EPRDF is a ruling party committed to realize Ethiopia's Renaissance.

Friday, 10 March 2017

ዛሬ ትናንት አይደለም!

(በክሩቤል መርሃጻድቅ)
መሃንዲሱን፣ ሀኪሙን፣ ወዘተየሚፈጥረው መምህር ነው። መምህር የሁሉም ሙያዎች መሰረት ነው፤ መምህርነት ከፍተኛ ኃላፊነት የተጣለበት ክቡር ሙያ ነው። ነገር ግን የሀገራችን የመክፈል አቅም ውስን በመሆኑአስተማሪዎች ክፍያ በቂ አይደለም። የሌላት እናትህ ከየትም ልታመጣ አትችልም። ሀገራችን እያደገች ስትሄድ የእናንተም ኑሮና ጥቅማ ጥቅም እየተሻሻለ ይሄዳል::’’ 
ይህንን ያሉት ታላቁ መሪ መለስ ዜናዊ በአንድ ወቅት ከመምህራን ጋር ውይይትያደርጉ ተገቢውን ጥቅማ ጥቅም ካለማግኘት ጋር ተያይዞ ለቀረበላቸው ጥያቄ የሰጡት ምላሽ ነበር፡፡

እውነት ነው፤ መምህር የለውጥ መሃንዲስ ነው፡፡ በዓለም ከሚገኙ ትላልቅ ድልድዮችና ህንጻዎች፣ ከአስደናቂ የህክምና ውጤቶች፣ ከህዋና የስነ ምድር ጥናትና ምርምሮች ግኝቶች፣ ወዘተ... ጀርባ አስተማሪዎች አሉ፡፡ ምክንያቱም እነዛ ሁሉም ውጤቶች ካለ መምህር ጥረት እዚህ አልደረሱምና፡፡ በሀገራችንም ‹‹መምህር እከሌ›› ሲባል የክብርና የአዋቂነት ምልክት ተደርጎ ነው የሚቆጠረው ለዚህ ነው፡፡
ሀገራችን አሁን ለደረሰችበት ደረጃ የመምህራን አስተዋፆ የማይተካ ነው፡፡ መምህራን ከጫፍ እስከ ጫፍ ባሉ የገጠር መንደሮች በመዝለቅ፣ መንገድና መብራት ተደራሽ ባልሆነባቸው አካባቢዎች ጭምር በመሰማራት የእውቀትን ጮራ ያበራሉ፤ ዜጎችን ከድቅድቅ ጨለማ ያወጣሉ፡፡ በሀገራችን በየደረጃው ባሉ የትምህርት እና የስልጠና እርከኖች እውቀት ገብይተው በተለያዩ መስኮች የተሰማሩ ባለሙያዎች በሙሉ የመምህራን አሻራ ያረፈባቸው ናቸው፡፡ ፈጣኑኢኮኖሚ እድገታችን፣ የመሰረተ ልማት ግንባታችንና ሌሎች አስደናቂ ውጤቶቻችን ደግሞ የመምህራን የድካም ፍሬ የተገለፀባቸው ህያው ምስክሮች ናቸው፡፡
ይሁንና መምህራኖች እንደ አብዛኛዎቹ የሀገራችን የመንግስት ተቀጣሪ ሰራተኞች ሁሉ ተገቢውን ያክል ክፍያና ጥቅማ ጥቅም እያገኙ አይደለም፡፡ ለዚህም ምክንያቱ ሀገራችን ያላት ውስን የመክፈል አቅም ነው፡፡ መምህራን በተለይ ደግሞ ድካማቸውንና ውጤታቸውን የማይመጥን ክፍያ እየተሰጣቸውና ጥቅማ ጥቅማቸውም ሳይከበር ለበርካታ አመታት ኖረዋል፡፡ በኢህአዴግ የሚመራው ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ መንግስት ግን የመምህርነት ሙያ የሌሎች ሙያዎች ሁሉ ምንጭ መሆኑን በመገንዘብ ተገቢውን እውቅና እንዲያገኝ፣ ባለሙያዎቹም የተሻለ ክፍያና ጥቅማ ጥቅም ያገኙ ዘንድ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ይገኛል፡፡ የመምህራን ደመወዝ ከሌላው ሰራተኛ በተወሰኑ እርከኖች ከፍ እንዲል መደረጉ፣ የነፃ የትምህርት እድል በስፋት ተጠቃሚ መሆናቸውና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ የመኖሪያ ቤት ባለቤት የሚሆኑበት ስርዓት መመቻቸቱነና በአዲስ አበባ ነፃ የከተማ ትራንስፖርት ተጠቃሚ መሆናቸው ለዚህ ተጠቃሽ ናቸው፡፡
በያዝነው በጀት አመት መጀመሪያ ለመምህራን የተደረገው የደመወዝ ስኬል ማሻሻያ ደግሞ መምህራን የሰው ኃይልን የመቅረፅ ትልቅ ተልዕኮ ያላቸው መሆኑን ከግምት ውስጥ በማስገባት በልዩ ትኩረት የተፈፀመ ተግባር ነው። ሰሞኑን የፐብሊክ ሰርቪስ ሚኒስቴርና የትምህርት ሚኒስቴር ባወጡት ማብራሪያ መምህራን ካላቸው ትውልድን የመቅረጽ ኃላፊነት አንጻር የሚከፈላቸው ክፍያ ከሌሎች የመንግስት ሰራተኞች የተሻለ እንዲሆን መደረጉን አብነቶችን በመጥቀስ አስረድተዋል። ለምሳሌ ከ9-10ኛ ክፍል ጀማሪ መምህር 3,137 ብር የሚያገኝ ሲሆን የመጀመሪያ ዲግሪ ጀማሪ በሌሎች ተቋሞች 2,748 ብር ነው፡፡ ይህ የሶስት እርከን ልዩነት አለው። አንድ የመሰናዶ ት/ቤት 2ኛ ዲግሪ ያለው ጀማሪ መምህር 4,269 ብር የሚከፈለው ሲሆን 2ኛ ዲግሪ ያለው ጀማሪ ሰራተኛ በሌሎች ተቋማት 3,137 ብር ነው የሚከፈለው። ይህ ሰባት እርከን ልዩነት ያለው ነው። በተመሳሳይ ከፍተኛ መሪ ርዕሰ መምህር 12,112 ተከፋይ ሲሆን በሌሎች የመንግስት ተቋማት ያሉ መካከለኛ አመራሮች (ዳይሬክተር፣ ስራ ሂደት ባለቤት፣ ፅህፈት ቤት ሃላፊ፣ ወዘተ…) የሚከፈሉት ከ10 እርከን በላይ ዝቅ ብለው 7,647 ብር ነው።
ሌላው የመምህራን አንገብጋቢ ጥያቄ የቤት ጉዳይ በመሆኑ መንግስት የቤት ችግርን ለመፍታት በሚያከናውናቸው ጥረቶች ከሌላው ህዝብ ጋር በጋራ ተጠቃሚ መሆናቸው እንደተጠበቀ ሆኖ መምህራን በተለየ ሁኔታ ተጠቃሚ የሚሆኑበት መርሃ ግብር ስራ ላይ ውሏል፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሰሞኑን በከተማዋ ለሚገኙ መምህራን 5 በላይ ቤቶች በቅናሽ ኪራይ አቅርቧል፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመንግስት ትምህርት ቤቶች የሚያስተምሩ 16 798 መምህራን በእጣው የተካተቱ ሲሆን በአሁኑ ዙር ዕድለኛ የሆኑ መምህራን ባለ ስቱዲዮ 1 402 ቤቶች ባለ አንድ መኝታ ቤቶች 2 895 እና ባለሁለት መኝታ 703 መኖሪያ ቤቶች እንደየቤተሰባቸው ብዛት የሚያገኙ ይሆናል። የከተማዋ አስተዳደር ይህንኑ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጧል፡፡ በተመሳሳይ ክልሎችም የመምህራንን የቤት ችግር ለመፍታት ጥረት ማድረግ ጀምረዋል፡፡ የትግራይና የአማራ ክልሎች  ለመምህራን  መሬት ከሊዝ ነጻ ለማቅረብ አቅደዋል፡፡ 

ከላይ ከቀረቡ አብነቶች መገንዘብ እንደምንችለው ምንም እንኳን አሁን እያደገ መሄድ ያለበት ቢሆንም መምህራን ከፈጣን ኢኮኖሚያዊ ዕድገቱ ለአስተዋፆዋቸው የሚመጥን ጥቅም ማግኘት ጀምረዋል፡፡ መንግስትም መምህራንን ይበልጥ ተጠቃሚ ለማድረግ ጥረቱን አጠናክሮ ቀጥሏል፡፡ በአጠቃላይ ዛሬ ትናንት አይደለም፡፡ ዛሬ የመምህራንን ችግር ለመፍታት የቆረጠ መሪ ድርጅትና መንግስት አለ፡፡ መምህራን የልፋታቸውን ዋጋ እንዲያገኙ የሚያስችል ፈጣን ኢኮኖሚያዊ ዕድገትም እየተመዘገበ ነው፡፡ ይሁንና የመህራንን ችግር በአንድ ጀምር የሚፈታ አለመሆኑ መገንዘብ ይገባል፡፡ ዋናው ነገር ከምንም ጊዜውም በላይ የመምህራንን ኑሮ ለማሻሻል የተሟላ ቁርጠኝነትና ዝግጁነት ያለው መንግስትና መሪ ድርጅት መኖሩ ነው፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ሰሞኑን ከዚህ በፊት የደመወዝ ማስተካካያ ላልተደረገላቸው የመንግስት ተቋማት የደመወዝ ማስተካከያ መደረጉን ተከትሎ አንዳንድ ኃይሎች ጉዳዩን አውገርግረው በማቅረብ የፖለቲካ ትርፍን ለማጋበስ ላይ ታች በማለት ላይ ይገኛሉ፡፡ የመምህራን የደመወዝ ስኬል ማስተካከያ የተደረገው ከስድስት ወራት በፊት ባለፈው ሐምሌ ወር 2008 ዓም ነው፡፡ አሁን ደግሞ በዛን ወቅትም ሆነ ከዛ ቀደም ብሎ ማስተካከያ ላልተደረገላቸው ተቋማት የደመወዝ ስኬል ማስተካከያ ተደርጓል። ይሄም ሆኖ አሁንም ከላይ እንደተጠቀሰው የመምህራን ደመወዝ ከሌሎች የመንግስት ሰራተኞች የተሻለ መሆኑ ግልፅ ነው፡፡
ከጥር ወር 2009 ጀምሮ ማስተካከያ የተደረገው ከአሁን በፊት የደመወዝ ስኬል ማስተካከያ ላልተሰራላቸው ሌሎች የመንግስት ተቋማት ሆኖ ሳለ ግነ መምህራንን ያገለለ የደመወዝ ጭማሪ እንደተደረገ አስመስለው የሚያቀርቡና በመምህራንና በህዝቡ ውስጥ ውዥንብር ሲፈጥሩ የሚታዩ አሉ። ጸረ ሰላም ኃይሎች የተለያዩ አሉባልታዎችን በማራገብ መምህሩ በእነርሱ የጥፋት መረብ ውስጥ እንዲገባ የሚያደርጉት ጥረት መንግስት የመምህራንን ጥቅም ለማስጠበቅ እየወሰዳቸው ያሉ በጎ ጅምሮችን በዜሮ ለማጣፋት እና የመማር ማስተማር ሂደቱን ለማሰናከል ሆን ተብሎ የሚፈፀም እኩይ እንቅስቃሴ ነው።

በኢትዮጵያን የህዳሴ ጉዞ ላይ ደማቅ አሻራቸውን እያስቀመጡ የሚገኙ መምህራን ለእንደዚህ አይነት አሉባልታዎች ጆሮ ባለመስጠት ዛሬም እንደትላንቱ አኩሪ ተልዕኳቸውን አጠናክረው መቀጠል አለባቸው፡፡ ታላቁ መሪ እንደተናገሩት ሀገር ሲለወጥ የእነርሱም ኑሮም እንደሚለወጥ በተግባር እየታየ ነውና በመምህራን ስም የፖለቲካ ቁማር መጫወት ለሚሹ ሃይሎች ዛሬ ትናንት እንዳልሆነ ሊነግሯቸው ይገባል።

1 comment:

  1. ክልሎች ስትሉ እንዴት አማራና ትግራይ ተፈንጥረዉ ወጡ??? አቅርቦቱስ ምነዉ መሬት ብቻ ሆነ? እርግጥ ነዉ ቤት ገንብቶ ማስርከብ የክልሉ የአቅም ጉዳይ ይሆናል ሆኖም አቅም ያላቸዉ ክልሎችስ???ለምሳሌ ኦሮሚያ፡ ደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች! በዚ መሃልስ ኪሳቸዉን ለማደለብ #ስታንድባይ ሆነዉ ይሉትን ዝሆኖች ለመጠበቅስ ምን ዝግጅት አድርጋቹዋል???

    ReplyDelete