EPRDF is a ruling party committed to realize Ethiopia's Renaissance.

Thursday, 18 June 2015

ጓድ ዶ/ር አርከበ ዕቁባይ ከዘመን መፅሄት ጋር ያደረጉት ቆይታ


ታላላቅ የቤት ስራዎቿን ከፊቷ ደቅናና በረጅሙ አስባ እየተጋች ያለች አገራችን ከ10 ዓመታት በኋላ  ቀዳሚ የአፍሪካ የማኑፋክቸሪንግ ማዕከል ትሆናለች ይላሉ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ልዩ አማካሪ ዶክተር አርከበ ዑቕባይ ፡፡ ከ25 ዓመታት በኋላ ደግሞ ኢትዮጵያ የምትደርሰው መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሳይሆን ከፍተኛ ገቢ ካላቸው አገሮች ተርታ መሰለፍ የምትችልበት ዕድል ይፈጠራል ይላሉ በእርግጠኝነት ስሜት፡፡ ይሄ እንዴት ይሆናል? ራዕዩን እውን የምናደግባቸው መሰረቶች በእርግጥ ተጥለዋል? የያኔዋስ ኢትዮጵያ ምን ትመስላለች? ዶክተር አርከበ ዘመን መፅሄታችን ላቀረበችላቸው ጥያቄዎች ዝርዝር ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

ዘመን፡- በግንቦት 20 ድል ከተመዘገቡት ውጤቶች ለእርስዎ ጎላ ብለው የሚታዩት የትኞቹ ናቸው?

ዶክተር አርከበ፡- በእኔ እምነት ግንቦት 20ን ሳስብ መታሰብ ያለበት ነገር ለአንዳንዶች ቀላል ነገር ሊመስል ቢችልም ከዚያ በኋላ የታየው ሰላምና መረጋጋት ትልቁ ስኬት ነው፡፡ ፈጣን ዕድገት ያመጡ ሀገሮች ለዕድገታቸው መነሻ የሆናቸው መሠረቱ ሰላምና መረጋጋት ነው፡፡ ስለዚህ ሰላማችን ሳይናጋ መቆየቱ በአገራችን ብቻ ሳይሆን በአካባቢውም አገሮች ላለው ሰላምን የማረጋጋት ሥራ ኢትዮጵያ አስተዋጽኦ ማድረጓ እንደ አንድ ትልቅ ስኬት መታሰብ ያለበት ጉዳይ  ነው፡፡ ሁለተኛው ነጥብ ከዚያ በፊት አገሪቱ የመበታተን አደጋ ተጋርጦባት ነበር፡፡ ስለዚህ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች የተለያዩ ኃይሎች ለመብትና ለነፃነት እየታገሉ የነበሩበት ጊዜም ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ ግን አገራችን ሳትበታተን አንድነቷ ተጠብቆ የብሔሮችና ብሔረሰቦችም መብት የተረጋገጠባት አገር መሆኗ ሌላው ትልቁ ስኬት ነው፡፡ ለኢኮኖሚው ልማት መሠረቱም ይሄው ነው፡፡

ዘመን፡- በግንቦት 20 የተመዘገቡ ውጤቶች ካለፈው ዘመን ጋር ሲነፃፀሩ እንዴት ይገለፃሉ?

ዶክተር አርከበ፡- ከግንቦት 20/ 1983 .ም በፊትና በኋላ የነበረውን ሁኔታ ማነጻጸር ካለብን ተጨባጭ በሆኑ ነገሮች ላይ ተመሥርተን መነጋገሩ ጠቃሚ ይሆናል፡፡ በእርግጥ በሁሉም መስክ የተሠሩ ሥራዎችን ለመዘርዘር ጊዜውም አይበቃም፤ አስፈላጊም ላይሆን ይችላል፡፡ ከዚህ አንጻር እኔ የማተኩረው ማህበረሰቡን የሚመለከቱ ዋነኛ ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ ነው፡፡ በ1983 .ም የኢትዮጵያ ሕዝብ ቁጥር 47 ሚሊዮን ነበር፡፡ ዓለም አቀፍ አካላት አሁን ያለውን የህዝብ ቁጥር እስከ 94 ሚሊዮን ይገምቱታል፡፡ ስለዚህ ሕዝቡ በእጥፍ አድጓል ማለት ነው፡፡ እንደ መነሻ አድርገን ይሄንን መያዝ አለብን፡፡ አሁን መንግሥት የያዘው ኃላፊነት 47 ሚሊዮን ሕዝብ ብቻ ተጠቃሚ የማድረግ አይደለም፡፡ እጥፍ ለሆነ ሕዝብ ነው ኃላፊነት ይዞ እየሠራ ያለው፡፡ ይሄንን መነሻ ስናደርግ ከ1983 .ም በፊት የነበረውን የድህነት ደረጃም ማስታወስ ይገባል፡፡ በዚያን ጊዜ ከድህነት ወለል በታች በሆነ ኑሮ ውስጥ የነበረው ሕዝብ 54 በመቶ ነበር፡፡ አሁን ግን እጥፍ የሆነ ሕዝብ ይዘን ድህነቱ ከግማሽ በታች ቀንሷል፡፡


በሌላ መልኩ እንደምናውቀው የኢኮኖሚው አንቀሳቃሽ ግብርና ነው፡፡ ግብርናው ደግሞ በተፈጥሮ ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ እኛ አገር ብቻም ሳይሆን አሜሪካና አውስትራሊያም ቢሆን በተፈጥሮ ላይ የተመሠረተ ግብርና አለ፡፡ ይህ ደግሞ እንደ ፋብሪካ አይደለም፡፡ ፋብሪካ ተፈጥሮ ላይ የተመሠረተ አይደለም፡፡ ስለሆነም ባለፉት ዘመናት አገራችንን ስናይ ያጋጠሟት በርካታ ድርቆችና ረሃቦች  ነበሩ፡፡ የ1966 .ም አብዮት እንዲነሳ አንዱ ምክንያት ያ ረሃብ ነበር፡፡ ከዚያም በኋላ በ1977 .ም የነበረውንም ስናስብ በተለይ በሰሜኑ ክፍል ብዙዎች የሞቱበት ረሃብ ነበር፡፡ በመቶ ሺዎች የሚገመቱ አልቀዋል፡፡ ባለፉት 24 ዓመታት የነበረውን ሁኔታ ስናይ ግን በድርቅና በረሃብ በመቶ ሺዎች አይደለም በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች አልሞቱም፡፡ አደጋም በሚያጋጥምበት ጊዜ መንግሥት ያስቀመጠው አቅጣጫ አለ፡፡ በዚህም መሠረት አሁን አንደኛ የአርሶ አደሮች ምርት ጨምሯል፡፡ ነገር ግን በተፈጥሮ ላይ የተመሠረተ ግብርና በመሆኑ ድርቅ ቢያጋጥምም እንኳን መንግሥት ያስቀመጠውን ስትራቴጂክ እቅድ ተጠቅሞ ሊታደግ ስለሚችል አንድም ሰው እንዳይሞት እያደረግን ነበር፡፡ ስለዚህ የአንድም ዜጋ ሕይወት ቢሆን ሳይጠፋ ዛሬ ላይ አገሪቱ በምግብ ራሷን የምትችልበት ደረጃ ላይ እየደረሰች ነው፡፡

ሌላው ደግሞ አንዱ ጥቅል የኢኮኖሚና የዕድገት መለኪያ የአንድ ሰው አማካኝ የዕድሜ ጣሪያ ነው፡፡ በ1983 .ም የነበረው አማካይ የዕድሜ ጣሪያ 47 ዓመት ነበር፡፡ አሁን ግን በዓለም አቀፍ መረጃዎች መሠረት ከሁለት ሦስት ዓመት ወዲህ የኢትዮጵያ የዕድሜ ጣሪያ 63 ዓመት ደርሷል፡፡ ይሄ ማለት እያንዳንዱ ዜጋ በአማካይ 16 ዓመት የዕድሜ ጭማሪ እንዲኖረው ሆኗል ማለት ነው፡፡ ይህ የብዙ ነገሮች ድምር ውጤት ነው፡፡ የጤና መሻሻል፣ የምግብና የትምህርት አቅርቦት ሁሉ ድምር ውጤት ነው፡፡ የሰላምና መረጋጋት ውጤት ነው፡፡ በአፍሪካ እንኳን በ1983 .ም የነበረው የዕድሜ ጣሪያ 50 ነበር፡፡ የእኛን በሦስት ዓመት ይበልጥ ነበር፡፡ አሁን በ2012 ..አ ላይ አድጎ 57 ላይ ነው ያለው፡፡ ስለዚህ ኢትዮጵያ ከአፍሪካ በአማካይ ከ6 ዓመት በላይ ነች፡፡ ከዚህ ውጪ ትምህርት ተስፋፍቷል፡፡ አንድ ሦስተኛ የሚሆኑት ዜጎቻችን በትምህርት ቤት ናቸው፡፡ መሠረተ ልማት በብዛት ተስፋፍቷል፡፡ ስለዚህ ያለፈውን ጊዜ ስናስብ በተለይ አርሶ አደሩ ምርቱን ያሻሻለበት፣ መሠረተ ልማት የተስፋፋበት፣ የማህበራዊ አገልግሎቶች በስፋት የቀረቡበት ሁኔታ ነው የሚታየው፡፡ እነዚህ ሁሉ እንደትልቅ ስኬት መወሰድ ያለባቸው ናቸው፡፡

