EPRDF is a ruling party committed to realize Ethiopia's Renaissance.

Monday 31 July 2017

በሕዝብ ጥቅም የማይደራደር ፓርቲ፤ ኢሕአዴግ!

(በወጋገን አማኑኤል)
ኢህአዴግ ከተመሰረተበት ጊዜ ጀምሮ መላ የኢትዮጵያ ሕዝቦችን በተለይም ደግሞ ማህበራዊ መሰረቱ የሆኑትን አርሶ አደሩንና አነስተኛና መካከለኛ ገቢ ያለውን ሕዝብ ይዞ ሲታገልና ሲያታግል የመጣ አብዮታዊና ዴሞክራሲያዊ ድርጅት ነው፡፡ በባህሪውም ህዝባዊና ለሰፊው ሕዝብ ጥቅም የወገነ ደርጅት መሆኑ ይታወቃል፡፡ በታሪኩ ባለፈባቸው የተለያዩ ውጣ ውረዶችም ውስጥ ሆኖ እንኳን ከዚህ ባህሪው ፈቀቅ ላለማለት መስዋዕትነቶችን ከፍሏል፡፡

በቅርቡ በሀገሪቱ አንዳድ አካባቢዎች ተከስቶ የነበረው አለመረጋጋትና የፀጥታ ችግር የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነው፡፡ መስረታዊ ችግሩ የመልካም አስተዳደር እና የልማት ጥያቄ ሲሆን ፀረ-ሰላም ሃይሎች ግን አጋጣሚዉን እንደሽፋን በመጠቀም የራሳችውን የፓለቲካ አጀንዳ ለማስፈጸም ላይ ታች ሲራወጡ ነበር፡፡ ሁሌም የሚወስናቸውን ውሳኔዎች ከሕዝብ ጥቅም አንጸር የሚመዝነው ኢህአዴግ ግን ከችግሮቹ ማግስት ጥልቅ ተሃድሶ በማወጅ የተፈጠሩ ችግሮች ምንነት፣ መገለጫቸውን፣ መንስዔያቸውንና መፍትሄያቸውን ለይቷል፡፡
በዚህ ጥልቅ ተሃድሶ ሕዝቡን ያማረሩት የመልካም አስተዳደር ችግሮች ምን ምን እንደሆኑ ከለየ በኋላ ከዚህ ችግር መውጣት እንደ ድርጅትም ሆነ እንደሀገር የህልውና ጉዳይ መሆኑን አስምሮበታል፡፡ በጥልቅ ተሃድሶው ሂደት መግባባት ከተደረሰባቸው አንኳር ችግሮች አንዱ መንግስታዊ ስልጣንን ለሕዝብ ጥቅም ከማዋል ይልቅ ለግል ህይወት ማበልፀግያ አድርጎ መጠቀም አንዱ ነው፡፡ ይህ ሁኔታ ኢሕአዴግ በውስጡ ችግሮች ሲፈጠሩ በማንም ውጫዊ አካል ላይ ሳያስታክክ ወደ ውስጡ ለመመልከት ያለውን የሁልጊዜ ዝግጁነት ዳግም ያሳያበት ነው፡፡
የጥልቅ ተሃድሶው ዋና አላማ በመሰረታዊ ችግሮች ላይ መግባባት ከዚያም ችግሮቹን ደረጃ በደረጃ በመፍታት ጥልቅ ተሃድሶውን ወደ ሕዝብ አውርዶ ሕዝቡን የተሃድሶው ባለቤት ማድረግ እንጂ ጥፋት ያጠፉ አመራሮችንና አባላትን ሁሉ ቆርጦ መጣል አይደለም፡፡ ይህም የሆነው ኢሕአዴግ ሀገር እንደሚመራ ፓርቲና በሱ የሚመራው መንግስት ከገቡበት ችግር እንዲወጡ በአባላትና በአመራሩ ብሎም በአጠቃላይ በፈፃሚው ውስጥ የሚታዩ የአመለካከት ችግሮችን በመፍታት ሳይወሰን ችግሮቹን ከስር መሰረታቸው መንቀል ስለሚገባ ነው፡፡
ይህ መሰረታዊ መርህ እንዳለ ሆኖ በሁሉም ብሔራዊ ድርጅቶች ደረጃ የተሰጣቸውን ሃላፊነት ለሕዝብ ጥቅም ከማዋል ይልቅ የግል ጥቅማቸውን ማበልፀጊያ ማድረጋቸው በተጨባጭ የተረጋገጠባቸው አመራሮች ላይ እርምጃ ተወስዷል፡፡ በዚህም መሰረት ጥልቅ ተሃድሶ ከታወጀ ጊዜ ጀምሮ ብሄራዊ ድርጅቶች ቁጥራቸው የማይናቁ አመራሮች ላይ በየደረጃው እርምጃ ወስደዋል፡፡
