EPRDF is a ruling party committed to realize Ethiopia's Renaissance.

Friday 15 July 2016

የጥፋት ሃይሎችን ስንኩል አላማ ያከሸፈ የፈተና ስርዓት


(በእውነቱ ይታወቅ)
የከፍተኛ ትምህርት መግቢያ ፈተና ከሃምሌ 4-7/2008 ሲካሄድ ቆይቶ በሰላም ተጠናቋል። በዘንድሮው ፈተና ላይ 253ሺህ 424 ተማሪዎች ተሳትፈዋል። የ2008 ዓ.ም የከፍተኛ ትምህርት መግቢያ ፈተና አፈፃፀም ሲቃኝ ከወትሮው የተለዩ ክስተቶችን ያስተናገደ ሆኖ ነው ያለፈው።
ፈተናው አስቀድሞ ከግንቦት 22-25/2008 እንዲሰጥ የታቀደ ቢሆንም የእንግሊዝኛ ፈተና ሞራል በጎደላቸው ሰዎች ተሰርቆ መውጣቱን በማረጋገጡ እና ሌሎች ፈተናዎች ላለመውጣታቸው ማረጋገጫ ባለማግኘቱ የትምህርት ሚኒስቴር ፈተናው እንዳይካሄድ አድርጎ ነበር። ምንም እንኳን የፈተና ስርቆት አዲስ ባይሆንም የዘንድሮው ድርጊት ግን የተወሰኑ ተማሪዎች የማይገባቸውን ውጤት እንዲያገኙ ለመጥቀም በማሰብ የተፈፀመ ሳይሆን በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ተማሪዎችን ልፋት ከንቱ በማድረግ የፖለቲካ ትርፍ የማግኘት ስንኩል አላማን ያነገበ መሆኑ ልዩ ያደርገዋል።
የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መግቢያ ፈተና ተሰርቆ መውጣቱን እንዳረጋገጠ መንግስት ሃላፊት የሚሰማው ውሳኔ አሳልፏል። በአንድ በኩል ማንም ያልለፋበትን ጥቅም እንዳያገኝ በሌላ በኩል ሌሎች ማግኘት የሚገባቸውን ውጤት እንዳያጡ በማሰብ ፈተናውን ለሌላ ጊዜ ካዛወረ በኋላ በአጭር ጊዜ ውስጥ በከፍተኛ ጥንቃቄና ጥበቃ ሌላ ፈተና ተዘጋጅቶ ተማሪዎቹ እንዲፈተኑ አድርጓል። ምስጋና ለስራዊ ፈፃሚዎችና ለባለድርሻ አካላት ይሁንና ዳግመኛ የተዘጋጀው ፈተና በመላ ሃገሪቱ ፍፁም ሰላማዊና አስተማማኝ በሆነ መልኩ ያለምንም እንከን ነው የተጠናቀቀው፡፡ እንዲህ አይነት ችግር ሊያጋጥም እንደሚችል በመገመት መጠባበቂያ እቅድ ጭምር ያዘጋጀ የፈተና ስርዓት መዘርጋቱ ፈተናውን በአጭር ጊዜ ውስጥ ያለምንም ችግር ዳግም ለመፈፀም አስችሏል፡፡ ይህ በሰብዓዊ ሃብት ልማት ላይ ከተሰማራ መንግስት የሚጠበቅ ሃላፊነት ነው። 
በኢሕአዴግ የሚመራው መንግስት በትምህርት ዘርፉ ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ የሚመድበው ከድህነትና ኋላቀርነት የመውጫ ብቸኛው መንገድ ትምህርት መሆኑን ስለሚያምን ነው። ትምህርት መብትና ግዴታቸውን ጠንቅቀው የተረዱ ዜጎችን በማፍራት ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታም ቁልፍ መሳሪያ ነው። ያለፉ አመታትን ሰነዶች ላገላበጠ ሰው የላቀውን የሃገሪቱን በጀት ከያዘው የድህነት ቅነሳ ፕሮጀክቶች በጀት ውስጥ የትምህርቱ ዘርፍ ድርሻ እጅግ ከፍተኛ መሆኑን ይረዳል። መላ ህብረተሰቡ፣ የግል ባለሃብቱና መንግስት በዚህ ዘርፍ ባደረጉት ርብርብ አሁን ላይ 27 ሚሊዮን በላይ ዜጎች በትምህርት ገበታ ላይ የሚገኙባት ሀገር ለመፍጠር ተችሏል። በየዓመቱ ለከፍተኛ ትምህርት ተገቢውን ማለፊያ ነጥብ እያስመዘገቡ ወደ መንግስት ዩኒቨርስቲ የሚገቡ ተማሪዎች ቁጥርም ከመቶ ሀምሳ ሺህ በላይ ደርሷል። አሁን በስራ ላይ ካሉት ዩኒቨርስቲዎች በተጨማሪ የአስራ አንዱ አዳዲስ ዩኒቨርስቲዎች ግንባታ ሲጠናቀቅ ደግሞ ይህ ቁጥር በከፍተኛ መጠን እንደሚጨምር ይጠበቃል።
ይህን ሃገራዊ ድል ጠብቆ ማስቀጠል መንግስት ለነገ የማይለው የልማት አጀንዳ ነው። በዚህ የድል ጉዞ ላይ የሚሰነዘር ጥቃት አጠቃላይ የሀገራችንን ህዳሴ ለማሰናል የሚቃጣ መሆኑን በመረዳት አስፈላጊውን የእርም እርምጃ መውሰድም እንዲሁ። መንግስት በመጀመሪያው እቅድ የያዘውን ፈተና ሙሉ በሙሉ በመሰረዝና የመፈተኛ ጊዜውን በማስተላለፍ ለተፈጠረው ችግር አፋጣኝና አስተማማኝ መፍትሄ የሰጠውም በፀረ ድህነትና ኋላቀርነት ትግሉ ሂደት በሰው ሃብት ልማት ላይ ከሚሰነዘር ጥቃት የከፋ እንቅፋት እንደሌለ ስለሚያምን ጭምር ነው። በርግጥም ይህን አይነቱ እኩይ ተግባር ትውልድን ለመቅረፅ የሚተጋን መንግስት ካልሆነ በስተቀር ለዜጎቹ የወደፊት ህይወት የማይጨነቅን መንግስት የሚያሳስበው አልነበረም።
