EPRDF is a ruling party committed to realize Ethiopia's Renaissance.

Friday, 11 August 2017

የቶጎው ተጋድሎ

(በሚሚ ታደሰ)     
የዛሬ 17 አመት፤ በወረሀ ሐምሌ፤ የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን 36ኛ መደበኛ ስብሰባ ያስተናገደው የሎሜዉ አዳራሽ ከወትሮዉ በተለየ ሁኔታ ሙቀቱ ከፍ ብሏል፡፡ የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን ወደ አፍሪካ ሕብረት ለመቀየር ወሳኝ ወቅት ላይ እንደመሆናቸው 33 የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች ተገኝተዋል፤ የአለምና የአፍሪቃ ብዙሀን መገናኛዎች አይንና ጆሮ ከአዳራሹ በሚነሱ የሀሳብ ፍጭቶች፤ ልዩነቶችና አስተያየቶች እንዲሁም ዉሳኔዎች ላይ ያነጣጠሩበት ሳምንት ነበር፡፡ በዚህ ታላቅ የመሪዎች ስብሰባ ላይ በቅጽበት የሚገኙ ትኩስ መረጃዎችን በብርሀን ፍጥነት ለአድማጭ ተመልካቾቻቸዉ ለማቅረብ አቆብቁበዋል፡፡