ለመጥቀስ ያህል ብአዴን ባካሄደው ግምገማ መሰረት 130 ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች፣ 2468 የቀበሌ አመራሮች እንዲሁም 670 በላይ ባለሞያዎች እርምጃ የወሰደ ሲሆን 748 ያክል አመራሮችን ደግሞ ከኃላፊነት አንስቷል፡፡ በተመሳሳይ መልኩ ሕወሓት በበኩሉ ያደረገውን የጥልቅ ተሃድሶ ግምገማ ተከትሎ ችግር ፈጥረዋል በተባሉ 640 በላይ አመራሮች ላይ እርምጃ መውሰዱም የሚታወስ ሲሆን ኦህዴድም የከፍተኛ አመራሮች መሰረታዊ ሹም ሽር ካካሄደ በኋላ 5 በላይ መካከለኛ አመራር ግምገማ በማካሄድ እርምጃ ወስዷል፡፡ በድሬዳዋ አስተዳደርም ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ባልተወጡና ለመልካም አስተዳደር ችግሮች ምክንያት ናቸው በተባሉ 167 የመንግስት ሠራተኞችና 110 አመራሮች ላይ እርምጃ የተወሰደ ሲሆን እንዲሁም ደኢህዴን ባካሄደው የጥልቅ ተሃድሶ ንቅናቄ አመራሩን በአዲስ መልክ በማደራጀት ሂደቱ ህዝቡ እንዲተች በማድረግ  የተሰጣቸውን ተልዕኮ በብቃት ያልተወጡ 1ሺህ 911 አመራሮች  ከኃላፊነት እንዲነሱ መደረጉና ከእነዚህም ውስጥ 19  ከፍተኛ አመራሮች እንደነበሩ የቅርብ ጊዜ ትውስታችን ነው፡፡ ይህ ብቻም ሳይሆን በጋምቤላ ክልልም በመንግሥት ውስጥ ያሉ የአሠራር ክፍተቶችን ተጠቅመው በመመሳጠር የሕዝብና የመንግሥት የጋራ ሀብት የሆነውን መሬት በመዝረፍ ላይ ተሰማርተው የነበሩ ግለሰቦች የማጋለጥ ስራ ተሰርቷል፡፡
ይህ በብሔራዊ ድርጅቶችና በክልሎች ደረጃ ሰፋ ባለና ሕዝቡን ባሳተፈ ደረጃ የተወሰደው እርምጃ አሁን ደግሞ በፌዴራል ደረጃ ባሉ ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎችም ላይ ቀጥሏል፡፡ የመንግስትና የህዝብ ሀብትን በሙስና በመመዝበር ለግል ጥቅማቸው ያዋሉ የመንግስት የሥራ ሀላፊዎች እና ደላሎች ከፍተኛ ክትትል በማድረግ በቂ ማስረጃ በመያዝ መንግሰት በቁጥጥር ስር ማዋል የጀመረ ሲሆን ህብረተሰቡ ባሳተፈ መልኩ ተጠናክሮ ቀጥሏል:: በሙስና የህዝብና መንግስት ሀብት የመዘበሩ ከፍተኛ የመንግስት ስራ ሀላፊዎችና ደላሎች ቁጥራቸው አሁን ባለንበት ደረጃ 42 ደርሷል፡፡
በዚህም መሰረት ከፌደራል መንገዶች ባለስልጣን 1 ቢሊየን 358 ሚሊየን ብር ከስኳር ኮርፖሬሽን፣ ከመተሃራ፣ ተንዳሆ እና ኦሞ ኩራዝ የስኳር ልማት ፕሮጀክቶች 1 ቢሊየን 21 ሚሊየን ብር ከገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር 1 ነጥብ 1 ቢሊየን ብር ከአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን 198 ሚሊየን ብር በላይ እና ከአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ኤጀንሲ 41 ሚሊየን ብር በላይ መመሪያው ከሚያዘው ውጪ ክፍያ እና ግዢ በመፈፀሙ በመንግስት ላይ ጉዳት መድረሱ ለህዝብ ይፋ መደረጉና ሙሰኞችን የማጋለጥ ስራም መቀጠሉ መንግስትን የሚመራውን ድርጅት ለፀረ ሙስና ትግሉ ያለውን ቁርጠኝነት እንዲሁም በህዝብ ጥቅም ላይ የማይደራደር መሆኑን የሚያሳይ ነው፡፡
ከተሃድሶው ወዲህ በሁሉም ደረጃዎች እየተተገበረ ያለው ስልጣንን ለሕዝብ ጥቅም በማዋል ረገድ የሚታዩ ችግሮችን በመቅረፍ ወደ ትክክለኛው ሕዝባዊና አብዮታዊ መስመራችን የመመለስ ሁኔታ ከመነሻዉም የኢሕአዴግን በውግንናና በአሰላለፉ በሕዝብ ጥቅም ላይ የማይደራደር ደርጅት መሆኑን የሚያረጋግጥ ነው፡፡ ሰላም!

No comments:

Post a Comment