በኤፊ ሰውነት
ወጣትነት ለነገ መሰረት የሚጥሉበት፤ የእርጅና ጊዜዎ በሃሴት እንዲያልፍ የሚተጉበት ሁሉን
ማሰብ ማቀድና መከወን የሚችሉበት የጉብዝና ጊዜ ነው፡፡ ወጣትነት ያሰቡትን ሁሉ ማድረግ እንደሚችሉና አንዳንዴም በአዕምሮ
የመጣን ነገር ሁሉ ለማስተናገድ የሚራወጡበት፤ ህልምዎን ለማሳካት አማራጭ ያሉትን መንገድ ሁሉ የሚጠቀሙበት የትኩስነት ወቅትም
ነው፡፡ ወጣትነትን ሁሉም የሚደርስበትና የሚያልፍበት በመሆኑ ከራስ ሁኔታ በመነሳት ብቻ ስለወጣትነት ብዙ ማለት አያዳግትም፡፡
ይህ እውነታ እንዳለ ሆኖ ወጣትነት ብስለት በተሞላበት ሁኔታ መመራት የሚገባው የእድሜ ክልል መሆኑም አያጠያይቅም፡፡ ይህን የትኩስነት
ጊዜ ረጋና ሰከን ብሎ ወጣት በመሆን ብቻ የሚገኝን ብርታትና ጉጉት ወደ መልካም ሁኔታዎች መቀየር ግድ የሚል ይሆናል፤ ወጣትነት
በቅጡ ካልተመራ ጥፋትም ሊሆን ይችላልና፡፡
ይህን ካልኩ በአገራችን ታሪክን ስለቀየሩ ወጣቶችና ዛሬም ታሪክ እየቀየሩ ስላሉ የዘመናችን
ብሩሃን አንዳንድ ነገር ማንሳት ፈለኩኝ፡፡ መቼም ትናንት ከሌለ ዛሬ፤ ዛሬ ከሌለ ደግሞ ነገ የለምና እናንተንም ወደ ትናንት
ልመልሳችሁ ግድ ሆኗል፡፡ ከዛሬ ሃያ አምስት ዓመታት በፊት በደርግ ዘመነ መንግስት፤ ከዛሬ ሰላሳና አርባ ዓመታት በፊት ደግሞ የአፄ
ሃይለስላሴ ዘመነ መንግስትን በዓይነ ህሊናችን ስናስታውስ የወጣትን ህዝባዊነትና አገር የመለወጥ ሃይል በተጨባጭ መመዘን
ያስችለናል፡፡ እነዛ ወጣቶች ምን ያህል በአገራቸው ያልነበረውን የእኩልነትና በአገር ሃብት እኩል የመጠቀም መብት ለማረጋገጥ መስዋዕት
እንደከፈሉና እንደተሳካላቸውም እናያለን፡፡ የመሬት ላራሹ ንቅናቄን ጨምሮ የአገራችን ምሁራንና አርሶ አደር ወጣቶች ለመላው
የአገራችን ጭቁን ህዝብ ነፃነት የከፈሉትን ተጋድሎ ማሰብ የወጣትን ሃያልነት ለመረዳት ቀላል ነው፡፡
የቅርቡን ብናነሳም የህዝብ ሸክም በጫንቃቸው የተሸከሙ፤ የህዝብ ህመም ህመማቸው የሆኑ
ጥቂት የአገራችን ወጣቶች የዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸው፤ ፓይለትነት፣ መሃንዲስነትና ዶክተርነት ሳያጓጓቸው የአገራችን ጭቁን ህዝብ
እየከፈለው ያለው ዋጋ እንቅልፍ ቢነሳቸው ሁሉን እርግፍ አድርገው የህዝብን ትግል በመምራት በከፈሉት መስዋዕትነት ሩቅ
የመሰለውን ቅርብ ከባድ የመሰለውን ቀላል አድርገው በእልህ አስጨራሽ ትግልና በመሪር ተጋድሎ የአገራችን ህዝብ የሰላም አየር
እንዲተነፍስ መብቱና ነፃነቱ ህገ መንግስታዊ እውቅና እንዲያገኝና አገራችን ብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች ተከባብረውቧት የሚኖሩ
የመፈቃቀድና የመተባበር አገር እንድትሆን አስችለዋል፡፡
የዛሬዋ ኢትዮጵያ ከትናንት የተለየች እንድትሆን ያደረጉ የትናንት ወጣቶች ናቸው፡፡ ዛሬ
