናኝ ሆነ፡፡ የአድዋ ድልም ዓለም ስለኢትዮጵያውያን የሚዘክረው ድንቅ ታሪክ ሆኖ ተመዘገበ፡፡ በእርግጥ ኢትዮጵያውያን ከዓድዋ ጦርነት በፊትም ግብጾችንና ጣሊያኖችን በተደጋጋሚ አሸንፈዋል፡፡ በጉራዕና ጉንደት  የጦር ግንባሮች ኢትዮጵያውን የውጭ ወራሪዎች አሳፍረው መልሰዋል፡፡

እነሆ በዚህ ዘመን የኢትዮጵያ ህዝብ ሌላ አዲስ ታሪክ የሚሰራበት ምዕራፍ ላይ እንገኛለን፡፡  መላው ህዝቡ ጉልበቱን ጊዜውን እና እውቀቱን ለመስጠት የሚረባረብበትና ቋሚ የልማት ሃውልት የሚያቆሙበት አዲስ ምዕራፍ ተከፈቷል፡፡ ለዚህም ነው የመንግስት ሰራተኛው፣ ነጋዴው፣ አርሶ አደሩ…ወዘተ ለግድቡ የአቅሙን ለማድረግ እየተረባረበ የሚገኘው፡፡  

ለዘመናት ኢትዮጵያውያንን የበይ ተመልካች አድርጎ የታችኛው ተፋሰስ ሀገሮች ሲሳይ ሆኖ የኖረው የአባይ ወንዝ በሀገሩ አረፍ ብሎ መብራት አመንጭቶ ጉዞው ይቀጥል ዘንድ ሲወሰን በኢትዮጵያውን ዘንድ ትልቅ ብስራት ሆነ፡፡

አንዳንድ የውጭ ኃይሎች ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሃብቶቿን እንዳትጠቀም የሚያደርጉት ጥረት እንዳለ ሆኖ በውሳጣችን ድክመትም ጭምር በአባይ ወንዝ ላይ ምንም ዓይነት የልማት ስራ ሳይሰራ ቆይቷል፡፡ በውጭ ኃይሎች አፍራሽ እንቅስቃሴ ምክንያት ታላቁን የህዳሴ ግድብ ግንባታ ለማከናወን የሚውል ብድርና እርዳታ ሊገኝ አልቻለምና የህዳሴው ግድብ ግንባታ በኢትዮጵያ መንግስትና ህዝብ ጫንቃ ላይ መውደቁ ግድ ሆነ፡፡ 

በኢህአዴግ የሚመራው ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ መንግስት ምስጋና ይግባውና የአሁኗ ኢትዮጵያ በራሷ አቅም ትላልቅ የልማት ስራዎች ማከናወን የምትችል ሀገር ሆናለች፡፡ በጥንቱ ዘመን ከታላላቅ የዓለም ስልጣኔዎች የሚመደብ ስልጣኔ ባለቤት የሆነች ሀገር  ወደ ነበረችበት የገናና ዘመን ለመመለስ በትክክለኛ መንገድ ላይ መሆኗን የሚያረጋግጡ  ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶች በመገንባት ላይ ናቸው፡፡

በመሆኑም ድሮም ልማትን ተጠምቶ ለቆየው የኢትዮጵያ ህዝብ የህዳሴውን ግድብ ግንባታን ለማሳካት አስተዋጽኦውን አጠናክሮ እየቀጠለ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ ለህዳሴው ጉዞ ያለውን ድጋፍ አጠናክሮ የቀጠለው የታላቁን የህዳሴው ግድብ ፕሮጀክት የተጀመረውን የህዳሴ ጉዞ ለማሳካት ያለውን ትልቅ ፋይዳ በውል በመገንዘቡ ነው፡፡ 

እንደሚታወቀው ህዝብ ያላመነበት ልማት የትም ሊደርስ አይችልም፡፡ አንድ የልማት ፕሮጀክት ከዳር ማድረስ የሚቻለው  ህዝብ ያሳተፈ ሲሆን ብቻ ነው፡፡ 

ህዝብ ሳያምንበት የሚከናወኑ ማናቸውም ስራዎች የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር አመቺ ሁኔታ ሲፈጠር ህዝቡ ራሱ ያፈርሳቸዋል፡፡ ለአብነት በደርግ ወቅት በግዳጅ የተተከሉ የደን ችግኞች፣ የተሰሩ ትምህርት ቤቶች፣ ጤና ጣያዎች..ወዘተ በማህበረሰቡ በራሱ ሊወድሙ ችለዋል፡፡ በግዳጅ እንዲጠበቁ ተደርገው የነበሩት ፓርኮች ስርዓቱ ሲወገድ የግጦሽ ስፍራ ሆነዋል፡፡ እንደ ቆርኪ ያሉት እንስሳትንም አድኖ ገድሎ ለራሱ ጥቅም አውሏቸዋል፡፡

