(በአሜሳይ ከነዓን)
የጥንታዊ
ስልጣኔ ባለቤት የሆነችው ኢትዮጵያ በማናቸውም ጊዚያቶች በውጭ ወራሪ ኃይላት ያልተንበረከከችና ለዘመናት ሉአላዊነቷን ጠብቃ የቆየች
ሀገር ናት። ሁሉም የአፍሪካ ሀገራት በቅኝ ግዛት ስር በወደቁበት ጊዜም ከየአቅጣጫው የተደቀኑባትን ወረራዎች በብቃት በመመከት የራሷን
ሉዓላዊነት ከመጠበቅ ባሻገር ለሌሎች የነፃነት ታጋዮችም የአይበገሬነት ተምሳሌት በመሆን ታግሎ
ማሸነፍ እንደሚቻል በተግባር ያስተማረች ነች ሀገራችን።
የኢትዮጵያና
የአሜሪካ ሁለትዮሽ ግንኙነትም የተጀመረው አብዛኞቹ የአፍሪካ ሀገራት በቅኝ ግዛት ስር በነበሩበት ዘመን ነበር፡፡ እናም ግንኙነቱ
እ.አ.አ ከ1903ዓ.ም ጀምሮ አንዴ ዝቅ ሌላ ጊዜ ደግሞ ሞቅ እያለ መጥቶ በአምባገነኑ የደርግ ስርዓት በጎሪጥ እስከመተያየት ደርሶ
ነበር። ለዚህ ግንኙነት መቋረጥ ደግሞ ደርግ የተከተለው የተሳሳተ የውጭ ግንኙነት አቅጣጫ ሲሆን ይህም ስርዓቱ የሶሻሊዝም ርእዮተዓለም
እከተላለሁ በማለት የጀመረው ፀረ-አሜሪካ ፕሮፓጋንዳ ነበር።
ከደርግ
ወድቀት ማግስት በዴሞክራሲያዊ ሁኔታ ህዝባዊ ስልጣን የተረከበው ኢህአዴግ በጋራ ጥቅም ላይ የተመሰረተና ማንንም በወዳጅነት እንዲሁም
ማንንም በጠላትነት የማይፈርጅ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ በመቅረፅ ኢትዮጵያ ከአለም ሀገራት ጋር ያላት ግንኙነት በእኩልነትና በመከባበር
ላይ እንዲመሰረት እልህ አስጨራሽ ትግል አድርጓል። ከአሜሪካ ጋር ለ17 ዓመታት ያክል ተቋርጦ የነበረውንም ግንኙነት በተሻለ ሁኔታ
በማስቀጠል እንዲጠናከርም አድርጓል፡፡
ባለፉት
ሁለት አስርተ አመታት ሀገራችን በምስራቅ አፍሪካም ይሁን በመላው አለም ለቱሪዝምና ለኢንቨስትመንት የተመቸች፣ በተለያዩ የዓለማችን
አካባቢዎች የሚገኙ ባለሃብቶች መዋእለንዋያቸውን ኢንቨስት ለማድረግ የሚመርጧትና በተለይ ወትሮ ትታወቀበት ከነበረውና ሁሉንም ኢትዮጵያዊ
አንገት ከሚያስደፋው የረሃብ፣ የኋላቀርነትና የጦርነት ታሪኳ ተላቃ በራሷ አቅም መቆም የምትችል ዴሞክራሲያዊት ሀገር ለመገንባት
ያለመታከት ተሰርቷል፡፡
ኢህአዴግ
በቀየሳቸው ትክክለኛ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ከራሳችን አልፈን አለም በእኛ ለውጥ እንዲያምን ያስገደደ ፈጣንና ተከታታይነት ያለው
ፍትሐዊ እድገት ተመዝግቧል፡፡ ሀገራችን ከፈጣን እድገቷ ባሻገር የተረጋጋና ዘላቂ ሰላም ያለባትም ሀገር ለመሆን በቅታለች፡፡ ከውስጣችን
አልፈን የአፍሪካውያን ወንድሞቻችንን ሰላም ለመጠበቅም ከፍተኛ መስዋዕትነት እየከፈልን ያልተቆጠበ ጥረት በማድረግ ላይ እንገኛለን፡፡
ይህ ሁለንተናዊ
ለውጣችን ታዲያ ሀገራችን ስሟ በዓለም አቀፍ መድረኮች የሚጠራው እንደከዚህ ቀደሙ በተመፅዋችነቷ ሳይሆን በልማት አጋርነቷና በኢንቨስትመንት
መዳረሻነቷ እንዲሆን አስችሏል። የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት በመሳብ ረገድም አሁንም ብዙ መስራት የሚጠበቅብንና ከዘርፉ የተሻለ ጥቅም
ለማግኘት የሚያስችለን ምቹ ሁኔታ መፍጠር ያለብን ቢሆንም እስካሁን የተገኙ ልምዶች ግን በዘርፉ እያስመዘገብነው ያለው ለውጥ የሚያበረታታ
መሆኑን የሚያመላክት ነው፡፡ ዛሬ ከቱርክ፣ ህንድና ቻይና ግዙፍ ኩባንያዎች ባሻገር የአውሮፓውያንና የአሜሪካዊያን ባለሃብቶችም በሀገራችን
መዋዕለ ንዋያቸውን በማፍሰስ ላይ ይገኛሉ፡፡ ይህ ሁሉ ደግሞ በተከተልነው ትክክለኛ የዕድገት አቅጣጫ የተገኘ ስኬት ነው።
ሀገራችን
ኢትዮጵያ የተለጠጠና ወደ ተሻለ የእድገት ምዕራፍ ሊያሸጋግረን የሚችል የአምስት ዓመት የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ በማውጣት
የምእተ ዓመቱን የእድገት ግቦች እንዲሳኩ ከማንም በላይ በቁርጠኝነት
የተጋች ለመሆን ችላለች፡፡ በዚህም በምእተ ዓመቱ የእድገት ግብ የተቀመጡ
ተግባራትን በማሳካት ዓለም በአንድ ድምፁ ቁርጠኝነቷን እንዲመሰክርላት
ተደርጓል፡፡ የህፃናት ሞትን ለመቀነስ የተያዘውን እቅድ ቀድማ አሳክታለች፡፡ የእድገት ግቡ መጀመሪያ ላይ የነበረውን የ46 በመቶ
የድህነት መጠንን ወደ 22 በመቶ በማውረድ በርካታ ሚሊዮን ዜጎቻችን ከድህነት አረንቋ እንዲወጡ በማስቻል አንፀባራቂ ድል ተመዝግቧል፤
አሁንም የእነዚህን በድህነት ውስጥ የሚኖሩ ዜጎቻችንን ህይወት ለመለወጥ ቀጣይ ርብርብ ማድረግ ያለብን ቢሆንም፡፡
ይህ ሁሉ
የሚያሳየው ሀገራችን ከድህነት ለመላቀቅ ያላትን ቁርጠኝነት ነው፡፡ ለዚህም ነው በዓለም አቀፍ ደረጃ ከኢትዮጵያ ጋር በአጋርነት
መስራት እንደ ጥሩ አጋጣሚ እየተወሰደ ያለው። የተለያዩ አለም አቀፍ መድረኮችን በማዘጋጀት እውቅናን ያተረፈችው ሀገራችን በያዝነው
በ2007 ዓ.ም ሶስተኛውን አለም አቀፍ የፋይናንስ ለልማት ጉባኤ
በማዘጋጀትም አቅሟንና የልማት አጋርነቷን በተግባር አረጋግጣለች፡፡ የተመድ ኢኮኖሚና ማህበራዊ ጉዳዮች ጀነራልና የሶስተኛው አለም
አቀፍ የፋይናንስ ለልማት ጉባኤ ሴክሬታሪ ጀነራል ዉ ሆንግቦ ጉባኤው ከመካሄዱ በፊት በኢትየጵያ የሚካሄደው ጉባኤ ተገቢነቱን በማመላከት
በሀገሪቱ እየተመዘገበ ያለው ፈጣንና ተከታታይነት ያለው ፍትሐዊ እድገት ጉባኤውን በስኬታማነት እንድታዘጋጅ ያግዛታል ሲሉ ተደምጠዋል፡፡
በእርግጥም
ከኳታርና ከሜክሲኮ በኋላ በሶስተኛነት ሀገራችን የአለም አበዳሪ ተቋማትና መሪዎች የተገኙበትን ጉባኤ በስኬታማነት በማጠናቀቅ ያለችበትን
ሁለንተናዊ የለውጥ ቁመና በተጨባጭ ማሳየት ችላለች፡፡ ይህ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ባራክ ሁሴን ኦባማ ጉብኝትም ይህችን አለም ለውጧን
እየመሰከረላት ያለችውንና ብሩህ ተስፋዋ ፍንትው ብሎ የሚታየውን ሀገር እውቅና መስጠት ተገቢና ወቅታዊ ነው የሚል እምነት አለኝ፡፡
የፕሬዝዳንቱም ይፋዊ ጉብኝት የኢትዮጵያና የአሜሪካ ስትራቴጂክ ግንኙነት ሁለቱንም ሀገራት የሚጠቅምና በመተማመንና መደጋገፍ ላይ
የተመሰረት እንዲሆን የሚያግዝ ነው፡፡
አሜሪካ
በሀገራችን እየተመዘገበ ያለው ሁለንተናዊ እድገት አስተማማኝና ቀጣይነቱም አስተማማኝ እንደሆነ በማመኗ ግንኙነቷን ማጠናከሯና ለሀገራችን
ለውጥም እውቅና መስጠቷ ተገቢ ነው፡፡ በሀገራችን ባለፉት ዓመታት የተመዘገቡት የሰላም፣ የልማትና የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ እመርታዎች
አሜሪካን ጨምሮ በርካታ ሀገሮች ሀገራችን ምርጫቸው እንድትሆን አስችሏል፡፡ ይህ ማለት ግን ሁሉ ነገር አበቃለት ማለትም አይደለም፡፡
በጀመርነው ፍጥነት በመቀጠል ሀገራችን ከድህንት ተላቃ መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገራት ተርታ ለማሰለፍ በከፍተኛ ቁርጠኝነት መስራታችንን
አጠናክረን መቀጠል ይኖርብናል። ኦባማ በጉብኝታቸው ወቅት እንደገለፁት 100 ፐርሰንት ትክክል የሚባል ዴሞክራሲ የትም የለም፣ በሀገረ
አሜሪካም ቢሆን፡፡ ለውጡንም እንዲሁ በአንድ ጀምበር ዳር ማድረስ አይቻልምና ሁሉም የራሱን ጊዜና ጉልበት ይፈልጋል፡፡
የሀገራችን
አርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮች፣ ኢንዱስትሪያሊስቶች፣ ባለሃብቶች፣ ወጣቶችና ሴቶች ሁሉም በጋራ ሲተባበሩ ነገ ከበድ ያለውን የቤት ስራ
ከመስራት የሚያግዳቸው አንዳች ኃይል እንደሌለ የእስካሁን ስኬታቸው ዓይነተኛ ማሳያ ተደርጎ የሚወሰድ ነው። ዛሬ ትናንት ያሰፈርነውን
የቤት ስራችንን በአግባቡ በማጠናቀቃችን አለም ድጋፉን እድገታችንን እውቅና በመስጠት እያሳወቀን ነው፡፡ ነገ ደግሞ የተሻለች ሀገር፣
የተሻልን ህዝቦች ሆነን በዓለም አደባባይ አንገታችንን ይበልጥ ቀና ለማድረግ አሁንም እንደ ትናንቱ ልማት፣ ሰላምና ዴሞክራሲ የህልውናችን
መሰረቶች ናቸው ብለን ከፍተኛ ርብርብ ማድረግ ይኖርብናል፡፡
No comments:
Post a Comment