ዘመን፡- ግን አንዳንድ ወገኖች የህዝቡ ኑሮ አልተሻሻለም እያሉ ነውና በዚህ ላይ ምን አስተያየት አለዎት?

ዶክተር አርከበ፡- ይሄንን የሚቃወሙ ወገኖች የደሃውን ማህበረሰብ ኑሮ የማያውቁ ናቸው፡፡ ዱሮም አያውቁትም፤ አሁንም አያውቁትም፡፡ ስለዚህም መሻሻሉን ሊገነዘቡ አይችሉም፡፡ አሁን የተገኙት ስኬቶች ግን በዓለም አቀፍ መረጃዎችም ጭምር የጠሩ ሆነው የቀረቡ ናቸው፡፡ ለምሳሌ ትምህርት የሚደበቅ አይደለም፡፡ ማንም የሚረዳውና ፊት ለፊት የሚያየው ነው፡፡ ከዚያ ውጪ የሰውን ኑሮ ከሁኔታውና ከአለባበሱ ማየት ይቻላል፡፡ ይህን እውነታ የሚቃወሙ ሰዎች ጉዳዩን የሚያነሱት ከፖለቲካ አቋም ነው፡፡ እነርሱ አማራጭ እንዳላቸው ለማስመሰልና የኢህአዴግን ሥራ ሁሉ አሳንሶ ለማሳየት ስለሚፈልጉ ብቻ ነው፡፡ ስለዚህ ነው የደሀውን ጥቅም አያውቁትም የምለው፡፡ ግድም የላቸውም፡፡

ዘመን፡- ከግንቦት 20 ድል ወዲህ የተገኘውን አጠቃላይ የኢኮኖሚ ዕድገት ሁኔታ በተጨባጭ በአኀዝ  ሊያስገነዝቡን ይችላሉ? ይሄ ዕድገት በትግሉ የተገኘውን ድልስ የሚመጥን ነው?

ዶክተር አርከበ፡- ከግንቦት 20 ወዲህ በሁሉም መስክ የተመዘገቡ በርካታ መልካም ውጤቶች አሉ፡፡ በጣም በተሟላ ሁኔታ ዴሞክራሲያዊ የሚባል አዲስ ሕገ መንግሥት አውጥተናል፡፡ እንደዚሁ ኢኮኖሚውም አምስት ከመቶ፣ ስድስት ከመቶ እያለ ከድሉ በኋላ በነበሩ በመጀመሪያዎቹ ዓመታት ዕድገት ሲታይበት ነበር፡፡ በእርግጥ በመጀመሪያዎቹ አሥር ዓመታት ዕድገቱ ላይና ታች እያለ ነበር የሚሄደው፡፡ ባለፉት 11 ዓመታት ግን በየዓመቱ የ11 በመቶ ዕድገት እየተመዘገበ ቆይቷል፡፡ ባለፉት 11 ዓመታት በተከታታይ 11 በመቶ በዓለም ላይ ያደገ ኢኮኖሚ የኢትዮጵያ ብቻ ነው፡፡ የዚህ ቁጥር አንድምታ ምን እንደሆነ ማየት እንችላለን፡፡ የሩቅ ምሥራቅ ሀገሮች ኮሪያ፣ ታይዋን፣ ቻይናን ያየን እንደሆነ በዚሁ መጠን ነው የሚያድጉት፡፡ ስለዚህ ወደ እነሱ የዕድገት ሁኔታ የምንደርስበት አጋጣሚ እንዳለ አመላካች ነው፡፡ የሚለየው ነገር ካለ በእኛ ሀገር ባለፉት ዓመታት ዋነኛው የኢኮኖሚ አንቀሳቃሽ ሞተር ግብርና መሆኑ ነው፡፡ አንዱ መረሳት የሌለበት ነጥብ በዓለም ላይ ከ11 በመቶ በላይም የሚያድጉ አገሮች አሉ፡፡ እንደነ ኳታር ያሉት አንዳንዴ እስከ 25 በመቶ በዓመት ያደጉበት ሁኔታ አለ፡፡የእነርሱ የዕድገት ምንጭ ግን ነዳጅ ነው፡፡ ስለዚህ የዕድገቱ ደረጃ ሳይሆን የዕድገቱ ምንጭም ወሳኝ ጉዳይ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ግን ቀዳሚው ግብርና ነው፡፡ ተከታዩ ደግሞ ኢንዱስትሪ ነው፡፡ ስለዚህ በአብዛኛው የዕድገቱ ተጠቃሚ በግብርናው ውስጥ ያለው ብዙው ሕዝብ ነው፡፡ ነዳጅ ሲሆን ግን ጥቂት ባለሀብቶች ወይም ግለሰቦች የሚከብሩበት ሁኔታ ነው የሚኖረው፡፡ አንዱ የእኛን ዕድገት ተመራጭ የሚያደርገው አብዛኛውን ሕዝብ ተጠቃሚ የሚያደርገውን ግብርናን መሠረት ማድረጉ ነው፡፡


ዘመን፡- መንግሥት እስከአሁን በዚህ ደረጃ ሠርቷል ከተባለ በሚቀጥሉት አሥር ዓመታት አገራችን ምን ደረጃ ላይ እንድትደርስ ነው ታስቦ እየተሠራ ያለው ?

ዶክተር አርከበ፡- ይሄ መሠረታዊ ጥያቄ ነው፡፡ መንግሥት ይሄን ጉዳይ  በስፋት አስቦበታል፡፡ በተለይ ባለፉት አምስት ዓመታት ፈጣን ዕድገትና መዋቅራዊ ለውጥ ማምጣት የሚያስችል ዕቅድ ተይዞ ነበር ይሠራ የነበረው፡፡ ስለዚህ በዋናነት  የተነሳንበት የኢኮኖሚ ደረጃ ዝቅተኛ ነበር፡፡ 80 ከመቶ ያህሉ ግብርና ነው፡፡ ስለዚህ ግብርናችን መሻሻል እንዳለበት ነው መንግሥት ያየው፡፡ ስለዚህ መንግሥት አሁን የሚያስበው ፈጣን ዕድገት ማምጣት ብቻ ሳይሆን መዋቅራዊ ለውጥ በሚያመጡ ጉዳዮች ላይ ማተኮር አለብን የሚለው ነጥብ ላይ ነው፡፡ ይህ ምን ማለት ነው? ግብርና በማኑፋክቸሪንግ ካልታገዘና የግብርና ምርቶች ለኢንዱስትሪ መቅረብ ካልቻሉ፤ እንደዚሁም ግብርናው የተሻሻሉ ቴክኖሎጂዎችንና የኢንዱስትሪ ግብአቶችን መጠቀም ካልቻለ የግብርና ምርታማነት አይሻሻልም፡፡ ሄዶ ሄዶ መቆሙ አይቀርም፡፡ ስለዚህ በአሁኑ ወቅት ትልቁ አጀንዳችን ማኑፋክቸሪንግ ኢኮኖሚውን እንዴት ይምራው? የሚለው ነው፡፡ እርሱን ስናጠናክር ደግሞ ግብርናውን ከዚህ በተሻለ ደረጃና ጥራት እንዴት ማሳደግ ይቻላል? የሚሉት ቁልፍ ጥያቄዎች ዋነኞቹ ይሆናሉ፡፡ ስለዚህ በዚህ ዙሪያ በመንግሥት የተያዘው ዕቅድ ከፈጣን ኢኮኖሚ ዕድገት አኳያ ለሚቀጥሉት አስር ዓመታት 10 እና 11 በመቶ በየዓመቱ ማደግ አለብን የሚል ነው፡፡ በዚህ ደረጃ ካላደግን ሌሎች ላይ መድረስ አንችልም፡፡ አሰላለፋችን ከኋላ ነው የሚሆነው፡፡ ስለዚህ ይሄንን መለወጥ ካስፈለገ ቢያንስ ለአሥር ዓመታት 11 በመቶ ማደግ ይኖርብናል ፡፡ ይህን በምናደርግበት ጊዜ የዜጎችም የነፍስ ወከፍ ገቢ እንደዚሁ ይሻሻላል፡፡ እስከአሁን መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገራት ተርታ መሰለፍ አለብን የሚለው ጉዳይ ብዙ ጊዜ ይነሳል፡፡ ይሄ ማለት 1500 ዶላር ነው፡፡ እኛ ግን በተባለው መንገድ ማደግ ከቻልን ከ10 ዓመት በኋላ እስከ 2300 ዶላር መድረስ እንችላለን፡፡ በፈረንጆቹ 2025 ላይ የሕዝቡም ብዛት ይቀየራል፤ እስከ 115 ሚሊዮን እንደሚደርስ ይገመታል፡፡ ያም ሆኖ የነፍስ ወከፍ ገቢው እየጨመረ ይሄዳል ማለት ነው፡፡

