EPRDF is a ruling party committed to realize Ethiopia's Renaissance.

Saturday 27 May 2017

ልክ የዛሬ 26 አመት …

(በሚሚ ታደሰ)
አገር ተጨንቋል፡፡ በመዲናዋ አዲስ አበባ ዉጥረት አይሏል፡፡ ነዋሪዎች በየእምነታቸው ጸሎታቸዉን ለማድረስና ከሚመጣዉ እልቂት ፈጣሪያቸው እንዲታደጋቸዉ ጸሎታቸዉን እያደረሱ ይገኛሉ፡፡ አለም አቀፍ ሚዲያዎች ኢትዮጲያን ዳግማዊት ዩጎዚላቪያ፤ አልያም የአርማጌዶ ምድር ትሆናለች ሲሉ በየሰአቱ ደም ደም የሚል መላ ምታቸዉን ያስተጋባሉ፡፡
ለወትሮው ግርግር የማይለያቸው የአዲስ አበባ ጎዳናዎችና አደባባዮች ጭር ብለዋል፡፡ እዚህም እዚያም ይታዩ የነበሩ ባለቤት አልባ ዉሾቸ ሣይቀር እንደ መርዶ ነጋሪ ይቁነጠነጣሉ፡፡ መዝናኛ ቤቶች ከነአካቴዉ ተከርችመዋል፡፡ ጣዕረ ሞት በአበሻ ምድር ላይ እሳት ለብሶ እሳት ጎርሶ በዜጎች ጭንቀትና አልፎ አልፎ በሚሰማው የከባድ መሳሪያ ተኩስ አዝመራዉ በደንብ እንዳሸተለት አርሶ አደር ዳንኪራ ያወርዳል፡፡

ልክ የዛሬ 26 አመት ግንቦት 1983፣ በኢህአዴግ የሚመራው ህዝባዊ ሀይል አዲሰ አበባን ለመያዝ የመጨረሻውን እልህ አስጨራሸ ውጊያ ሊያደርግ ከእንጦጦ ከፍተኛ ስፍራዎች ጀርባ መሽጓል፡፡ በቤተ መንግስት የተቀመጠው የደርግ ልዩ ጦር የኢዮቤልዩ ቤተ መንግስትን ዙሪያ በታንክና ብረት ለበስ ተሸከርካሪዎች ከቦ በተጠንቀቅ ቆሟል፡፡ በሀገሪቱ ያለው ሁኔታ አለም አቀፍ  የዜና አዉታሮች ከሚሉትም በላይ እጅግ አስፈሪ ሆኗል፡፡
ወትሮም ቢሆን ለሰላም የሚከፍለዉ ዋጋ የሌለዉ ደርግ ሁኔታውን በትረ ስልጣኑን ከማስጠበቅ ጋር ብቻ ስለተመለከተዉ ከአናት ያለው መሪ ጥሎት በፈረጠጠበትና ወታደራዊ አቅሙ በተሟጠጠበት ጊዜ ላይ ሆኖ እንኳን ለድርድር እምቢተኛ ሆኗል፡፡ በአንፃሩ ድል በድል እየተቀዳጀ ወደ መሃል ከተማዋ የተጠጋው ኢህአዴግ ሀገሪቱ ለገባችበት ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ መፍትሄ ለመስጠት ከአምባገነኑ ደርግ ጋር ለመደራደር ቢቀርብም ድርድሩ ውጤት አልባ ስለሆነበት የመጨረሻው አማራጭ ደርግን ራሱ በመረጠው የሃይል መንገድ ማስወገድ ብቻ እንደሆነ ደምድሟል፡፡ ይህም ቢሆን ግን መፈፀም ያለበት በዋና ከተማዋ የከፋ እልቂት ሳይፈጠር፣ ዝርፊያና ህግ አልባነት ሳይነግስ የተፈረካከሰዉን ደርግ በመደምሰስ እንደሆነ ኢህአዴግ አስምሮበታል፡፡

እናም ልክ የዛሬ 26 አመት፣ ግንቦት 20 ቀን ጀግናዉ የኢህአዴግ ሰራዊት አስቀድሞ በተያዘለት የአፈፃፀም ስልት መሰረት ያለምንም ፍጅት አስከፊዉን የደርግ ስርአት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ በተባበረ ክንድ ወደ መቃብር አወረደው፡፡ በጭንቀት ተወጥረው ጆሯቸውን መገናኛ ብዙሃን ላይ የተከሉ መላ የኢትዮጵያ ሕዝቦችም ይህን የድል ብስራት አደመጡ፡፡ 
የዘመናት ብሶት የወለደው ጀግናው የኢህአዴግ ሰራዊት ከዚህ በፊት ደርግ ሲጠቀምበት የነበረውን የሬድዮ ጣቢያ ለሰፊው ህዝብ ጥቅም ተቆጣጥሮታል፤ ግንቦት ሃያ ዘጠኝ መቶ ሰማኒያ ሶስት አመተ ምህረት!”
እነሆ ዛሬ ላይ 26 አመት በፊት ከተሟረተው በተጻራሪ ኢትዮጵያ ሀገራዊ አንድነቷን ጠብቃ ቀጥላለች፡፡ 17 በላይ ነፍጥ ከታጠቁ በአንድ ሀገር፣ በአንድ ሃይማኖት ቀምበር ስር ሲማቅቁ ከነበሩና ተገቢዉን ሀገራዊ ዉክልና አጥተዉ ብረት ካነገቡ አካላት ጋር በክብ ጠረጴዛ ዙሪያ ተወያይቶ ለጥያቄያቸዉ ህገ መንግስታዊ ዋስትና በመስጠት ወደዉና ፈቅደው የሚኖሩባትን የሁሉም ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ሃገር አዲሲቷን ኢትዮጵያ እውን አድርጓል፡፡ ሁሉም በእኩልነት የሚስተናገዱባት፤ የክርስቲያኑም፣ የሙስሊሙም፣ የዋቄ ፈታዉም፣…. የሁሉም የእኩልነት ሀገር የሆነችዉን ኢትዮጵያን መፍጠር ችሏል፡፡ ብሔር ብሔረሰቦቿም ወደዉና ፈቅደው፤ መርጠዉ የሚኖሩባት አገር እንደሆነች በመቀበል መብታቸዉን ያለገደብ በሚያስከብርላቸዉ ህገ መንግሰት ማአቀፍ ዉስጥ አንድ ሆነዉ እንደብዙ፣ ብዙ ሆነዉ እንደ አንድ ታሪክ መስራታቸዉን ቀጥለዋል፡፡
ኢትዮጵያ ዛሬ በተረት ተረት የቆመ ማንነት የላትም፡፡ ህዝቦቿ በላባቸው ወዝ ሌት ተቀን የሚገነቧት ሀገር እንጂ የዛኔው የሞት፣ የመታረዝ፣ የመጠፋፋት ምልክት የነበረው ኢትዮጲያዊነት ገፅታ ተቀይሯል፡፡ ባለፉት 26 አመታትም ህዝቦችዋ የሚጓጉላት፤ በገነባችዉ የጦር አፈሙዝ ሳይሆን እየገነባች ባለዉ ጠንካራ ኢኮኖሚ የተነሳ በመደጋግፍና በጋራ ተጠቃሚነት ላይ በተመሰረተ አፍሪካዊ አስተሳስብ ሁሉም ሊወዳጃት የሚፈልጋት ሀገር ሆናለች፡፡ ከመበታተን ይልቅ ይበልጥ ጠንካራ ሀገር ሆናለች፡፡ ያኔ የመበታተን ስጋት ላይ የነበረችው ኢትዮጵያ በህገ መንግስታዊ ዋሰትና ወደ ነበረችበት ታላቅነት ለመመለስ የቁልቁለት ጉዞዋን ታሪክ ካደረገች ሰንብታለች፡፡ ኢህአዴግ እለተ ሞቷ የተተነበየላትን ሃገር በሰላም፣ በልማትና በዴሞክራሲ መንገድ ላይ ማስቀጠሉ ምንጊዜም በታሪክ ምዕራፍ ጉልህ ስፍራ ይዞ ይኖራል፡፡

ክብርና ሞገስ ለዚች ቀን ላበቁን ሰማእታት!

1 comment:







  1. EPRDF is a ruling party committed to realize Ethiopia's Renaissance. I believe EPRDF can do it. March on EPRDF to build a prospers, peaceful and democratic Nation. The future is bright









    EPRDF is a ruling party committed to realize Ethiopia's Renaissance.


    ReplyDelete