ኢትዮጲያ ደግሞ ባልተገመተ መንገድ ከባድ ጋሬጣ ከፊቷ ተደቅኖባታል፡፡ ከምስረታው ጀምሮ ለአራት አስርት አመታት ገደማ ማዕከል ሆና የመሪነት ሚና የተጫወተችበትን የአፍሪካ አንድነት ድርጅት መቀመጫ ከአዲስ አበባ ወደ ሌላ የአፍሪካ ከተማ ለማዛወር በተለይ በሊቢያና በሴኔጋል በኩል ውስጥ ለውጥ ሲሰራ የነበረው የማግባባት ስራ እየተጠናከረ መጥቷል፡፡ የየሀገራቱ ሚኒስትሮች ከመሪዎቹ ስብሰባ አንድ ቀን ቀደም ብለው ባሻሻሉትና በመሪዎቹ እንደሚፀድቅ በሚጠበቀው የሕብረቱ ማቋቋሚያ ደንብ ላይ ከተጠቀሱት 33 አንቀፆች አንዱ ደግሞ የሕብረቱን መቀመጫ የተመለከተ ነው፡፡ በረቂቁ ላይ አዲስ አበባ የሕብረቱ መቀመጫ ሆኖ እንድትቀጥል የሚል አንቀፅ ተካቷል፡፡
መሪዎቹ በሚኒስትሮች ምክር ቤት የቀረበውን ረቂቅ ያለምንም ማሻሻያና ልዩነት ሊያፀድቁት ከጫፍ ደርሰዋል፡፡ የሴኔጋሉ ዲፕሎማት ግን ሁኔታው ስላላማራቸው የአፍሪካ ሕብረት መቀመጫ አዲስ አበባ ይሆናል የሚለው አንቀፅ 24 በጣም ውስብስብ በመሆኑ ውሳኔ ለመስጠት እንደሚያዳግታቸው ገልፀው በጉዳዩ ላይ ተጨማሪ ውይይት ማድረግ ይቻል ዘንድ በዚህ አንቀፅ ላይ በሌላ ጊዜ ውሳኔ እንዲሰጥበት ሃሳብ አቀረቡ፡፡ የዲፕሎማቱ ሃሳብ በግልፅ የሚያመለክተው ጉዳይ የሕብረቱ መቀመጫ አዲስ አበባ መሆኑን እንደሚቃወሙ ነገር ግን ደግሞ በዚህ ወቅት ክርክሩን ቢጀምሩት አዋጭነቱ አጠራጣሪ እንደሆነባቸው ነው፡፡ ስለሆነም የተጀመረውን በተናጠል የማሳመን ስራ (lobbying) ለመቀጠል ያመቻቸው ዘንድ የጊዜ ይሰጠን ጥያቄ ነው ያቀረቡት፡፡
ሀገራችንን ወክሎ በመድረኩ የተገኘው ጓድ መለስ ዜናዊ ለኢትዮጵያ የታሰበላትን የጥፋት ድግስ ስለተረዳው ዲፕሎማቱ ያነሱት ጉዳይ ለመወሰን በጣም ቀላል እንደሆነ በመጥቀስ ክርክር ካሻውም በግልፅ እንዲቀርብ ሽንጡን ገትሮ ተከራከረ፡፡ በርግጥ የመለስ መከራከሪያ ሃሳብና አቀራረቡ የሎሜን የመሰብሰቢያ አዳራሽ ሙቀት ይበልጥ ከፍ ያደረገና በሚሊዮን በሚቆጠሩ አፍሪካዉያን ወንድሞቻችን በተለይም በእሱ በተወከልነው በእኛ ኢትዮጲያዉያን ልብ ዉስጥ ዘላለም የማይዘነጋ ደማቅ ታሪክ የፃፈበት ነው፡፡
መለስ በተረጋጋና በሰከነ አእምሮ ቀድሞውንም የአፍሪካ አንድነት ድርጅት መቀመጫ አዲስ አበባ እንዲሆን የወሰኑት ኔሬሬና ኑክሩማን የመሰሉ ታላላቅ የአፍሪካ ልጆች መሆናቸውን በማውሳት ኢትዮጵያም የተሰጣትን ትልቅ ሃላፊነት በከፍተኛ ቁርጠኝነት ስትፈፅም መኖሯን አብራራ፡፡
“ኢትዮጵያ በየትኛዉም መንግስታዊ ስርአት ዉስጥ ትሁን ለአፍሪካ ሉዓላዊነት እና ነጻነት ቁርጠኛ ነች፡፡ ማንዴላን ማን ነዉ ያሰለጠነዉ? አድሃሪዉ ኃይለ ስላሴ አብዮታዊዉ ማንዴላን አሰልጥነዋል፡፡ ማንዴላ ስልጠና ያገኘው በኢትዮጲያ ነበር፡፡ ሙጋቤ ሩዲዝምን ሲዋጋ ማን ነበር ከጎኑ? መንግስቱ ነዉ፡፡ መንግስቱ በሀገር ዉስጥ ጨፍጫፊ ነዉ፡፡ ነገር ግን በአፍሪካ ጉዳይ ልክ እንደ አፄ ኃይለ ስላሴ የማያወላውል አቋም ነበረው፡፡ ኢትዮጲያ ለአፍሪካ ጉዳዮች ያላት ቁርጠኝነት በመንግስታት ለውጥ ዉስጥ አልተቀያየረም፡፡ በአፄ ኃይለ ስላሴ አመራር ስርም ሆነች በመንግስቱ፣ አልያም በሌላ የመንግስት ስርአት ምንም ለውጥ የለውም፡፡” አለ፡፡
በየትኛዉም የታሪክ ስሌት ለአፍሪካ አንድነትና ነጻነት በአለም አደባባይ ጭምር ከኢትዮጲያ የተሻለ የታገለ፤ በሁሉም የትዉልድ ቅብብሎሽ የማያወላዳ አቋም ያሳየ ካለ በግልፅ ይቅረብና ያስረዳ ነበር ያለው መለስ፡፡ ሙሉ መተማመን በሚንፀባረቅበት ንግግሩ ኢትዮጵያ ሃላፊነቷን አልተወጣችም የሚል ካለም ይቅረብና ይውቀሰን አለ፡፡ "ይሄ ጉባኤ ኢትዮጵያ ሃላፊነቷን በአግባቡ አልተወጣችም ካለ ውሳኔውን ለመቀበል ፈቃደኞች ነን" በማለት ሲገልፅም ውስጥ ውስጡን የሚደረገው ማባበል አደባባይ ወጥቶ በፅናት ሊቆም እንደማይችል እርግጠኛ ነበር፡፡
መለስ ደጋግሞ ለድርጅቱ መቀመጫነት የተሻልኩ ተመራጭ ነኝ የሚሉ እጩዎች ካሉ ጉዳያቸውን በግልፅ ያስቀምጡና ከዛ በጥንካሬውና በጉድለቱ ላይ ተከራክረን እንወስንበታለን ቢልም ማንም በመድረኩ የተገዳደረው አልነበረም፡፡
እናም በመጨረሻ አማራጮቹ ቀርበው በጉዳዩ ላይ ግልጽ ክርክር ባልተካሄደበት ሁኔታ የሕብረቱን መቀመጫ የተመለከተው አንቀፅ በጣም የተወሳሰበ ነው ብሎ መከራከርና ሌሎች አንቀጾችን አፅድቆ ይሄኛው ለሌላ ጊዜ እንዲሸጋገር ሃሳብ መስጠት በእኔ አስተያየት የኪራይ ሰብሳቢነት ኢኮኖሚ መሸፈኛ ነው::  በማለት ንግግሩን አጠናቀቀ፡፡ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት 36ኛ መደበኛ ስብሰባም በሚኒስትሮች ምክር ቤቱ የቀረበለትን ረቂቅ ተቀብሎ አፀደቀ፡፡ ኢትዮጵያም የአፍሪካ ሕብረት መቀመጫ ሆኖ እስካሁን እንድትዘልቅ ያስቻላት ሌላ አንፀባራቂ ታሪክ በጓድ መለስ ዜናዊ ስም ተመዘገበ፡፡ የቶጎው ተጋድሎ በብዙዎቻችን የአእምሮ ጓዳ የማይዘነጋ ታሪክ ሆኖ ይሄው በማይደበዝዝ ቀለም ተፅፋል፡፡
ኢትዮጵያ የቀደሙት መሪዎቿ ለአፍሪካውያን አንድነትና ነፃነት ባሳዩት ቁርጠኝነት ልክ ዛሬም በፓን አፍሪካኒዝም ቅኝት እየተመራች ትገኛለች፡፡ የአፍሪካዉያን ወንድሞቻችንን ሰላምና ጸጥታ እንደራሳችን ጉዳይ በማየት አብረን እየደማን፤ አብረን እየቆሰልን ከጎናቸው ቆመናል፡፡ በቀጠናዊም ሆነ አህጉራዊ ልማትና የኢኮኖሚ ትስስርም የአፍሪካን ብርሃን ያሳየ ፍኖተ ካርታችንን ዘርግተን ለተግባራዊነቱ ሌት ከቀን እየሰራን እንገኛለን፡፡ ዛሬም ኢሕአዴግ የአፍሪካን ሕዳሴ እውን ለማድረግ ከአፍሪካውያን ተራማጆች ጋር በአህጉሪቱ ዘላቂ ሰላም፣ ልማትና እድገት ዙሪያ በትብብርና በፍፁም ወንድማዊነት ስሜት ትግሉን እንደቀጠለ ነው፡፡

(ለትዉስታ፣ የቶጎ ሎሚ ንግግር ቪዲዮዉን ከትርጉም ጋር ፌስቡክ ገፃችን ላይ ያገኙታል፡፡)

1 comment: