EPRDF is a ruling party committed to realize Ethiopia's Renaissance.

Saturday 18 November 2017

መርህና መስዋዕትነት ያስተሳሰራቸው፤ ህወሓትና ብአዴን

(በእውነቱ ይታወቅ)
የአማራ እና የትግራይ ህዝቦች የህዝብ ለህዝብ ውይይት በጎንደር ከተማ ተካሂዷል፡፡ ይህ መድረክ በአንድ በኩል ባለፈው አመት ክረምት ላይ በመቀሌ ከተማ የተካሄደው ኮንፈረንስ ቀጣይ መድረክ ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ በሀገር አቀፍ ደረጃ መንግስት ትኩረት ሰጥቶ ሊሰራበት  በእቅድ የያዘው የህዝብ ለህዝብ ትስስሮች ማጠናከሪያ መድረኮች አንድ አካል ተደርጎ የሚወሰድ ነው፡፡


በዚህ የትግራይና የአማራ ህዝቦች የህዝብ ለህዝብ መድረክ ላይ ከእያንዳንዳቸው ክልሎች 500 የሃገር ሽማግሌዎች ተሳትፈዋል፡፡ የሃይማኖት አባቶችና የፌዴራልና የክልሎቹን ከፍተኛ አመራሮች ጨምሮ 1276 ሰዎች ናቸው የተሳተፉት፡፡

ሁለቱ ህዝቦች በታሪክ፣ በማህበራዊ ሂወት፣ በደም፣ የተሳሰሩ ናቸው፡፡ በዚህ ማስታወሻዬ ሁለቱ ህዝቦች አምባገነኑን ስርዓት ለማስወገድ በተደረገው ትግል የነበራቸውን በደም የተፃፈ ታሪካዊ ትስስር መለስ ብለን እንድናስብ የሚያደርጉ ፅሁፎችን ለማስቃኘት እሞክራለሁ፡፡

እንደሚታወቀው የአማራና የትግራይ ሕዝቦችን የፀረ ጭቆና ትግል የመሩት መሪ ድርጅቶቻቸው ብአዴን/ኢህዴን እና ህወሓት ስር የሰደደ ግንኙነት ያላቸው፤ ይህም ግንኙነት በመርህና በጋራ መስዋዕትነት ላይ የተመሰረተ ነው፡፡

ጋድ ህላዌ ዮሴፍ “ታሪክና ጥበብ” በሚል ርዕስ በ2007 ዓ.ም ያወጣው መፅሃፍ ለዚህ ሁነኛ ማሳያ ፅሁፎችን አካቶ ይዟል፡፡ ማን ያርዳ የቀበረ፤ ማን ያውራ የነበረ እንዲሉ ጓድ ህላዌ ህወሓትና የቀድሞው ኢሕዴን የአሁኑ ብአዴን የነበራቸውን ትስስር እንዲህ በሚጥም መልኩ ተርኮታል፡፡

“ኢህአፓ/ኢህአሠ ሲበታተን 112 ያክል የኢህአፓ/ኢህአሠ አካሄድ ያልጣመን ታጋዮች እንደሌሎች ጓዶቻችን “ምህረት” ጠይቀን ወደ ደርግ መግባትም ሆነ ወደ ሱዳን መሰደድ እየቻልን ህወሓት ወደሚቆጣጠረው ነፃ መሬት ማፈግፈግን መርጠናል፡፡ ይህ ምርጫ የተወሰደው ስለ ህወሓት ባህርይ ግልፅ መረጃ ተይዞ አልነበረም፡፡ በድርጅቱ ዴሞክራሲያዊነትና ሕዝባዊነት ላይ ከፍተኛ ጥርጣሬ የነበረን ቢሆንም፣ ደርግን በፅናት የሚታገል ድርጅት በመሆኑ ላይ ግን ብዥታ አልነበረንም፡፡ በዚህም መሰረት ህወሓት ዴሞክራሲያዊና ሕዝባዊ ከሆነና ነፃ መሬቱን ተጠቅመን እንድንደራጅ፣ እግር ተክለንም እስክንሰማራ በነፃነት እንድንንቀሳቀስ የሚፈቅድልን ከሆነ ይህንን እድል እንጠቀምበታለን፣ ይህንን የማይፈቅድልን ከሆነ ወደ ሱዳን እንሰደዳለን ብለን ወሰንን፡፡

ህወሓት ዴሞክራሲያዊ ሆነም አልሆነም በትግል ጓዶቻችን ደም የተገኙ ጠመንጃዎችን፣ ድግን መትረየሶችንና ተተኳሾችን ለደርግ ከማስረከብ ለህወሓት መስጠት ተገቢ ይሆናል ብለን አምነንም ነው ወደ ትግራይ የተንቀሳቀስነው፡፡

