EPRDF is a ruling party committed to realize Ethiopia's Renaissance.

Tuesday, 5 August 2014

የሀገራችን የፕሬስ ነፃነት ሁኔታ ሲቃኝ



በልጅ አኪናሆም
በኢትዮዽያ የመገናኛ ብዙሀን አጀማመር ከህትመት ሚዲያው ጋር የሚገናኝ እንደሆነ በርካታ ፀሀፍት ይስማማሉ። ከቀዳሚዎቹ የህትመት ውጤቶች መካከል በአፄ ምኒልክ ዘመነ መንግስት ታትሞ ይሰራጭ የነበረውአዕምሮጋዜጣ ይጠቀሳል። ሌሎች ደግሞ ቀዳሚው ጋዜጣጎህነው የሚል መከራከሪያ ሐሳብ ያቀርባሉ። የዚህ ፅሑፍ ዓላማ የትኛው ነው የሚጀመርያ ጋዜጣ ለምለው ያቄ ምላሽ መስጠት ሳይሆን በሃገራችን ታሪክ የፕሬስ አጀማመርና ይዘት በተወሰነ መልኩ ለመዳሰስ  ነው፡፡ በቀደምት ነገስታት ማለትም በአፄ ምኒልክና በአፄ ኃይለስላሴ ዘመናት የህትመት ውጤቶች አጀንዳ በይዘት የየነስታቱ ፍፁምነት የሚሰብኩ ነበሩ። በተለይ ደግሞ በአፄ ኃይለስላሴ ዘመን በይዘት ላይ የተረጋገጠ ልዩነት ባይኖርም የሚታተሙ ጋዜጦች ቁጥር ግን እየጨመረ እንደመጣ ታሪክ ያስረዳል።የዛሬይቱ ኢትዮዽያሰንደቅ አላማችንህብረትኢክሎቲዲያኖአል አለምበሪሳአዲስ ዘመንእናኢትዮዽያን ሄራልድጋዜጦች እና በእቴጌ መነን ስም በየወሩ የሚታተም ብቸኛ መፅሄት ነበር። ንጉሱ ከስልጣን ሲወርዱም የካቲት የተባለ መፅሄት እየታተመ ይሰራጭ እንደነበር ድርሳናት ይጠቁማሉ።
በደርግ ዘመነ መንግስትም በአንፃሩ ቀደም ብለው ይታተሙ የነበሩ የህትመት ውጤቶችን በመዝጋትና በመውረስ ዘርፉን ጠቅልሎ በመያዝ የሶሻሊዝም ፕሮፖጋንዳ መሳሪያ ያደረገው ሲሆን በምትካቸውምየዛሬይቱ ኢትዮዽያእናሰርቶ አደርጋዜጦችን በማተም ለፕሮፖጋንዳ መሳሪያነት ተጠቅሞባቸዋል። በደርግ ስርዓት ምንም አይነት የግል ፕሬስ ያልነበረ ሲሆን በዘርፉ እንዲሳተፉም አይፈቀድም ነበር። በመንግስት የሚታተሙ የህትመት ውጤቶች በሙሉ በቅድመ ምርመራ ማለፍ ግድ ይላቸው  ነበር። እዚህ ላይ ልብ ማለት የሚገባን 1983 በፊት የነበሩት የሕትመት ውጤቶች የየስርዓቱ አመስጋኝና አወዳሲ፤ የታዘዙትን ብቻ የሚፅፉ የስርዓቱ ልሳኖች፣ የሐሳብ ልዩነት ማስተናገድ በፍፁም የማይችሉ፣ ጥብቅ የሆነ ቅድመ ምርመራ የሚደረግባቸው የግሉ ዘርፍ የማይሳተፍባቸውና የነፃ ሚዲያ ጉዳይ ሊታሰብ የማይቻልባቸው ዘመናት መሆናቸውን ነው። በተለይ በደርግ ስርዓት የተለየ ሐሳብ በግላጭ ማራመድ ይቅርና የተለየ ሐሳብ አስበህ ይሆናል በሚል በርካታ ዜጎች ለእንግልትና ግርፋት እንዲሁም ለህልፈተ ህይወት ይዳረጉ ነበር። 

