EPRDF is a ruling party committed to realize Ethiopia's Renaissance.

Monday, 27 March 2017

ለተሻለ ውጤት የጋራ ጥረት




በኤፊ ሰውነት
ኢህአዴግ የሚመራው ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ መንግስት የአገራችንን ነባራዊ ሁኔታ ያገናዘበ ፖሊሲና ስትራቴጂ በመንደፍ ፋና ወጊ መሆኑ ግልፅ ነው፡፡ በአገራችን አሁን እየተተገበሩ ያሉት ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎችም አገር በቀልና ውስጣችንን ያገናዘቡ መሆናቸው ከነተግዳሮታችንም ቢሆን በለውጥ ውስጥ እንድንሆን ያስቻሉን ውጤታማ መሳሪያዎቻችን ናቸው፡፡ ኢህአዴግ በአገራችን ግብርና መርኢንዱስትሪ ልማት ፖሊሲ ተግባራዊ ማድረግ በመቻሉ ባለፉት ዓመታት ፈጣንና ተከታታይነት ያለው ኢኮኖሚያዊ እድገት ማስመዝገብ ተችሏል። ይህ እድገት አገራችን ከግብርና መር ኢኮኖሚ ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ ለምታደርገው መዋቅራዊ ሽግግር አቅምና መደላድል የመሆን ተልዕኮም አለው፡፡ የግብርና ክፍለ ኢኮኖሚያችን መጎልበት የኢንዱስትሪ ልማት እንዲፋጠን በር የሚከፍትና በተደጋጋሚ እንደሚገለፀው የኢንዱስትሪ ልማት አንቀሳቃሽ ሞተር የሆነው የግል ባለሃብቱ ይህን አጋጣሚ በመጠቀም በተለይ በማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ዘርፍ እንዲሰማራ የሚያበረታታ መሆኑ እሙን ነው፡፡  

መንግስት የግል ባለሃብቱ ወደ ማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ እንዲገባ አስፈላጊውን ሁላ ርብርብ በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡ የተለያዩ ማበረታቻዎችን ለግል ባለሃብቱ በማድረግ የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ልማት እንዲፋጠን በትጋት እየሰራ ይገኛል፡፡ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት መንግስት የዘርፉን ልማት ለማፋጠን እየወሰዳቸው ካሉት እርምጃዎች ተጠቃሽ ነው፡፡   

የኢንዱስትሪ ልማት የመለወጥ፣ የብልጽግናና የስልጣኔ መለያ ነው። ዓለምን አንዱን ያደገ፣ ሌላውን ወደኋላ የቀረ ወይም በማደግ ላይ ያለ በሚል ክፍፍል ውስጥ እንድትገባ ያደረጋትም የኢንዱስትሪ ልማት እድገት የፈጠረው ሰፊ ልዩነት ነው፡፡ በአገራችንም የኢንዱስትሪ ልማትን ማፋጠን ጊዜው የሚጠይቀው ወሳኝ ጉዳይ ሆኗል፡፡ ካለየተጠናከረ ያለ ጠንካራ የኢንዱስትሪ ልማት በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪነትን መገንባትም ሆነ በአገር ውስጥ ራስን ችሎ ማቆም ፈፅሞ አዳጋች ይሆናል፡፡  

ኢህአዴግ በአገራችን የሚገነባው የኢንዱስትሪ ልማት በሰፊ መሰረትና አስተማማኝ በሆነ ሁኔታ እንዲሆን ሰፋፊ ተግባራት በማከናወን ላይ ነው፡፡ አስተማማኝ የሚሆነው ደግሞ የአገራችን ባለሃብቶች በሙሉ አቅማቸው በዘርፉ ሲሰማሩ ሲሆን ሰፊ መሰረት ሊይዝ የሚችለውም ከጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማት ጀምሮ ከኪራይ ሰብሳቢነት በፀዳ አኳኋን በርካቶችን የያዘ ኢንዱስትሪ መገንባት ሲቻል ነው፡፡ የአነስተኛና ጥቃቅን ተቋማትን ማስፋፋትና በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ እንዲሰማሩ ማድረግ አንዱ ሲሆን ከላይ ለመግለፅ እንደተሞከረው የግል ባለሃብቱን ማሳተፍና ድጋፍ ማድረግ ሌላኛው የፖሊሲው ምሶሶ ነው፡፡ 