በሀገር ግንባታና በሰው ሃይል ልማት የተቃርኖ መስመር ላይ የተሰለፉ ሃይሎች በፈፀሙት በዚህ ተግባር ተማሪዎች፣ ወላጆችና መላው ህብረተሰብ አዝነዋል። እዚህ ላይ እነዚህ የጥፋት ሃይሎች ለምን የከፍተኛ ትምህርት መግቢያ ፈተና ላይ አነጣጠሩ የሚለውን ማየት ተገቢ ነው። ትምህርት ዜጎች እርምጃዎቻቸውን ሁሉ ካላቸው ፋይዳና ተገቢነት አንፃር የሚመዝኑበት፣ በስሜት ሳይሆን በምክንያት ላይ የተመሰረተ ውሳኔን ለማስተላለፍ አቅም የሚገነቡበት ነው። በተቃራኒው ያልተማረ ህብረተሰብ በሃሰተኛ መረጃዎች በቀላሉ የሚወናበድና ለማጣራት የሚከብደው፤ ፈፃሚዎቹንም በተጠናጠልም ሆነ በጋራ ለመታገል የሚቸገር ነው። ስለሆነም ፊት ለፊት ከሚናገሩት ጀርባ ስውር አጀንዳ ያላቸው ሃይሎች የዜጎችን ግንዛቤ ለማሳደግና የእውቀት አድማስን ለማስፋት የሚደረጉ ሂደቶችን ለማደናቀፍ ይጥራሉ።
ለዚህም ነው የጥፋት ሃይሎች ከአሁን በፊትም በተደጋጋሚ የሃገራችንን የትምህርት ስርዓት የእኩይ ተግባራቸው ኢላማ በማድረግ የትምህርት ስርዓቱን ለማስተጓጎል ሙከራዎችን ያደረጉት። ባለፉት 10 አመታት እንኳን በተለያዩ ዩንቨርስቲዎች ሽብርና ሁከት በመፍጠር ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደቱ እንዲስተጓጎል ሳይታክቱ ሰርተዋል። የዘረኝነት አባዜያቸውን በዩንቨርስቲ ተማሪዎች መካከል በመርጨት ጥላቻን ሲዘሩ፣ የእርስ በርስ ግጭቶችን ሲሰብኩ ከርመዋል። ተማሪዎች የመልካም አስተዳደር ችግሮች ሲያጋጥሟቸውና ተገቢ የመብት ጥያቄዎችን ሲያነሱ አጀንዳቸውን በመጠምዘዝ ትምህርት ቤቶችን የነውጥ ማዕከል ለማድረግ ጥረዋል። በጊዜያዊነት ባወናበዷቸው ጥቂት ተማሪዎች ፊት አውራሪነት የትምህርት ተቋማቱ እንዲታወኩ፣ ንብረት እንዲወድም፣ የትምህርት ሂደቱ ለቀናትም ቢሆን እንዲቋረጥ አድርገዋል። በአንዳንድ ዩንቨርስቲዎችም ቦምብ በመወርወር ጭምር ተማሪዎች ላይ ጉዳት አድርሰዋል። መንግስትና የየዩንቨርስቲዎቹ መላ ማህበረሰብ ግን የፀረ ሰላም ሃይሎቹን ሴራ በማጋለጥና በማክሸፍ የተጀመረው የትምህርት ልማት እንዲቀጥል አድርገዋል።
በዩንቨርስቲዎችና ሌሎች ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ማህበራዊ መሰረት ያጡትና ያሰቡትን ለመፈፀም የተሳናቸው እነዚህ ሃይሎች ታዲያ ባለፉት ጥቂት አመታት የጥፋት ተግባራቸውን ወደ አንዳንድ የሁለተኛ ደረጃና መሰናዶ ትምህርት ቤቶች በማስፋት የቀቢፀ ተስፋ እርምጃዎችን ሲወስዱ እየተስተዋሉ ነው። የዘንድሮውን የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መግቢያ ፈተናም በአጠቃላይ ወጣት ተማሪዎች ያሉበትን የእድሜ ደረጃ ታሳቢ በማድረግ በስሜታዊነት የተሳሳተ እርምጃ ውስጥ እንዲገቡ በማነሳሳት ቀድሞውንም ሃገራዊ አለመረጋጋት ለመፍጠር ሲያደርጉት የነበረው ሙከራ ሌላ ማሳያ ነው።
የፈተና ስርዓቱን በማዛባት ተማሪዎችንና ወላጆችን ለሁከትና አመፅ ተግባሮች በቀላሉ ለማስነሳት የጎመጁት የጥፋት ሃይሎች ለሁለተኛ ጊዜ የተዘጋጀውንም ፈተና “እጃችን ገብቷል” በማለት በተፈታኞችና ወላጆቻቸው ስነ ልቦና ላይ ሲዘባበቱ ቆይተዋል። በአንድ በኩል እራሳቸው ያዘጋጁትን የሃሰት ፈተና በማህበራዊ ሚዲያ እያሰራጩ በሌላ በኩል “ተማሪዎች ተረጋግተው እንዲፈተኑ ስንል ፈተናውን አንለቅም” እያሉ የተፈጥሮ ቆዳቸውን ቀይረው ለመታየት ሞክረዋል። ቅሉ የአህያን ቆዳ የለበሰ ጅብ፣ ጅብ እንጂ አህያ ሊሆን አይችልምና በዚህ አስነዋሪ ድርጊታቸው ያተረፉት ቢኖር ይበልጥ መጋለጥንና ይበልጥ መገፋትን  ነው።
በወሰዳቸው የጥንቃቄ እርምጃዎች ብቻ ሳይሆን በተሰራጨው ሃሰተኛ ፈተናም ፈተናው እንዳልተሰረቀ መንግስት ቢያረጋግጥም ተማሪዎች በተረጋጋ መልኩ እንዲፈተኑና በማህበራዊ ሚዲያ ላይ እየተናፈሱ ያሉ ወዥንብሮችን ለመግታት ሲባል ፈተናው እስኪጠናቀቅ ድረስ ማህበራዊ ድረ-ገጾች እንዲዘጉ አድርጓል። ስርቆትን እንደ በጎ ምግባር በአደባባይ በመስበክ የኪራይ ሰብሳቢነት ጥጋቸው የት ድረስ እንደሚዘልቅ ያሳዩን የጥፋት ሃይሎች ይሄኔም ተመልሰው የመረጃ ነፃነትና የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ሆነው ቀርበዋል። እነሱንስ ያስለቀሳቸው የጥፋት መንገዳቸው ስለተዘጋባቸው እንጂ በየጊዜው ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ በመመደብ መላ ሃገሪቱን በመረጃ መረብ እያስተሳሰረ ያለው በኢሕአዴግ የሚመራው መንግስት መሆኑን ማወቅ ተስኗቸው አይደለም።