በአገራችን ያለው የኢኮኖሚያዊ ማህበራዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችና ነፃነቶች መከበር የቻሉት የትናንት ወጣቶች መላው የአገራችንን
ህዝብ አስተባብረው ለድል በማብቃታቸው ነው፡፡ ይህ እውነታ ወጣቶች ሁሌም ቢሆን በአገራቸው የትናንትና የዛሬ ታሪክ ውስጥ በማይጠፋ
ማዕተም የተፃፈ ታሪክ ባለቤትና ባለውለታ ብሎም ወጣቶች በአገራቸው ጉዳይ ሁሌም ቢሆን የማይደራደሩ መሆናቸውን የሚያረጋግጥ
ተጨባጭ ማሳያ ነው፡፡
የዛሬ 25 ዓመት በህዝብ ትግል፤ በቆራጥ
ወጣቶች መሪነት አምባገነንና በተለይ ለወጣቶች ፈፅሞ የማይመቸው ስርዓት ተገርስሶ በምትኩ ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ ድርጅት የሆነው
ኢህአዴግ አገር የማስተዳደር ስልጣን ከተረከበ በኋላ ከህገ
መንግስቱ ጀምሮ የተለያዩ ህጎች፣ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች እንዲሁም አሰራሮችና አደረጃጀቶች ሁሉ የወጣቶችን ተሳትፎና ተጠቃሚነት
የሚያረጋግጡ ሆነው ተቀርፀዋል፡፡ በዚህም ባለፉት 25 ዓመታት በአገራችን ቀላል የማይባል ቁጥር ያለውን ወጣት በሁለንተናዊ
መልኩ ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል፡፡ የወጣቶችን ጉዳይ የሚከታተል መዋቅር ከፌዴራል ጀምሮ እስከ ወረዳ ድረስ በመዘርጋትም የወጣቶችን ተሳትፎና
ተጠቃሚነት የሚያጎለብት ተግባር ተፈፅሟል፡፡
ኢህአዴግ የሚመራው ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ መንግስት ባለፉት ዓመታት ለወጣቶች ልዩ ትኩረት
በመስጠት ባከናወናቸው ተግባራት በገጠር ወጣቶች በግብርናና ከግብርና ውጭ ባሉ የስራ አማራጮች ሰፊ የስራ እድል እንዲፈጠርላቸውና
የኢኮኖሚ አቅማቸውን በማሳደግ ህይወታቸው እንዲለወጥ ተደርጓል፡፡ በከተማም የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ልማት
ስትራቴጂን በመቅረፅና ተግባራዊ በማድረግ ወጣቶች በአምስቱ የእድገት ተኮር ዘርፎች ተሰማርተው ተጠቃሚ እንዲሆኑ በመደረጉ ቁጥራቸው
የማይናቅ ወጣቶችም ወደ መካከለኛ ባለሃብትነት በመሸጋገር ከራሳቸው አልፈው ህብረተሰባቸውንና አገራቸውን መጥቀም የሚችሉና ለሌሎች
አርዓያ መሆን የሚችሉ ወጣቶች ማፍራት ተችሏል፡፡
ከዚህ ባሻገር የአርብቶ አደርና ከፊል አርብቶ አደር ወጣቶችን ዘርፈ ብዙ ችግሮች ለመፍታት
የማህበረሰቡን የአኗኗር ዘይቤ መሰረት ያደረጉ የኢኮኖሚ፣ የማህበራዊና የፖለቲካ ስራዎች በመከናወናቸው በተበታተነ ሁኔታ ሲኖሩ
የነበሩትን የአርብቶ አደርና ከፊል አርብቶ አደር ወጣቶች መሰረታዊ ችግሮች የማቃለልና ቋሚ የአኗኗር ዘይቤ እንዲከተሉ ማድረግ
ተችሏል፡፡
ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ አሁንም የወጣቶችን ተሳትፎና ተጠቃሚነት