ኢህአዴግ አገር የማስተዳደር ህዝባዊ ኃላፊነት ሲረከብ በአገራችን በተለይ የኢንዱስትሪ ልማትን ከማፋጠን አኳያ አስቻይ ሁኔታ ያልነበረ በመሆኑ ባለሃብቱም ደፍሮ ሃብቱን የሚያፈስበት ሁኔታ አልነበረም፡፡ በአጠቃላይ የኢንዱስትሪ ልማቱ ከዜሮ ነው የተጀመረው ማለት ይቻላል፡፡ ይህን ሁኔታ በመቀየር ከፖሊሲ ጀምሮ የኢንዱስትሪ ልማቱን የሚያፋጥን አቅጣጫ በመቀየስ ኢህአዴግ የሚመራው መንግስት በርካታ ተግባራትን ፈፅሟል፡፡ በዚህም የኢንዱስትሪ ልማት እድገቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ የመጣበትን ሁኔታ ማስተዋል ይቻላል፡፡ 

ሰሞኑን የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ የጥልቅ ተሃድሶ ንቅናቄው የደረሰበትንና በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዘመን የሁለተኛው ዓመት አጋማሽ አፈፃፀም ሪፖርት ግምገማ አድርጓል፡፡ የኢንዱስትሪ ልማት አፈፃፀሙ አንዱ አጀንዳ የነበረ ሲሆን የማምረቻ ኢንዱስትሪው 18.4 በመቶ እድገት ማስመዝገቡን ገልጿል፡፡ በሪፖርቱ እንደተመላከተው በዋናነት የኢንዱስትሪ ልማቱን ለማፋጠንና ባለሃብቱንም ለማበረታታት ጭምር የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት በመፋጠኑና 2008 በጀት ዓመት አዳዲስ የኢንዱስትሪ ኢንቨስትመንቶች ወደ ስራ በመግባታቸው የለውጡ መነሻ ተደርጓል፡፡ 

ከዚህ አኳያ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው አገራዊ አቅም ለማጎልበት የሚረዳውን የማምረቻ ኢንዱስትሪ ልማት በማፋጠን የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግር ለማምጣት ትኩረት ተሰጥቶት እየተከናወነ መሆኑን ተመላክቷል፡፡ 13 የሚሆኑ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ስራ በተሻለ አፈፃፀም እየተከናወነ መሆኑንም አስታውቋል፡፡ ከእነዚህ የኢንዱስትሪ ፓርኮች መካከል በቦሌ ለሚ ምዕራፍ አንድ 20 እንዲሁም በሐዋሳ 11 የሚሆኑ የፋብሪካ ሼዶች ወደ ምርት በመግባት የውጭ ምንዛሬ ማስገኘት መጀመራቸውንም ገምግሟል፡፡   

ኢህአዴግ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት በአንድ ማዕከል ውስጥ የመሰረት ልማት አቅርቦት ችግር ሳይገታ በጥራትና በቅልጥፍና ማምረት እንዲችሉ የሚያደርግ በመሆኑ ባለሃብቱን በማበረታታትና በመሳብ ወደ ማምረቻ ኢንዱስትሪው እንዲያዘነብልና በረጅም ያሰበውን እቅድ የሚያሳካ በመሆኑ የፓርኮች ልማት ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑንም አስታውቋል፡፡ 

በአገራችን የኢንዱስትሪ ልማት ታሪክ በ1983 በመንግስት ከተያዙት ውጭ እዚህ ግባ የሚባል መሰረተ ሰፊ የኢንዱስትሪ ልማት ያልነበረ ሲሆን በአሁን ጊዜ ከአነስተኛና ጥቃቅን ኢንተርፕራይዝ ወደ መካከለኛና ከፍተኛ ኢንዱስትሪዎች የተሸጋገሩትን ጨምሮ የአገር ውስጥና የውጭ ኢንቨስትመንት በመስፋፋቱ የኢንዱስትሪ ልማቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያበበ መምጣት ችሏል፡፡ ከመንግስት አሰራሮችና የፋይናንስ ማበረታቻዎች ባሻገር የኢንዱትሪ ፓርክ ልማትም ለኢንዱስትሪ መስፋፋት የራሱን ጉልህ ድርሻ እያበረከተ ነው፡፡ በጥቅሉ ከላይ ያነሳናቸው ነጥቦች ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ መንግስታችን አገራችንን ወደፊት ሊያራምዱ በሚችሉ ዘርፎች ላይ ትኩረት በማድረግ ከድህነት ጋር የምናደርገውን ትግል በድል ለመወጣት ርብርብ ላይ መሆኑን የሚያረጋግጡ ናቸው፡፡ 