የኢኮኖሚው ዋነኛ አንቀሳቃሽም ማኑፋክቸሪንግ መሆን አለበት እያልን ነው፡፡ ይሄ ግብርናውንም በፍጥነት እንዲያድግ ያደርገዋል፡፡ ይሄ በሁሉም በኢንዱስትሪ የበለጸጉ አገሮች የታየና የተረጋገጠ ነው፡፡ ስለዚህ አሁን የተያዘው ዕቅድ በማኑፋክቸሪንግ ሁለት ሚሊዮን የሥራ ዕድል መፍጠር አለብን የሚል ነው፡፡ ይሄ በአነስተኛና ጥቃቅን የሚፈጠረውን የሥራ ዕድል ሳይጨምር ነው፡፡ ይሄ በመካከለኛና በከፍተኛ ኢንዱስትሪዎች የሚፈጠረውን የሚመለከት ነው፡፡ ስለዚህ በየዓመቱ በአማካኝ ሁለት መቶ ሺህ የሥራ ዕድል እንዲፈጠር ነው ግብ ያስቀመጥነው፡፡ ይሄ ትልቅ ነው ወይስ ትንሽ ነው? የሚለውን ለመረዳት የሚጠቅመን በአገራችን ባለፉት ሃምሳ ዓመታት በመካከለኛና ከፍተኛ ኢንዱስትሪዎች ውስጥ የሥራ ዕድል ያገኘው ሰው ቁጥር ምን ያህል ነው? የሚለውን ስንረዳ ነው፡፡ ይሄ ሦስት መቶ ሃምሳ ሺ ነው፡፡ ሦስት መቶ ሃምሳ ሺ ትልቅ ቁጥር አይደለም፡፡ ስለዚህ እኛ እያልን ያለነው በየዓመቱ የዚህን ግማሽ ያህል የሥራ ዕድል እንፍጠር ነው፡፡ ስለዚህ ይህ መሠረታዊ ለውጥ የሚያመጣ ነው፡፡

ሁለተኛው ማኑፋክቸሪንግ በኢኮኖሚው ውስጥ ያለው ድርሻ ከአምስት ከመቶ ያልበለጠ ነው፡፡ ኢንዱስትሪውን በጥቅል ስናይ እስከ 15 ከመቶ ነው ድርሻው፡፡ ኢንዱስትሪ ሲባል ማዕድንን፣ ኮንስትራክሽንን ማኑፋክቸሪንግንም ይይዛል፡፡ ካሉት ልምዶች ሲታይ ግን ዕድገት የሚያመጣው ማዕድንም ኮንስትራክሽንም አይደለም፡፡ ዕድገት ሊያመጣ የሚችለው ማኑፋክቸሪንግ ሴክተሩ ነው፡፡ ስለዚህ በሚቀጥሉት አሥር ዓመታት ማኑፋክቸሪንግ ሴክተሩ በአራት እጥፍ እንዲያድግ ነው ግብ የተቀመጠው፡፡ በኢኮኖሚው ውስጥ ሃያ በመቶ ድርሻ ሊኖረው ይገባል ማለት ነው፡፡ መካከለኛ ገቢ ላይ የደረሱና በማኑፋክቸሪንግ ላይ ያተኮሩ እንደነ ቻይና፣ ኮሪያ፣ ታይዋን፣ ቬትናም፣ ቱርክና ብራዚል የመሳሰሉት አገሮች የደረሱበትን ስናይ ማኑፋክቸሪንግ ሴክተሩ በአማካኝ እስከ ሃያ በመቶ ነው ድርሻ ያለው፡፡ አንዳንዶቹ በማኑፋክቸሪንግ ውስጥ ያልገቡ ነገር ግን መካከለኛ ገቢ ካላቸው ውስጥ የገቡ እንደ ናይጄሪያ ያሉ አገሮችም አሉ፡፡ የእነርሱ ግን በነዳጅ ላይ የተመሠረተ ነው፡፡

 ሌላው መታሰብ ያለበት ደግሞ የኤክስፖርት ድርሻው ነው፡፡ እዚህ ላይ መጠኑ አይደለም መታሰብ ያለበት፡፡ ኤክስፖርት የሚደረጉ ነገሮች ምንድንናቸው? የሚለው ነው፡፡ ጥራጥሬና ቡና ኤክስፖርት ማድረግ የዕድገት መገለጫ አይደለም፡፡ ወሳኙ ጉዳይ የኤክስፖርቱ ድርሻ ምን ያህል ነው? የሚለው ነው፡፡ አሁን የዚህ ድርሻው ወደ አሥር በመቶ ነው፡፡ በሚቀጥለው አሥር ዓመት ውስጥ በአራት እጥፍ ማደግ አለበት ነው፡፡ ስለዚህ የኤክስፖርት ድርሻ አርባ በመቶ እንዲሆን እንሠራለን፡፡ ስለዚህ ያስቀመጥናቸው ግቦች በፋብሪካዎች ሁለት ሚሊዮን የሥራ ዕድል መፍጠር፣ ይሄም በትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ ውስጥ የሚኖረውን ድርሻ ሃያ በመቶ ማድረስ፣ በኤክስፖርት ያለውን ድርሻ ደግሞ አርባ ከመቶ ማድረስ ነው፡፡ ይሄንን ለማድረግ ግን ኢኮኖሚው በጥቅል በየዓመቱ 11 ከመቶ ማደግ አለበት ብለናል፡፡ ይህ ሲሆን ከአጠቃላዩ ዕድገት ማኑፋክቸሪንግ የ20 በመቶ የዕድገት ድርሻውን መውሰድ አለበት እያልን ነው፡፡ ይህ በእርግጥ ፈታኝ ነው፡፡ ሆኖም ይህን ማድረግ ከቻልን ግን ያሰብነውን ውጤት ማምጣት እንችላለን፡፡