በሁለንተናዊ መንገድ ከማጎልበት አኳያ ብዙ የሚቀሩ ስራዎች እንዳሉ እሙን ነው፡፡ በተደጋጋሚ እንደሚገለፀው ከጠቅላላው
የአገራችን ህዝብ ከሰላሳ በመቶ በላይ የሚሸፍነው አምራች ወጣት የህብረተሰብ
ክፍል ነው ይህ አሃዝ የሚያመላክተው አገራችን ኢትዮጵያ የወጣቶች አገር መሆኗን ጭምር ነው፡፡ በመሆኑም ዘላቂ
ልማትና ቀጣይነት ያለው ዴሞክራሲ ለማረጋገጥም ሆነ የኢትዮጵያን ህዳሴ እውን ለማድረግ የወጣቶችን ተሳትፎ ማሳደግና
ተጠቃሚነታቸውንም ማረጋገጥ ወሳኝ ጉዳይ ነው፡፡ ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ መንግስታችን ይህን እውነት በቅጡ በመገንዘብ ለወጣቶች ልዩ
ትኩረት ሰጥቶ ባለፉት ዓመታት ብሄራዊ የወጣቶች ፖሊሲ እና የወጣቶች የእድገት ፓኬጆችን በማዘጋጀትና የአሰራር ስርዓት
በመዘርጋት ተግባራዊ ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ በያዝነው በጀት ዓመትም መንግስት የወጣቶችን ተሳትፎ የማጎልበትና ተጠቃሚነታቸውንም የማረጋገጥ
ጉዳይን በልዩ ሁኔታ በመያዝ ከፍተኛ ርብርብ በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡
በአገራችን አሁን ያለው ነባራዊ ሁኔታ እንደሚያረጋግጠው ማንኛውም ዜጋ በነፃነት የመስራት
የፈለገውን ያህል ሃብት የማፍራት ነፃነቱ የተጠበቀ በመሆኑ ወጣቶችን ጨምሮ በርካታ ዜጎች ተጠቃሚ መሆን ችለዋል፡፡ በገጠርም
በከተማም ሚሊዬነር የሆኑ ወጣት ባለሃብቶችን ማፍራት ተችሏል፡፡ ምርትና አገልግሎታቸውን ወደ ውጭ መላክ የጀመሩ የጥቃቅንና
አነስተኛ ተቋማት ሚሊዬነር አንቀሳቃሾችም ያለፉት ዓመታት ትሩፋቶች ናቸው፡፡ ከራሳቸው አልፈው ቤታቸውን ቤተሰባቸውንና
ህብረተሰባቸውን መጥቀም የጀመሩ ወጣቶች ቁጥር ቀላል አይደለም ይህ መጠናከር ያለበት መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ በራሱ ግን ቀላል
ውጤት ተደርጎ አይወሰድም፡፡ ወጣቶች ህገ መንግስታዊ መብታቸውን በመጠቀምና ከአቻዎቻቸው ጋር በመደራጀት መብቶቻቸውን
የሚጠቀሙበት ስርዓት እውን መሆኑ የወጣቶች የፖለቲካ ተሳትፎና የውሳኔ ሰጭነት ሚናን ከማሳደጉ ባሻገር ችግራቸውን በራሳቸው
መንገድ ተወያይተው የሚፈቱበትን ሰፊ እድልም የፈጠረ መሆኑን ካለፉት ዓመታት ተጨባጭ ውጤቶች መገንዘብ ይቻላል፡፡
ውድ አንባብያን ኢህአዴግ የሚመራው ልማታዊና ዴሞከራሲያዊ መንግስት የወጣቶችን ተሳትፎና
ተጠቃሚነት ለማጎልበት እንቅፋቶች ሁሉ መወገድ እንደሚገባቸው ያምናል፡፡ በአድሎአዊና ግልፅ ባለሆነ አፈፃፀም የሚፈጠሩ
መስተጓጎሎችንም ሆነ ሌሎች በአገልግሎት አሰጣጥ በኩል ያሉ የመልካም አስተዳደር እንቅፋቶችን ጨምሮ የወጣቶችን የፋይናንስና
የክህሎት ክፍተትን ለመሙላት እየተሰራ ይገኛል፡፡ ወጣቶች ስራ ፈጣሪ ከመሆንም