በሌላ በኩል ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው ካያቸው ዓበይት ጉዳዮች መካከል የማህበራዊ ልማት ዘርፍ ይገኝበታል፡፡ በአገራችን የማህበራዊ ልማት ስራችን ከጊዜ ወደ ጊዜ በበርካታ ስኬቶች እየታጀበ ለመምጣቱ የለውጡ ባለቤት የሆነው ህዝቡ ህያው ምስክር ነው፡፡ የትምህርትና የጤና ልማት ስራችን ከጅማሬው አንፃር ሲታይ በእመርታዊ ለውጥ ውስጥ ይገኛል፡፡ የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴም በትምህርትና ጤና ዘርፍ የተገኘውን ስኬት በሚዛኑ በማየት በቀጣይ ጉድለቶቹ ላይ መረባረብ እንደሚገባ አስምሮበታል፡፡

በትምህርት ልማት ዘርፍ የትምህርት ተደራሽነትና ጥራት ለማረጋገጥ የተከናወኑ ስራዎች ውጤታማ እንደነበሩ ገምግሟል፡፡ ሰፋ ያለ ጉድለት የሚታይባቸውን የመዋዕለ ህፃናትና የከፍተኛ ትምህርት ተሳትፎ ለማሳደግ ትኩረት እንደሚያሻና የአንደኛ ደረጃ መጠነ ማቋረጥ ለማስቀረት መረባረብ እንደሚገባም አመላክቷል፡፡ በተመሳሳይ የጎልማሶች ትምህርትም ለህዳሴ ጉዞው ከሚኖረው ፋይዳ አንፃር በመመዘን በቀሪ ጊዜ ውጤታማ ስራ ለማከናወን መረባረብ እንደሚገባ አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡
 
ኢህአዴግ የሚመራው ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ መንግስት ለሰው ሃይል ልማት ትኩረት በመስጠት የሰው ሃይል ልማትን ሊያበለፅጉ የሚችሉ አሰራሮችን ጭምር ተግባራዊ በማድረግ ከመጀመሪያ ደረጃ እስከ ምርምር ድረስ ያለውን የሰው ሃይል ልማት እያጠናከርና ከአገሪቱ እድገት ጋር ሊመጣጠን በሚችል ደረጃ ለማድረስ እየተጋ ይገኛል፡፡ በአገራችን አሁን ያለው የሰው ሃይል ልማት ስራችንም በስኬት የታጀበ መሆኑም የተነሳንበት ዳራ ያረጋግጣል፡፡ በአገራችን በቅድመ 1983 ዓም ትምህርት ለአብዛኛው የአገራችን ህዝብ በፍትሃዊነት ይዳረስ ያልነበረ ከመሆኑ ባሻገር በገጠርና በከተማ፣ በብሄረሰቦች መካከልና ከፆታ አኳያም ቢሆን ተደራሸነቱ ችግር የነበረበት እንደነበረ ይታወቃል፡፡ 

ኢህአዴግ አገር የማስተዳደር ስልጣን ከተረከበበት ጊዜ ጀምሮ የትምህርት ተደራሸነት ከጫፍ እስከ ጫፍ እየጎለበት መምጣት ችሏል፡፡ ትምህርት ቅንጦት ሳይሆን መሰረታዊ መብት መሆኑን አስረግጦ በተግባር ማሳየትም ተችሏል፡፡ የ2008 የትምህርት ልማት ሪፖርት እንደሚያሳየው የትምህርት ተሳትፎን ለማሳደግ ቤት ለቤት በተደረገ ቆጠረና በተደረገው ርብርብ ከቅድመ መደበኛ እስከ 12ኛ ክፍል ብቻ 26 ሚሊዮን 413ሺህ 120 ተማሪዎች የትምህርት ገበታ ተቋዳሽ መሆን ችለዋል፡፡ 

መንግስት የቴክኒክና ሙያ ተቋማትን ማስፋፋት ላይ ባደረገው ርብርብም በ2008 ዓም 10 ነባር ተቋማትን ከማስፋፋት ባሸገር 42 አዳዲስ ተቋማት እንዲገነቡ በማድረግ የቅበላ አቅማቸውም በዛው ልክ ማደግ ችሏል፡፡ በተጨማሪ በዚሁ በጀት ዓመት በመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች 123ሺህ 286 ተማሪዎችን ማስተናገድ ተችሏል፡፡ የምርምር ተቋማትና የመምህራንን አቅም ማሳደግም ተችሏል፡፡ የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል የሚያግዙ አሰራሮች ተግባራዊ በመደረጋቸው ከመጀመሪያ ደረጃ ጀምሮ ያለው የመማር ማስተማር ሂደት በለውጥ ላይ ይገኛል፡፡ ትምህርት ቤቶች የምርምር ማዕከላትም ጭምር እየሆኑ መጥተዋል፡፡ የነገ የአገራችንን ፍላጎት መሸከም የሚችል ትውልድ ለመቅረፅም እየተጋ ይገኛል፡፡ እነዚህ ስኬቶች የተመዘገቡትም መንግስት ለትምህርት ልማት በሰጠው ትኩረት መሆኑ የማይታበል ሃቅ ነው፡፡

በማህበራዊ ልማት ዘርፍ ከትምህርት ልማታችን ባሻገር በጤና መስክ እንደ አገር የተመዘገበው ስኬት አገራችን ዓለም አቅፍ እውቅና ጭምር ያገኘችበት ነው፡፡ የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴም በተለይ የእናቶችና የህፃናት ሞት በመቀነስ የተመዘገቡ ስኬታማ ስራዎችን ተመልክቷል፡፡ የጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም ለዚህ ውጤት መመዝገብ የአንበሳውን ድርሻ ይወስዳል፡፡ እናቶች የቅድመና ድህር ወሊድ ግንዛቤ እንዲይዙ በመደረጋቸውና በጤና ተቋማት የሚወልድ እናቶች ቁጥር በመጨመሩ የእናቶች ሞት ለመቀነሱ ምክንያት ሆኗል፡፡ 

በአገራችን በአሁን ጊዜ ከ38 ሺህ   በላይ የጤና ኤክስንቴንሽን በለሙያዎች በስራ ላይ ሲሆኑ የጤና ልማት ስራችንን የሚያሳልጡ የጤና ተቋማት ተደራሽነትም ጨምሯል፡፡ ከዚህ አኳያ የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ከጤና ኤክስንቴንሽን አገልግሎት ጋር በተያያዘ ማነቆዎችን በጥናት ላይ የተመሰረተ ምላሽ ለመስጠት መዘጋጀት እንደሚገባ ያመላከተ ሲሆን በዘርፉ የሚስተዋለውን የጥራት መጓደል ችግር ለመፍታትም ቀጣይ ትኩረት እንደሚሻ አስምሮበታል፡፡  

የአገራችን የህዳሴ ጉዞ እውን የሚሆነው በሁለንተናዊ መልኩ ያስቀመጥናቸውን ራዕዮችን ማሳካት ሲቻል ብቻ ነው፡፡ አገራችን የምትመራበት ግልፅ ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ የሆነ ፖሊሲና ስትራጂ ባለቤት ናት፡፡ መመሪያዎችና አሰራሮችም እንዲሁ፡፡ እስካሁን የመጣንባቸው መንገዶች አልጋ ባልጋ አልነበሩም፡፡ ፈተናዎች እያጋጠሙን እና ፈተናዎቹን በብቃት እየተወጣን ብቻ ሳይሆን ለቀጣይ ጉዞም ትምህርት እየወሰድንባቸው ስለመጣን ነው በስኬት ጉዳና እንድንራመድ ያስቻሉን፡፡ በየደረጃው ያለ ባለድርሻ አካልም የህዳሴ ጉዟችንን ለማሳለጥ አስፈላጊውን ርብርብ እያደረገ መጥቷል፡፡ አሁንም ቢሆን በአንድ በኩል በየዘርፉ ያስመዘገብናቸው ስኬቶችን ይበልጥ አጠናክረን በመቀጠል በሌላ በኩል ደግሞ ያላሳካናቸው እቅዶች በእኛው የማስፈፀም አቅም ውስንነት ወይም ድክመት መሆኑን በመገንዘብ ነገን በጊዜ የለኝም መንፈስ እና በከፍተኛ ዲስፕሊን መረባረብ ያስፈልጋል፡፡ 

ጤናው የተጠበቀ፣ አቅሙ የጎለበትና ምርታማ የሆነ የሰው ሃይል በማፍራት የበለፀገች ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን መገንባት የሚቻለው በጋራ ጥረት በመሆኑ ሁሉም በየተሰማራበት መስክ በትጋትና በቁርጠኝነት ለተሻለ ውጤት መረባረብ ይገባዋል፡፡  ሰላም ለናንተ ይሁን፡፡ 

1 comment:

  1. ስራ የጀመሩትና ወደፊትም የሚጀምሩት የኢንዱስትሪ ፓርኮቸች አገራችን በያዘችው የእድገት ጉዞ ላይ ትልቅ እምርታ የሚያመጡ ከመሆናቸውም በላይ በተለይ ለበርካታ ወጣቶች የሚፈጥሩት ሰፊ የስራ እድል እጅግ የሚያስደስት ነው፡፡

    ReplyDelete