ኢህአዴግና በኢህአዴግ የሚመራው ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ መንግስት በሀገሪቱ በሁሉም መስኮች አስደናቂ ድል እንዲያስመዘገቡ ካስቻላቸው ምክንያቶች አንዱ በሁሉም እንቅስቃሴዎቻቸው ህዝብን አሳምነው ወደ ተግባር የመግባት የዳበረ ልምድ ስላላቸው ነው፡፡ ኢህአዴግ ‹‹ደርግን ማሸነፍ ተራራን እንደ መግፋት ይቆጠራል›› የተባለለትን ስርዓት ማስወገድ የቻለው ትክክለኛ መስመር ስላለው ብቻ አይደለም፡፡ ይልቁንስ  በመስመሩ ዙርያ ከህዝቡ ዘንድ መተማመን ላይ ድርሶ ህዝቡም ያልተቆጠበ ድጋፍ በማድረጉ እንጂ፡፡ 

የሀገሪቱን የኋልዮሽ ጉዞ ቀልብሶ ፈጣን ልማት ማስመዝገብ የቻለው ህዝቡን ከጎኑ በማሰለፉ ነው፡፡ ህዝብን ሳያሳምኑና ከጎን ሳያሳልፉ ፈጣን ልማት ማስመዝገብ ደግሞ የሚታሰብ አይደለም፡፡ እስከ ሩቅ ገጠሮች ጭምር የተስፋፋው የትምህርት ሽፋን፣ የጤና ልማት፣ የተፋሰስ ልማት እና የመሰረተ ልማት ግንባታ የህዝቡ ተሳትፎ የታከለባቸው ናቸው፡፡ የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ሂደቱም ቢሆን ካለ ህዝቡ  ንቁ ተሳትፎ የተመዘገበ አይደለም፡፡ 

መላውን ህዝብ በህዳሴው ግድብ ግንባታ በከፍተኛ የባለቤትነት ስሜት ድጋፍ እያደረገ የሚገኘውም ከፍተኛ የሆነ የመልማት ፍላጎት እያሳደረ በመምጣቱ ነው፡፡ ለዚህም ነው በቢልዮን ብሮች ለግድቡ ግንባታ አስተዋጽኦ ያደረገው፡፡ የህዝቡ አስተዋጽኦ እስከአሁን ሳይቀዘቅዝ መቀጠሉ ደግሞ ህዝብና መንግስት በአባይ ግድብ ግንባታ ዙርያ አንድ ቋንቋ እየተናገሩ መሆናቸውን ያሳያል፡፡ 

አሁን መጠየቅ ያለብን በሌሎች የልማት መስኮችስ ህዝብን አሳምኖ የመስራት ባህሉና ችሎታው በቦታው አለ ወይ? የሚል ነው፡፡ እርግጥ ነው ህዝቡ ለህዳሴው ግድብ የሚያደርገው ጥረት ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡ በሌሎች የልማት ስራዎች እና መልካም አስተዳደርን ለማስፈን በሚደረጉ ስራዎች ግን ቀሪ ስራዎች እንደሚጠብቁ ማጤን ተገቢ ነው፡፡ 

ከህዝቡ የሚነሱ ቅሬታዎች በዋናነት ስራዎቹን በጋራ መተማመን ላይ ደርሶ ካለመስራት የሚመነጩ ናቸው፡፡ በመሰረቱ ከህዝብ ጋር ተማምኖ ለህዝብ የሚጠቅም ስራን ለመስራት ህዝባዊነት መላበስ፣ ከራስ ጥቅም ይልቅ ለህዝብ ጥቅም መቆም፣ ህዝቡ የሚፈልገውን ብቻ ለመፈጸም ቁርጠኛ መሆንን ይጠይቃል፡፡ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በተለያዩ የስልጣን እርከኖች እነዚህ መርሆች እየተጣሱ በመምጣታቸው ህዝቡ ቅሬታን እንዲያሳድር ሆኗል፡፡ 

ልክ እንደ ህዳሴው ግድብ ህዝቡን  በሁሉም የልማትና የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ሂደቶች ላይ በማወያየት እና ግልጽነት በመፍጠር መተግበር ብቻ በህዝቡ ዘንድ የተፈጠሩ የመልካም አስተዳደር ቅሬታዎችን መቀነስ ያስችላል፡፡ እናም በህዳሴው ግድብና በሌሎች ልማቶች የተዘረጉ የህዝቡን እጆች ለሁለንተናዊ ልማቱ ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖራቸው ዘንድ ከህዝብ ጋር ተማክሮና ተማምኖ የመስራት ባህል እንዳይሸረሸር መጠበቅ የግድ ይላል፡፡

No comments:

Post a Comment