EPRDF is a ruling party committed to realize Ethiopia's Renaissance.

Friday, 17 October 2014

የዓመፅ ጥሪዎችን ያመከነ ትውልድ!

የረድኤት ልጅ
ለአንድ ሀገር ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ልማት የሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ንቁ ተሳትፎ አስፈላጊ የመሆኑን ያህል ወጣቶች ደግሞ አዳዲስ ሃሳቦችን በማፍለቅና በመቀበል እንዲሁም እምቅ የፈጠራ አቅም ባለቤቶች ናቸውና ዕድሉ ከተመቻቸላቸው በሁሉም የልማት ዘርፎች  የላቀ ሚና መጫወት ይችላሉ፡፡ በተግባርም ወጣቶች በሃገራችን የለውጥ ታሪክ የማይተካ ሚና በመጫወት የአኩሪ ታሪክ አካልና ባለቤቶች ናቸው።
የኢትዮጵያ ወጣቶች የእነሱን ተሳትፎና መስዋእትነት የሚጠይቁ ሀገራዊ የጋራ ጉዳዮች በሚያጋጥሙበት ጊዜ በአንድነት መንቀሳቀሳቸው የነበረና አሁንም አብሮን ያለ ነው። የውጭ ወራሪ ሀይሎች በሀገራችን ባስነሷቸው የእብሪት ጦርነቶች በሙሉ እምቢ ለጭቆና በማለት ለሀገሪቷ ሉዓላዊነት ግንባር ቀደም ተሰላፊ ነበሩ፡፡ አገራችን በአምባገነን አገዛዝ ስርዓት ስር በወደቀችበት ወቅትም ወጣቶች በግንባር ቀደምትነት ተዋድቀዋል፡፡ አዲሲቷን ኢትዮጵያ እውን ለማድረግ የከፈሉት ክቡር መስዋእትነት ሁሌም ሲታወስ የሚኖር ነው።
ቅድመ 1983. ዜጎች አስከፊ ህይወት የሚገፉበትና በሀገራቸው እንደ ሁለተኛ ደረጃ ዜጋ የሚታዩበት ጊዜ ነበር። ጭቆናው በሁሉም የሕብረተሰብ ክፍሎች ላይ የተጣለ አስከፊ ታሪክ ቢሆንም በወጣቶች ላይ በከፋ መልኩ ይታይ ነበር። በመሆኑም ወጣቶች በሀገር ግንባታ ሂደት ውስጥ በብቃት ተሳትፈው ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ልማትን በማፋጠን የራሳቸውንና የሀገራቸውን ጥቅም ለማረጋገጥ የሚያስችል የተመቻቻ ሁኔታ አላገኙም፡፡
ተማሪዎች በተለይ 1960ዎቹ ጀምሮ ህብረተሰቡን በማንቀሳቀስ የፀረ ጭቆና ትግሉ ፋና ወጊ ሆነዋል፡፡ የመሬትና የብሔር ጥያቄን፣ ህዝባዊ መንግስት የመመስረት ግብን በማንገብ በሀገራችን ፖለቲካዊ ታሪክ መሰረታዊ ለውጥ ለማምጣት እልህ አስጨራሽ ትግል አካሂደዋል፤ ክቡር መስዋዕትነትም ከፍለዋል፡፡ ወጣቶቹ ጭቆና ይብቃ ብለው ያደረጉት መራር ትግል ፍሬ አፍርቶ እነሆ አሁን ዜጎቿ በእኩልነት የሚታዩባትና የሚኮሩባት አዲሲቷን ኢትዮጵያ አስረክበውናል፡፡ አሁን ደግሞ የህዳሴ ጉዟችንን እውን በማድረግ በዓለም አቀፍ መድረኮች ያለንን ሚና ከፍ ለማድረግ በከፍተኛ ወኔ እየተረባረቡ ይገኛሉ።
በኢትዮጵያም ከአጠቃላይ የህዝብ ቁጥራችን 30በመቶ በላይ የሚሆኑት ወጣቶች ናቸው። የወጣቶችን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየተጋ ያለው በድርጅታችን የሚመራው መንግስትም ወጣቶች ዴሞክራሲያዊ አመለካከት፤ የሙያ ብቃት፣ ክህሎትና መልካም ስነ-ምግባር ያላቸው ዜጎች ሆነው ሀገሪቱ በተያያዘችው የህዳሴ ጉዞ በንቃት ተሳትፊና ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማድረግ ትኩረት ሰጥቶ በመንቀሳቀስ ላይ ነው። ለዚህም ተልዕኮ እውን መሆን የነበሩትን የፖሊሲና የመዋቅር ክፍተቶች መሙላት የግድ ስለነበር ከፌደራል እስከ ታችኛው የመንግስት መዋቅር  የወጣቶችን ጉዳይ የሚመራና የሚያስተባብር መስሪያ ቤት በማቋቋም ቁርጠኝነቱን በተግባር አሳይቷል፡፡
ሀገር አቀፍ የወጣቶች ፖሊሲ በማዘጋጀት፤ ፖሊሲውን ሊደግፉ የሚችሉ ስትራቲጂዎችና የወጣቶች የከተማና የገጠር እድገት ፓኬጅን በመቅረፅና ወደ ተግባር በማስገባት የወጣቱን ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በርካታ ተግባራት ተከናውነዋል፡፡ የወጣቶች ፖሊሲ ዴሞክራሲያዊ አመለካከትና አስተሳሰብ ያለው በእውቀትና ሙያዊ ክህሎት የጎለበተ፣ የተደራጀና በስነ-ምግባር የታነፀ ትውልድ እንዲፈጠር ማድረግን ራዕዩ አድርጎ ወጣቶች በዴሞክራሲያዊ ስርዓትና መልካም አስተዳደር ግንባታ እንዲሁም በኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ባህላዊ ልማት እንቅስቃሴዎች ውስጥ በተደራጀ አኳኋን የነቃ ተሳትፎ እንዲያደርጉና ከውጤቱም ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማብቃት የፖሊሲው ዓላማ ነው፡፡
ፓኬጁ የገጠርና የከተማ ወጣቶች ያሉባቸውን መሰረታዊ ችግሮችና የመፍትሔ አቅጣጫዎች በዝርዝር ያስቀመጠ ሲሆን የወጣቱን አጠቃላይ ተሳትፎና ተጠቃሚነት እንዲሁም የአፈፃፀም ስልቶችና አቅጣጫዎች በግልፅ አመልክቷል። በውጤቱም የአገራችን ወጣቶች በልማት፣ በመልካም አስተዳደርና በዴሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታ በስፋት ለመሳተፍ በቅተዋል። በገጠር የወጣቶች እድገትና የለውጥ ፖኬጅ በዋናነት በመስኖ ልማት፣ በእንስሳት ሃብት፣ በተፈጥሮ ሃብት እንክብካቤ፣ በምርትና ምርታማነት ማሳደግ በሚደረገው ጥረት አስፈላጊ የሆኑ ቴክኖሎጂዎች በአግባቡ በመጠቀም በተለይ በተራራ ልማት በመሳሳሉት የልማት ስራዎች በስፋት በመሳተፍ በርካታ ወጣቶች ተጠቃሚ እየሆኑ ነው። በከተማም እንዲሁ የወጣቶችን የእድገት ፓኬጅ መሰረት በማድረግ በጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማት ልማት፣ በስራ ፈጠራ፣ በመልካም አሽተደደርና ሲቪል ሰርቪስ ሪፎርም እንዲሁም የትምህርት ጥራት በማረጋገጥ ረገድ ወጣቶች እየተረባረቡ ይገኛሉ፡፡
ወጣቶች በማህበራዊ መስክ እያደረጉት ባለ ሁሉን አቀፍ ርብርብም በክረምትና በበጋ የበጐ ፍቃድ አገልግሎት በመስጠት በርካታ ወጣቶች ተሳትፈዋል። በበጋ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ላይ በተለይ ደግሞ ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርን በመታገል ረገድ  የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎችን በማከናወን ውጤታማ ስራዎችን ሰርተዋል፡፡ በአዲስ አበባ የተለያዩ የወጣት አደረጃጀቶች በጋራ በመንቀሳቀስ ከስደት የተመለሱ ዜጐችን በመቀበል ላይ የተሰማሩ ወጣቶች የፈፀሙት ስራ የሚደነቅ ነበር፡፡ የታላቁ የህዳሴ ግድብ ስራን በድል ለማጠናቀቅ በሚደረገው ህዝባዊ ንቅናቄ ወጣቱ በየደረጃው ሰፊ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ ነው፡፡ እስካሁን በተደረገው እንቅስቃሴም ወጣቱ 6 ሚሊየን ብር በላይ የቦንድ ግዥ በመፈፀም የልማት አርበኝነቱን በተግባር አረጋግጧል።
ኢሕአዴግ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን በተገቢው ሁኔታ ለመመለስ ትግሉን በህዝቡ የተደራጀ እንቅስቃሴ መምራት ያስፈልጋል ብሎ ያምናል፡፡ በመሆኑም የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች በተደራጀ ሁኔታ እንዲታገሉ የሚያስችሉ ስልቶች ተቀምጠው ርበብርብ እየተደረገ መሆኑ ይታወቃ ወጣቶችም በየአካባቢያቸው ያሉትን የመልካም አስተዳደር ችግሮች በመለየት፣ የመፍትሔ ሐሳቦችን በማፍለቅና መልካም አስተዳደር ለማስፈን በሚደረገው ትግል ግንባር ቀደም ተዋናይ ሆነዋል፡፡ የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከትና ተግባር ለማክሰምና በምትኩ ልማታዊነትን ለማጠናከር በሚደረገው ሁሉን አቀፍ ትግል ድርሻቸውን ለመወጣት ያላሰለሰ ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛሉ፡፡
በሃይማኖት መከባበርና መቻቻል በዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ ዘንድ በጥሩ ተምሳሌትነት የምትታወቀውን ሀገራችንን ለመሸርሸር ሃይማኖታዊ ሽታ በሌላቸው አክራሪዎችና ፅንፈኞች የተደቀኑብንን የአክራሪነትና የሽብርተኝነት ተግዳሮቶች በመታገል በመቻቻልና መከባበር ላይ የተመሰረተች ዴሞክራሲያዊት ሀገር በማስቀጠል ስራ ላይ ወጣቱ የሚጠበቅበትን ሀገራዊ ኃላፊነት በአግባቡ ለመወጣት የተለያዩ ጥረቶች በማድረግ ላይ ነው። ፅንፈኛ ተቃዋሚ ሃይሎች ከኒዮሊበራል ሀይሉና በሃይማኖት ሽፋን ከሚንቀሳቀሱ አክራሪ ሃይሎች ጋር ያልተቀደሰ ጋብቻ በመፈፀም  አንዳንድ ወጣቶችን በመመልመል ከተያያዘዉ የህደሴ ጉዞ ለማደናቀፍና ተጠቃሚነቱን ለማኮላሸት ሌትቀን እየሰሩ ይገኛሉ። እነዚህ የጥፋት ሃይሎች ወጣቱን የጥፋት ተልዕኳቸው ማስፈፀሚያ አድርገው ለመጠቀም የማይፈነቅሉት ድንጋይ የለም። እንዲያውም ወጣቱ ትውልድ ምክንያታዊ ሆኖ በሀገሪቱ እየተከናወኑ ስላሉ የልማት፣ የሰላምና የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ስኬቶች ለማስቀጠል በቁርጠኝነት ባይነሳ ኖሮ አፍራሽ ኃይሉ ለእኩይ ተግባር ማስፈፀሚያ መጠቀሙ የማይቀር ነበር።
እነዚህ አፍራሽ ኃይሎች ሕጋዊና ሕገ ወጥ መንገዶችን እያጣቀሱ የቀለም አብዮት ስትራቴጂያቸዉን ተግባራዊ ለማድረግ የመጨረሻ ዕድላቸውን ለመሞከር ደፋ ቀና ማለታቸውን አጠናክረው እየገፉበት ሲሆን የመጪዉ 2007 ምርጫ የማሽነፍ ብቃትና ዝግጁነቱ ስለሌላቸዉ የጎዳና ላይ ነውጥ በማቀጣጠል የመንግስትን ስልጣን በአቋራጭ ለመቆናጠጥ የሚያደርጉት ጥረትም ከወዲሁ ግልፅ እየሆነ መጥቷል። 
አፍራሽ ሃይሉ ወጣቱን ለመጠቀም ቢኳትኑም ወጣቱ ትውልድ ግን የሀገሪቱን ዕድገት በመገንዘብና የነገው ጉዞአችንን ምንነት በሚገባ በመረዳት ፀረ-ሰላም ኃይሎቹ የተለያዩ የዓመፅ ጥሪዎች ቢያቀርቡለትም ሰሚ ጆሮ አልሰጣቸውም፡፡ በሃሰት ስብከቶችና በረጅም ጊዜ ውትወታዎች ተወናብዶ በየጊዜው በሚጠሯቸው የዓመፅ ሰልፎች ላይ የሚገኘው ወጣትም ቢሆን እዚህ ግባ የሚባል አይደለም።
ያሁኑ ትውልድ ለነፃነትና ለእኩልነት፣ ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ለሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችና ነፃነቶች መከበር የተከፈለውን መስዋዕትነትም በየጊዜው እያደሰ የራሱን አዳዲስ ታሪኮች በመስራት ላይ ይገኛል። በአሁኑ ሰዓት ኢትዮጵያችን የትናንት ፅልመት ገፅታዋ እየተፋቀ በአዲሱ የህዳሴ ግስጋሴዋ እየተተካ ይገኛል፡፡ የዛሬው ወጣትም ለሀገሪቱ እድገት እንቅፋት የሆኑት የመልካም አስተዳደርና የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከትና ተግባርን፤ ሽብርተኝነትና የሀይማኖት አክራሪነትን፣ የህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርና መሰል ችግሮችን ለማስወገድ በሚደረገው ሁሉን አቀፍ ርብርብ  ግንባር ቀደም ሆኖ በመትጋት ላይ ይገኛል።

ያለፈውን ትውልድ ተባብሮ አስከፊውን ስርዓት እንደጣለው ሁሉ የአሁኑ ወቅት የትግል አልፋና ኦሜጋ ድህነትና ኋላቀርነት ታሪክ ማድረግ ነው። በተለያዩ ምክንያቶች የህዝባችን እርካታ እንዳይረጋገጥ ሳንካ እየሆኑ ያሉ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን የመፍታትና መልካም አስተዳደርን የማስፈን ጉዳይም ሌላኛው የአሁኑ ትውልድ የርብርብ ማዕከል ነው። በሃይማኖት ሽፋን የሚካሄድ የአክራሪነትና የፅንፈኝነት እንቅስቃሴም የአሁኑ ትውልድ ትኩረት የሚሻ ጉዳይ ነው። በመሆኑም ወጣቱ የጀመረውን እንቅስቃሴ በማጠናከር የሚጠበቅበትን ሀገራዊ ኃላፊነት በብቃት መወጣት አለበት እላለሁ።

1 comment:

  1. ያለፈውን ትውልድ ተባብሮ አስከፊውን ስርዓት እንደጣለው ሁሉ የአሁኑ ወቅት የትግል አልፋና ኦሜጋ ድህነትና ኋላቀርነት ታሪክ ማድረግ ነው። በተለያዩ ምክንያቶች የህዝባችን እርካታ እንዳይረጋገጥ ሳንካ እየሆኑ ያሉ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን የመፍታትና መልካም አስተዳደርን የማስፈን ጉዳይም ሌላኛው የአሁኑ ትውልድ የርብርብ ማዕከል ነው። በሃይማኖት ሽፋን የሚካሄድ የአክራሪነትና የፅንፈኝነት እንቅስቃሴም የአሁኑ ትውልድ ትኩረት የሚሻ ጉዳይ ነው። በመሆኑም ወጣቱ የጀመረውን እንቅስቃሴ በማጠናከር የሚጠበቅበትን ሀገራዊ ኃላፊነት በብቃት መወጣት አለበት እላለሁ።

    ReplyDelete