በዚህ ጉዳይ ላይ ያስቀመጥናቸው ነገሮች ግን እነዚህ ብቻ አይደሉም፡፡ ይሄንን ለማሳካት ምን ማድረግ አለብን? የሚለው ተነስቷል፡፡ አንደኛ ሠፊ ኢንቨስትመንት ወደ ማኑፋክቸሪንግ መፍሰስ አለበት፡፡ አሁን ያሉት ፋብሪካዎች ያላቸውን አቅም ሁሉ አሟጠው ቢጠቀሙም የምናስበውን ውጤት ሊያመጡ አይችሉም፡፡ ስለዚህ ከአገር ውስጥም ከውጭም ትልቅ የኢንቨስትመንት ፍሰት መኖር አለበት፡፡ የውጭ ኢንቨስትመንት የሚጠቅመን የሚያስፈልገውን ቴክኖሎጂ ለመማር፣ የገበያ አቅም ለመገንባት፣ የአመራር ዘዴ ለማወቅ ነው፡፡ ሁለተኛው ግን የአገራችን ባለሀብት በኢንዱስትሪው መሰማራት አለበት የሚል ነው፡፡ አሁን በአብዛኛው የአገራችን ባለሀብት የሚሰማራው በንግድና በአገልግሎት ዘርፍ ነው፡፡ ይህ ሁኔታ መቀየር አለበት፡፡ ስለዚህ መንግሥት ለዚህ ማበረታቻ በመስጠት ባለሀብቶቻችን ወደዚህ እንዲገቡ በተለይ ደግሞ ወጣት ኢዱስትሪያሊስቶች እንዲፈጠሩ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ይሄ አንዱ ቁልፍ ስትራቴጂ ብለን የወሰድነው  ጉዳይ ነው፡፡ ከውጭ ኢንቨስትመንት ስንስብም ሁሉም አገሮች ላይ ማተኮር የለብንም ብለናል፡፡ አንደኛ የማኑፋክቸሪንግ አቅም ያላቸው አገሮች ላይ እናተኩር የሚል ነው፡፡ ምክንያቱም የኢንቨስትመንት ማስፋፋት አቅማችን ውሱን ነው፡፡ ስለዚህ በእነርሱ ላይ ብቻ ማተኮር አለብን፤ እንደነ ቱርክ፣ ቻይና በመሳሰሉት ላይ ማለቴ ነው፡፡

ሌላው እያልን ያለነው በማኑፋክቸሪንግ ሴክተርም ቅድሚያ የምንሰጣቸው የተለዩ ሴክተሮች ይኑሩን ነው፡፡ ለምሳሌ ቆዳና የቆዳ ውጤቶች፣ የጨርቃ ጨርቅና የአልባሳት፣ የመድሃኒትና የአግሮ ኢንዱስትሪ በመንግሥት የተለዩ ቁልፍ ሴክተሮች ናቸው፡፡እንደዚሁም የምንስባቸውም የውጭ ኢንቨስተሮች ሁሉም መሆን የለባቸውም፡፡ ማተኮር ያለብን ትላልቆቹ ላይና በቴክኖሎጂና በገበያ ትልቅ አቅም ያላቸው ላይ መሆን አለበት የሚል ነው፡፡ ለዚህ ዋናው ምክንያት እነዚህ ምርጥ ድርጅቶች ከአገራቸው ውጭ በሚንቀሳቀሱበት ጊዜ ብዙ ማነቆ  ቢሚያጋጥማቸውም በቀላሉ አይወድቁም፡፡ ይህ አንዱ መነሻችን ነው፡፡ ሁለተኛው ምክንያት ግን የአገራችን ኢንዱስትሪያሊስቶች መማር ያለባቸው ምርጥ ከሚባሉ ከእነዚህ አገሮች ነው፡፡ ሩጫ ለመልመድና በሩጫው ብልጫ ለማሳየት መማር ያለብህ ከኃይሌ ገብረሥላሴ ወይም ከደራርቱ ነው፡፡ ስለዚህ መንግሥትም ሁሉንም ማግበስበስ የለበትም ነው፡፡

ሌላው አቅጣጫ ብለን የያዝነው የኢንዱስትሪ ፓርኮችን ማስፋፋት ነው፡፡ አሁን ባስቀመጥነው አቅጣጫ መሠረት በየዓመቱ ካሉን ፋብሪካዎች ግማሽ ያህሉን በየዓመቱ እንፍጠር እያልን ነው፡፡ ስለዚህ በየዓመቱ በመቶዎች የሚቆጠሩ ፋብሪካዎች ይመጣሉ ማለት ነው፡፡  ነገር ግን ሁሉም ቦታ ፋብሪካዎች ተበታትነው ከተቋቋሙ የተለያዩ ጉዳቶች ያመጣሉ፡፡ አንዱ የአካባቢ መበከል ጉዳት ማስከተሉ ነው፡፡ ሁለተኛው ጉዳት ለሁሉም መሠረተ ልማት ለማቅረብ ይከብደናል፡፡ በዚህም የተነሳ ትልቅ የመሠረተ ልማት እንቅፋት ያጋጥማቸዋል፡፡ በዚህም የተነሳ ቶሎ ወደ ሥራ አይገቡም፡፡ አሁን በቆየው አካሄድ ኢንቨስተሮች ወደ ምርት ለመሸጋገር እስከ ሦስት ዓመት ይፈጅባቸዋል፡፡ በሌላ መልኩ ደግሞ ይሄ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን ማስፋፋት ሥራ መሬት በቁጠባ ለመጠቀምም ይረዳል፡፡ ለምሳሌ አንዳንዶች አንድ ሺህ ካሬ ሜትር ሲበቃቸው የሚወስዱት አስር ሺህ ካሬ ሜትር ነበር፡፡ በኢንዱስትሪ ፓርክ ሲሆን ግን ይሄን ብክነት መቆጣጠር ይቻላል፡፡ ከዚህ በፊት መሬት ሲወስዱ ለሌላ አገልግሎት እናውለዋለን ብለው አስበው ነው የሚወስዱት፡፡ በፓርክ ሲሆን ግን መሬት ሲወስዱ መሬቱን ለሌላ ተግባር ሊለውጡት አይችሉም፡፡ በተለይ ለኢትዮጵያውያን ኢንዱስትሪያሊስቶች ደግሞ በትንሽ ካፒታል ወደ ሥራ እንዲገቡ ያስችላቸዋል፡፡ ምክንያቱም ከባንክ ብድር የሚፈልጉት ለማሽነሪ ግዢና ለሥራ ማስኬጃ ብቻ ነው፡፡ ሕንፃውና  መሠረተ ልማቱ በሙሉ የተዘጋጀ ነው፡፡ ተከራይተው መጠቀም ይችላሉ፡፡ ስለዚህ በስመ ኢንቨስትመንት ከባንክ ብዙ ሚሊዮኖች እየወሰዱ ለሌላ ለፈለጉት ዓላማ መጠቀሙንም ያስቀርልናል፡፡

የኢንዱስትሪ ፓርኮች እጅግ በጣም ትልቅ ፋይዳ ያላቸው ናቸው፡፡ ኪራይ ሰብሳቢነትንም ለመግታት ያስችለናል፡፡  የመሬት፣ የመሠረተ ልማትና የካፒታል ሀብታችንን በቁጠባ መጠቀም ያስችለናል፡፡ ሌላው ፋብሪካዎች አንድ አካባቢ ሲሰባሰቡ አንዱ ከሌላው ለመማርና የግብዓት ትስስርም ለመፍጠር ያስችላል፡፡ የቴክኖሎጂ ዕድገት ለማረጋገጥም ይረዳናል፡፡ የቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ፓርክ ከመጀመሩ ውጪ እስከ አሁን በኢንዱስትሪ ፓርክ ዙሪያ ብዙ ሥራ ገና አልሠራንም፡፡ ያም ቢሆን ረጅም ጊዜ ነው የፈጀው፡፡ ስለዚህ መንግሥት ከኢሲያ  እንደ ቻይና፣ ኮሪያ፣ ሲንጋፖር ካሉት አገሮች ከአፍሪካም እንደነ ናይጀሪያ ልምዳቸውን በሚገባ በመቀመር አስቀድሞ የጥናት ፖሊሲ ሰነድ አዘጋጅቷል፡፡ እርሱ ላይ አመራሩ በሚገባ ከተወያየበት በኋላ ቀጣይ እርምጃዎች እየወሰደ ነው፡፡ ለምሳሌ ከወር በፊት የኢንዱስትሪ ፓርኮች አዋጅ ተዘጋጅቷል፡፡ ምርጥ ልምዶችን መነሻ ያደረገ አስፈላጊ የህግ ማዕቀፍ ተዘጋጅቷል፡፡ ይሄን ጉዳይ የሚያስፈጽም ተቋም ማለትም የኢንዱስትሪ ልማት ፓርኮች ኮርፖሬሽን ተመሥርቷል፡፡ ለዚህ የሚያስፈልገውን ፋይናንስ መንግሥት እየመደበ ነው፡፡ ለምሳሌ በአሁኑ ወቅት መጀመሪያ ለምናለማቸው ፓርኮች 750 ሚሊዮን ዶላር መድቧል፡፡ እንደዚሁም ቦሌ ለሚ 2 የሚገነባው በዓለም ባንክ 250 ሚሊዮን ዶላር ነው፡፡ ስለዚህ በድምሩ አንድ ቢሊዮን ዶላር አድርገን ነው ሥራ የምንጀምረው፡፡ በየዓመቱ ያን ያህል ለማስፋት ነው የምናስበው፡፡ ስለዚህ ሁለት ሚሊዮን የፋብሪካ ሠራተኞች ይኖሩናል ካልን በአማካይ የሚያስፈልገን የኢንዱስትሪ ሕንፃዎች ስፋት ሃያ ሚሊዮን ካሬ ሜትር የፋብሪካ ሕንፃ ነው፡፡ ይሄ በጣም ሠፊ ነው፡፡ ያሰብንውን ዕቅድ ለማሳካት ግን የግድ ያስፈልገናል፡፡ 

በዚህ ረገድ ምን ያህል መሬት መልማት አለበት? ብንል በየዓመቱ 10 ሺህ ሄክታር ያስፈልገናል፡፡ በአስር ዓመት 100 ሺህ ሄክታር ነው የሚለማው፡፡ ይሄን ዓይነት ሥራ ጥራት ባለው መልክ ከሠራን ኢንቨስትመንት በቀላሉ ወደ ሥራ ይገባል፡፡ በሦስት ወር ውስጥ ወደ ምርት ይገባሉ፡፡ የፋብሪካ ሕንፃ ይከራያሉ፤ ማሽኖቻቸውን ይተክላሉ፤ ሰው ቀጥረው ያሠለጥናሉ፤ ከሦስት ወር በኋላ ኤክስፖርት ማድረግ ይችላሉ፡፡ አሁን ግን ከሦስት ዓመት በኋላ ነው ወደ ሥራ የእየገቡ ያሉት፡፡ ስለዚህ አጭር የዝግጅት ጊዜ እንዲሆን ይረዳናል፡፡ እንደገናም መንግሥት እያሰበ ያለው በእያንዳንዱ የኢንዱስትሪ ፓርክ የአንድ ማዕከል የመንግሥት አገልግሎት እንዲኖር ነው፡፡ የቪዛ አገልግሎት እዚያ እንዲያገኙ፤ የፈቃድና ምዝገባ፣ እድሳት እዚያ እንዲያገኙ፤ ባንኮች ፓርኩ ጋ ቅርንጫፍ እንዲከፍቱ፤ እዚያ ያሉ ፋብሪካዎችም ስለምርትና ስለ ሽያጭ ብቻ እዲያስቡ፤ የመንግሥት አገልግሎቶች እንቅፋት  እንዳያጋጥማቸው ለማድረግ ነው፡፡ የጉምሩክ ፍተሻና አጠቃላይ ሂደቱም ሙሉ በሙሉ በፓርኩ እንዲያልቅ ነው፡፡ ስለዚህ አሁን የምናያቸው በርካታ የቢሮክራሲ ማነቆዎችን በአስተማማኝ ሁኔታ ለመፍታት የሚቻልበት መንገድ ነው አሁን የተቀየሰው፡፡ የኢንዱስትሪ ፓርክ በጣም ውድ ነው፡፡ ግን ደግሞ ሠፊ ማኑፋክቸሪንግ እናድርግ ካልን ያለ እርሱ ሊሆን የሚችል አይደለም፡፡ 

በመጀመሪው ዙር የኢንዱስተሪ ፓርኮች እንዲስፋፉባቸው ከተመረጡት ከተሞች አንደኛው አዲስ አበባ ነው፡፡ ቦሌ ለሚ 2 እና ሌላ ተጨማሪ ይኖረናል፡፡ ሁለተኛ ድሬዳዋ ከተማ ነው፡፡ ሦስተኛ አዳማ፤ አራተኛ ሃዋሳ፤ አምስተኛ ኮምቦልቻ፤ ስድስተኛ መቀሌ ናቸው፡፡ የኢንዱስትሪ ልማቱ ፍላጎት ሲያድግ ተጨማሪ ከተሞች በዚህ ረድፍ እንዲገቡ እናደርጋለን፡፡ ለምሳሌ ጅማ፣ ባሕር ዳር፣ አዋሽ አርባ የመሳሰሉትም ይኖሩናል፡፡ እዚህ ላይ አንዱ ግልጽ ሊሆንልን የሚገባው ከተሞችን ስንመረጥ ዋና መነሻ የምናደርገው አንደኛ አካባቢው ሠፊ ጉልበት ያለው መሆን አለበት፡፡ ምክንያቱም ጉልበት ካለ ነው ፋብሪካዎቹ ማሠራት የሚችሉት፡፡ ሁለተኛ ደግሞ የመሠረተ ልማትና የባቡር ጣቢያዎች ያሉበት አካባቢ መሆን አለበት፡፡ የባቡር ትራንስፖርት መጠቀም ካልቻልን በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ መሆን አንችልም፡፡ ከተቻለም የአውሮፕላን ማረፊያ እዲኖር ያስፈልጋል፡፡ በርካታ የውጭ ዜጎች፣ ገዢዎችም፣ ባለሙያዎችም ብዙ ምልልስ ስለሚያደርጉ የአውሮፕላን ማረፊያ ያስፈልጋል፡፡ ፡፡ እናም በዚህ ሁኔታ በኢንዱስትሪ ፓርክ ልማት በአፍሪካ ውስጥ ምናልባትም የመጀመሪያው ስኬታማ የሆነ የኢንዱስሪ ፓርኮች የሚስፋፉበትን ሁኔታ ነው የምንፈጥረው፡፡

የኢንዱስትሪ ፓርኮች ስንገነባ ደረጃቸው ከፍተኛ መሆን አለበት ነው እያልን ያለነው፡፡  በየዘርፉ ነው መሆን ያለባቸው፡፡ለምሳሌ የሃዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ የጨርቃጨርቅ ነው ከተባለ በዚህ ዘርፍ የሚሰማሩ ፋብሪካዎች በሙሉ እዚያ ይገባሉ ማለት ነው፡፡ አንድ ዓይነት ይሆናሉ፡፡ መሠረተ ልማቱም ለእነርሱ በሚመች መልኩ ነው የሚሠራው፡፡ ድሬዳዋም የኢንዱስትሪ መሣሪያዎች ማምረቻ ካለ እደዚያው፡፡ ስለዚህ በየዘርፉ እንዲደራጁ ነው እያሰብን ያለነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ፓርኮቹ አረንጓዴ የኢንዱስትሪ ልማት እዲሆኑ ነው እያሰብን ያለነው፡፡ ይሄም ኢኮ ኢንዱስትሪያል ፓርክ ተብሎ ነው የሚጠራው፡፡ አካባቢን የማይበክል እዲሆን ተደርጎም ነው የሚሠራው፡፡ ሀብት የሚቆጥብ እንዲሆን ነው የሚፈለገው፡፡ ለምሳሌ ውሃን ዳግም መጠቀም የሚስችል፤ ኃይል የሚቆጠብበት ሁኔታ መፈጠር አለበት የሚል ነው፡፡ ይህ ትልቅ የውድድር ምንጭ ሊሆነን ይችላል፡፡ ሦስተኛ በተለይ ለሠራተኞች ደህንነት የሚያስፈልጉ ነገሮች የተሟሉ መሆን አለባቸው፡፡ ፋብሪካዎች በተለይ የኢንዱስትሪ ፓርኮች  ብዙ ሠራተኛ መቅጠራቸው ስለማይቀርና የመኖሪያ ቤት ችግር ስለሚኖር መንግሥት ሊያበረታታቸው ነው ጥረት የሚያደርገው፡፡ ስለዚህ ማደሪያ ክፍሎች መገንባት ለሚፈልጉ መሬት በነፃ እንሰጣቸዋለን፡፡ ይሁን እንጂ ቤቶቹ ፋብሪካ ውስጥ አይደለም የሚገነቡት፡፡ ከፓርኩ አንድ ጫፋ ጋ ነው የሚሆኑት፡፡ ለአገር ውስጥ ባለሀብቶች ብድርም ሌላም ይመቻችላቸዋል፡፡ ግን ደግሞ ውጤታማ መሆን አለባቸው፡፡ ከተወሰነ ዓመት በኋላ ውጤት ያመጡት በተጨማሪ እንዲስፋፉ ይደረጋሉ፡፡ ውጤት ያላመጡት ደግሞ መውጣት አለባቸው፡፡ አልቻሉም ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ፓርኮቹ ትልቅ ለውጥ ያመጣሉ፡፡ ሌላው ለውጥ እናመጣለን ብለን ያሰብነው ወይም ዝግጅት እያደረግን ያለነው በማኑፋክቸሪንግ የሚፈለጉ መሠረተ ልማቶችን ማስፋፋት ነው፡፡ ሁሉም መሠረተ ልማት ለኢንዱስትሪ እኩል ጠቀሜታ ነው ያለው፡፡ አሁን በተለይ የምንገነባቸው ኢንዱስትሪዎች ብዙ ስለሆኑ ራዕያችን በአፍሪካ ትልቁን የማኑፋክቸሪንግ አቅም በቀጣይ አስር ዓመት እንገነባለን እያልን ነው ያለነው፡፡