ይሁን በተፈጠረው የስራ እድል ከመጠቀም አኳያ ያለባቸውን የአመለካከትም ሆነ የአሰራር ማነቆ ለመፍታት መንግስት ከመቼውም ጊዜ
በተሻለ መልኩ እየሰራ ይገኛል፡፡ ወጣቶች በተለያየ ጊዜ የሚያነሱትን የተሳትፎና የተጠቃሚነት ጥያቄ ደረጃ በደረጃ ለመመለስም
ጥረት እያደረገ ይገኛል፡፡ ከዚህ አኳያ ከጊዜው ጋር የሚሄድና የወጣቶችን የተጠቃሚነት ደረጃ የሚያሳድግ ፓኬጃና ማስፈፀሚያ
ስትራቴጂ ወጥቷል፡፡ በያዝነው ዓመት ተሻሽሎ የወጣው ይህ የኢትዮጵያ ወጣቶች የልማትና የእድገት ፓኬጅና ስትራቴጂ እንዲሁም
አሰራሮችን ለመተግበር እየተወሰደ ያሉ ሌሎች እርምጃዎች የልማታዊ መንግስታችንን ቁርጠኝነት የሚያመላክቱ ናቸው፡፡
ሁላችንም እንደምናውቀው በ1998 እና በ2002 አጠቃላይ ከወጣቶች ብሄራዊ ፖሊሲና ህገ
መንግስት መርሆዎች ጋር የተቃኘ የወጣቶች ፓኬጅና የእሱ ማስፈፀሚያ ስትራቴጂ ወጥቶ ተግባራዊ ተደርጓል፡፡ በዚህም በርካታ
ወጣቶችም ተጠቃሚ መሆን ችለዋል፡፡ በያዝነው በጀት ዓመት ደግሞ ይህን በማሻሻልና በመከለስ የኢትዮጵያ ወጣቶች የልማትና
የእድገት ፓኬጅና ስትራቴጂ ተቀርፆ ወጣቶች ግንዛቤ እንዲይዙበት ስልጠና በመሰጠት ላይ ይገኛል፡፡ የጉዳዩ ባለቤት የሆኑ ወጣቶች
በፓኬጁና በስትራቴጂው ላይ እውቀት እንዲጨብጡና አለ የሚሉትን ተግዳሮትና ቀጣይ አቅጣጫዎችን የሚያመላክት ውይይት የሚያደርጉበት
እድል መመቻቸቱም የመንግስትን ህዝባዊነት የሚያረጋግጥ መሆኑ ለሁላችንም ግልፅ ነው፡፡
በሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሰቲ እየተሰጠ ባለው ስልጠና ተሳታፊ ወጣቶች በፓኬጁና ስትራቴጂው አጠቃላይ አፈፃፀምና ያለፉ ልምዶች ላይ ተንተርሰው ጥያቄዎችን በማንሳትና
ውይይት በማድረግ የጋራ መግባባት ፈጥረዋል፡፡ በፀጥታ ዘርፍ የሚታዩ የአፈፃፀም ችግሮች፣ የስራ እድል ፈጠራ በቂ አለመሆንና፣
ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር፣ በጥቃቅንና አነስተኛ የስራ መስክ ላይ የሚታዩ ተግዳሮቶችና መሰል ጉዳዮች ላይ አለ የሚሉትን ሃሳብ
ከፓኬጁ በመነሳት የሰነዘሩ ሲሆን የወጣቶችና ስፖርት ሚንስቴር የሆኑት አቶ ርስቱ ይርዳው ለወጣቶቹ ምላሽ በመስጠት በቀጣይ በጋራ መስራት እንደሚገባ አመላክተዋል፡፡
አቶ ርስቱ ወጣቶች አለ ብለው ያነሷቸው ችግሮች
በመሰረታዊነት በአፈፃፀም የሚታዩና መንግስትም መቀረፍ ያለባቸው ችግሮች መሆናቸውን አስቀምጦ እየሰራበት መሆኑን
አስገንዝበዋል፡፡ በተለይ ከፀጥታ ሃይሉ ጋር ተያይዞ የተነሳው በማስተማርና በመገምገም እንዲሁም እርምጃ በመውሰድ ጭምር
መንግስት የማስተካከያ ተግባራትን እየፈፀመ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ በተጨማሪም ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውርን በተመለከተ አሰራር
ከመዘርጋት ባለፈ በዚህ ተግባር ላይ የተሰማሩ የህብረተሰብ ክፍሎችን ከህዝቡ ጋር በመሆን በመለየት እርምጃ እየተወሰደ መሆኑን
አመላክተዋል፡፡ በተመሳሳይ የስራ እድል ፈጠራውን ለማስፋትና የፋይናንስና የክፍሎት ክፈተቱንም ለመሙላት መንግስት የአስር
ቢሊዮን ብር ተዘዋዋሪ ፈንድ ከመመደብ ጀምሮ የተለያዩ እርምጃዎችን እየወሰደ መሆኑን አቶ ርስቱ ለሰልጣኞቹ ተናግረዋል፡፡
ኢህአዴግ የሚመራው ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ
መንግስት ፓኬጁን መከለስ የፈለገበት ዋናው ዓላማም የወጣቶችን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማሳደግ በመሆኑ በፓኬጁ ያሉትን መልካም
እድሎች አሟጦ በመጠቀምና በአፈፃፀም የሚታዩ ክፍተቶችንም በጋራ በመታገል ለተግባራዊነታቸው ሁሉም ወጣት በእኔነት መንፈስ ሊሰራ
ይገባል የሚል እይታ አለኝ፡፡ የወጣቶች ችግር ጊዜ የማይሰጥና
የተቀናጀ መፍትሄ የሚጠይቅ ጉዳይ በመሆኑ መንግስት በየጊዜው እያደገ የመጣውን የወጣቶች ቁጥርና የወጣቶች ወቅታዊ ጥያቄን በማጤን
አገራችን ከደረሰችበትና ልትደርስበት ካቀደችው የእድገት ደረጃ ጋር የሚጣጣሙ ፕሮግራሞችን መንደፉ ይበል የሚያሰኝ ተግባር መሆኑ
አያጠያይቅም፡፡ በመሆኑም የወጣቶችን ተሳትፎና ተጠቃሚነታቸውን በማሳደግ የአገራችንን እድገት ማረጋገጥ ለቀጣይ መሰረት የሚጥል በመሆኑ
ወጣቶችም ሆነ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል በዚህ መንፈስ በመረዳት ፓኬጁ መሬት ሲወርድ ሳይሸራረፍ እንዲተገበር መታገል ይጠበቃል፡፡
ውድ አንባብያን የወጣቶችን ተሳትፎና ተጠቃሚነት
በተመለከት እስካሁን ያሉትን መልካም ልምዶች በማጎልበት ክፍተቶችን ደግሞ በመሙላትና ወደ ተሻለ ምዕራፍ በማሸጋገር ሁሉም ዜጋ
በተለይ ወጣቶች በተረጋጋና ብስለት በተሞላበት መንፈስ ነገን ያማረ ለማድረግ መታገል ይኖርባቸዋል፡፡ ነገ የሚያምረው የአገራችን
ሰላሳ በመቶ የሚሆነው ወጣት የራሱን ተሳትፎና ተጠቃሚነት በማሳደግ ለህብረተሰቡና ለአገሩ ለውጥ መስራት ሲችል ነውና ወጣትንትን
መጠቀም ብሩህና የበለፀገች ኢትዮጵያን መገንባት በመሆኑ በዚህ መንፍስ መስራት ግድ የሚል ይሆናል፡፡ ወጣቱ ትውልድ የነገ አገር
ተረካቢ ብቻ ሳይሆን የአገራችንን ህዳሴ እውን ለማድረግ በሚካሄደው ዘርፍ ብዙ ርብርብም ያለውን እምቅ እውቅት፣ ክህሎቱንና
ጉልበቱንም ጭምር በተገቢው መንገድ ለተገቢው ሁኔታ በመጠቀም የማይተካ ሚናውን ሊጫወት ይገባል፡፡ ወጣቱ የአገራችን ህዳሴ
መሰረት መሆኑን በማመን አገራዊ ኃላፊነቱንም ጭምር በቁርጠኝነት ለመወጣት ዝግጁ ሊሆን ይገባል ባይ ነኝ፡፡ ሰላም፡፡
ያለ ወጣቱ የተሟላ ተሳትፎና ተጠቃሚነት
የተጀመረውን ፈጣንና ተከታታይ የኢኮኖሚ እድገት ማስቀጠልና የአገራችንን ህዳሴ እውን ማድረግ አይቻልም!
No comments:
Post a Comment