በህዝቦች መራራ ትግልና ክቡር መስዋእትነት አምባገነኑን የደርግ ስርዓት በተገረሰሰበት ማግስት ግን የዘመናት የዜጎች ጥማት የነበረው ሐሳብን በነፃነት የመግለፅ ጥያቄ ለመተግበር የሚረዱ በርካታ የፕሬስ ውጤቶች ብቅ ብቅ ማለት ጀመሩ። በእርግጥ የግል ፕሬሱ ሲጀምር በአንድ በኩል ለበርካታ ዘመናት የታፈነ ስሜት ልቅ በሆነ ሁኔታ በመፈንዳቱ በሌላ በኩል ደግሞ የግል የሕትመት ሚዲደያው በደርግ ርዝራዦች የተቋቋመ በመሆኑ በርካታ እጥረቶች የነበሩበት ነው። ያም ሆነ ይህ ግን በመንንግስት በኩል የደርግ ስርዓት መውደቅን ተከትሎ ለፕሬስ ለፃነትም ሆነ አጠቃላይ  ዘርፉን ለማሳደግ በርካታ አወንታዊ እርምጃዎች ተወስደዋል።
ሐሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት በማረጋገጥ በኩል ሀምሌ 15 ቀን 1983 የፀደቀው የኢትዮዽያ የሽግግር ወቅት ቻርተር በቀዳሚነት የሚጠቀስ ሲሆን  በአንቀፅ አንድ   ላይ እያንዳንዱ ግለሰብ ሀሳቡን ያለ አንዳች ገደብ በነፃነት የመግለፅ መብትን ሰጥቷል። ይህን ተከትሎም እጅግ በርካታ የግል የህትመት ውጤቶች ወደ ኢንዱስትሪው ተቀላቅለዋል። ሌላው ለህትመት ኢንዱስትሪው የነፃነት መደላድል የፈጠረው አዋጅ ቁጥር 34/85 ሲሆን ዜጎች ሀሳባቸውን በነፃነት የመግለፅ መብታቸው የህግ ማዕቀፍ እንዲኖረው አስችሏል። ዋናውና ለነፃው ፕሬስ መረጋገጥ ዋስትና የሆነው ግን 1987 በሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ተሳትፎና ይሁንታ በፀደቀው ህገ መንግስት አማካኝነት ነው። በዚህም በአንቀፅ 29 የአመለካከትና ሃሳብን በነፃ የመያዝና የመግለፅ መብት ሰባት መሰረታዊ ንኡስ አንቀፆችን በማካተት በታሪካችን ለመጀመሪያ ጊዜ ሕገ መንግስታዊ ዋስትና አግኝቷል። 
በዚህም ማነኛውም ሰው ያለማንም ጣልቃ ገብነት የመሰለውን አመለካከት መያዝ መቻሉ፣ ማንኛውም ሰው ያለማንም ጣልቃ ገብነት ሃሳቡን የመግለፅ መብት መጎናፀፉ፣ የፕሬስና ሌሎች መገናኛ ብዙሃን እንዲሁም የስነ ጥበብ ፈጠራ ነፃነት መረጋገጡ፣ በተለይ የፕሬስ ነፃነቱ የቅድሚያ ምርመራን በማንኛውም መልኩ መከልከሉ፣ የህዝብን ጥቅም የሚመለከት መረጃ ማግኘት እድልን መስጠቱ፣ ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት አስፈላጊ የሆኑ መረጃዎች፣ ሃሳቦችና አመለካከቶች በነፃ መንሸራሸራቸውን ለማረጋገጥ ሲባል ፕሬስ በተቋምነቱ የአሰራር ነፃነትና የተለያዩ አስተያየቶችን የማስተናገድ ችሎታ እንዲኖረው የሚያስችል ሁኔታ መፈጠሩ በሀገራችን የፕሬስ ታሪክ ውስጥ ፈርቀዳጅ ውሳኔ ነው። ሕገ መንግስቱ  የፕሬስ ነፃነትና ሐሳብን በነፃነት በመግለፅ በኩል በመብትነትም ሆነ በነፃነት በማረጋገጥ ረገድ ከላይ የተዘረዘሩት መብቶች ገደብ ሊጣልባቸው የሚችልባቸውን ሁኔታዎችንም እንዲሁ በግልፅ አስቀምጧል።
ሐሳብን በነፃነት የመግለፅ ነፃነት በተመለከተ የሚኖር ሕገ መንግስታዊ ገደብ በዋናነት የወጣቶችን ደህንንት፣ የሰውን ክብርና መልካም ስም  ለመጠበቅ ሲባል በሚወጡ ሕጎች መሰረት ሊፈፀም እንደሚችል በግልፅ ተቀምጧል። ይህ ገደብ ደግሞ ከዓለም አቀፍ መርሆች ጋር በእጅጉ የተጣጣመ ነው። በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሲቪልና የፖለቲካዊ መብቶች ስምምነት አንቀፅ 19 ንኡስ አንቀፅ ሶስት ላይ በግልፅ እንደተቀመጠው የፕሬስ ነፃነት የሰው ክብርንና መልካም ስምን ለመጠበቅ እንዲሁም ብሔራዊ ደህንነትንና ማሕበራዊ ጤንነትን ለመጠበቅና ለማስጠበቅ ሲባል  እገዳ ሊጣልበት እንደሚችል በማያሻማ ሁኔታ ያስቀምጣል። የኢፌድሪ ህገ መንግስትም የጦርነት ቅስቀሳዎችና ሰብዓዊ ክብርን የሚነኩ የአደባባይ መግለጫዎች በህግ ሊከለከሉ እንደሚችሉ በማስቀመጥ ሐሳቡን ይበልጥ ያጠናክረዋል።
ፕሬስ በዜጎች መብቶች አጠቃቀም ረገድ የተጣሉ ገደቦችን አልፎ ከተገኘ በህግ ተጠያቂ እንደሚሆን የሕገ መንግስታችን አንቀፅ 29 ንኡስ አንቀፅ 7 ያስረዳል።ነፃ ፕሬስ መፈቀዱን ተከትሎ በይዘትና በአይነት ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የህትመት ውጤቶች ለገበያ ቀርበዋል። ለአብነትም 1985 ብቻ 118 በላይ ጋዜጦችና መፅሄቶች ተመዝግበው ወደ ስራ ገብተው ነበር። ይህ የግሉ ዘርፍ የህትመት ተሳትፎ እያደገ መጥቶ 1990 554 የሚደርሱ የተለያዩ የህትመት ውጤቶች ለህዝቡ ይደርሱ እነደነበር መዛግብት ያትታሉ። ዘርፉ ያሳየው የአሃዝ መጨመር  ከቁጥር ባለፈ በይዘታቸውም የተለያዩ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ ሲሆን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ፣ ንግድና ማስታወቂያ፣ ባህልና ኪነ ጥበብ፣ ፋሽንና ሞዴሊንግ፣ የህፃናት፣ የሃይማኖት፣ ስፖርት፣ ጤናና ስነልቦና፣ ትምህርት ነክና የሴቶች ጉዳይ መጥቀስ ይቻላል።   በኢትዮዽያ ሚሊኒየም ማክበሪያ ሰሞን በህትመት ዘርፉ ተመዝግበው የነበሩ 1 ሺህ በላይ የህትመት ውጤቶች ነበሩ።