ስለሆነም በቀጣይ አንዱ የሚያስፈልገን የባቡር መስመር ማስፋፋት ነው፡፡ በባቡር መስመር እስከአሁን ድረስ ላለፉት አምስት ዓመታት ውጤታማ የሆነ ሥራ ሠርተናል፡፡ ከጅቡቲ አዲስ አበባ ነው ትልቁ ኮሪደራችን፡፡ እርሱም በሚቀጥለው ጥቅምት ሥራ ይጀምራል፡፡ ይሄ በኢኮኖሚያችን ላይ ከፍተኛ ለውጥ ያመጣል፡፡

ሌሎች የተጀመሩትን ስናይ ወደ 1500 .. ያክል ግንባታ እየተካሄደ ነው፡፡ ተጨማሪ 1500 .. ለመገንባት የሚያስችል ቅድመ ሁኔታ እያደረግን ነው የቆየነው፡፡ አሁን ባቀድነው መሠረት በሚቀጥሉት 5 ዓመታት ከባቡር መስመሮቻችን እስከ 50 በመቶ በዋናው ዕቅዳችን  50 በመቶ ደግሞ በዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ እንገነባለን ብለን ነው ያሰብነው፡፡ እዚህ ላይ ያካተትናቸው በርካታ አዲስ መስመሮች አሉ፡፡ አንደኛው ታጁራ ከሚባው የጅቡቲ ወደብ (አዲስ ወደብ ነው፤ ከወደ ሰሜኑወደ ሰመራ አሳኢታ ከዚያም ወደ ወልዲያ፤ ከወልዲያ ወረታ፤ ከወረታ ባሕር ዳር፤ የሚገነባ የባቡር መስመር ነው፡፡

አሁን በሁለተኛው የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን  ጀምረን እጨርሰዋለን፡፡ ይሄ ወደ 800 ኪሜ ነው፡፡ ሁለተኛ ከአዲስ አበባ ወይም ሰበታ ወደ አምቦ፤ ኢጃጂ፤ ከዚያም ጅማ፤ ከዚያ ወደ በደሌ 500 ኪሜ እንገነባለን፡፡ ሦስተኛው ከሞጆ እስከ ሃዋሳ እንዲሁም ከሻሸመኔ እስከ ሶዶ እና አርባ ምንጭ እንዲገባ ነው የምናደርገው፡፡ ሦስቱም ሥራ ነው፡፡ እነዚህን በሁለተኛው የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን ማሳካት ከቻልን አብዛኛው ተገንብቷል ማለት ነው፡፡ በሦስተኛው የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን  የሚቀረን ከ1000 ኪሜ ኪሎ ሜትር ያልበለጠ ነው፡፡ ይህም በግንባታው ስፋትም ሆነ በአህጉራችን በጣም ትልቁ ሊባል የሚችል ነው፡፡ የግንባታው አካሄድም በፈለግነው መልክ ነው እየሄደ ያለው፡፡ ከአዲስ አበባ እስከ ጅቡቲ ያለው በአሁኑ ወቅት መስመር የመዘርጋት ሥራ ተጠናቋል፡፡ ይህ ሥራ በዓለም ደረጃ ፈጣን ከሚባሉት ፕሮጀክቶች አንዱ ሆኗል፡፡ በዚህ አካሄዳችን ባቡሮች የምንጠቀመው በኤሌክትሪክ ኃይል ነው፡፡ ስለዚህ አካባቢ አይበክሉም፤ ወጪያቸው ትንሽ ነው፤ እንደዚሁም በአገር ውስጥ የሚመረት ኃይል ነው የምንጠቀመው፡፡ ፍጥነቱ እስከ 120 ኪሜ በሰዓት ነው፡፡ ይህ ማለት ከጅቡቲ ተነስቶ በዘጠኝ እና አስር ሰዓት አዲስ አበባ መድረስ ይቻላል ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ይሄ ለማኑፋክቸሪንግ በጣም ወሳኝ ነው፡፡

ሁለተኛ በኃይል አቅርቦት ዙሪያ መንግሥት ለማስፋፋት ሥራ  የላቀ ትኩረት ይሰጣል፡፡ ሥራው ግን በጣም ውድ ነው፡፡ ለኤሌክትሪክ ሥራ የሚፈልገው ወጪ ከፍተኛ ነው፡፡  ትልቁን ለውጥ ያመጣል ብለን የምናስበው የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ነው፡፡ እነዚህ አሁን እየተካሄዱ ያሉ ፕሮጀክቶች በቀጣይ ሁለት ዓመታት ሲጠናቀቁ ያኔ የሚኖረን ኃይል ወደ 12 ሺ ሜጋ ዋት ይጠጋል፡፡ 12 ሺህ ሜጋ ዋት ብዙ ነው ወይስ ትንሽ ነው? የሚል ጥያቄ ሊነሳ ይችላል፡፡ ይሄን ለማነጻጸር የሚረዳን በአፍሪካ ትልቁ ኢኮኖሚ የናይጄሪያ ነው የሚባለው፡፡ ናይጄሪያ የምታመነጨው ስንት ነው? ስንል 4 ሺህ ሜጋ ዋት ነው፡፡ ስለዚህ ከሁለትና ሦስት ዓመት በኋላ የናይጄሪያን ሦስት እጥፍ ነው የምናመርተው፡፡ ግን ይሄ በቂ አይደለም፡፡ ስለዚህ መንግሥት በሁለተኛውና በሶስተኛው የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን  በከፍኛ ደረጃ ለማስፋፋት አስቧል፡፡  አሁን የኃይል መቆራረጥ እንዳለ እውቃለሁ፡፡ መቆራረጥ ካለ ምርታማ መሆን አይቻልም፡፡ ምርቶች ይበላሻሉ፡፡ ስለዚህ ይሄን ለማሻሻል ትልቁና ቁልፍ ሥራ የተቋሙ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ይሄንን ለመደገፍ ተጨማሪ የኃይል አማራጭ አቅርቦት እዲገነባ እያሰብን ነው፡፡ በኢንዱስትሪ ፓርኮች አካባቢ አስተማማኝ የኃይል ምንጭ ሊኖር ይገባል፡፡

ሌላው ደግሞ ፈጣን መንገድ የምንለው ነው፡፡ ባቡር ብቻ በቂ አይደለም፡፡ ስለዚህ የፍጥነት መንገድ  ማስፋፋት አለብን፡፡ እነዚህን ካሟላን በማኑፋክቸሪንግ ሴክተር ላይ የምንፈልገውን ጥራት እናመጣለን ማለት ነው፡፡

እነዚህ ብቻ በቂ አይደሉም፡፡ ሰፊ የቴክኖሎጂ ሽግግርም ማምጣት አለብን፡፡ የቴክኒክና ሙያ ተማሪዎቻችንን ለኢንዱስትሪው ማዘጋጀት አለብን፡፡ በዩኒቨርሲቲ እየተማሩ ያሉ ተማሪዎቻችን ሰፊ የኢንዱስትሪ ልምድ ማግኘት አለባቸው፡፡ ወጣቱም ትኩረት ማድረግ ያለበት የራሱን ተቋም ለማቋቋም መሆን አለበት፡፡ ወጣቱ የፋብሪካ ሰው መሆን አለበት፡፡ የፋብሪካ ልምድ ከያዘ ከፋብሪካም ወጥቶ የራሱን ተቋም መመሥረት ይችላል፡፡ ስለዚህ ወጣቱ መሰማራት ያለበት በአገልግሎት ዘርፍ ብቻ ሳይሆን በፋብሪካ ዙሪያም መሆን አለበት፡፡ ይሄም ለየት ያለ ዲሲፕሊን ፣የሥራ ፍላጎትና ተነሳሽነት ያስፈልገዋል፡፡ ይሄ የቴክኖሎጂ ሽግግር ሥራ በዩኒቨርሲቲ፣ በቴክኒክና ሙያ፤ በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችና በሌሎቹም የሂሳብና ሣይንስ ትምህርቶች ላይ ትኩረት ተደርጎ ሊሰራበት ይገባል፡፡ጥራቱ እንዲሻሻል ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ በተያያዘም የቴክኖሎጂ ሽግግር ላይ ቁልፍ ሚና የሚኖራቸው የመንግሥት ድርጅቶች ናቸው፡፡ እነዚህም የመንግሥት ድርጅቶች በዓለም አቀፍ ደረጃ ተፎካካሪ የሚያደርግ ቁመና መፍጠር አለባቸው፡፡ ኢኮኖሚው እንደዚያ ዓይነት ብቃት ይፈልጋል፡፡

ከዚህም ጋር ተያይዞ ሰፊ የቁጠባ ሥራ ያስፈልጋል፡፡ አሁን ያለውን የቁጠባ ደረጃ በእጥፍ ማሳደግ አለብን፡፡ እያንዳንዱ ዜጋ መቆጠብ ይኖርበታል፡፡

በመጨረሻም ይሄን ሁሉ ማድረግ የምንችለው ሰላምና መረጋጋት ሲኖር ነው፡፡ ባለፉት 11 ዓመታት ኢኮኖሚው እያደገ ያለበት ምክንያት ከኤርትራ ጦርነት ማግስት ሙሉ ለሙሉ ሰላም የተረጋገጠበትና መረጋጋት የነበረበት ሁኔታ ስለነበረ ነው፡፡ ይህ ሁኔታ እንዳይደፈርስ መጠንቀቅ አለብን፡፡ በተለይ አሁን የአሸባሪዎች እንቅስቃሴ ሰፊ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊያንን ነው በዋናነት ለማጥቃት ሚፈልጉት፡፡ መከላከያ ሠራዊታችን፣ የፀጥታ ኃይላችንና መላው ሕዝብ ፀጥታችን እንዳይደፈርስ ማድረግ አለባቸው፡፡ ባለሀብቶች ለምንድን ነው ወደ ኢትዮጵያ እየተመለሳችሁ ያላችሁት? ተብለው ሲጠየቁ የሚመልሱት የመጀመሪያው መልስ ኢትዮጵያ ሰላምና መረጋጋት አላት የሚል ነው፡፡ የኢኮኖሚው አቅም ናይጀሪያ ሊኖር ይችላል፡፡ ግን የተረጋጋ ሰላም የለም፡፡ እዚህ ግን ጥሩ ሰላም አለ፡፡ ይሄ በእጃችን ስላለ ልንረሳው የማይገባን ቁምነገር ነው፡፡ ግንቦት 20ን ስናስታውስ ይበልጥ ለሰላምንና መረጋጋት ትኩረት ልንሰጥ ይገባናል፡፡  ሁሉም የመንግሥት አካላት መልካም አስተዳደር ላይ ሊሰሩ ይገባል፡፡ አሁን የምናስበውን ትልቅ ራዕይ ለማሳካት ባለፈው አስር ዓመት ከነበረው የሕዝብ ተሳትፎ የላቀ ተሳትፎ ነው የሚፈለገው፡፡

ሰፊ መነሳሳት እንዲኖርና የአስተሳሰብ ለውጥ እንዲኖር መሥራት ኖርብናል፡፡ አሁን ያለው አስተሳሰብ ሙሉ ለሙሉ ልማታዊ ነው ማለት አይቻልም፡፡ ይሄንን ሁኔታ መለወጥ ይኖርብናል፡፡ እነዚህን ነገሮች ካደረግን ከ10 ዓመት በኋላ ኢትዮጵያ ቀዳሚ የአፍሪካ የማኑፋክቸሪንግ ማዕከል ትሆናለች፡፡ እንደዚሁም ደግሞ ከ20 እና 30 ዓመት በኋላ የት ነው የምንደርሰው? ተብሎ የተጠየቀውን ጥያቄ ስናይ ከ25 ዓመት በኋላ ኢትዮጵያ የምትደርሰው መካከለኛ ገቢ ያላቸው አገሮች ላይ ሳይሆን ከፍተና ገቢ ካላቸው አገሮች ተርታ መሰለፍ የምትችልበት ዕድል ይፈጠራል፡፡ ከፍተኛ ገቢ ያላቸው አገሮች 12,750 ዶላር አካባቢ ነው፡፡አሁን ባለው ዓይነት ፍጥነት ከሄድን ና ማኑፋክቸሪንግ ላይ ይበልጥ ካተኮርን እንዲሁም መሠረታዊ የመሠረተ ልማት ሥራዎችን ከሠራን በመጪዎቹ 25 ዓመታት ያለምንም ጥርጥር እዚህ ደረጃ መድረስ እንችላለን፡፡



ዘመን፡- ግንቦት 20 ኤርትራንም ወደብም አሳጥቶናል የሚሉ ወገኖች አሉና ለእነዚህ ወገኖች ምላሽዎ ምንድን ነው?

ዶክተር አርከበ፡- ስለ ወደብ የሚያነሳ ነገር ግን ስለ ሕዝብ የማያነሳና የማያስብ ግለሰብ ወይም ቡድን ብቻ ነው ስለ መሬት የሚያነሳው። አገር ማለት ሕዝብ ነው። ስለሆነም ስለ ሕዝቦች በምናስብበት ጊዜ የኤርትራ ሕዝብ እንደ ሕዝብ ነው መወሰድ ያለበት። የኤርትራ ሕዝቡ ምን ይፈልጋል? ለብዙ ዓመት በጦርነት ውስጥ የቆየ ሕዝብ ነው፤ ከ30 ዓመታት በላይ። ከኢትዮጵያ መገንጠል እንፈልጋለን አሉ። ይሔንን በማየት ኢህአዴግ ጦርነቱ መራዘም የለበትም ብሎ ከድል በኋላ ዓመትም ሳይሞላው ሪፍረንደም እንዲካሔድ አደረገ። በዚያን ወቅት እንደ ኤርትራ ሕዝብ ተመሳሳይ ጥያቄ የነበራቸው ሕዝቦች ነበሩ፤ አንደ ዩጐዝላቪያ ያሉ። እናም የዚያን ጊዜ የተደረገው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሪፈረንደሙን እንዲመራ ነበር። በዚህም 99 በመቶ የሚሆነው የኤርትራ ሕዝብ ነፃ ኤርትራን እንፈልጋለን አለ። ሕዝቡ ፍላጐቱን በድምፅ አረጋገጠ ማለት ነው። የሕዝቡ ፍላጐት ደግሞ መሟላት አለበት። ዴሞክራሲ ማለት ለህዝብ መቆም ማለት ነው። ማነው የመጀመሪያ አገር ኤርትራን እንደ አገር የተቀበለው? የኢትዮጵያ መንግሥት ነበር። ያ ሆኖ ሰላም ማረጋገጥ ተችሏል። ስለዚህ ያንን ያደረግነው ከሰላም፣ ከዴሞክራሲ፣ ከሕዝቦች መብት ማረጋገጥ አንፃር ነውና ይሔ መሆኑ ተገቢ ነው። ግን ዋናው ነጥብ ምንድንነው ወደብ ልማት ያመጣል ብለው የሚያስቡ ሰዎች ስለ ኢኮኖሚ ልማት ምንም የማይገባቸው ሰዎች ናቸው። በአካባቢያችን ሠፋፊ ወደብና የባህር ዳርቻ ያላቸው አገሮች እነማን ናቸው? አንዷ ሶማሊያ ናት። ሁለተኛዋ ማናት? ኤርትራ ናት። ሁለቱንም እንያቸው በጥፋት ሂደት ያሉ አገሮች ናቸው። ሶማሊያ ግን አሁን በተሻለ እንቅስቃሴና መረጋጋት ውስጥ ናት። እናም ኢኮኖሚ የሚባል ልማት በእነዚህ አገራት የለም። 

ስለዚህ ልማትና ዕድገትን የሚያመጣው ወደብና የባህር ዳርቻ ነው የሚለው አስተሳሰብ ሕዝብን እንደ ሕዝብ ያለ ማየት አስተሳሰብ ምንጭ ነው። እኛ ወደብ መች ቸገረን፡፡ በጂቡቲና በበርበራ መጠቀም እንችላለን። የኤርትራም ሁኔታ መቀየሩ አይቀርም፡፡ አሁን ያለው ሁኔታ ለዘለአለም ይኖራል ብለን አንገምትም። በእኔ ግምት በሚቀጥሉት አስር ዓመታት ውስጥ ለውጥ ይመጣል ባይ ነኝ። የኤርትራን ወደብ እንጠቀማለን። የኬኒያን ወደብ መጠቀም እንችላለን። ከዚያ ወደ ኢትዮጵያ የሚገባ መስመር ለመገንባት ታቅዷል። የሱዳንንም እንጠቀማለን። ቢቻል ወደብ ቢኖረን ጥሩ ነበር ግን የሁሉም መቋጫና መፍትሔ እርሱ ነው ማለት አይደለም። የሚያመጣው መሠረታዊ ለውጥም የለም በእኔ እምነት። ሰሞኑን  በውጭ ጉዳይ ላይ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ክርክር በሚዲያ ሳይ ነበር። ከተቃዋሚዎች አንዱ እንዴት ብለን ነው የኢትዮጵያን ውሀ ለጅቡቲ የምንሰጠው? የሚል ሃሳብ ነው ያነሳው። እነዚህ ሰዎች በእኔ ግምት ምን ዓይነት አስተሳሰብ እንዳላቸው አይገባኝም። ውሃ ልከን ገቢ ብናገኝ ምንድን ነው ችግሩ? የኤሌክትሪክ ኃይል ልከን ገቢ እንደምናገኘው ሁሉ ውሃም ልከን ገቢ ብናመጣ ጉዳት የለውም ጥቅም እንጂ፡፡ ውሃ መላክ ነዳጅ ከመላክስ ምን ልዩነት አለውምንም ልዩነት የለውም። እና የዚህ ሰው አስተሳሰብ ልማታዊ አስተሳሰብ ነው? ጅቡቲ ያለው ሕዝብ ውሃ እየፈለገ ውሃ የጠማውን ሰው ውሃ መከልከል ተገቢ ነው? በባህላችንስ ይሔ አለ? ስለዚህ የሚነሱ ነጥቦች በጣም አሳፋሪ ናቸው። እና ተቃዋሚ ፓርቲዎች በዚህ ዙሪያ የእይታቸው አድማስ መለወጥ አለበት። ጊዜው ግን አልፏቸው ሔዷል። አጀንዳው ተቀይሯል። እያወሩ ያሉት ግን ከአስር ዓመት በፊት የነበረ አጀንዳ ነው። እና ችግሩ የአቋምና የአስተሳሰብ ችግር ነው።

ዘመን፡- እንደ ግለሰብ መጪዋን ኢትዮጵያ እንዴት ይገልጿታል?

ዶክተር አርከበ፡- የግሌ አስተሳሰብ እንግዲህ እኔ ለአስራ ሰባት ዓመታት በትጥቅ ትግሉ ተሳትፌአለሁ። ከዚያ በኋላ ማለትም ከደርግ መደምሰስ ወዲህም በአቅሜ አስተዋፅኦ እያደረግሁ ነው። አሁን የደረስንበትን ሁኔታ ሳየው ብዙ መስዋዕትነት ከፍለን ደርግን ደምስሰናል። ባለፉት ሃያ አራት ዓመታትም ኢኮኖሚው ትልቅ ዕድገት አሳይቷል። ግን ደግሞ ይሔ ጉዞ የልምምድ ጉዞ ነበር። ብዙ እንቅፋቶች የነበሩበት ነበር። አሁን ኢትዮጵያ እየለማች ነው፡፡ የውጭ ኢንቨስትመንትን እንመልከት የማይመጣ ኢንቨስተር የለም። አሁን እየመጡ ያሉት ኢንቨስተሮች ከአራትና አምስት ዓመት በፊት ሲመጡ የነበሩት ዓይነት አይደሉም፡፡ ቀደም ሲሉ ይመጡ የነበሩት ኢንቨስተሮች ከገልፍም ከአረብም ብርም ሳይኖራቸው አንዳንዶቹም አጭበርብረው ለመሔድ የሚመጡ ዓይነት ነበሩ። አሁን እየመጡ ያሉት ግን በጣም ትላልቅ ኩባንያዎች ናቸው። በሃዋሳ የኢንዱስትሪ ፓርክ ለማቋቋም ዝግጅት እያደረግን ነው። እዚያ የሚገቡ ፋብሪካዎች አንድ አምስት ስድስት የሚሆኑና ትላልቆች የሚባሉት ናቸው። ምን ዓይነት ፋብሪካዎች ናቸው? እነዚህ ከሕንድ፣ ከስሪላንካ፣ ከቻይና፣ ከማሌዥያ፣ ከባንግላዴሽ የሚመጡ ናቸው። እያንዳንዳቸው 6070 ሺ ሠራተኛ መያዝ የሚችሉ ፋብሪካዎች ናቸው። ሁለት ቢሊዮን ዶላር ኤክስፖርት የሚያደርጉ ናቸው። እና ሁኔታው ተቀይሯል። የአሜሪካ ኩባንያዎች ብዙውን ጊዜ ወደዚህ አይመጡም ነበር። አሁን ግን እየመጡ ናቸው፡፡ የአውሮፓ ኩባንያዎች እየመጡ ናቸው። 

ከአሁን ቀደም የአንዳንድ አገራት ኤምባሲዎች ኢትዮጵያን የሚያዩት በዕርዳታ የምትኖር አገር አድርገው ስለነበር የሚያስቡት አጀንዳቸው ስለ ብድርና ዕርዳታ ነበር፡፡ እኛ ግን አሁን እያልን ያለነው ከእናንተ የምንፈልገው ዕርዳታ አይደለም የንግድና የኢንቨስትመንት ግንኙነት ነው። በዚህ ላይ ነው ልንሠራ የምንፈልገው እያልናቸው ነው። እነርሱጋም የማዳመጥ ሁኔታ አለ። አቅምህና የኢኮኖሚ ጡንቻህ ሲሻሻል አዳማጭም ታገኛለህ። ስለዚህ በቀጣዩ አስር ዓመት በእኔ እምነት የተዓምር ወቅት ይሆናል። ባለፉት ሃያ አራት ዓመታት ያላየነውን ለየት ያለ ልማት እናያለን። ይሔ ዕድል ደግሞ ሊያመልጠን አይገባም። ከሁሉም በላይ ደግሞ ይህንን ዕድል መጠቀም ያለበት  ወጣቱ ነው። ወጣቱ ይሔ ዕድል ሊያመልጠን አይገባም ማለት አለበት። በተለያዩ ኃይሎችና በእኛ መካከል ያለውን ልዩነት በሁለተኛ ደረጃ እንየው። ይሔንን ዕድል በጋራ መጠቀም አለብን። በጋራ የአገሪቱን ገፅታ መገንባት አለብን። ለምሳሌ በዲያስፖራ ውስጥ  በልማቱ እየተሳተፉ ያሉ በጣም ጥሩ ወጣቶችን እያየን ነው። ግን ደግሞ በሌላ መልክ ኢትዮጵያ ዕርዳታ፣ ብድርና ኢንቨስትመንት እንዳታገኝ የሚለፉ ኢትዮጵያዊ ዲያስፓራዎች አሉ። ከዚህ ማን ይጠቀማል? ኢህአዴግ  አይደለም የሚጐዳው። አገሪቱ ናት እንደ አገር የምትጐዳው። ስለዚህ ጥላቻ ያላቸው ሰዎች በኢህአዴግና በአገሪቱ ላይ ያላቸውን ጥላቻ መለየት አለባቸው። ኢትዮጵያ ወደፊት በሁሉም ረገድ ቀዳሚ ልትሆን የምትችል አገር ናት ብለን ካሰብን ሁላችንም በጋራ በመሥራት የአገሪቱን ገፅታ ይበልጥ ማሻሻል ይኖርብናል፡፡ ይሄ ደግሞ ይቻላል። ይሄ ሲሆን ደግሞ ብዙ ፈላጊ እናገኛለን። እና ወጣቱ ይሔንን ማሰብ አለበት። በሙያም መማር አለበት። ወደ ኢንዱስትሪ ልማት ነው እየገባን ያለነው። ይሔ ዘርፍ የሚፈልገው አስተሳሰብና ሙያ የተለየ ነው። ስለዚህ ወጣቱ ሥራ በሚገባ መልመድና መማር ይኖርበታል። ይሔን ካደረግን ትልቅ ውጤት እናመጣለን።

1 comment: