EPRDF is a ruling party committed to realize Ethiopia's Renaissance.

Monday 2 October 2017

የምንከተለው እውን የጎሳ ፌዴራሊዝም ነውን?

(በሣዲቅ አደም)
ተቆጥረውና ተሰፍረው የማያልቁ የጭቆናና የብዝበዛ አይነቶች ለኢትዮጵያ የፌደራል ሥርዓት መወለድ መነሻ ምክንያቶች ስለመሆናቸው አያከራክርም፡፡ ይህ የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ስርአት ሌሎች የአለም ፌዴራል ሃገራት የሚከተሏቸውን የጋራ ባህሪያት ያሟላ፣ ከራሱ ታሪካዊና ነባራዊ ሁኔታዎች የመነጩ ልዩ ባህሪያት ያሉት፣ በሁሉም የዲሞክራሲያዊ ይዘት መስፈርቶች ሲመዘን የላቀ ዲሞክራሲያዊነት ያለውን ህገ መንግስት በማጽደቅ እየተመራ የሚገኝ ስርአት ነው፡፡

ሆኖም በአሁኑ ጊዜ የዴሞክራሲያዊ ፌዴራላዊ ስርዓት ግንባታ ሂደትን የሚፈታተኑ ተግዳሮቶች ጎልተው እየታዩ ናቸው፡፡ ከዚህም አንዱ በስርዓቱ ደጋፊዎችም ሆነ ተቃዋሚዎቹ ላይ የሚታየው ስለ ስርዓቱ ያለ የግንዛቤ ማነስ ነው፡፡ ስርዓቱ በጎሳ ላይ የተመሰረተ ነው ከሚል ጀምሮ እስከ ለማንነቶች እኩል እውቅናና መብት አልሰጠም የሚል የተሳሳተ ወቀሳ ድረስ፤ ስርዓቱ ትብብርን ሳይሆን ፉክክርን ያበረታታል ከሚለው ጀምሮ እስከ በሀገሪቱ ውስጥ ግጭቶች እንዲስፋፉ ምክንያት ሆኗል የሚሉት ድረስ ክሶች ይቀርቡበታል፡፡
የፌዴራል ስርዓቱን ምንነት በመገንዘብ የግንባታ ሂደቱን ማሳካትና ተግዳሮቶቹን በመታገል የኢትዮጵያን የህዳሴ ጉዞ እውን ማድረግ አስፈላጊ በመሆኑ በፌደራሊዝም ፅንሰ ሃሳብ ዙሪያ የተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጥ ስራዎች በመሰራት ላይ ናቸው፡፡ ይህ እንዳለ ሆኖ በዚህ ፅሁፌ እውን የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ስርዓት በጎሳ ላይ የተመሰረተ ነውን የሚለውን ነጥብ ለማየት እሞክራለሁ።
እዚህ ላይ በቅድሚያ ጎሳ ማለት ምን ማለት ነው የሚለው ጥያቄ ምላሽ ማግኘት አለበት፡፡ ጎሳ ማለት በአንድ የማህበረሰብ የእድገት ደረጃ ውስጥ በተዋረድ ከግለሰብና ከቤተሰብ ቀጥሎ የሚፈጠር፣ የቤተሰብ ከፍተኛ የእድገት ደረጃ የሆነ፣ የብዙ ቤተሰቦች ስብስብ የሆነ፣ በደምና በዝምድና ሀረግ ግንኙነት ላይ የተመሰረተ እንዲሁም የጥንታዊ ጋርዮሽ ሥርዓተ ማህበር አይነተኛ ባህሪ መገለጫ እና አሁንም በአንዳንድ በእድገት ወደኋላ በቀሩ ሀገሮችና አካባቢዎች የሚታይ የማህበረሰብ አካል ነው፡፡
በአንፃሩ የኢትዮጵያ የፌደራል መንግስት በክልሎች የተደራጀ ሲሆን በህገ መንግስቱ አንቀፅ 46 ላይ እንደተመለከተው ደግሞ ክልሎቹ የተዋቀሩት በህዝብ አሰፋፈር፣ በቋንቋ፣ በማንነት እና በህዝብ ፈቃድ ላይ ተመስርቶ ነው፡፡ ህገ መንግስቱ ስለ ማንነቶች ሲያብራራም መገለጫዎቹ ብሔር፣ ብሔረሰብና ሕዝብ መሆናቸውን አመልክቷል።
እነዚህ አራት መስፈርቶች አንዳቸውም በትርጉም ደረጃ ጎሳን የሚወክሉ አይደሉም። ይህ ብቻ ሳይሆን የጎሳ ትርጉም ከአሁኑ የኢትዮጵያ ፌደራሊዝም ጋር በየትኛም አመክንዮና ትንተና አይገናኝም፤ አይዛመድም፡፡ እናም የፌዴራል ስርዓታችን መሰረቱ ህብረ ብሄራዊነት እንጂ ጎሰኝነት አይደለም፡፡
ከላይ በፌዴራሊዝም የአስተዳደር አወቃቀር ላይ የተነሱት አራት መስፈርቶች በሀገራችን ብቻ ሳይሆን በስዊዘርላንድ፣ በቤልጂየም፣ በካናዳና በሌሎችም የፌዴራል ሥርዓትን በሚከተሉ የበለፀጉ ሀገራት ሥራ ላይ የዋሉ ናቸው። በእነዚህና ሌሎች መሰል አገራት የፈዴራሉን መንግስት በጥምረት የመሰረቱት አካሎች የሚጠሩት ክልሎች፣ ክፍለ ሀገሮች፣ ካንቶኖች፣ ላንደሮች፣ ማህበረሰቦች አልያም ደሴቶች በሚል እንጂ ጎሳ የሚል ወይም ከጎሳ ጋር የተያያዘ ስያሜ ተሰጥቷቸው አይታወቅም፡፡ በአጭሩ የፈዴራሊዝምን ሥርዓት ያራምዳሉ ተብለው ከሚታመኑ ከሁለት ደርዘን በላይ የሚሆኑ አገራት ውስጥ የጎሳ ፌደራሊዝም የሚል ስያሜ የተሰጠው አገር የለም፡፡

እነዚህን ጉዳዮች መሰረት አድርገን ስንነሳ የፌዴራል ስርዓታችን በጎሳ ላይ የተመሰረተ ፌዴራሊዝም ሳይሆን በዲሞክራሲያዊ ብሄርተኝነት ላይ የተመሰረተ ህብረ ብሔራዊ ፌዴራሊዝም (multinational federalism) መሆኑን ለመረዳት አይከብድም፡፡

No comments:

Post a Comment