(በአደም ሓምዛ)
በሀገራችን የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ሂደት ፈተና ሆነው ከሚታዩ ጉዳዮች መካከል የትምክህትና የጠባብነት አስተሳሰቦች የራሳቸውን ድርሻ ይዘው ይገኛሉ፡፡ የሀገራችን ዴሞክራሲያዊ የፌዴራሊዝም ስርዓት ገና በትንሽ እድሜው በርካታ ትሩፋቶችን የማጎናጸፉን ያክል መነሻቸው የትምክህትና የጠባብነት አስተሳሰቦች በሆኑ በርካታ ፈተናዎች ምክንያት በተለያዩ ጊዜያት በተጋረጡበት አደጋዎች ሀገራችንና ህዝቦቿ ያልተገባ መስዋዕትነት እንዲከፍሉ መዳረጋቸውን እናያለን፡፡
በተለያዩ አካባቢዎች በአመለካከት ደረጃ ለሚስተዋሉም ይሁን ምቹ ሁኔታዎችን ተገን አድርገው ለሚፈፀሙ የትምክህተኝነትና የጠባብነት አስተሳሰብና ተግባር መፈጠር ዋና ምክንያት ቀደም ሲል በሀገራችን የነበሩት ገዢዎች የተከተሉት ፀረ ዴሞክራሲያዊና አድሏዊ አስተዳደር ጥሎት ያለፈው ጠባሳ ነው፡፡ እነዚህ የተሳሳቱ አመለካከቶች በሀገራችን ሁሉንም ዜጋ በእኩልነት ተሳታፊና ተጠቃሚ የሚያደርግ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት እየተፈጠረ በሚገኝበት ሁኔታም እንኳን ለዴሞክራሲያዊ ስርዓቱ አደጋ ሆነው ይታያሉ፡፡
በመሆኑም እነዚህን አስተሳሰቦች በሚገባ ታግሎ ማሸነፍ በመላ ህዝቦች መፈቃቀድ ላይ ተመስርቶ ተግባራዊ እየተደረገ ያለውን የሀገራችንን ዴሞክራሲያዊ ፌዴራሊዝም የበለጠ እንዲጎለብትና ሁሉንም ህዝቦች ፍትሃዊ በሆነ መንገድ ያሳተፈ ልማትና ብልፅግና በማምጣት አንድ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማህበረሰብ ለመፍጠር ያለው ፋይዳ እጅግ ከፍተኛ ነው፡፡
በሀገራችን የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ የአንበሳውን ድርሻ በመያዝ አንባገነናዊውን ስርዓት ለማስወገድ የትጥቅ ትግል በማድረግና ቀጥሎም በህዝብ ይሁንታ በተመሰረተ ዴሞክራሲያዊ የመንግስት አስተዳደር እስካሁንም ትልቁን ሚና በመጫወት ላይ የሚገኘው ኢህአዴግ ገና ከጅምሩ አንስቶ የትምክህትና የጠባብነት አስተሳሰቦች ለሀገራችን የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ዋነኛ አደጋዎች መሆናቸውን ተረድቶ አስተሳሰቦቹን መሰረት ያደረገ ትግል በማካሄድ ላይ ይገኛል፡፡ መላ የሀገራችን ህዝቦች እነዚህ አመለካከቶች ለአብሮነታቸውና በጋራ ለሚገነቧት አዲሲቷ ኢትዮጵያ የማይጠቅሙና አፍራሽ መሆናቸውን ተገንዝበው እንዲያወግዟቸውና ህዝባዊ መሰረት እንዲያሳጧቸውም አስተሳሰቦቹን በግልፅ ለይቶ በመተንተንና መታገያ አቅጣጫ በማስቀመጥ ሲታገል ቆይቷል፡፡
ሆኖም ኢህአዴግ ሲያከናውናቸው የነበሩ ተግባራት በተግዳሮቶችና ውጣ ውረዶች የተሞሉ እንጂ የስኬትን ጫፍ የረገጡ አይደሉም፡፡ ለዚህ አንዱ መገለጫ የሚሆነው እነዚህ የኪራይ ሰብሳቢነት መገለጫ የሆኑ አስተሳሰቦች ትግሉን መቋቋም ሲያቅታቸውና በተግባር እየተደፈቁ ሲሄዱ አንገታቸው ቀብረው ይከርሙና በአመለካከቶቹ ላይ የሚደረገው ትግል ሲቀዛቀዝ ደግሞ መልሰው ማንሰራራት መቻላቸው ነው። ከዚህ አንፃር መታየት ያለበት ሌላው ጉዳይ የእነዚህ አስተሳሰቦች አራማጆች ባልተቋረጠ አጥፊ ዘመቻቸው የተለያየ የማደናገሪያ ስልቶችን ተጠቅመው የተወሰኑ የህብረተሰብ ክፍሎችን የአስተሳሰባቸው ሰለባና ተሸካሚ በማድረግ ከሀገሪቱ እድገት በተቃራኒው እንዲሰለፉ ማድረጋቸው ነው፡፡
ሌላውና በተለይም አሁን ላይ እየታየ እንዳለው እነዚህ በሁለት ፅንፍ ላይ የሚገኙ አስተሳሰቦች በመሰረታዊ ባህሪያቸው አንዳቸው ሌላኛውን በዋና ጠላትነት የሚፈርጁ ቢሆኑም የጋራ ግንባር ፈጥረው በስርዓታችን ላይ የጋረጡት ፈተና ነው። እነዚህ የማይታረቁ አጀንዳዎች ያሏቸው ሃይሎች በጋራና በተናጠል በሚያካሂዱት ዘመቻ ህብረተሰቡን በማደናገርና አንዳንዶችንም የጥፋት መሳሪያቸው በማድረግ ለዜጎች ህይወት ማለፍ፣ ለአካል መጉደልና ለንብረት መውደም ብሎም ለአካባቢያዊ አለመረጋጋት ምክንያት ሆነዋል። እስካሁን የደረሰው ጉዳት ቀላል ባይሆንም ህዝብና መንግስት በአንድ ላይ በመሆን በሚያደርጉት ብስለትና ትዕግስት የተሞላበት እንቅስቃሴ ውጥናቸው በመክሸፉ ድብቅ አጀንዳቸውን ያሰቡትን ያክል ሳይሳካላቸው ቀርቷል፡፡
ነገር ግን ዛሬም ሆነ ወደፊት እነዚህ የትምክህትና ጠባብነት አስተሳሰቦች እየተንፏቀቁም ቢሆን ከጥፋት ተልዕኳቸው የማይቦዝኑ በመሆናቸውና የተለያዩ ስልቶችንና ምቹ ሁኔታዎችን እየተጠቀሙ የትርምስ አጀንዳቸውን ለማሳካት መጣራቸው ስለማይቀር መላ የሀገራችን ህዝቦች ከመንግስት ጋር በመሆን ልንመክታቸውና በምትኩ ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ ስርዓታችን እንዲጎለብት፣ ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት እንዲያብብ ድርሻችንን መወጣት አለብን።
የሀገራችንን እድገትና ብልፅግና ወደ ላቀ ምዕራፍ በማሸጋገር የጋራ ፕሮጀክታችን የሆነውን የኢትዮጵያን ሕዳሴ እውን ማድረግ የምንችለው እነዚህን አፍራሽ አመለካከቶች ታግለን ስናሸንፍ ብቻ ነው፡፡
የሀገራችንን እድገትና ብልፅግና ወደ ላቀ ምዕራፍ በማሸጋገር የጋራ ፕሮጀክታችን የሆነውን የኢትዮጵያን ሕዳሴ እውን ማድረግ የምንችለው እነዚህን አፍራሽ አመለካከቶች ታግለን ስናሸንፍ ብቻ ነው፡፡
No comments:
Post a Comment