የዘንድሮው የከፍተኛ ትምህርት መግቢያ ፈተና ማን ምን እንደሆነ በተግባር ቁልጭ አድርጎ ያሳየ ከመሆኑ ባለፈም ወደፊት ለሚሰጡ መሰል ፈተናዎችም ትምህርት ሰጥቶ ያለፈ ነው። ከፈተናው ዝግጅት ጀምሮ እስከ ስርጭትና የፈተና ቀናት ድረስ መደረግ ያለባቸውን ጥንቃቄዎች አጠናክረው የሚያስቀጥሉ አዳዲስ አሰራሮች እንዲዘረጉ አድርጓል። ከጊዜው ጋር እየዘመኑ የመጡ የስርቆት ስልቶችን ለመከላከልም የማንቂያ ደወል ሆኗል። እነዚህን አሰራሮች ይበልጥ ማጥራትና ማጠንከር የፀረ ሰላም ሃይሎችን እኩይ ተግባር ማክሸፍ ብቻ ሳይሆን ከአሁን በፊት በተራ ስርቆት ጥቂት ተማሪዎችን የሚጠቅሙ ክፍተቶችን በመድፈን ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚገባው በጥረት ብቻ መሆኑን ለማረጋገጥ ያስችላል።

No comments:

Post a Comment