በአሁኑ ወቅትም (2006.) የስርጭት አድማሳቸው ከአንድ ክልል በላይ የሆኑና በኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን የተመዘገቡ 102 ጋዜጦችና 173 መፅሔቶች በድምሩ 275 የሕትመት ውጤቶች ይገኛሉ። በአንድ ወቅት የተሻለ  ቁጥር የነበራቸው የህትመት ውጤቶች አሁን በምን ሁኔታ ላይ ናቸው  የሚል ጥያቄ ማንሳትና ተገቢ የሆነ ምላሽ መሻት ጠቃሚ ነው። በእርግጥ ከእነዚህ የሕትመት ውጤቶች መካከል የተወሰኑት አሁንም ህትመታቸውን ቀጥለው እየሰሩ ሲሆን ሌሎች ደግሞ እንደየወቅቱ ፖለቲካዊ ሙቀት አሊያም ትኩሳት የሚለዋወጡና ዓላማቸውም ቢሆን የዘላቂነት ባህርይ የሌላቸው የአንድ ወቅት ዓላማ ማስፈፀሚያ ናቸው ማለት ይቻላል። ለሕትመት ውጤቶቹ መክሰም አሊያም መጎልበት በዋናነት የሚያወጧቸው ርእስ ጉዳዮችና ጭብጦች  ሲሆኑ በተለይ የከሰሙቱ ግን የዜጎችን የመረጃ ጥማት የማያረኩ፣ ከአንድነት ይልቅ በመበታተን ላይ ያተኮሩ፣ ከዕድገትና ብልፅግና ይልቅ እሮሮና ጨለምተኛነትን የሚሰብኩ፣፣ ሁሌም ከፍቅርና መከባበር ይልቅ ጥላቻና ዛቻን የሚዘምሩ፣  ስኬቶች ከመዘገብ ይልቅ ጥቃቅን ክፍተቶችን በማጋነን ላይ የተጠመዱ፣ ከሰላም ይልቅ ሁከትና ጦርነትን በማቀንቀን ሀገሪቱ በጎሳ ተከፋፍላ አለቀች፣ ተገነጣጠለች፣ ተበታተነች፣ የሚሉና ወደ ፊት ከመራመድ ይልቅ ጎታችና በሀገር ልማትና አንድነት ላይ ምንም አይነት አስተዋፅኦ እንደሌላቸው ሲረዳ አንባቢው አንቅሮ በመትፋቱ  ምክንያት የህትመት ውጤቶቹ ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ ተለዋዋጭ እንዲሆን አድርጓል። 
የህትመት ውጤቶቹ ዘርፉን እንደሌሎች የቢዝነስ መስኮች ተመልክተው ገንዘብ ለመግኘት ብቻ ሲሉ ውሃ የማይቋጥሩ፣ይህ ነው የሚባል መረጃ የሌላቸው፣ በሐሜትና አሉቧልታ የታጀቡ፣ የግለሰቦችን ስብዕና የሚያንቋሽሹና ሌሎች መሰል ግጭቶችን የማራገብ ዘገባዎች ላይ ማተኮራቸው ጭምር በህትመት ውጤት ተጠቃሚው ዘንድ ተቀባይነት እንዲያጡ አድርጓቸዋል። ከዚህ ውጪ አሁንም በርካታ የህትመት ውጤቶች በገበያ ላይ አሉ