ሰኔ 10/1972 ዓ.ም ፃኢ በተባለው ቦታ ከህወሓት ከፍተኛ አመራች ጋር ውይይት ከተደረገበት ጊዜ ጀምሮ ህወሓት በተለያዩ የፖለቲካ ጉዳዮች ላይ ከኢህዴን ጋር ለመወያየት ብቻ ሳይሆን በበሰለ ሁኔታ ለመከራከር ዝግጁነትና አቅምም ያለው ድርጅት መሆኑን ተገነዘብን፡፡ ከህወሓት ጋር የማንስማማባቸው ጉዳዮች ካሉ ሀሳባችንን በነፃነት ይዘን በቀጣይነት ለመከራከር እንደምንችልም አረጋገጥን፡፡ ህወሓት ስህተት ሆኖ ኢህዴን ትክክል የሆነባቸው፤ ኢህዴን ስህተተኛ አቋም ይዞ ህወሓት ትክክለኛ አቋም የያዘባቸው የፖለቲካ ጉዳዮች የነበሩ ቢሆንም በቀጣይ ግንኙነትና ግልፅ ውይይት የሁለቱ ድርጅቶቻችን አቋሞች ከሞላ ጎደል ተመሳሳይ እየሆኑ ሄዱ፡፡ ለኢህአዴግ ምስረታ መሰረት የሆነውም ይህ የአቋም መቀራረብ ነው፡፡” በማለት ገልፆታል፡፡

ሌላው አንጋፋ ታጋይና ደራሲ መዝሙር ፈንቴ ‘አገር ጫታ’ በሚል ርእስ በታተመው መፅሃፉ እንዳሰፈረው “ህወሓት የደርግን ዘመቻ በመመከት ረገድ በአርማጭሆ ምድር የከፈለው መስዋዕትነት ቀላል አይደለም፡፡ በሳንጃ፣ በሙሴ ባምብ፣ ወዘተ… ዉጊያዎች በርካታ የህወሓት ታጋዮች፣ ጀግና የትግራይ ልጆች ደማቸውን አፍስሰዋል፡፡ ከቆፍጣናዎቹ የአማራ አርበኞች ጎን ቆመው በአንድ ግንባር ወድቀዋል፡፡ አላማቸው አንድ ሆኖ በእምነት፣ በስጋና በደም መስዋዕትነት ተዋህደዋል፡፡”

ህወሓት ሕዝባዊና ዴሞክራሲያዊ ድርጅት መሆኑን ያመኑት የኢህዴን ታጋዮች አብረንህ እንታገላለን፣ ለጋራ አላማችን አብረን እንሰዋለን የሚለውን የትግር አጋርነት ለማሳየት “ባንድ ግንባር እንወድቃለን” ሲሉ ገጥመዋል፡፡ ይህን ግጥም በ2007 ዓ.ም ታሪክና ጥበብ በሚል ርዕስ ከታተመው የጓድ ህላዌ ዮሴፍ የግጥም መድብል ላይ እንድታነቡት እየጋበዝኩ ከዚሁ ግጥም ጋር ተመሳሳይ መነሻና ይዘት ያለውን “ባንዴራችን አንድ ይሆናል” የሚለውን ግጥም እነሆ ጀባ ብያለሁ፡፡

ባንዴራችን አንድ ይሆናል
በስጋችን ቁስል በደማችን ቀልሞ፣
ሕይወታችን አልፎ በአጥንታችን ቆሞ፣
በአንድ ግንባር ወድቀን ግባችን ይመጣል፣
ባንዴራችን አንድ ይሆናል፡፡
ትግላችን አንድ ነው የሩቅ አላማችን፣
በደም የቀለመው ቀናው መስመራችን፣
መብትን አስከብሮ በአንድነት ይዘልቃል፣
በነጻነት ፍልሚያ ብዝበዛን ይቀብራል፡፡
ኢህዴን አብቢ ቤዛ ሁኝ ለምዝብር፣
መብረቅ ክንድሽ ያይል ፋሽዝምን ያሸብር፡፡
የአመፁ ነበልባል በየቦታው ይነዳል፣
የጭቆኖች ጥይት ትግልን ያስተጋባል፣
የተዳፈነው ፍም ሁሉም ጋ ይቃጠላል፣
ምዝብር ለፋሽቶች አልገዛም ይላል፣
ነፃነት አዝመራሽ በኛ ደም ይለምልም፣
ባንዲራችን ደምቀሽ ብሪ ለዘለዓለም፡፡
መተክላዊ ክንዶች በአንድ ላይ ተሳስረን፣
ፋሽስት አድርባዩን በትግላችን ጥለን፣
የሁሉን ብሔሮች አርማ እንተክላለን፣
ደም የተፃፈበት ባንዴራ እንወልዳለን፡፡
ህወሓት አብቢ ቤዛ ሁኝ ለምዝብር፣
መብረቅ ክንድሽ ያይል ፋሽዝም ያሸብር፡፡
ፋሽስቶች ከእንግዲህ መርዷቸውን ይስሙ፣
በጭቁኖች ሕብረት ቆስለው ይታመሙ፣
የጠመንጃችን አፍ ምስራች ያበስራል፣
የአዲሱን ቀን መዝሙር ድምፃችን ያሰማል፡፡
ኢህዴን ህወሓት ጣምራ የአመፅ ክንዶች፣
የፋሽዝም እብሪት ቅስም ሰባሪዎች፡፡
በጓድ ህላዌ ዮሴፍ

No comments:

Post a Comment