መንግስት በተለያዩ ጊዜያት ነፃው ፕሬስ በህጋዊ መስመሩ ውስጥ ሆኖ ገንቢ ትችቶችን በመስጠትና በሀገር ግንባታ ሂደት ውስጥ አወንታዊ ሚና መጫወት የሚያስችልቱ የመገናኛ ብዙሃንና የመረጃ ነፃነት አዋጅ 590/2000 እና የኢፌደሪ የብሮድካስት አገልግሎት አዋጅ ቁጥር 533/1999 በሕገ-መንግስቱ የተዘረዘሩ የመረጃ ነፃነቶች ለማስጠበቅና በአገባቡ ለመጠቀም በሚያስችል መልኩ  የሕግ ማዕቀፎች በማዘጋጀት ለኢንዱስትሪው ማበብ ያለው ቁርጠኝነት በተግባር አረጋግጧል። 
ፋኖወዲ ሰመራ የተባለ ፀሀፊ 2004 የኢትዮጵያ የፕሬስ ዕድገትና አብሮ መጓዝ የተሳነው ሲፒጄበሚል ርዕስ ባዘጋጀው አርቲከል ላይ እንዳሰፈረው መንግስት ያወጣቸው አዋጆች ለሀገሪቱ የፕሬስ ዘርፍ እድገት ወሳኝ የማዕዘን ድንጋይ ናቸው በማለት ይገልፃቸዋል። የፕሬስ ነፃነትና የመገናኛ ብዙሃን አዋጁ በሕገ-መንግስቱ የተረጋገጡ የፕሬስና የሌሎች መገናኛ ብዙሃን ተቋሞች ነፃነቶችና መብቶች ለማረጋገጥ ዓይነተኛ መሳሪያም ነው። ይህ አዋጅ መነሻ ካደረጋቸው መሰረታዊ ዓላማዎች መካከል በዜጎች መካከል የሚደርጉት ነፃ የሐሳብና የመረጃ ልውውጥ እንዲሁም በመገናኛ ብዙሃን የአሰራር ነፃነት ላይ መሰናክል የነበሩ ተቋማዊና መዋቅራዊ ችግሮችን በማስወገድ በነፃ ሐሳብን የመገለፅና የመገናኛ ብዙሃን ነፃነት የማስከበር አስፈላጊነት በዋናነት ይገኝበታል።
በአዋጁ የመገናኛ ብዙሃን ነፃነት በሚያብራራው አንቀፅ አራት ንኡስ አንቀፅ ሶስት ላይ ማንኛውም የመንግስት አካላት መገናኛ ብዙሃን ማሕበራዊ ተግባራቸውን ለመወጣት ) ዜና ወይም መረጃን የመሰብሰብ፣ የመቀበልና የማሰራጨት፣ ) በልዩልየዩ ጉዳዮች ላይ አስተያየት ወይም ትችት የማቅረብ ወይም፣ ) የተለያዩ   ዘዴዎችን በመጠቀም የህዝብን አስተያየት በመቅረፅ ሂደት የመሳተፍ መብታቸውን ማክበር እንዳለበት ይደነግጋል። ይህም የኢፌዴሪ መንግሥት ለሚዲያው ኢንዱስትሪ ዕድገት መረጋገጥ ቁልፍ የሕግ ከለላ ማበጀቱን ከአዋጁ መንፈስ በግልፅ መረዳት ይቻላል።
በተመሳሳይ ሁኔታ የአዋጁ አንቀፅ 12/1 በአዋጁ በተለየ ሁኔታ ከልተደነገገ በስተቀር ማንኛውም ሰው ከማንኛውም መንግሥታዊ አካል መረጃን የመጠየቅ፣ የማግኘትና የማስተላለፍ መብት እንዳለው ይደነግጋል። በዚሁ አንቀፅ ንኡስ አንቀፅ ሁለት ደግሞ ይህ መረጃ የማግኘት መብት በማንኛውም የመንግስታዊ አካል እጅ የሚገኝ ሰነድ የመመልከት ወይም ማስታዎሻዎችን የመውሰድ ወይም ጥቅሶችን የመገልበጥ እንዲሁም ሰነዱን በሚገኝበት መልክ ትክክለኛ ግልባጭ የመውሰድ መብትን ያካትታል። በነገራችን ላይ መብትና ግዴታ (ገደብ) የአንድ እውነታ ሁለት ገፅታዎቸ ናቸው ማለት ይቻላል። 
የብሮድካስት አገልግሎት አዋጅ ቁጥር 533/1999 በተመሳሳይ ሁኔታ በሕገ መንግሰቱ የተቀመጡ ሐሳብን በነፃነት የመግላፅ መብቶችና ነፃነቶች ተግባራዊ ለማድረግ የተዘጋጀ የሕግ ማዕቀፍ ነው።  የአዋጁ ዓላማ በሚብያራራው አንቀፅ ስድስት ላይ የብሮድካስት ባለስልጣን ዓላማ ለፖለቲካዊ፣ ለማሕበራዊና ለኢኮኖሚያዊ ዕድገት አስተዋፅኦ የሚያደርግ፣ ጥራቱ የተጠበቀ፣ ቀልጣፋና አስተማማኝ የብሮድካስት አገልግሎት እንዲስፋፉ ለማድረግ እንደሆነ በግልፅ ተደንግጓል።
ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ በዚህ አዋጅ አንቀፅ 16/2 ላይም ማንኛውም የመንግስት የብሮድካስት አገልግሎት /የመንግስት ፖሊሲዎችንና ስትራቴጅዎችን እንዲሁም የልማት፣ የዴሞክራሲና የመልካም አስተዳደር እንቅስቃሴዎችን በማቅረብ የህዝቡን ተሳተፎ ያዳብራል፣ /ህዝቡን የሚያሳውቁ፣ የሚያስተምሩና የሚያዝናኑ ፕሮግራሞችን ያቀርባል፤ /በእኩልነት ላይ የተመሰረተ የህዝቦችን አንድነት የሚያንፀባርቁ ፕሮግራሞችን ያቀርባል፤ / የሕዝቡን ባህላዊና ጥበባዊ እሴቶች ያስተዋውቃል፣ ያጎለብታል፣ /በአገሪቱ ሕገ-መንግስትና የምርጫ ሕግ መሰረት የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ድርጅቶችን በፍትሓዊነት ያገለግላል ይላል።
በተመሳሳይ ሁኔታ የዚህ አዋጅ አንቀፅ 30  መሰረታዊ መርሆዎችን አስቀምጧል። እነዚህም ) ማንኛውም ለስርጭት የሚቀርብ ፕሮግራም የተለያዩ አመለካከቶችን በማንፀባረቅ ሕብረተሰቡን በአጠቃላይ እንዲያገለግል ሚዛናዊ ሆኖ  መቅረብ እንዳለበት፤ ) ማንኛውም ለስርጭት የሚቀርብ ፕሮግራም ይዘቱና ምንጩ ትክክለኛ መሆኑ መረጋገጥ እንደሚያስፈልግ፤ እንዲሁም ) ማንኛውም ዜና ከአድልዎ የፀዳ፣ ትክክለኛና ሚዛናዊ መሆን እንዳለበት ይደነግጋል። 
እስካሁን በዝርዝር ያየናቸው ጉዳዮች በአገራችን ተጨባጭ የሚዲያው አካባቢ (Media Landscape) እንዲሁም ሓሳብን በነፃነት የመግለፅ ሁኔታዎች ምን እንደሚመስሉ በጨረፍታ ቢሆንም የአገሪቱን አጠቃላይ ምስል የሚያመላክቱ ናቸው። እላይ ከተዘረዘሩት ሕጎችና የሕግ ማዕቀፎች በመነሳት በአገሪቱ ለሚዲያው ኢንዱስትሪ የተመቻቸ ሕገ-መንግስታዊና ሕጋዊ ማዕቀፎች በአግባቡ እንዳሉ እንገነዘባለን።ሕጋዊ ማዕቀፎች መኖራቸው ብቻ ሳይሆን የኢፌዴሪ መንግስትም ለሚዲያው ዕድገትና መስፋፋት ቁርጠኝነት እንዳለው ከላይ የዘረዘርናቸው ማሳያዎች ለነፃ ሚዲያ አስቻይ የሆነ የስራ አካባቢ መኖሩን እንድንረዳ የሚያግዙ ናቸው።
ይሁን እንጂ እነዚህ ምቹ ሁኔታዎች ቢኖሩም በግሉ የሕትመት ሚዲያ ዘርፍ የሚስተዋለው ከሙያዊ ስነ ምግባር ባፈነገጠ መልኩ ፍፁም ተአማኒነት የሌላቸው ስሜታዊ መረጃዎች በማሰራጨት፣ የሀገር፣ የመንግስት፣ የቡድኖችና የግለሰዎች መልካም ስምና ክብር በወረደ መልኩ በማብጠልጠል፣ ሚዛን የጎደላቸውና የአንድ ፅንፍ ሐሳብ ላይ በማተኮር ህዝቡን በማደናገር፣ ሕገ መንግስታዊ ስርዓቱን የሚንዱና ብሔርን ከብሔር የሚያጋጩ መረጃዎች በማሰራጨት፣ የሀገር ህልውና የሚንዱ የተውገረገሩ መረጃዎች በማናፈስ፣ የዓመፅ ጥሪዎችን በግልፅና በማያሻማ ሁኔታ በማስተላለፍ ሕገ ወጥነትን በጠራራው ፀሀይ በማወጅ ወዘተ ላይ በመጠመድ መብቱን አላግባብ እየተጠቀመበት ይገኛል። 
ዛሬ ላይ እንዲህ በቀላሉ መንግስትን መዘርጠጥ፤ ያሻቸውን መፃፍ ያስቻለ ዴሞክራሲያዊ መንግስት ማመስገን ባይችሉም እንኳ ያረጋገጣቸውን ዴሞክራሲያዊ መብቶች ዋጋ የሚሰጥ ስብእና ማዳበር ተገቢ ይሆን  ነበር። ሌላውና ዋናው ጉዳይ ደግሞ መንግስት በህገ መንግስቱ የተፈቀዱና የተረጋገጡ የዜጎች መብቶችን በመተግበር ሂደት የህግ ጥሰት ሲፈፀም እየተመለከተ በሆደ ሰፊነት የሚያልፈው ሰዶ ከማሰዳደድ ይልቅ ታዳጊ ዴሞክራሲያዊ ባህል ባላት ሀገር ላይ እየወደቁ እየተነሱ መማር ይቻላል ከሚል የፀና እምነት መሆኑ ግልፅ  ነው፡፡  ይሁን እንጂ የወጣቶችን ደህንንት አደጋ ላይ የሚጥሉ፤ የሰውን ክብርና መልካም ስም የሚያጎድፉ፣ ብሔራዊ ደህንነትንና ማሕበራዊ ጤንነትን የሚያቃውሱና የሚያናጉ የጦርነት ቅስቀሳዎች ማተም እንዲሁም ሰብዓዊ ክብርን የሚነኩ የአደባባይ መግለጫዎች በህገ መንግስቱ የተከለከሉ መሆናቸውን ግልፅ ሆኖ እያለ  በተግባር ግን ሕገ መንግስታዊ ክልከላዎችን በመተላለፍ በርካታ የወንጀል ድርጊቶችን አሊያም ወንጀለኞችን የሚያበረታቱና የሚያሞግሱ ዘገባዎች በቀጣይነት ለሕትመት ሲበቁ ማየት የተለመደ ጉዳይ ሆኗል። በዚህ ዙሪያ ብዙ ማለት፤ ብዙ መፃፍ ቢቻልም ወሳኙ ነጥብ ግን በሕገ ወጥነት የተካኑና እራሳቸውን ከሕግ በላይ በመቁጠር መንግስትን የማፍረስ ዓላማ በግልፅ እስከማራመድ የሚሰሩ የግል የሕትመት ውጤቶች በየትኛውም መስፈርትም ቢሆን ሚዲያ/ፕሬስ ናቸው የሚያስብል አንድም ነገር እንደሌላቸው ነው።
ሐሳብን በነፃነት የመግለፅ ጉዳይ ሕገ መንግስታዊ ዋስትና ያገኘና በተግባርም ሀገራችን ሕገ ወጥ ዘገባም ጭምር እንደ ሕጋዊ ተግባር ተደርጎ በሚታይበት ሁኔታ ፕሬሱ በተለይ ደግሞ የግል የሕትመት ሚዲያው በልቅነት በሚዘግብበት ሁኔታ የፕሬስ ነፃነት ጉዳይ ለአፍታም ቢሆን ጥያቄ አይነሳበትም። መነሳት ካለበት ግን መንግስት እነዚህ ፅንፍ ይዘው የፕሬስ ሳይሆን ስርዓት የሌለው አፍራሽ አጀንዳ ይዘው የሚንቀሳቀሱ የፕሬስ ውጤቶች እስከ መቼ ድረስ በሆደ ሰፊነት ያልፋቸዋል በሚል ይሆናል። ሐሳብን በጋዜጣ አልያም በመፅሔት ካልሆነም በዘመኑ ድረ-ገፅ ማሰራጨት ብቻም ጋዜጠኛ አያስብልም። የተለያየ የውስጥ ዓላማ ይዘው በግልፅም ሆነ በህቡእ፣ በተደራጀም ሆነ በተናጠል አፍራሽ ተልዕኮአቸውን ለመፈፀምና ለማስፈፀም የሚንቀሳቀሱ ግለሰዎችና ቡድኖች ደግሞ የጋዜጠኝነት ካባ ደርበው በኢንዱስትሪው ሊወሸቁ አይገባም። ካልሆነ ግን ኢንዱስትሪው ተገቢውን እይታ እንዳያገኝ ያደርጋሉና ነው። ሀገር በማተራመስ፣ ዓማፅን በመቀስቀስ፣ ብሔርን ከብሔር ጋር በማጋጨት፣ የሽብር ተልዕኮ ይዞ ሕገ መንግስቱንና ሕገ መንግስታዊ ስርዓቱን በኃይልና በዓመፅ ለመናድ፣ ሕገ ወጥ በሆኑ መሰል ድርጊቶች ሲሳተፉ ጋዜጠኛ ነኝ፣ ፀሐፊ ነኝ ወዘተ የሚባል ነገር ደግሞ ሀገሪቱ የሕግ የበላይነት የተረጋገጠባት ናትና በፍፁም የማይታሰብ ይሆናል። 

ሕጋዊ በሆነ መንገድ ሐሳባቸውን በነፃነት ማራመድ ለሚፈልጉ የፕሬስ ውጤቶች ግን አማራጩና ዕድሉ አሁንም እጅግ ሰፊ ነው። መንግስትም ሕጋዊ በሆነ መንግድ ለሚንቀሳቀሱና በሀገሪቱ የሚዲያ ኢንዱስትሪ ውስጥ የበኩላቸውን አስተዋፅኦ ለማበርከት ለሚታክቱ ጥቅት የፕሬስ ውጤቶች አስፋላጊውን ድጋፍና ማበረታቻ ማድረግ ይኖርበታል የሚል እምነት አለኝ፡፡

1 comment:

  1. በመንግሥት ቁጥጥር ስር ያሉ መገናኛ ብዙሃን በተራ ቁጥር (ሠ) የተጠቀሰውን ቢያሟሉ ኖሮ የግሉ ፕሬስም ሚዛናዊ ሊሆን ይችላል ብዬ አስባለሁ። የመንግሥት ሚዲያ የኢሕአዴግ ፕሮፖጋንዳ ማሰራጫ ነው የሚለው ስሜት እስካለ ድረስ ግን ከጥቅም አንፃር (ገበያ ለማግኘት) ለግሉ ሚዲያ የሚያዋጣው ተቃዋሚ መሆን ብቻ ነው።

    ReplyDelete